ቡናን ለዓለም ያበረከተች አገር ስለመሆኗ በማያሻማ ቋንቋ የሚነገርላት ኢትዮጵያ፣ ለዘመናት አንጡራ ሀብቷ የሆነውን የቡና ምርት ለዓለም ባጋራችበት ልክ የሚገባትን ጥቅም ያህል ሳታገኝ መቆየቷ የአደባባይ ሃቅ ነው፡፡
‹‹አረንጓዴ ወርቅ›› የሚል መጠሪያ ተሰጥቶት ከቆየው ባለጣዕም ተክል፣ ማሳ ለማሳና ዱር ለዱር እየተንገላታ ለገበያው እንካቹ ካለው ገበሬ ይልቅ በአቋራጭ መንገድ ገብቶ ገበያውን የሚያጦዘው አካልና ተቀባዩ የባዕድ አገር ገዥ ይበልጡን ሲጠቀምና ስሙን ሲያዳብር እንደቆየ በርካታ አመላካቾቹ አሉ፡፡
የተለያየ ጣዕም ያላቸውን የተፈጥሮ ቡና ዝርያዎች በተለያየ መልክዓ ምድር የምታመርተው አገር በዓመት ውስጥ ከዘርፉ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ይህን ያህል ጊዜ መጠበቋ የሚያስገርማቸው አካላት ቀላል አይደሉም፡፡
‹‹የኢኮኖሚ ዋልታ›› የሚባለው ቡና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከውጭ ንግድ ጋር ተያይዞ የሚፈለገውን ያህል ላለመራመዱ ሲነሱ የቆዩ በርካታ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡ የቡና ዋጋ መዋዠቅ፣ የገዢዎች ቀልጣፋ ያልሆነ የግዥ ሒደት፣ ከሎጂስቲክስ ጋር ተያይዞ በተለይም የኮንቴይነር አቅርቦት እጥረት የሚጠቀሱ ሲሆኑ፣ ነገር ግን በዋናነት እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ አለመላክ፣ የፀጥታ ችግር፣ የቡና ምርት ከአንዱ ወደ ሌላ ቦታ ሲጓጓዝ የሚያጋጥሙ የተደራጀ ስርቆትና ዝርፊያ እንዲሁም የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎች ተጠቃሾቹ መሆናቸውን የዘርፉ ተዋንያን ይናገራሉ፡፡
ለበርካታ ጊዜያት በሕገወጥ የቡና ንግድና ዝውውር ላይ ቁጥጥር እየተካሄደ ነው ተብሎ ቢገለጽም፣ ችግሩ መልኩን እየለዋወጠ በመቀጠሉ የውስን ግለሰቦች ኪስ እየደለበ የቡና ኤክስፖርቱ ደግሞ እያሽቆለቆለ መሆኑን ጉዳዩን ሲከታተሉ የቆዩ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ባሉበት ሁኔታ በተለይም የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ምርታማነትና የግብይት ሥርዓትን የማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠው የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ከአሠራርና አደረጃጀት ጋር ተያይዞ ያደረጋቸው ለውጦች (ሪፎርሞች) ከዘርፉ ምርታማነትና የወጭ ንግድ ገቢ መጨመር ጋር ተያይዞ መሻሻሎች እንዲስተዋሉ ማድረጉን በርካቶች ይናገራሉ፡፡
ለአብነትም ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ከቡና የወጭ ንግድ ለቢሊዮን ዶላር የተጠጋና ከዚያም የተሻገረ ገቢ ማግኘቷ የሚገለጽ ሲሆን፣ ይህም አገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች የምታገኘው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ጭምር እንዲይዝ እያስቻለ ነው፡፡ በ2013 የበጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከቡና የወጪ ንግድ ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ 907 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ፣ ይህም 248,311 ቶን ቡና በመላክ የተገኘ መሆኑን የመንግሥት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት አገሪቱ የቡናን ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በመጠንም ሆነ በገቢ ከፍተኛ ገቢ ማግኘቷ የተገለጸ ሲሆን፣ በ2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ ወደ የተለያዩ የዓለም አገሮች ከላከችው 300 ሺሕ ቶን የቡና ምርት 1.4 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች፡፡
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ኤክስፖርት ካደረገችው አጠቃላይ ምርቶቿ ያገኘችው ገቢ 4.12 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከአንድ አራተኛ በላይ የሚሆነው ገቢ የተገኘው ከቡና ምርት ኤክስፖርት ነበር፡፡ በወቅቱ ኤክስፖርት ከተደረጉት ምርቶች ውስጥ 72 ከመቶ የሚሆኑት የግብርና ውጤቶች ሲሆኑ፣ ከዚህ ውስጥ 35 በመቶ የሚሆነው ቡና ነው፡፡
የውጭ ምንዛሪ ለአገሪቱ በማምጣት ግንባር ቀደም የሆነው የቡና ምርት ኤክስፖርት ለአገሪቱ የምንዛሪ ፍላጎት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ በተጠናቀቀው ሳምንት አጋማሽ የኢትዮጵያ የቡና ቀን በተከበረበት መድረክ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ተናግረዋል። ሚንስትሩ አክለውም በተጠናቀቀው ዓመት ከተገኘው የውጭ ምንዛሪ በላይ በእጥፍ ለማምጣት ጥረት ሊደረግ እንደሚገባና አርሶ አደሩም ሆነ ባለሀብቱ ጠንክረው መቀጠል ከቻሉ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡
የቡና ኤክስፖርት የተሻለ የውጪ ምንዛሪ እንዲያስገኝ ምን ተሠርቷል?
የቡናና ሻይ ባለሥልጣን እንዳስታወቀው፣ የኤክስፖርት ግቡን ለማሳካት ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የሎጂስቲክስ አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን በኮንቴነር አቅርቦት፣ በምድር ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥና በአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የታዩ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ተደርጓል፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖች (በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በዱባይ) እና በበይነ መረብ በሚካሄዱ ዝግጅቶች ላይ አገሪቱ በመሳተፍ ቡናዋ እንዲተዋወቅ ተደርጓል፣ አዳዲስ ገበያን በማፈላለግ በኩል የእስያ አገሮች ላይ ትኩረት ተደርጎ በመሠራቱ በተለይም ቻይናና ታይዋን ወደ ምርጥ አሥር ዋና የቡና ገዥ አገሮች ተርታ እንዲገቡ ስለመደረጉ ተገልጿል፡፡
በባለሥልጣኑ የገበያ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር እንደሚሉት፣ መሥሪያ ቤቱ ሁለት ዓይነት ስትራቴጂዎችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው ነባር ወይም ትላልቅ ገዥ የሆኑ አገሮች ገበያ ላይ መቆየት ሲሆን፣ በሌላ በኩል አዳዲስ ገበያ በማፈላለግ የተሠራው ሥራ ይጠቀሳል፡፡ በተለይም ወደ እስያና የሩቅ ምሥራቅ አገሮች በማምራት ቻይና፣ ታይዋን፣ ሩሲያ በኢትዮጵያ የቡና ገዥ አገሮች ዝርዝር ውስጥ ለማካተት የተሠራው ሥራ ቀላል አለመሆኑን አቶ ሻፊ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ቤልጂየም፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና ጣሊያን ነባር የአውሮፓና የአሜሪካ ገበያዎች የኢትዮጵያን ስፔሻሊቲ ቡና የሚወስዱ በመሆናቸው በእነዚህ ገበያዎች ለመቆየት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይገልጻሉ፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ የተደረገው የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ጥራት ውድድር (ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ) በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አስተባባሪነት በተሳካ ሁኔታ መካሄዱ አገሪቱ ከቡና ባገኘችው አጠቃላይ ገቢ ላይ ጉልህ አበርክቶ እንደነበረው የቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ የዚህን ያህል የውጭ ምንዛሪ ቡና ሊገኝ ከቻለባቸው ምክንያቶች ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና ዋጋ እያደገ መምጣትና የብራዚልና የኮሎምቢያ ቡና በውርጭ መመታት ከግምት ውስጥም ሊገባ እንደሚገባው ዘርፉን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የባለልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር የኢትዮጵያ ቡና የገበያ መዳረሻን በማስፋት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ለዓብነትም ደቡብ ኮሪያ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የቡና መዳረሻ አገሮች ዝርዝር ውስጥ አናሳ ድርሻ የነበራት መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ወቅት ደቡብ ኮሪያና ቻይና የኢትዮጵያን ቡና በስፋት እየገዙ ያሉት በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ምክንያት እንደሆነ አስታውቀው ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ለሦስት ዙሮች የተካሄደው የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ውድድር የአገሪቱን ገጽታ ከመቀየሩ ባለፈ አዳዲስ የቡና ዓይነቶች (ዝርያዎች) የወጡበት ነው ተብሏል፡፡ እነዚህን ዝርያዎች በጥናትና ምርምር ተደግፎ ወደ ብዜት ለማስገባት በባለሥልጣኑ በኩል ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩም ተገልጿል።
በውድድሩ አሸንፎ ወደ ውጭ ገበያ የወጣው ቡና በተሸጠበት አገር ብቻ ሳይሆን ገዥው ባለባቸው የተለያዩ አገሮች ማዕከሎች ተከፋፍሎ ስለሚሄድ የቡና ተቀባይነትን የሚጨምር እንደሆነም ይገልጻል፡፡
በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ የሚያሸንፈው ቡና ጥቅሙ በውድድሩ ለተሳተፈው አርሶ አደር ብቻ አይደለም የሚሉት የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ገዥዎች አሸናፊው አርሶ አደር በሚገኝበት አካባቢ በመምጣት የገበያ ትስሰር ስለሚፈጥሩ በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች ቡና አብቃይ አርሶ አደሮችንም ጭምር ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ያስረዳሉ፡፡
በዘንድሮው የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ 2022 ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ቡና በጥራቱ ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገብ ዓለም ዓቀፍ ኦንላይን (በበይነመረብ የተደረገ) ጨረታ አሸናፊ ሆኗል፡፡ በጨረታው አንድ ኪሎ ግራም ቡና 884.10 ዶላር ወይም 47,236.23 ብር ተሽጧል፡፡
በመጀመሪያው ዙር ውድድር አንደኛ የወጣው አርሶ አደር አምስት ኬሻ (300 ኪሎ) ቡና በመሸጥ ስድስት ሚሊዮን ብር እንዳገኘ የተገለጸ ሲሆን፣ በ2013 የበጀት ዓመት ቁጥሩ ጭማሪ በማሳየት 19 ኬሻ (1,140 ኪሎ) በመሸጥ ወደ 16 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር በግለሰብ ደረጃ እንደተገኘ ተጠቁሟል፡፡ ሦስተኛውን ዙር ያሸነፋውና ከሲዳማ ክልል የመጣው ቡና አብቃይ አርሶ አደር አቶ ለገሠ ቦታሳ ደግሞ ለውድድሩ ያቀረበውን ቡና ከ22.6 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ዋጋ ሸጧል፡፡
አገሪቱ ለቡና ምርትና ኤክስፖርት የ15 ዓመት ስትራቴጂ ይፋ ማድረጓ የሚታወስ ሲሆን፣ በስትራቴጂው ከተቀመጡ ግቦች ውስጥ ከቡና ኤክስፖርት አገሪቱ ከአምስት ዓመታት በኋላ ዓመታዊ ገቢዋ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል የሚል ግብ ተጥሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ አርሶ አደሩ ጋር የሚደርሰው ገቢ 3.6 ቢሊዮን ዶላር (80 በመቶ) ይሆናል የሚል ሐሳብ በዕቅዱ ይገኝበታል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በሦስት ምዕራፎች በተተለመው የ15 ዓመት ስትራቴጂ፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ቡና ወደ 1.26 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ከፍ ለማድረግ ታቅዷል።
ምንም እንኳን የቡና ኤክስፖርት ያለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት እንቅስቃሴ አበረታች ውጤቶችን ያሳየ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተው ጦርነትና በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው ግጭት በተለይም ቡና አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ሥጋታቸውን የሚያነሱ በርካቶች ናቸው፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን እ.ኤ.አ. ከጃንዋሪ 1 ቀን 2022 ጀምሮ ተፈጻሚ መሆን የጀመረው ኢትዮጵያ ከአሜሪካ መንግሥት ታገኘው የነበረው ከኮታና ከቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድል (አጎዋ) መሰረዝ ውሳኔ ሌላው ምናልባትም ከአገሪቱ ጋር የሚደረገውን የቡና ግብይት እንቅስቃሴ ላይ ጥላ እንዳያጠላ በሥጋትነት ሲነሳ ይሰማል፡፡
ኢትዮጵያ ከአጎዋ በመሰረዟ ከቡና ጋር ተያይዞ እስካሁን ድረስ የፈጠረው ተፅዕኖ የለም የሚሉት አቶ ሻፊ፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት አጋማሽ ከኢትዮጵያ ምርጥ አሥር ቡና ገዥ አገሮች ዝርዝር ውስጥ ወገብ ላይ የነበረችው አሜሪካ፣ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከጀርመን ቀጥላ ሁለተኛዋ ከፍተኛ ቡና የገዛች አገር ሆና ማሳለፏን በማስረጃነት ይገልጻሉ፡፡
ከኮቪድ አንስቶ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ተፅዕኖ ሳያሳድሩ እንዳማያልፉ የታወቀ ቢሆንም፣ መሠረታዊ የሚባል ተፅዕኖ በተለይም በቡና የውጭ ንግድ እስካሁን እንዳልተፈጠረ በመግለጽ፣ በ2015 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ 360 ሺሕ ቶን ቡና ወደ ውጪ በመላክ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡