እቴጌ ምንትዋብ በጎንደር እስከ ዛሬ ከደርቡሽ ቃጠሎ ተርፎ ፍራሹ የሚያስደንቀውን የቅድስት ቁስቋምን ቤተ ክርስቲያን በዘመናቸው አሠሩ። ለዚህ ሥራ ሺሕ ወቄት ወርቅ… የማይበቃ ቢሆን የጣታቸውን ቀለበት አውልቀው እንደጨመሩ ታሪካቸው ይገልጻል። … ስለዚህም እቴጌ ምንትዋብ የኅዳር ቁስቋም በዋለችበት ቀን በዚሁ በዓል ምክንያት የቁስቋምንና የሌላውንም አድባራትና ገዳማት ቀሳውስትና ካህናት ጠርተው ትልቅ ግብር ሲያበሉ «ሁል ጊዜ በንግግርም በመጠጥም ካህን ያሸንፈኛል ዛሬ ግን እኔ ሳላሸንፍ አልሰደውምና ዋናውንም የስርቆሹንም በር ደኅና አድርጋችሁ ዝጉ፣ ለካህኑም የወይን ጠጅ እየደጋገማችሁ ስጡ» ብለው እቴጌ አሳላፊዎቻቸውን አዘዙ ይባላል።
ካህኑ ከበላ በኋላ በዚህ ጊዜ እየጠጣ ሽንቱ መጣበት፣ እሥጋጃውም ላይ እንዳይሸና ብልግና ነው እንዳይወጣ በሩ ሁሉ በጥብቅ ትዕዛዝ ስለ ተዘጋ አልተቻለም። በዚህ ጊዜ ካህኑ እርስ በርሱ እየተጨነቀ የሚያደርገውን አጣ። በዚህ መካከል ከተጨናቂዎቹ ውስጥ አንዱ አለቃ ኢሳይያስ የሚባል ሊቅ እንዳደገደገ ተነሥቶ አንድ ነገር እንድጠይቅ ይፈቀደልኝ ብሎ እቴጌን ለመነ። እቴጌም ተፈቅዶልኻልና ጠይቅ አሉት፤ እሱም 500 እና 500 ሲጋጠም ስንት ይሆናል? ብሎ ጠየቃቸው። እሳቸውም ሺ ነዋ ብለው መለሱ። አለቃ ኢሳይያስም ከእቴጌይቱ ይህችን ቃል ሰምቶ ከነጠቀ በኋላ ወደ ጓደኞቹ ወደ ካህናቱ ፊቱን አዙሮ ሺነዋ ብለውኻል ብሎ ተናገረ፣ በዚያ ጊዜ የተቸገረው ሁሉ በየተቀመጠበት ምንጣፍ ላይ ሸናበት። እቴጌይቱም አለቃ ኢሳይያስ ባመጣው የነገር ብልሀት ተደንቀው ሸልመው ሰደዱት ይባላል።
- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ልብነ ድንግል እስከ ዐፄ ቴዎድሮስ›› (1951)