Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊእየተስፋፋ የመጣው የመንገድ ዳር መብራቶች ስርቆት

እየተስፋፋ የመጣው የመንገድ ዳር መብራቶች ስርቆት

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ በምሽት የሚንቀሳቀሱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን፣ እንዲሁም የትራፊክ እንቅስቃሴ ደኅንነት ምቾትን ለመጠበቅ ዓይነተኛ ሚና ካላቸው መካከል የመንገድ ዳር መብራት አንዱ መሆኑ ይታመናል፡፡ በተለይም የከተማዋን ገጽታ ከማሳየት ባለፈ በምሽት በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ለሚዘዋወሩ ምቾትን መፍጠር አይታበልም፡፡ ይሁን እንጂ ከሰሞኑ የመንገድ ዳር መብራቶች ላይ ከሚፈጸመው ስርቆት የተነሳ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና ለትራፊክ አደጋ መንስዔ እየሆነ መምጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ሰለሞን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በስርቆት ምክንያት የመንገድ ዳር መብራት አገልግሎት መቆራረጥ በምሽት ወቅት የሚኖረውን የትራፊክ ፍሰት ከማስተጓጎሉም በተጨማሪ ለወንጀል ድርጊትና ለአደጋዎች መጨመር ምክንያት ሆኗል፡፡

ባለሥልጣኑ ከሚያከናውናቸው የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎች ጎን ለጎን የመንገድ ዳር መብራት ተከላና የጥገና ሥራ የሚጠቀስ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በእነዚህም የመንገድ ዳር መብራቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን በኅብረተሰቡ ቸልተኝነት የተነሳ ኬብሎቹ እየተሰረቁ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ከመንገድ ዳር መብራት አንፃር በ2014 ዓ.ም. ላይ ወደ 13 ሺሕ የመንገድ ዳር መብራት ፖሎችን ለመቀየር ዕቅድ ተይዞ 16,263 ፖሎችን ለመቀየርና ለማደስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን በ2015 በጀት ዓመት ከ14 ሺሕ በላይ የመንገድ ዳር መብራት ፖሎችን ለማደስ ዕቅድ መያዙን ያስታወሱት አቶ ኢያሱ፣ በቅርቡም ባለሥልጣኑ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በተለያዩ ቦታዎች ላይ ዝርፊያ የተከናወነባቸውን የመንገድ ዳር መብራቶች መለየቱን አክለው ገልጸዋል፡፡

ዝርፊያ ከተፈጸመባቸው የመንገድ ዳር መብራቶች ለአብነት ያህል ከኃይሌ ጋርመንት ወደ ጎሮ የሚወስደው መንገድ ተጠቃሽ እንደሆነ፣ በዚህም መንገድ ላይ በተደጋጋሚ ስርቆት መፈጸሙን አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ከጀሞ ሚካኤል አደባባይ ወደ ሮክ፣ ከጎጃም በር ወደ ጄኔራል ዊንጌትና ከኃይሌ ጋርመንት ወደ አቦ በሚወስዱ መንገዶች ላይ የመንገድ ዳር መብራቶች ኬብል ስርቆት የተፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስርቆቱ የተፈጸሙባቸው አካባቢዎች አንዳንዶቹ እድሳት የተደረገላቸው ሲሆን፣ ሌሎቹን ደግሞ በቅርቡ እድሳት የሚደረግላቸው ይሆናል ያሉት አቶ ኢያሱ፣ ‹‹በየቦታው እየተፈጸመ ያለውን የኬብል ዝርፊያ ለማቆም ማኅበረሰቡ ከፀጥታ አካላት ጎን መቆም አለበት፤›› ብለዋል፡፡

በከተማዋ አዳዲስ የመንገድ ግንባታ የተከናወኑባቸው ቦታዎች ላይ የመንገድ መብራት ፖሎች የተዘረጉ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት በኩል የኃይል አቅርቦት ያልተሰጠባቸው እንደሆነ፣ በዚህም የተነሳ ኬብሎች ሊዘረፉ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል በ2013 በጀት ዓመት ከተመረቁ መንገዶች አንዱ የሆነው ከቦሌ ሚካኤል ወደ ቡልቡላ መሄጃ መንገድ ተጠቃሽ እንደሆነ፣ ቦታውም እስካሁን የመንገድ ዳር መብራት አገልግሎት እያገኘ አለመሆኑን አቶ ኢያሱ ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም ከመገናኛ ወደ ሃያ አራት፣ ከአያት ቦሌ አራብሳ፣ ከጎሮ አያት መንገዶች ላይም ይህ ችግር እየታየ መሆኑን የገለጹት ምክልት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ከስርቆት ጋር በተያያዘ የመብራት ፖል የማኖል ክዳን ላይ የሚገኙ ፌሮዎች እየተወሰዱ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ባለሥልጣኑም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር እየሠራ መሆኑን፣ ይሁን እንጂ በከተማዋ ላይ ከሚታየው የመንገድ ስፋት አንፃር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ለባለሥልጣኑ ብቻ የሚተው እንዳልሆነና በቂ አለመሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ ባለሥልጣኑ ከሚሠራቸው ሥራዎች አንዱ በክረምት ወቅት በማኅበረሰቡ ላይ የጎርፍ አደጋ እንዳይደርስ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ መሆኑን፣ በ2014 ዓ.ም. ክረምት ላይ ሲከሰት የነበረው የጎርፍ አደጋ አንዱና ዋነኛ ችግር ሆኖ የነበረው የድሬኔጅ መስመር ደኅንነቱ አለመጠበቁ እንደሆነ አቶ ኢያሱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ይህንንም ችግር ለመፍታት ባለሥልጣኑ 317 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የድሬኔጅ መስመር ፅዳትና ጥገና ለማከናወን አቅዶ፣ 315 ኪሎ ሜትር የሚደርሰውን የድሬኔጅ መስመር መጠገን መቻሉን አብራርተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የድሬኔጅ መስመሮችን ባለመጠገን የተነሳ ከፍተኛ የሆነ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት መቻሉን አስታውሰዋል፡፡

ተቋሙም የመንገድ ዳር መብራቶች ላይ የደረሰበትን ዝርፊያ ለከፍተኛ ኪሳራ እንዳጋለጠው፣ በገንዘብም ሲተመን ከፍተኛ የሆነ ወጪ መሆኑን የገለጹት አቶ ኢያሱ፣ ይህንንም ችግር ለመቅረፍና በዘርፉ ላይ ወጥ የሆነ ለውጥ ለማምጣት፣ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አንድ የቁጥጥር ማዕከል እያስገነባ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት ባለሥልጣኑ ለመንገድ ግንባታና ጥገና ስድስት ቢሊዮን ብር ይዞ እንደነበረ ነገር ግን ያለውን አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የከተማ አስተዳደሩ በመጋቢት ወር ላይ 1.2 ቢሊዮን ብር በመጨመር የተለያዩ ሥራዎች ሊሠሩ መቻላቸውን አክለዋል፡፡

በአጠቃላይ በ7.2 ቢሊዮን ብር ባለሥልጣኑ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ የመንገድ ዳር መብራቶችንና የተለያዩ ጥገናዎችን ሊያከናውን መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በመንገድ ዳር መብራት እየተፈጸመ ያለውን ሕገወጥ ተግባር ለማስቆም ማኅበረሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አቶ ኢያሱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...