ከተፈጥሮ ጋር ስለአለው ግንኙነት አቶ ኮይነር ተጠይቆ፣ እንዲህ ሲል መልስ ሰጥቷል፡፡ «ከቤት ስወጣ አንድ ሁለት ዛፎችን ባይ ደስ ይለኛል፡፡ በተለይም በየቀኑ እና በየዓመቱ በተለያዩ ጊዜዎች በሚያገኙት የመልክ ለውጥ የተነሣ የእውነትን ልዩ ደረጃ የሚጐናጸፉ ስለሆነ፡፡ ከዚህም ሌላ፣ በየከተሞቻችን ሁል ጊዜ የሚታዩት አገልግሎት ተቋሞች፣ ማለትም ቤቶች እና መንገዶች ብቻ ሲሆኑ፣ እነዚህም ካልተኖረባቸው ባዶ፣ ጥቅም ላይ ካልዋሉ ከንቱ ስለሚሆኑ፣ ቀስ በቀስ፣ እንወናበዳለን፡፡ የያዝነው ልዩ የኅብረተሰብ ሥርዓት፣ በበኩሉ፣ ሰዎችንም የእነዚህ የአገልግሎት ተቋሞች አካል አድርገን እንድንቆጥር፣ ተጽዕኖ አሳድሮብናል፡፡ ስለዚህም፣ ዛፎች ቢያንስ ቢያንስ ለእኔ፣ አናጢ ላልሆንኩት፣ እራሱን የቻለ የሚያረጋጋ እኔን በተለይ የማይመለከት አንድ የሆነ ነገር አላቸው፡፡ እንዲያውም እኔ ተስፋ የማደርገው፣ ዛፎች ለአናጢዎችም እንኳን ቢሆን ዋጋው በገንዘብ ብቻ የማይተመን ጥቅም ይኖራቸዋል ብዬ ነው፡፡»
(ከዚህም ሌላ አቶ ኮይነር እንደዚህ አሉ፡፡) «ሰዎች በተፈጥሮ ስንጠቀም ፣አጠቃቀማችንን ቁጠባ አዘል ማድረግ ያስፈልገናል፡፡ ሥራ ፈትቶ በተፈጥሮ ውስጥ በመንቀዋለል ሰው በቀላሉ በሽታ ላይ ሊወድቅ ይችላል፣እንደ ትኩሳት ያለ ዱብዳ ላይ፡፡»
***