Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቢኖሩ ግጭቶች ላይከሰቱ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ይሆን ነበር›› አቶ ፋሲካው ሞላ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ከአራት ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን ከወጣ በኋላ ሪፎርም ካደረገባቸው የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል ቀዳሚው የሲቪል ማኅበረሰብ ዘርፉን የሚመራው ባለሥልጣን ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም. የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ከወጣ በኋላ ከሁለት ሺሕ በላይ አዳዲስ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ ወስደው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ከአዋጁ ጋር አብሮ እንደ አዲስ የተቋቋመው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣንም አዋጁን ለማስፈጸም እስካሁን 18 መመርያዎችን አዘጋጅቷል፡፡ አማኑኤል ይልቃል ከባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ጋር ተቋሙ ከሪፎርሙ በኋላ ስለነበረው የሦስት ዓመት ቆይታ፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ላይ ስላደረሰው ተፅዕኖ፣ ድርጅቶቹ ስለሚያገኟቸው ፈንዶችና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡-  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የሚረዳቸው በምን ዓይነት መንገድ ነው?

አቶ ፋሲካው፡- ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ብለን ስናስብ የመደራጀት መብት መገለጫ ነው፣ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ፈርማ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ የመደራጀት መብት ተረጋግጧል፡፡ ይህ መብት የሚገለጽበት አንዱ መንገድ ደግሞ ዜጎች በነፃነት ማኅበር ወይም ድርጅት አቋቁመው መሥራት የሚችሉበት ዕድል ሲፈጠር ነው፡፡ ይህም በሕገ መንግሥቱና ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የተረጋገጠውን የመደራጀት መብት በተሟላ መንገድ ማስፈጸም ነው፡፡ ስለዚህ ውስጡ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አለው ማለት ነው፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ስንል ለትርፍ ያልተቋቋሙ፣ ነፃ፣ ገለልተኛ፣ በተለይ ደግሞ የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸው ለሕዝብና ለአገር ጥቅም የሚሠሩ ናቸው፡፡ አገሮች እነዚህን ድርጅቶች በተለያየ መንገድ ያስተዳድራሉ፡፡ እኛ አገር እነዚህን ድርጅቶች የሚያስተዳድር በ2011 ዓ.ም. የወጣ አዋጅ አለን፡፡ በሌላ ሕግ የማይተዳደሩ ማኅበራት በዚህ አዋጅ ይመራሉ፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ዓይነት ባህሪ ኖሯቸው ደግሞ በተለየ መንገድ የሚተዳደሩ አሉ፡፡ የሠራተኞች ማኅበራትና የኅብረት ሥራ ማኅበራት በባህሪያቸው ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቢሆኑም የሚተዳደሩት በሌላ አዋጅ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሕጋዊ ዓላማን ለማሳካት ከአገር ሕግና ሞራል ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለማከናወን የተቋቋሙ ናቸው፡፡ በዚህ መንገድ ትርጉም ሰጥተን እየሠራን ነው ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- በ2011 ዓ.ም. የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ከፀደቀ በኋላ በዘርፉና ዘርፉን በሚመራው ተቋም ላይ የተደረገው ለውጥ ምንድነው?

አቶ ፋሲካው፡- በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዘመናዊ ታሪክ የሚጀምረው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1952 ዓ.ም. የማኅበራት ምዝገባ ደንብ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ የደርግ ዘመነ መንግሥት ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥሩ ጊዜ አልነበረም፡፡ በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ያለው ደግሞ የሽግግር ጊዜ ከሚባለው ከ1983 እስከ 2001 ዓ.ም. እና ከዚያ በኋላ ያለው በሚል ለሁለት መከፈል የሚችል ነው፡፡ በደርግ ጊዜ ተከልክሎ ስለነበር የሽግግር ጊዜው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቁጥርና ተሳትፎ የጨመረበት ነው፡፡ በኋላ ደግሞ በወቅቱ የነበረው መንግሥት ድርጅቶቹ በተለይ የውጭ ኃይሎች ዓላማ ማራመጃ ናቸው የሚል ግምገማ በማስቀመጥ በ2001 ዓ.ም. የበጎ አድራጎቶች ማኅበራት አዋጅ አውጥቷል፡፡ ከሕጉ መውጣት በኋላ ያለው ጊዜ በጣም አስቸጋሪ የሚባል ነበር፡፡ ይኼ ሕግ በበጎ ጎኑ ሲታይ ተበታትኖ በተለያዩ ሕጎች ላይ የነበረውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጉዳይ ሁሉን አቀፍ በሆነ አንድ ሕግ እንዲመራ ያደረገ ነው፡፡ ሕጉ ከወጣ በኋላ በአሁኑ ፍትሕ ሚኒስቴር ውስጥ በነበረ አንድ ክፍል ሲመራ ለነበረው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጉዳይ የበጎ አድራጎቶች ማኅበራት ኤጀንሲ በሚባል ራሱን በቻለ ተቋም እንዲመራ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ሕጉ ብዙ ገዳቢ ነገሮች የተቀመጡበት ነው፡፡ የማኅበራቱ እንቅስቃሴ ከዴሞክራሲ፣ ከሰብዓዊ መብትና ከግጭት አፈታት ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ደረጃ የቀጨጨበትና ቁጥራቸውም በጣም የቀነሰበት ነው፡፡ መብትና አዲቮኬሲ ላይ ሲሠሩ የነበሩ ድርጅቶች ዓላማቸውን እየቀየሩ ልማትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የተንቀሳቀሱበት ጊዜ ነው፡፡ በተለይ መብት ላይ ለሚሠሩ ድርጅቶች ድጋፍ የሚደረግበት፣ ክልከላ የሚበዛበት ነበር፡፡ ከሕጉ በላይ ደግሞ ሕጉ የተፈጸመበት መንገድ በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡

ኤጀንሲው ሲቪል ማኅበረሰቡ የሌላ ፖለቲካ አጀንዳ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ስለሆነ በደንብ መቆጣጠርና መከታተል ያስፈልጋል፣ ከማብቃት ይልቅ ዕርምጃ መውሰድና ማደግን እንደ ስኬት የሚወስድ ነበር፡፡ አገራዊ ሪፎርሙ በ2010 ዓ.ም. ከመጣ በኋላ ቀድመው መቀየርና መስተካከል አለባቸው ተብለው ከቀረቡ ጉዳዮች መካከል አንደኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጉዳይ ነው፡፡ በወቅቱ መብትን ያጠበቡ ተብለው ከተለዩት ሕጎች ከሁሉም ቀድሞ የተሻሻለውና የፀደቀው የዚህ ዘርፍ አዋጅ ነው፡፡ የድሮው አዋጅ ተሽሮ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ሲወጣ ቀድሞ የነበሩት በርካታ ገደቦች በሙሉ ተነስተዋል፡፡ ከውጭ አገር ሀብት አሰባስቦ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት መሥራት ይከለከል ነበር፣ የሲቪል ማኅበሰረብ ድርጅቶች የሚኖሯቸው ሥራዎች እየተገመገመ የሚከለከልበት ጊዜ ነበር፣ ፈቃድ ለማግኘት መሥፈርቶቹ ጥብቅ ነበሩ፣ ኤጀንሲው በድርጅቶቹ ላይ የማፍረስና የማገድ ዕርምጃ ሊወስድ ይግባኝ ማለት አይቻልም ነበር፡፡ አዲሱ ሕግ ግን እነዚህን ሁሉ አንስቶ ያስቀመጠው ግዴታ ሕጋዊነትና የአገሪቱን የሞራል እሴት ጠብቆ መንቀሳቀስን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመገፋፋት ጉዳይ ለውጭ አገር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተከልክሏል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው የተፈቀደ ነው፡፡

አዲሱ ሕግ ይዞ የመጣው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጉዳይ የመብት ጉዳይ ነው የሚል ምልከታን ነው፡፡ ድርጅቶቹ የአገር ግንባታ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የአገር ልማት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው የሚል መነሻም አለው፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሚያከናውኗቸው ሥራዎች የሕዝብን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይቻላል ብሎም ያስባል፡፡ ለዚህም ድጋፍና ክትትል ይደረጋል፡፡ አዋጁ በጥር 2011 ዓ.ም. ከፀደቀ በኋላ ወደ ሥራ የተገባው መጋቢት ላይ ነው፡፡ ሕግ ማውጣት በራሱ ግብ ስላልሆነ ሕጉን ለማስፈጸም የተቋቋመው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን፣ ሕጉ በተሟላ መንገድ ለመተግበር ሪፎርም ማድረግ ነበረበት፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ተኩል ጥልቅ ሪፎርም አድርገናል፡፡ በዚህም ለዘርፉ ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች ተፈጥረዋል ብለን እናስባለን፡፡ ተቋማዊ አቅሙ የተገነባ፣ አዋጁን ተረድቶ ማስፈጸም የሚችል፣ አዋጁን የሚመስል ተቋማዊ አሠራር የዘረጋ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ የሚያከናውን ተቋም ገንብተናል፡፡ ከፌዴራል፣ ከክልልና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ጠንካራ ተቋማዊ ቅንጅት ፈጥረን ለውጡ ወደ ታች እንዲወርድ አድርገናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በአገራዊ ጉዳይ ላይና ዓላማን በተሟላ መንገድ ከመፈጸም አንፃር ዘርፉ ውስጥ ከፍተኛ መነቃቃት ታይቷል፡፡

ከዚህ ቀደም ሲቪል ማኅበረሰቡ ይኼንን ይፈራው ነበር፡፡ ከዚህ ተቋም ስልክ ከተደወለላቸው ምን ዕርምጃ ሊወሰድብን ነው የሚል ሥጋት ሲፈጠርባቸው ቆይቷል፡፡ አሁን ድርጅቶቹ ችግር ሲያጋጥማቸው መጀመርያ የሚያንኳኩት እዚህ ተቋም ዘንድ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ተቋም ፈጥረናል፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡ ሳይሳተፍ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ መደረግ የለበትም የሚል መርህ አስቀምጠናል፡፡ የተሠሩት ሥራዎች አመርቂና አበረታታች ቢሆኑም መከናወን ከሚገባው፣ ለዘርፉ ከተፈጠረው ሕጋዊና ተቋማዊ ሁኔታ አንፃር አሁንም ያልተከናወኑና መሠራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህ ላይ በደንብ መሥራት ያስፈልገናል፡፡

ሪፖርተር፡- አልተከናወኑም የሚባሉት ጉዳዮች ምንድናቸው?

አቶ ፋሲካው፡- ብዙ ክልከላዎች የነበሩበት የበፊቱ አዋጅ የሲቪል ማኅበረሰብ በዘርፉ ላይ ከፍተና ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ በተለይ ደግሞ ከመብት፣ ዴሞክራሲ፣ ከሰላምና ከግጭት አፈታት ጋር በተያያዘ በቂ አቅም፣ ዕውቀትና ልምድ እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡ ከዚህ ችግር ወጥቶ አሁን ከሚጠበቀው አንፃር ብዙ ሥራ ለማከናወን ብዙ ጥረት ቢያደርግም ውስንነቶች አሉበት፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ደርጅቶች በዴሞክራሲም በልማትም ግንባር ቀደምና አጀንዳ የሚቀርፁ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡ የአገርና የሕዝብን ጥቅም የሚያረጋግጥ መሆን አለበት፡፡ አገርና ሕዝብ ጥቅምን የሚጎዳ ነገር ሲያጋጥም መጀመርያ ቀርቦ ችግሮቹን ማስተካከል ያለበት ሲቪል ማኅበረሰቡ ነው፡፡ በትንሹ በአገራችን የተፈጠሩ ግጭቶችን ማየት እንችላለን፡፡ ጠንካራ፣ በንቃትና ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቢኖሩ ኖሮ እነዚህ ችግሮች ላይከሰቱ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ይሆን ነበር፡፡ ከግጭት እንድንወጣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቱ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ነበረበት፡፡

በእርግጥ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ከተፈጠረው ጦርነት ጋር በተያያዘ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሰላም ነው የሚያስፈልገው በሚል እዚህም መንግሥትን አናግረዋል፣ መቀሌ ድረስም በመሄድ የሲቪል ማኅበረሰቡ ተወካይ እናቶች እያለቀሱ ለምነዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ጥሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ዞሮ ዞሮ ከግጭት አላዳኑንም፡፡ ከዚህ በላይ አቅም ቢኖር፣ ከዚህ በላይ ቢሠራ፣ ዕቅድ ባለው መንገድ አንድ ጊዜ ሳይሆን በተካታታይ ቢከናወን ኖሮ ከዚህ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊቀረፉ ይችሉ ነበር፡፡ በእርግጥ ይኼም ብቻውን አይሆንም፣ የፖለቲካ ፍላጎት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ግን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አቅም የሚፈጥሩበትና የሚደገፉበት ሁኔታ ነው አሁን ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- አዋጁ በ2011 ዓ.ም. ከፀደቀ በኋላ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች 4,200 ደርሰዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ከሁለት ሺሕ በላይ የሚሆኑት በሦስት ዓመት ውስጥ የተመዘገቡ ናቸው፡፡ አጠቃላይ ቁጥሩን እንዴት ታዩታላችሁ? አገሪቱ ውስጥ በ4,200 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሥራ እየተሠራ ነው?

አቶ ፋሲካው፡- በዚህ ለውጥ ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰቡ ምኅዳር ሰፍቷል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው በቁጥር ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ የምናውቃቸው ሪፖርት የሚያቀርቡ 4,200 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተፈጠሩት፡፡ በንቃት የሚሳተፉ ናቸው፣ እንዲሁ ዝም ብሎ መዝገብ ላይ ብቻ ያሉ አይደሉም፡፡ ከለውጡ በፊት በየዓመቱ ይመዘገቡ የነበሩ ድርጅቶችን ዳታ ወስደን አሁን ካለው ጋር ስናነፃፅረው በየዓመቱ በ500 በመቶ አድጓል፡፡ ሕጉ የፈጠረው ነገር ብቻ ሳይሆን አፈጻጸሙም ያመጣው ነው፡፡ የምዝገባ ሥርዓቱ ቀልጣፋና ቀላል እንዲሆን ተደርጓል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አንድ ድርጅት ፈቃድ ለማግኘት የሚፈጅበት አማካይ ቆይታ 15 ቀናት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥም አሥር ቀናት አዲስ የሚመዘገብ ድርጅት ሳይመዘገብ ተቃዋሚ ካለ በጋዜጣ መውጣት ስላለበት ይኼ ተጨምሮ ነው 15 ቀናት የሆነው፡፡ አሁን ደግሞ የምዝገባ ሥርዓቱ በአካል ሳይሆን በኦንላይን ሆኗል፡፡ በፊት ፈቃድ ለማግኘት ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ማዘጋጀት ግዴታ ነበር፡፡ ከተዘጋጀ በኋላ ደግሞ ድርጅቱ የሚሰማራበትን ዘርፍ የሚመለከት ተቋም ፕሮፖዛሉን ይገመግማል፡፡ ይኼ ወራትን ይወስዳል፡፡ አንዳንዴም ይጣላል፣ ይኼ ይውጣ ይኼ ይግባ ይባላል፡፡ በተለይ መብት የሚል ነገር ካለበት እንዲወጣ ይደረግ ነበር፡፡ አሁን ይኼ ሁሉ ቀርቷል፡፡ የምዝገባ ሒደቱ ስለቀለለ የድርጅቶቹ ቁጥር ጨምሯል፡፡

በ115 ሚሊዮን ሕዝብ በፌዴራል ደረጃ የተመዘገቡ 4,200 ድርጅቶች ትንሽ ናቸው፡፡ ቱርክ ውስጥ 122 ሺሕ የተመዘገቡ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አሉ፡፡ ከአገራችን ሕዝብ ቁጥር፣ ስፋትና ሥራ የሚፈልጉ ጉዳዮች ብዛት አንፃር ያሉን ድርጅቶች አነስተኛ ናቸው፡፡ በአሥር ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅዳችን በ2022 ዓ.ም. 14 ሺሕ ይደርሳሉ የሚል ግምት አለን፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያለውን ቁጥር ስንመለከተው ግን በየዓመቱ የሚመዘገቡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር የመቀነስ አዝማሚያ ይታይበታል፡፡ አገራዊ ሁኔታው ተግዳሮት እንደፈጠረ ነው የእኛ ግምት፡፡ አገልግሎት ለማስተካከል የምዝገባ ሥርዓትም አቋርጠን ነበር፡፡ ነገር ግን ቁጥራቸው መጨመሩ ብቻውን ምንም ትርጉም የለውም ብለን ነው የምናስበው፡፡ ውጤታማ በሆነ መንገድ መሥራት፣ መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ እኛ ይኼንን ስንገመግመው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በመላ አገሪቱ ከ2,600 በላይ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ባለፈው ዓመት ዓይተናል፡፡ ይኼ ጤና፣ ትምህርት፣ ግብርና ማዘመን፣ በተለይ ደግሞ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ማኅበረሰቦች ተሳትፎና ለማረጋገጥ ከፍተኛ ለውጥና አስተዋፅኦ አለው፡፡ ከዴሞክራሲም አኳያ አድቮኬሲ የሚያደርጉ፣ ስለግጭት አፈታት፣ ስለሰላም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ቁጥር ጨምሯል፡፡ በእርግጥ ዘርፉ የልምድና የዕውቀት ውስንነት አለበት፡፡ መገንባትና መደገፍ አለበት ብለን እናስባለን፡፡ በትንሹ እንኳን ብናይ ግን በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከ45 ሺሕ በላይ ምርጫ ታዛቢዎችን ያንቀሳቀሱት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ናቸው፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ምርጫውን አንታዘብም ባሉበት ጊዜ ድርጅቶቹ ለአገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አረጋግጠዋል፡፡ በዓባይ ውኃ ላይ የኢትዮጵያን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ኮቪድ-19 ሲከሰት ዕርዳታ በማሰባሰብ፣ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ በጦርትና በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች ላይ ሰብዓዊ ዕርዳታ በማቅረብ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ ጦርነቱ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ሲስፋፋ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ስናቀርብ፣ 460 ሚሊዮን ብር በዓይነትና 17 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ በራሳቸው ደግሞ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን አገራችን ሰፊ ነው፣ ችግራችንም ውስብስብ ነው፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከዚህም በላይ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አስተዋፅኦ ማድረግ አለባቸው የሚል እምነት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም በነበረው ሕግ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በዴሞክራሲ፣ በመብትና በአድቮኬሲ ጉዳዮች የሚኖራቸው ተሳትፎ ላይ ምኅዳሩ የጠበበ እንደሆነ ተነስቷል፡፡ አሁንስ ከሕግ ማሻሻያ ባሻገር ይህንን መብት በሚፈለገው ደረጃ የሚያንቀሳቅሱበት ምኅዳር ተፈጥሯል?

አቶ ፋሲካው፡- በጣም የተሻለ ምኅዳር እንደተፈጠረ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ ለውጡ እነዚህ ተቋም ጋር ብቻ ሳይሆን እስከ ታች ወርዷል፡፡ በእኛና በድርጅቶቹ መካከል ገንቢ የሆነ ግንኙነት ተፈጥሯል፡፡ መጠራጠር፣ ዳርና ዳር ቆሞ መተቻቸት ሳይሆን በአገር ጉዳይ ላይ የበኩላችንን ማድረግ አለብን የሚል ግንኙነት ተፈጥሯል፡፡ አዋጁን ማስፈጸም የሚያስችልና የአገልግሎት አሰጣጡ 91.3 በመቶ እንዲደርስ ያደረገ ተቋማዊ አቅምም ተገንብቷል፡፡ ሥራው በሰው ላይ የተንጠለጠለ እንዳይሆን ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ 18 መመርያዎች ተዘጋጅተው ዘጠኙ ፀድቀው ወደ ሥራ እየገቡ ነው፡፡ ኦንላይን ሰርቪስ መስጠት ችለናል፡፡ ሥራችንን በቴክኖሎጂ ደግፈናል፡፡ ሌላው ዋና ነገር አሁን ያለው ለውጥ እኛ ተቋም ጋር ብቻ ሳይሆን የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ክልሎች ጋ ወርዷል፡፡ ከሚመለከታቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር ከፍተኛ ግንኙነት ተደርጓል፡፡ የፌዴራልና የክልል የመንግሥት ባለድርሻ አካላት የጋራ ጉባዔ ተቋቁሟል፡፡ በቋሚነት በየአራት ወሩ እንዲካሄድ በዚህ ዘርፍ ላይ ድርሻ ካላቸው ተቋማት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመን ያቋቋምነው ጉባዔ ነው፡፡ ሳይቆራረጥ ለአምስት ጊዜ ተካሂዷል፡፡ ይኼ ቅንጅት በዚህ ሁኔታ ስለተዘረጋ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሆነ ክልል ላይ ችግር ሲያጋጥማቸው በቀላሉ በስልክ በሚደረግ ግንኙነት መፍታት ይቻላል፡፡ ሁሉም ክልሎች ከፌዴራሉ አዋጅ ጋር የሚጣጣም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ አዘጋጅተዋል፡፡ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሲዳማና ጋምቤላ ክልሎች አዋጁን አፀድቀዋል፡፡ ሌሎቹ በረቂቅ ደረጃ አጠናቀውታል፡፡ ለውጡ የተሟላ እንዲሆን እየተሞከረ ነው፡፡ ይህ ቅንጅታዊ አሠራር እየጎለበተ ሲሄድ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ውጤታማ እየሆነ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ጥያቄ ያነሳሁበት አንድ ምክንያት ባለፈው ሳምንት ከ30 በላይ የሚሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በጋራ ‹‹አስቸኳይ ለሰላም ጥሪ›› በሚል ሊሰጡት የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ በፀጥታ ኃይሎች መከልከሉ ነው፡፡ ይህንን እንዴት ይመለከቱታል?

አቶ ፋሲካው፡- የተፈጠረውን ቅንጅታዊ አሠራር ያነሳሁት ምኅዳሩ ተፈጥሯል የሚለውን ለማሳየት ነው፡፡ ከሲቪል ማኅበረሰቡ ጋር በጋራ መሥራት እንደ አቅጣጫ ተወስዶ በክልልም በፌዴራልም ደረጃ ሁሉም የመንግሥት አካል የሚተገብረው ነው የሆነው፡፡ ጥቅምና አገልግሎታቸው እየታየ ስለሆነ፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡ ሕግን አክብሮ እንደፈለገ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል ምኅዳር ተፈጥሯል ብዬ ነው የማስበው፣ ያንን ያህል የከፋ ተግዳሮት የለም፡፡ እንደ ፖሊሲ እንደ መርህ ከተነጋገርን ይህ ምንም የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹም በየመድረኩ የሚመሰክሩት ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም የየራሱ ፍላጎት ይኖረዋል፡፡ ነጋዴው ለትርፉ ያሰላል፡፡ መንግሥትም ቢሆን በሚቀጥለውም መንግሥት ለመሆን ሥልጣኑን ሊያሰላ ይችላል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲውም የፖለቲካ ትርፉን ሊያሰላ ይችላል፡፡ የሲቪል ማኅበረሰቡ ግን የሚያሰላው ትርፍ የሕዝብና የአገር ተጠቃሚነት፣ የኢትዮጵያን አንድነትና የተሻለ መሆን ነው፡፡ ነገሮች ችግር ላይ በሚወድቁበት ጊዜ ሚዛኑን የሚያስጠብቀው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ነው፡፡ ይኼ በይፋ የሚታመን ነው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሌሎቹም የሚያነሱት ነው፡፡ መርህን፣ ሕግን፣ መረጃን፣ ማስረጃን መሠረት በማድረግ እንዲንቀሳቀስ ያስፈልፈጋል፡፡ አድርጌአለሁ ለማለት የምታደርገው ከሆነ መሸዋወድ ነው የሚሆነው፡፡ ይህንን አቅም እያጎለበቱ ሲሄዱ ታማኝነትን ያዳብራሉ፣ ይህ ደግሞ ለአገር ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ይህ ሁሉ ግልጽ የሆነ ፖሊሲ ባለበት፣ ተቋማችን ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ እያደረገ ባለበት፣ ለውጡ እስከ ወረዳ በወረደበት ምኅዳሩ የለም ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን እዚህም እዚያም መሸራረፎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ እነሱን እየተከታተሉ ማረም ነው የሚያስፈልገው፡፡ ሰሞኑን ተፈጠረ ስለተባለው ነገር ብዙም መረጃ የለኝም፣ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወር ከማየት ውጪ፡፡ ፕሮግራም እንዳለም የምናውቀው ነገር የለንም፡፡ መረጃው ስለሌለኝ እዚህ ላይ ብዙም አስተያየት ባልሰጥ የተሻለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ አገሪቱ ጦርነት ውስጥ ነች፡፡ ይኼ ጦርነት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ላይ የነበረው ተፅዕኖ ምንድነው? እንቅስቃሴያቸው እንዴት ይታያል?

አቶ ፋሲካው፡- የተፈጠረው ነገር እንዲህ መሆን አልነበረበትም፡፡ ነገር ግን መንግሥትና አገር ተገዶ ሌላ አማራጭ ስለጠፋ፣ በሌላው በኩል ያለው አሸባሪ ቡድን ጦርነትን ብቻ እንደ አማራጭ ስለወሰደ የተገባበት ነው፡፡ ሰላም ነው ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው፡፡ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም እዚህ ላይ ነው ትኩረት አድርገው መሥራት ያለባቸው፡፡ ሰላም መፍጠር ላይ በደንብ አቅደው፣ ውጤት በሚያመጣ መንገድ መሥራት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ጦርነቱ በእንቅስቃሴያቸው ላይ ትልቅ ተግዳሮት ነበረው፣ ምንም ጥርጥር የለው፡፡ ሰላም እንዲመጣና በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዕርዳታ እንዲያገኙም ጥረት አድርገዋል፡፡ ድጋፍ ላደረጉ ድርጅቶች የምሥጋና ፕሮግራምም አዘጋጅተናል፣ ዕውቅና ሰጥተናል፡፡ ተፅዕኖው ግን መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ሲቪል ማኅበረሰቡ ሥራውን ለመሥራት ወረዳ ድረስ የሚተገበር ፕሮጀክት ቀርፆ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች ሄደው መሥራት እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ደግሞ ችግሩ እንዲቆም እንዲህ ዓይነት ችግር እንዳይከሰት የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ነገሮች በሰላም እንዲጠናቀቁ ለማድረግ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዘላቂ መፍትሔ ላይ መሥራት ይጠይቃል፡፡

ትክክለኛ የኢትዮጵያ እውነታ እንዲታወቅ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ የዲፕሎማሲ ጫናው ከፍተኛ ነው፡፡ ግልጽ በሆነ መንገድ አሸባሪው ቡድን ሕፃናት ወታደሮችን ሲያሠልፍ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ብዙም እንደማይናገር እያየን ነው፡፡ ለዕርዳታ የገባ ነዳጅ ተዘርፎ ለጦርነት ሲውል እያየን ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ይህንን ሲናገር እያየን አይደለም፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡ ለመንግሥትም ለሌላውም እንዲያደላ አይደለም፣ ግን እውነታውን ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ በመረጃ ላይ በመመሥረት የኢትዮጵያን አቋም የማሳወቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የሲቪል ማኅበረሰቡ የሚንቀሳቀሰው ወቅትና ሁኔታን እያየ መሆን የለበትም፡፡ ለመርህ ተገዥ መሆን ያስፈልገዋል፡፡ በዲፕሎማሲው አካባቢ አገርና ሕዝብን የሚጠቅም ሥራ የመሥራት፣ እውነታው እንዲታወቅ የማድረግ፣ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የማድረግ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ የማቅረብ ሥራዎችን ማከናወን መቻል አለባቸው፡፡ ችግሮች ባረጀና ባፈጀ ዘዴ በጦርነት ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ መፈታት እንዲችሉ የሚያደርግ ባህል የመገንባት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አዋጁ በኅብረተሰቡ ውስጥ ይህንን ማድረግ የሚችሉ እንደሆኑ እምነት ያሳደረ ነው፡፡ መግለጫ በማውጣት የአንድ ጊዜ ሥራ ሳይሆን መሬት ላይ ያለውን ችግር በመረዳት ተከታታይ ባለው መንገድ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡ የሚያስፈልገው በእንዲህ ዓይነት ወቅት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ዘርፉ የሚያደርገው እውነታውን የተረዳ መሆን አለበት፡፡ የተሳሳተ አረዳድ በሚፈጥር መንገድ መደረግ የለበትም፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡ ነፃነቱን ጠብቆ ነው ማንኛውንም አስተዋፅኦ ማድረግ ያለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡  

ሪፖርተር፡- ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ‹‹አገር አፍራሽ›› መረጃ አሠራጭተዋል የሚል ክስ ጭምር የቀረበባቸው ሦስት ድርጅቶች ታግደው ነበር፡፡

አቶ ፋሲካው፡- ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ አይደለም፡፡ ምንም የሚያገናኘው ነገር አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የተጀመሩ ሒደቶች ናቸው፡፡ ቀድሞ ማስጠንቀቂያ የተጻፈባቸውና ከድርጅቶቹ ንግግር ያደረግንባቸው ናቸው፡፡ ሕግን አክብሮ የመሥራትና ያለ መሥራት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ብዙ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ ይነሳል፡፡ በተቋማችን ዕርምጃ መውሰድን እንደ መጨረሻ አማራጭ ነው የምናየው፡፡ ክትትልና ቁጥጥር የምናደርገው ዕርምጃ ለመውሰድ ሳይሆን ድጋፍ ለማድረግ ነው፡፡ ስህተቶች ሲገኙ እንዲስተካከሉ ዕርምት እንወስዳለን፣ የማይስተካከል ትልቅ ጥፋቶች ከሆኑ ዕርምጃ እንወስዳለን፡፡  ለምሳሌ አንደኛው ድርጅት በኢትዮጵያዊ ግለሰብ መሠራት ለሚችል ሥራ ፈቃድ ሳያገኝ የውጭ ዜጋ ቀጥሮ ሲያሠራ ነበር፡፡ ይህንን ለማድረግ ፈቃድ ማግኘት አለባቸው፣ ከዚህም በላይ የአገር ሉዓላዊነት መጣስ ነው፡፡ በጦርነቱ ሒደት ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያቀርቡ ድርጅቶች ትልቅ ድጋፍ አለን፡፡ መንግሥት በፈቀደው የሰብዓዊ ድጋፍ አሠራር መሠረት ድርጅቶች ትግራይ ክልልም፣ ሌላም ቦታ ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ ይህ በጣም የሚያስመሰግን ነው፡፡ የታገዱት ድርጅቶች ላይም ማጣራት ተደርጎ መግባባት ላይ ስለተደረሰ ዕግዶቹ ተነስተው ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ዕገዳ ተጥሎባቸው ከነበሩት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የድንበር የለሸ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ሦስት ሠራተኞቹ ሰኔ 2013 ዓ.ም. በትግራይ ክልል በዕርዳታ ሥራ ላይ እያሉ እንደተገደሉ አስታውቋል፡፡ የኤምኤስኤፍ ስፔን ፕሬዚዳንት ፓውላ ጊል ሐምሌ 2014 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስለተገደሉት ሠራተኞች የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለማናገር ቢሞክሩም እንዳልተሳካላቸው ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቷ ወደ እናንተ መጥተው ነበር?

አቶ ፋሲካው፡- በጭራሽ፡፡ ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ ዋና ዳይሬክተሩን ጨምሮ ማክሰኞና ሐሙስ በቋሚነት የባለጉዳይ ቀን ነው፡፡ ከአራት ሺሕ በላይ ደንበኛ ነው ያለን፣ ሁሉንም ለማስተናገድ 24 ሰዓት ቁጭ ማለት ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን ታች ካሉ ባለሙያዎቻችን ጀምሮ በጣም ክፍት የሆነ አካሄድ ነው የምንከተለው፡፡ እንዲህ ዓይነት ቅሬታም ቀርቦ አያውቅም፡፡ ማንኛውንም ነገር በመነጋገር ነው የምናምነው፡፡ የማያግባባ ነገር ከሆነም ተወያይቶ አለመግባባት ይቻላል፡፡ ማንም ላይ ቢሯችንን አንዘጋም፡፡ አሁን የተነሳው ነገር የለም፡፡ እንዲያውም በደንብ እንደተነጋገርን፣ ታች ካሉ ከእኛ ዳይሬክተሮች ጋር ብዙ እንደ ተወያዩ የሚል ነው ያለኝ መረጃ፡፡ የመረጃ ክፍተት ሊሆን ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኮቪድ-19 መከሰት አንስቶ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የበጀት እጥረት እያጋጠማቸው እንደሆነ ይወሳል፡፡ ከወራት በፊት የተነሳው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ለዚህ ችግር አንዱ ምክንያት ቢሆንም የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለዚህ ችግር ድርሻ አለው፡፡ የበጀት እጥረቱ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ ያሳደረው ተፅዕኖው ምን ያህል ነው?

አቶ ፋሲካው፡- ተቋማችን ተቆጣጣሪ ብቻ ሳይሆን ችግር ፈቺ ነው መሆን የሚፈልገው፡፡ አራት ሺሕ ድርጅቶች ፈቃድ ስላገኙ ብቻ እንደ ስኬት አናየውም፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈታ ነገር ካደረጉ ነው ተቋማችን ውጤታማ የሚባለው፡፡ ይህንን ካልሠሩና ለዚህም አመቺ ሁኔታ ክልተፈጠረላቸው ስኬታማ አይደለንም ማለት ነው፡፡ በዚህ አግባብ ከሲቪል ማኅበረሰቡ ጋር በተደጋጋሚ ውይይት እናደርጋለን፡፡ በምናደርጋቸው ውይይቶች የተነሳው አንዱ ነገር ዘርፉ የአቅም ችግር ስላለበት፣ አቅሙ መገንባት አለበት የሚል ነው፡፡ ዘርፉ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በግንባር ቀደምትነት የሚያደርገውን ሥራ ለማከናወን ዕውቀትና ልምድ ያስፈልገዋል፡፡ እዚህ ላይ ብዙ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ሁለተኛው ችግር ደግሞ የገንዘብ እጥረት ነው፡፡ የገንዘብ እጥረትን ለመፍታት ዘላቂው መፍትሔ ከውጭ ለጋሾች ዕርዳታ መጠየቅና ማሰባሰብ አይደለም፡፡ ዘላቂ መፍትሔው ሲቪል ማኅበረሰቡ የራሱ ኢትዮጵያዊ የፋይናንስ ምንጭ እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ በአዲሱ አዋጅ መሠረት ያወጣነው መመርያም ድርጅቶቹ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ይፈቅዳል፡፡ ድርጅቶቹ ፕሮጀክት ቀርፀውና ፈንድ መድበው ገቢ በሚያመጡ ኢንቨስትመንቶችና የንግድ ሥራዎች ላይ መሰማራት አለባቸው፡፡ ይህ ሥራቸው ኢኮኖሚንም ይጠቅማል፣ ትርፉ ደግሞ ወደ ሲቪል ማኅበረሰቡ ዓላማ ማስፈጸሚያ ይመጣል፡፡ ሁለተኛው ዘላቂ መፍትሔ የአገር ውስጥ የግል ዘርፉና ማኅበረሰቡ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የሚደግፉበትን መንገድ ማጠናከር ነው፡፡ ግንዛቤ መፈጠር አለበት፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡም ግልጽ ሆኖ የሠራውን ማሳየት ሲችል፣ ይኼንን አግኝቼ ይህንን ሠርቻለሁ ሲል መተማማን ይፈጠራል፣ ሰዎች መደገፍ ይችላሉ፡፡

      እዚህ ደረጃ እስከሚደረስ ድረስ የአገራችን ችግር እንዲፈታ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን መደገፍ የሚፈልጉ የልማት አጋሮች አስተዋፅኦ የሚናቅ አይደለም፡፡ ይህንን ድጋፍ መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ አሁን ከዚህ ድጋፍ ጋር የተያያዘ ችግር ነው እያጋጠመ ያለው፡፡ ብዙ ድጋፍ የሚገኘው ከውጭ ስለሆነ ለጋሾቹ ሀብት በሰጡ ጊዜ ጥሩ ይሆናል፣ ሳይሰጡ ሲቀሩ ደግሞ ሥራው ይቆማል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፕሮጀክት ተጀምሮ ለሁለት ዓመት ጥሩ ከሄደ በኋላ ከውጭ የሚመጣው ፋይናንስ ሲቋረጥ ሥራው ሙሉ ለሙሉ የሚቆም ከሆነ ሥራውን አለማስለመድ ይሻላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር የተረጂነት ስሜትንም ማስረፅ ነው የሚሆነው፡፡ እንደ አገር ለሚገነባው ልማትና ዴሞክራሲ ብዙም አዋጪ አይደለም፡፡ አሁን ላለው ሁኔታ ኮቪድ-19 ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ብዙ ለጋሾች ወደ አገራቸው ውስጥ ነው እያዩ ያሉት፡፡ አሁን ያለው አገራዊ ሁኔታን በተመለከተ ደግሞ በርካታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ድርጅቶች የተመደቡ ፋይናንስን ለጊዜው አዘግይቶ ወደ ሌላ የሚዞርበት ሁኔታ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ሰፊ አገር ብዙ ሕዝብ ነው፡፡ ችግሮቻችን ብዙ ናቸው፣ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉና የተጎዱ አካባቢዎች ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሲቪል ማኅበረሰቡ የሚያደርገው ድጋፍ ማጠናከር አለበት፡፡ ንፅፅር ተደርጎ ወደ ሌላ አካባቢ መሄድ የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ሌላም አገር እየተጎዳ ያለው ሰው ነው፡፡ በሰዎች መካከል ደግሞ ልዩነት መፍጠር ተገቢነት የለውም፡፡ የፈንድ እጥረቱ እዚህ ያሉ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቶቹ ጋ ዓይነት የፈንድ እጥረት ቢኖርም፣ በተቃራኒው ደግሞ የተገኘውን ፈንድ ለተፈለገው ዓላማ ያለማዋል ችግር እንዳለ ይነገራል፡፡ የእናንተ ምልከታ ምንድነው?

አቶ ፋሲካው፡- እኛ ዘርፉ በሙሉ በዚህ ይገለጻል ብለን አናስብም፡፡ ነገር ግን በዘርፉ ውስጥ ለተቋቋሙለት ዓላማ የማይሠሩ አሉ፡፡ ውኃ አቆፍራለሁ፣ ትምህርት ቤት እገነባለሁ ይልና አጀንዳ ስለተፈጠረ ብቻ ስለዴሞክራሲና ስለግጭት አፈታት የሚሠራ ከሆነ ከተቋቋመለት ዓላማ ውጪ መሥራት ነው፡፡ አንድ ድርጅት ፈቃድ ሲወስድ የሚንቀሳቀስባቸው ዓላማዎችን አስመዝግቦ፣ ዓላማዎቹ ሕጋዊ መሆናቸው ተረጋግጦ ነው ሥራ የሚጀምረው፡፡ ይኼ እንዲሁ ለሥነ ሥርዓት ማሟያ የሚደረግ አይደለም፡፡ ድርጅቱ በተቋቋመለት ዓላማ ላይ ብቻ የማይሠራ ከሆነ ሥራው ተፅዕኖ ፈጣሪ አይሆንም፡፡ በተቋቋመበት ዓላማ ላይ የሚሠራ ድርጅት በዘርፉ ላይ መረጃ፣ ልምድ፣ ዕውቀት ይኖረዋል፣ ተንትኖ መናገር ይችላል፡፡ በዚህ መንግድ የሚሠራ ሥራ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል፡፡ የሆነ አጀንዳ ስለተፈጠረና ሲቪል ማኅበረሰብ ስለሆንክ የሆነ ቦታ የምትሳተፍ ከሆነ፣ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝንበት ዕድል አለ፡፡ ለምሳሌ ከጦርነት ጋር በተያያዘ ዓላማ የሌለው ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ስለሰላምና ግጭት እንነጋገር ስለተባለ ብቻ፣ ምንም በማያገባውና በማያውቀው መንገድ ሄዶ የሆነ ነገር ሊያደርግ ይላል፡፡ ይህ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ብለን እናስባለን፡፡ በሕጉ መሠረት ከዓላማ ውጪ መንቀሳቀስ ሕገወጥ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የተገኘን ሀብት በትክክል ለዓላማው አለማዋል ይታያል፡፡ ለዚህ ነው ከሚያገኙት ድጋፍ ውስጥ ለአስተዳደራዊ ወጪዎቻቸው 20 በመቶ ብቻ አውለው 80 በመቶውን ተጠቃሚን ዓላማ ላደረገ ሥራ እንዲያውሉ ሕግ የወጣው፡፡ ይህንን እንከታተላለን፣ አብዛኛው ሲቪል ማኅበረሰብ ይህንን ተከትሎ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ሕግን ያልተከተሉ አሠራሮች ይኖራሉ፡፡ አንዳንዱ ከግንዛቤ እጥረት፣ አንዳንዱ ደግሞ ሆነ ተብሎ የሚደረግ ነው፡፡ ይኼ መታረም ስላለበት ማስጠንቀቂያና ዕግድ እንሰጣለን፡፡ በቅርቡም ለቦርድ አቅርበን እንዲፈርስ የተደረገ ድርጅት አለ፡፡ ለሲቪል ማኅበረሰብ ነው በሚል ገንዘብ ካሰባሰበ በኋላ የግል ጥቅም መዋል ላይ ተሰማርቶ ስለተገኘ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ በፖሊስም የተያዘ ጉዳይ ነው፡፡ የሚመለከታቸው የድርጅቱ ሰዎችን ማግኘት አልተቻለም፣ ጠፍተዋል፡፡ ፕሮጀክት ቀርፆና ድጋፍ ካሰባሰበ በኋላ ሪፖርት አቅርብ ሲባል ስልኩን ዘግቶ የጠፋ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት አጋጥሞናል፡፡ ለጋሾች ለእኛ አቤቱታ ያቀርባሉ፣ አንዳንዱ ይስተካከላል አንዳንዱ ደግሞ ስለማይስተካከል በፖሊስ ይያዛል፡፡

ሪፖርተር፡- በለጋሾች በኩልስ የሚታይ ችግር የለም?

አቶ ፋሲካው፡- ሲቪል ማኅበረሰቡ የሚያነሳው አንድ ነገር አለ፡፡ አዲስ ሕግ ወጥቶ ተመዝግበን እየተንቀሳቀስን ቢሆንም፣ ለጋሹ ማኅበረሰብ ለድጋፍ ጥሪ ሲያወጣ የሚያስቀምጠው መሥፈርት አዳዲሶቹን ድርጅቶች የሚያገል ነው የሚል ነው፡፡ ለጋሾች ጥሪ ሲያወጡ ወደኋላ የሦስት ዓመት የፋይናንስ ሪፖርት ማቅረብ የሚችል፣ ብዙ ዓመት ልምድ ያለው የሚሉ ጥብቅ መሥፈርቶችን ያስቀምጣሉ፡፡ ይህ ግልጽ በሆነ መንገድ አዳዲሶቹን የሚያገል ነው፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡ በተደጋጋሚ ይህንን ያነሳል፣ እኛም በጥናት ያረጋገጥነው ነው፡፡ ባደረግነው የዳሰሳ ጥናት (CSO mapping) የታየው አንዱ ይህ ነው፡፡ ለጋሾች ይህንን ተረድተው አዳዲስ ድርጅቶችን እንዴት ነው የምደግፈው? እንዴት አብረን እንሠራለን? የሚለውን ማየት አለባቸው፡፡ እነዚህን ነገሮች ለመፍታት ነው በጋራ መነጋገር ያለብን፡፡ በእነሱ በኩል ደግሞ የሚነሳ ሐሳብ ሊኖር ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልልቅ ክስተቶች እየታዩ ነው፡፡ በሰሜኑ ክፍል ጦርነት አለ፡፡ ለብዙ ጊዜ ሲነሳ የነበረውን የአገራዊ ምክክር ለማድረግም ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዴት ታዩታላችሁ? ምን ዓይነት ሚና እንዲኖራቸውስ ትፈልጋላችሁ?

አቶ ፋሲካው፡- አገራዊ ምክክሩ ከፖለቲካ ፓርቲ፣ ከመንግሥትና ከግለሰብ በላይ ነው፡፡ ለአገራችን ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፡፡ የማያስማሙን፣ የሚያከራክሩን፣ ለተለያዩ አገራዊ ተግዳሮቶቻችን ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚመለከተው ሁሉ ሰከን ብሎ ተነጋግሮ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ የሚያመጣበት ከሆኑ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ነገሩን በዚያ ልክ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የሲቪል ማኅበረሰቡ፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ፣ የሆነ ፖለቲካ ፓርቲም ጉዳይ አይደለም፡፡ የአገር ጉዳይ ነው፡፡፡  በጥንቃቄና በደንብ ውጤት ለማምጣት በሚያስችል መንገድ አስተዋጽኦ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በንቃት አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ እንፈልጋለን፡፡ የሌሎች አገሮች ምክክር ውጤታማነት ስናይ በአንዳንድ አገሮች ሲቪል ማኅበረሰቡ በሰከነና በጣም አስተዋይነት በተሞላበት መንገድ አስተዋፅኦ ማድረግ በመቻላቸው ውጤት እንዳመጡ ማየት ይችላል፡፡ ስለዚህ ሲቪል ማኅበረሰቡ በዚህ ጉዳይ ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ተሳትፎና እንቅስቃሴው በሙሉ የአገራዊ  ምክክር ኮሚሽኑን ውጤታማ ለማድረግ የታቀደ መሆን አለበት፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ከአራት ሺሕ በላይ ድርጅቶች የተሰማሩበት ዓላማና መስክ የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁሉም የራሱ ጥያቄ በኮሚሽኑ ሒደት ውስጥ እንዲመለስለት የሚፈልግ ከሆነ ጥሩ አይሆንም፡፡ በዚህ ደረጃ ቦታ የሚሰጣቸው ነገሮች ካሉ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ከዚያ ውጪ የኮሚሽኑ እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ ማድረግ፣ ከኮሚሽኑ ጋር ተናበው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ የተቀናጀ መሆን አለበት፡፡ አራት ሺሕ ድርጅቶች በኮሚሽኑ ሒደት ላይ አስተዋፅኦ ይኖረናል ብለው በተናጠል የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ውጤታማ አይሆንም፡፡ ኮሚሽኑ ትኩረጥ እንዲያጣ ማድረግ ይሆናል፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡ ድጋፍ የመስጠት፣ ማኅበረሰቡ የሚወያይበትን መድረክ የማመቻቸትና የመምራት ሚና ቢጫወት ውጤታማ ይሆናል ብለን እናስባለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...

‹‹ብሔራዊ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ሊያግዙ የሚችሉ ወጥ የሆኑ ሕጎች ያስፈልጉታል›› አቶ ኑሪ ሁሴን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት (ከወለድ ነፃ ባንክ...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስጀመር ብርቱ ትግል ተካሂዷል፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ እንዲሰጥ ተወስኖ፣ ከዚያም ከለውጡ ወዲህ ሙሉ በሙሉ ከወለድ...