አዲሱን ዓመት አንድ ብለን ከጀመርን ሰባት ቀን ሞላን፡፡ አንድ ሳምንት ከ2015 ዓ.ም. ላይ አነሳን ማለት ነው፡፡ በዚህች ባሳለፍነው አንድ ሳምንት ውስጥ ግን ብዙ መረጃዎች ጆሮዋችን ደርሷል፡፡ በሳምንቱ ከሰማናቸው አገራዊ ወሬዎች ሁሉ ግን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሲሚንቶ ግብይትን የተመለከተው መግለጫ በግሌ ትኩረቴን ስቦታል፡፡
በርካታ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ዜናዎች መሀል የሚኒስቴሩ መረጃ ትኩረቴን የሳበው በምክንያት ነው፡፡ የሲሚንቶ ገበያና አጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱን መስመር ማስያዝ ለመንግሥት የሮኬት ሳይንስ ሆነበት ይመስል አሁን ሌላ መፍትሔ ያለውን ውሳኔ ይዤ መጥቻለሁ ማለቱ ነው፡፡ እስካሁን የወጡት ለቁጥር የሚታክቱ መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉ መመርያዎች ምንም ሳይፈነዱ በአዲሱ ዓመት የመጀመርያው ሳምንት አጋማሽ ላይ ‹‹ሲሚንቶ …›› በሚል ዘመኑን መጀመሩም ለእኔ አስደማሚ አስደናቂም ሆኖብኛል፡፡ አዲሱ መመርያ የተለመደ ግን አዲስ የፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡
የሲሚንቶ ገበያ ባለፈው ዓመት እንዲሁ መግለጫ ሲሰጥበት፣ ማስጠንቀቂያዎች ሲጎርፉበት፣ ከዚህ በኋላ ገበያው ይስተካከላል ተብሎ ሲፎከርበት ነበር፡፡ ሕገወጥ ያላቸውን እንደሚቀጣ በመናገር ዓመቱን መጨረሱንም እናስታውሳለን፡፡
መረን የለቀቀውን ገበያና ጣሪያ የነካውን የሲሚንቶ ዋጋ ወደታች ለማውረድ በፌዴራልና በክልል መንግሥታታ ጭምር የተለያዩ ማሳሰቢያዎች የተሰጡበት ነበር፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ ሲሚንቶ የሚሸጠው በዚህን ያህል ዋጋ ነው፡፡ ከዚህ በላይ የሸጠ ይቀጣል፤›› የሚሉ ማስጠንቀቂያዎችን ሰምተናል፡፡ የትርፍ ህዳግ መጠን ሁሉ ተወስኗል ሲባል የተላለፈው ውሳኔ በተግባር ሳይታይ እንደሆነ እንደገና ለሲሚንቶ አዲስ ዋጋና መመርያ ወጥቷል፡፡ የሲሚንቶ አከፋፋዮች ከገበያ እንዲወጡ ከተደረገ መፍትሔ ይገኛል የሚለውንም ዜና ባለፈው ዓመት ሰምተን እንደነበር አይነዘጋም፡፡ ሲሚንቶ በኮታ እንዲሰጥ ሁሉ ተብሏል፡፡ ብቻ የሲሚንቶ ገበያን ለማስተካከል ሲባል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የተደረጉ ውይይቶች ብዙ ናቸው፡፡ የአሠራር ማሻሻያ ተብለው የወጡ መመርያዎችና የሕዝብ ማስታወቂያዎችም በተደጋጋሚ የመውጣታቸውን ያህል ገበያ አላረጋጉም፡፡ ዋጋ አላስቀነሱም፡፡ እጥረቱን አልቀረፉም፡፡
በነገራችን ላይ በሲሚንቶ ጉዳይ የምንሰማቸው የተለያዩ መረጃዎች በ2014 ዓ.ም. ጎልተው ይታዩ እንጂ ለ15 እና 20 ዓመታት በተመሳሳይ መንገድ ስንሰማቸው የነበሩ ግን ምንም ውጤት ያላመጡ ናቸው፡፡ ለ20 ዓመታት የሲሚንቶ ችግር ያለመፈታቱም ነው ነገሩን የሮኬት ሳይንስ አድርጎታል ለማለት የዳዳሁት፡፡
ዘንድሮም ዓመቱን አንድ ብለን በጀመርንበት አራተኛው ቀን ላይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ይፋ በሆነ መንገድ ሥራውን የጀመረው በዚሁ የሲሚንቶና ገበያ ጉዳይ መሆኑ ቢያስገርም ትክክል ነው፡፡ የሰሞነኛውን የአዲስ ውሳኔ ለማሳወቅና ነገሩን ክብደት ለመስጠትም የሲሚንቶ ዋጋን የተመለከተውን መግለጫ የሰጡት ክቡር ሚኒስትሩ ናቸው፡፡
ይህ መግለጫ ባጭሩ ፋብሪካዎች የፋብሪካ የመሸጫ ዋጋቸውን ያሳወቀበት ነው፡፡ ይህ የመንግሥት ዕርምጃ አሁን ካለው የሲሚንቶ ገበያ መዘበራረቅና የተጋነነ ዋጋ አንፃር ሲታይ ምንም ስህተት የሌለው ነው ልንል እንችላለን፡፡ ችግሩ ተፈጻሚነቱ ነው፡፡
የፋብሪካ መሸጫ ተብሎ የተተመነው ዋጋ እንደየፋብሪካዎቹ ቢለያይም ዝቅተኛው 510 ብር ከፍተኛው ደግሞ 646 ብር እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ ችግሩ ከፋብሪካው በዚህን ያህል ከወጣ ሸማቹ ዘንድ ሲደርስ የሚሸጥበት ዋጋ አሁን ካለው በእጅጉ ካልቀነሰ ትርጉም አይኖረውም፡፡ አዲሱ ተመን ፋብሪካዎችን ብቻ የጠቀመ ይሆናል ማለት ነው፡፡
እንዲህ ያለውን ውሳኔና ዕርምጃ ባለፈው ዓመት በተደጋጋሚ የሰማነው ከመሆኑ ያህል ሰሞኛውን ዕርምጃ በትክክል ስለመተግበሩ ብንጠራጠር ትክክል ነን፡፡ እስካሁን በተመሳሳይ የተወሰዱ ዕርምጃዎች ለአመል እንኳን ሲተገበር አላየንምና፡፡ አሁንም የተላለፈው መመርያም ሆነ ውሳኔ ትርጉም የሚኖረው ገበያው ሲረጋጋ አንዳንዶቹ ሲሚንቶ ከአንድ ሺሕ ብር በታች ሲሸጥ ብቻ ነው፡፡
በንግድና ትስስር ሚኒስቴር በባለሙያዎች ተጠንቶ የቀረበው ለፋብሪካዎች የተሰጠው ቁርጥ ዋጋ ፋብሪካዎቹ የሚሸጡበት ዋጋ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ከፋብሪካ ከወጣ በኋላ የትራንስፖርት፣ የጫኝና አውራጅና መሰል ወጪዎች ታሳቢ ተደርጎ ሲሚንቶው የሚሸጥበት ዋጋ ሲታሰብ ደግሞ አሁንም ገበያውን ምን ያህል ያረጋጋል? ያለውን የምናየው ይሆናል፡፡
ስለዚህ ማስተካከያ የተደረገው ፋብሪካዎቹ እንጂ ችርቻሮ ሲሸጥ ምን ያህል ዋጋ ያወጣል የሚለው የታሰበበት አይመስልም፡፡
ከሰሞኑ ከሌላኛው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የተሰጠው መረጃ እንደሚነግረን ደግሞ የአገሪቱ ዓመታዊ የሲሚንቶ ፍጆታ 50 ሚሊዮን ቶን ሆኖ ሳለ አሁን የሚመረተው ከሰባት ሚሊዮን ቶን ያልበለጠ ነው፡፡ ይህ ማለት በተጨባጭ የአቅርቦትና ፍላጎት ክፍተት ያለ መሆኑን ያሳየ ነው፡፡
አስገራሚው ነገር በአገራችን ያሉ የሲሚንቶ ፋብሪካ ዓመታዊ የማምረት አቅማቸው እስከ 18 ሚሊዮን ቶን የሚደርስ ሆኖ እያለ እያመረቱ ያሉት ግን 50 በመቶን ነው፡፡ ለዚህም ነው አሁን ያሉት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች 18 ሚሊዮን ቶን ማምረት ሲችሉ ሰባትና ስምንት ቶን ብቻ እያመረቱ ገበያውን ለማረጋጋት በአናት በአናቱ አዳዲስ ውሳኔዎች ቢወሰኑ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል የሚገባን፡፡
እንዲህ ካለው ተጨባጭ መረጃ መረዳት የምንችለውም አንድ ቁም ነገር ከጠቅላላ የአገሪቱ የሲሚንቶ ፍላጎት አንድ አምስተኛው ብቻ ገበያ ላይ ካለ ያለጥርጥር እጥረት መኖሩ ነው፡፡ ስለዚህ የችግሩ ምንጭ እጥረቱ ቢሆንም በዚህ እጥረት ተጠቃሚ ለመሆን ጡንቻቸው የፈረጠመ ተዋንያኖች አጋጣሚውን እየተጠቀሙበት ስለሚቀጥሉ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር የሚያስፈልግ ነው፡፡ የመመርያ ጋጋታና ማስጠንቀቂያ ሳይሆን በግድም ቢሆን ፋብሪካዎቹን በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ማድረግ ነው፡፡
የሚኒስቴሩ ቁጥጥር እንደተጠበቀ ሆኖ ዘላቂ መፍትሔው የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ በግማሽ አቅማቸው ለምን እያመረቱ እንደሆነ ምክንያቱን አውቆ በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ማድረግ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ባይቀረፍም ችግሩን ግን ያቃልላል፡፡
በግማሽ አቅም ማምረት ማለት ግን ሁለት ነገሮችን ያሳያል አንዱ ፍላጎት ማጣት ነው፡፡ ሌላው በትክክል ለማምረት የሚያስችል አቅም ማነስ ወይም የአቅርቦት እጥረት ነው፡፡
ይህ እጥረት ጥሬ ዕቃን የሚመለከት እንደማይሆን የሚታመን ሲሆን ችግሩ ከዚህ ውጪ ባለ ምክንያት ከሆነ ይህ ለምን አልተፈታም ብሎ ለዚህ መልስ መስጠት የመንግሥት ሥራ ነው፡፡
ስለዚህ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አዲሱ ውሳኔው ውጤት ያስገኝ አያስገኝ ቁልፍ መሆን ያለበት ጉዳይ ከአቅማቸው በታች እያመረቱ ያሉት ፋብሪካዎች ወደ ሙሉ አቅም እንዲሸጋገሩ ማስቻል ነው፡፡
በነገራችን ላይ ሲሚንቶ ጥብስ በሆነበት አገር ከአቅም በታች ማምረት ምን የሚሉት ነገር ነው? ሰበብ በመፈለግ ከአቅም በታች ማምረት ችግሩ ለማባባስ ሆን ተብሎ የሚከወን ሊሆን ቢችልስ? ስለዚህ በአቅም እንዲያመርቱ ማድረግ ግድ መሆን አለበት የሚባለው፡፡