በገለታ ገብረ ወልድ
የትግራይ ሕዝብ የሰሜኑ የአገራችን ክፍል በር ጠባቂ ሆኖ ለዘመናት የኖረ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀደምት አካል ነው፡፡ ወደ ጥንቱ ታሪክ ለመመለስ ቢሞከርም ከአክሱምና ታሪክ አንስቶ የሥልጣኔና የቅርስ መነሻ፣ የሃይማኖቶችና የፍልስፍና መፍለቂያነቱ ሊካድ የማችይል ነባራዊ ሀቅ ነው፡፡ ያም ሆኖ አገራችን በዘመናት ታሪክ ውስጥ፣ ነገሥታቱና መኳንንቱ በነበራቸው የሥልጣንና የሀብት መቀራመት ፍልሚያ ውስጥ እንደ ሕዝብ የትግራይ ወገኖችም የውስጥም ሆነ የውጭ ግጭትና ጦርነት ሰለባ መሆናቸው አልቀረም ነበር፡፡
በዘመናዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥም ቢሆን ይኸው መቆራቆስና ሥልጣን በኃይል መነጣጠቅ ከአገዛዞችም አልፎ ሕዝብን ወደ ማስኮረፍና ማናቆር የተሄደበት ሁኔታ መፈጠሩ አልቀረም ነበር፡፡ ይህን አገራዊ ነባራዊ ሁኔታ በሠለጠነ መንገድ በመፍታት የጋራ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያራምድ መንግሥት መገንባት ሲገባ፣ በ1967 ዓ.ም. ፊውዳላዊ ሥርዓቱን የመገርሰስ ትግል ሲጀመር፣ የተጠነሰሰው የተሃት (በኋላ ሕወሓት) አመለካከት በባለታሪኩ የትግራይ ሕዝብ ውስጥ የተነጣይነት ሥነ ልቦና ማሳደሩ አልቀረም፡፡
የሚያሳዝነው ነገር ሕወሓት ለ17 ዓመታት በትጥቅ ትግል ውስጥ አልፎ በአብዛኛውም የትግራይ ወጣት አሠልፎ ከፍተኛ በሚባል መስዋዕትነትና የአገር ሀብት ውድመት ሥልጣን ለመቆናጠጥ በቅቶ ነበር፡፡ በ25 ዓመታት የአገር አስተዳደር የሥልጣን ዘመኑም ምንም እንኳን አገር ቀላል የማይባል ዕዳ ውስጥ ብትገባም የማኅበረ ኢኮኖሚ ልማት መማጣት ሞክሮ ነበር (በዚህ ወቅትም ቢሆን ግን ለትግራይ ሕዝብ የተለየ ትሩፋት ከማምጣት ይልቅ፣ ገዥው መደብ ሕወሓት በሚፈጽመው ጭካኔ እንዲጠላ ነው ያደረገው)፡፡
በሒደት በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ከመገንባት ይልቅ፣ ዜጎች በማንነትና በብሔር እየተቧደኑ እንዲከፋፈሉ፣ የትግራይ ሕዝብና ሌሎች ወገኖችም ከመነጠል ዕሳቤ እንዳይላቀቁ ነበር ያደረገው፡፡ ከሁሉ በላይ አገራዊ ብሔርተኝነትን የሚያዳክሙ ትርክቶችን እንደ ሥልት በመቁጠር፣ ብሔረሰቦች በአሻቸው ጊዚ አገር ሆነው መቆም የሚችሉበትን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ዕብደት ውስጥ ነበር እንዲቆዩ ያደረገው፡፡
ከዚህም በላይ የሕወሓት የሴራና የጥፋት ፖለቲካ ዛሬም ድረስ በድምሩ 48 ዓመታት ገደማ ብዙ ኪሳራ አድርሶ አገርን አናውጧል፡፡ እነሆ አሁንም ጠንቁ በዋናነት ለትግራይ ሕዝብ፣ መከራው ደግሞ አልፎ ተርፎ ለሌላው የአገራችን ሕዝቦችና ለመለወጥ ተነሳሽነት አሳይቶ ለነበረው መንግሥትም ተርፎት ይታያል፡፡
ይህ ዕንቅርት የሆነ ኃይል በመጨረሻም “ሥልጣን ወይም ሞት” እያለ ሁሉን እቀብርበታለሁ ወዳለው መቃብር እየወረደ መሆኑን የሰሞኑ ዓውደ ውጊያ መረጃዎች እያሳዩ ነው፡፡ ሕወሓት ዛሬ በዕድሜ ጠንዝቶም አገርን የሚመሩና ሕግ የሚያስከብሩ ኃይሎችን ሁሉ “አድኃሪያን” ከማለት አልፎ መቀበሪያቸው ትግራይ ነው እያለ፣ የአገር አካል የሆነን አንድ ክልል የራሱ ርስትና ጉልት አስመስሎ በንፁኃን ደም እየነገደ ነው፡፡
ከዘመናት በፊትም ሆነ አሁን በተለይ አማራን ‘እምቀብረው እኔ ነኝ‘ ባይ ዕቡይነቱም አለቀቀውም፡፡ እስከ መቼ የሚለው ነው መልስ አጥቶ ያለው ጥያቄ፡፡ የሚያሳዝነው እውነታ ሕወሓት በእንዲህ ያለ ሴራ የሚመላለሰው ትግራይ የኢትዮጵያ ራስ መሆኗን ክዶ፣ ትግሬዎች ለዘመናት ከሌሎች ጋር የፈጠሩትን የተሰናሰለ ማንነት በመሸምጠጥ ብቻ ሳይሆን፣ መጨረሻ ግቡ ባልታወቀ የጦርነት አዙሪት ውስጥ በመጣል ነበር፡፡
ማን ይሙት በጥፋት ላይ ጥፋት እየጨመረ ለሦስተኛ ጊዚ አገርን የሚያደማ ጦርነት መጀመር የመሰለ ዕብደት ውስጥ እንዴት ደጋግሞ ይገባል? ከሁሉ በላይ የሰላምን በር ረግጦ፡፡ ይህ ኃይል ዛሬም ሆነ በአገር ማስተዳደር ዘመኑ አገሪቱን እንደ ግል ንብረቱ በመቁጠር በጉልበት ጨፍልቆ ለመግዛት ያደረገው ሙከራ ረጅም ርቀት ሊወስደው አለመቻሉን እንኳን ቆም ብሎ ማመን አልቻለም፡፡
በአንድ በኩል አካሄዱ በአናሳ ጉልበት፣ ብዝኃኑን ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት ውጪ በማድረጉ፣ በሌላ በኩል ሀልዮቱን ለማስቀጠል የተከተለው መንገድ ፀረ ዴሞክራሲያዊና ኢፍትሐዊነትን በመቆራኘቱ፣ የኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝብ በአንድም በሌላም ለውጥ እንዲያማትር አድርጎታል፡፡ ይህን መሬት ላይ ያለ ሀቅ በመካድ ዳግም ወደ ጦርነት እሳት መግባቱ ነው የሕወሓትን ብረት ነካሽነት ይበልጥ ያጋለጠው፡፡
ከሁሉ በላይ በታሪክም ሆነ በመልክዓ ምድር ለትግራይ ሕዝብ ጎረቤትና ገበያተኛ፣ ብሎም በክፉም ሆነ በደግ የቅርብ ደራሽ የሆኑትን የአማራና የአፋር ክልልን ሕዝቦች የጦርነት ሰለባ ማድረጉ ከታሪክ አለመማሩንና ዓላማ ቢስ ትግል ውስጥ መርመጥመጡን አንድ ማሳያ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝባዊነት የሌለው ጥገኝነቱንም ያጋልጣል፡፡
በተለይ ባለፈው ዓመት መንግሥት በተናጠል ተኩስ አቁም የትግራይ ክልልን ለቆ ሲወጣ በሰሜንና በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜንና በደቡብ ወሎ፣ እንዲሁም በአፋር ክልል ለወረራ የላካቸውን የትግራይ ክልል ወጣቶችና የጁንታው ተዋጊዎችን በገፍ በማዝመት የፈጸመው ጭካኔ ታሪክ ይቅር የማይለው ጠባሳ ጥሏል፡፡
ለዚህም ነው እንኳን በባለፈው ዓመት፣ አሁንም ድረስ ቢያንስ በፕሮፓጋንዳ ደረጃ ከጎረቤት ሕዝቦች ጋር ፀብ የለኝም እያለ የአማራ ብቻ ሳይሆን፣ መላው የአገሪቱ ሕዝብ ለአንድ ዓላማ ተሠልፎና ካለፉት ዘመናት ትምህርት ወስዶ ወያኔ በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ (እንደ ውጭ ጠላት ጦር) እንዲደመሰስ እየተረባረበ የሚገኘው፡፡ ጥምር ጦሩ ድል እየቀናው (ብዙውን ኃይሉን ሙትና ምርኮኛ ሲያደርግና ከዚያው ቦታ ሲገፈትረው) ሲታይም፣ የሕወሓትን የተሳሳተ ሥልትና ግብ አልባ ጉዞ እያጋለጠ ነው፡፡
በመሠረቱ ሕወሓት ገና በ1968 ዓ.ም. ኢትዮጵያዊነትን ለመካድና ሕዝቡን ለመበታተን ዋነኛ ጠላት አድርጎ የተነሳው የአማራ ሕዝብን ነበር፡፡ “ገረብ ገረብ ትግራይ መቃብር አማሀራይ” (የትግራይ ተራሮች የአማራ መቀበሪያ ይሆናሉ) እስከ ማለት ይደነፋ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ከትበውት ይገኛል። የመነሻው ክስረት እንጂ መንግሥታዊ ሥርዓትን መቃወምና ሕዝብን እንደ ሕዝብ ጠላት አድርጎ፣ ለትውልድ ቂምና ቁርሾ ማስተላለፍ ባልተገባው ነበር፡፡
ሕወሓት በዚህ የዛገ አስተሳሰቡ ታግሎ ሥልጣን ላይ መውጣቱ ባይካድም፣ የአማራንም ሆነ ሌላውን ሕዝብ ሲያማቅቅ ከመኖርና ከመበዝበዝ ያለፈ አስተዋጽኦ አለማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ አሁንም በመፍትሔ አልባው አካሄድ ያለፍዳው የዛሬውን የትግራይ ትውልድ በየሸጡና ተራራዎች ላይ እንዲቀበር ማድረጉ የሚያስቆጭና የሚያሳዝን ነው፡፡ ይህ ክስተትም በታሪክ እንደሚያስወግዘው ራሳቸው የትግራይ ተወላጆች በማስረዳት ላይ ናቸው፡፡
በመሠረቱ የአማራ ሕዝብ ከቀደሙት ሥርዓቶች ጀምሮ የጭቆና በደል ተቋዳሽ ቢሆንም፣ ባለፉት 32 ዓመታት ግን ማንነቱን መሠረት በማድረግ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጽምበት የቆየው ሕወሓት በዘረጋው ሴራ መሆኑ ግልጽ ሆኗል። ሌላው ቀርቶ በአገር ደረጃ ለውጥ መጣ ከተባለበት ጊዜ ወዲህ ባሉት አራት ዓመታት በዋናነት በኦሮሚያ ክልል፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና መሰል አካባቢዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ዜጎች፣ ሕፃናትና ሴቶች በግፍ እየተጨፈጨፉ ያሉት በማንነታቸው ላይ ብቻ በተነጣጠረ የጥላቻ ፖለቲካው ምክንያት ነው፡፡
በእርግጥ ትናንትም ሆነ ዛሬ አሸባሪው ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ጠባብ ብሔርተኞችንም ሁሉ አማራ ጠላቱ እንደሆነ እንዲያምን ሌት ተቀን ሠርቷል። አካሄዳችን ትክክል አይደለም ያሉትን የትግራይ ተወላጆችንም “ሸዋዊ ተጋሩ” (የሸዋ ትግሬዎች) እያለ ተሳልቆባቸዋል፣ አሸማቋቸዋል፣ እስከ ቅርብ ጊዜም ‘አደገኛ’ የሚላቸውን ገድሏል።
አማራ ‘ተመልሶ እንዳይነሳ’ አድርገው እንደሚቀብሩት ብቻ ሳይሆን በዚሁ መንደርደሪያ ኢትዮጵያዊነትም እንዲደከም፣ ዝተዋል፣ በተግባርም ብዙ ሥራ ሠርቷል፡፡ እነሆ ዳፋው እስካሁንም ደም እያፋሰሰ ነው፡፡ ሥልጣኑን በተቆጣጠሩበት ወቅት ‘አማራን ቆፍረን ቀብረነዋል’ ብለው መደንፋት ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝቡ ዝምታና ሁሉንም ቻይ መሆን ደግሞ ይህ አባባላቸው እውነት የሆነ እንዲመስል ማድረጉ ነው የአሁኑ ቀውስ መዳረሻ።
ለነገሩ ሕወሓት የሚሠራው የአማራ ሕዝብ (ለይስሙላ ልሂቃኑ ቢሉም) እንዲዳከም ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦችም ይህንን ግፍ እንዳላዩ ከማየት አልፈው ራሳቸውም የጥፋቱ አካል እንዲሆኑ የማድረግ ሴራ የተከተለ ነው ይላል የአማራ ክልል መንግሥት ህልውናችን (2014) በሚል ርዕስ ያወጣው ጽሑፍ፡፡ ምንም እንኳን ምኞታቸው ባይሳካላቸውም፡፡
በየአካባቢው ባሉና ራሱ በሚያሽከረክራቸው የብሔር ፖለቲከኞች አማካይነት ሌላውም ብሔረሰብ አብሮት የኖረውን ጎረቤቱን እንዲያባርር፣ እንዲገድል፣ ንብረቱን እንዲያቃጥል፣ ‘በቀል’ እንዲፈጽም በመወትወቱም ነው፡፡ አልፎ ተርፎ በተደጋጋሚ ይህ ኃይል ወረራ በፈጸመባቸው የክልሉ አካባቢዎች (ማይካድራ፣ ጭላና ቆቦን ልብ ይሏል) የፈጸመውን ወንጀል በግልጽ ማየት ተችሏል።
እስካሁን እንዳየነው በአገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የሕወሓት ቅጥረኞች በኢንተርኔት ጫካ ተደብቀው በተለያየ ስም አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግራይ፣ ጉራጌ፣ ቅማንት፣ አገው፣ ወዘተ. እየመሰሉ አንዱን ብሔር ሲሰድቡ፣ በሌላው ስማቸው ደግሞ መልስ ሲሰጡ የነበረውም ሕዝቡን ለማባላት ነበር፡፡ በተጣላና በተለያየ ሕዝብ ውስጥ በአጉራ ዘለልነት ያሻቸውን ለመፈጸም ከልካይ እንደማይኖር ጠንቅቀው ስለሚያውቁ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በርካታ ዩቲበሮችና ውዥንብር ረጪዎችን እየከፈሉ ማሰራቸው እየታየ ነው፡፡
በቅርቡ በጀመሩት ሦስተኛው ዙር ጥቃትና የአማራና የአፋር ክልል ዳግም ወረራ ብሎም ሥርዓተ መንግሥቱን የማፈራረስ ቅት የተከተሉት ሥልትም ይኸው ነው፡፡ ምንም እንኳን ሁሉም ምኞታቸው ከንቱ ሆኖ ይቀር ዘንድ፣ መላው የአገሪቱ ሕዝብ በአንድነት ቆሞ እየታገላቸው ቢሆንም፡፡
በመሠረቱ ሕወሓት ምንም ያህል የአገር ሀብት ቢዘርፍ፣ የትኛውንም ያህል የጦር መሣሪያ በ30 ዓመት የሥልጣን ዘመኑ ቢደብቅምና ከቅርብ ዓመታት ወዲህም ግጭት ቢያባብስም፣ ከአንድ አናሳ ክልል የወጣ መሆኑን አይቀይረውም፡፡ በዚያ ላይ የበቀለበት የትግራይ ክልል በሕዝብ ቁጥር አቻ ከሚባሉት እንደ ሲዳማና ሶማሌ ከመሰሉ ክልሎች አንፃር ሲታይ፣ ወይም በቆዳ ስፋት ከሚመጣጠኑት ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ወይም አፋር ክልሎች አንፃር እንኳን ሲታይ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብትና የእርሻ ምርታማነት ውስንነት ያለበት ነው፡፡ ይህ እየታወቀ ነው ሕዝቡን ለዳግም ውድቀት እየዳረገ ያለው፡፡
በዚህ ምክንያት በሌሎች ክልሎች ተዋትኦ ጭምር፣ በፌዴራሉ መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ የሚደጎም ክልል መሆኑ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው የክልሉ ሕዝብ በመላው አገሪቱ ተንቀሳቅሶ በሚያገኘው ገንዘብ የመኖር ዕድሉን እያከሰሙት ይገኛል፡፡ ጁንታው ባልተገባ መንገድ እየነገደበት ቢሆንም፣ በታሪክ አጋጣሚ በመላው ዓለም ተበታትኖ የሚኖረው የትግራይ ዳያስፖራ ድጎማም ነበር፣ ሲያግደረድረው የቆየው፡፡
ይህን ሁሉ ግን እየተጠቀመበት ያለው ለልማት ሳይሆን ለጥፋት መሆኑ ነው የኪሳራው ኪሳራ፡፡ እናም የትግራይ ሕዝብ ኪዚህ አውዳሚ ኃይል እንዲፋታ መሥራት የሁሉም ግዴታ ሊሆን ይገባል፡፡ በመሠረቱ የትኛውንም የፖለቲካ ግብ ለማሳካትስ ቢሆን ትውልድን አስፈጅቶ ምን ያህል አትራፊ መሆን ይቻላል፡፡
ከእውነትና ቀልቡ ጋር ብቻ ሳይሆን ከነባራዊው ሀቅ ጋር እየተላተመ ያለው የሕወሓት አክራሪ ኃይል፣ ከብዙኃኑ የአገሪቱ ሕዝቦች ጋር ተስማምቶና ተግባብቶ መኖር ሲገባው፣ በግፍ ጦርነት የለኮሰው ከመንግሥት (ቢያንስ ከደርግ ጋር እንዳደረገው ውጊያ) ጋር ብቻ አለመሆኑ ነው ሌላው የኪሳራው ማሳያ፡፡ ከመላው አገሪቱ ሕዝብ ጋር እንጂ፡፡ በአንድ ክልል ጫማ ላይ ሆኖ ከሌሎች ዘጠኝ ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደር ዜጎች ጋር መናከሱንና በጥቅማቸው ላይ የመጣ መሆኑንም የዘነጋው መስሏል፡፡
በመጥፎው የጦርነት አጋጣሚ ከስድስት ሚሊዮን ያልበለጡ የትግራይ ሕዝቦችን (ያውም አብዛኛውን በግዳጅ አሰተባብሮ) ይዞ፣ ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ ጋር ሊያላትም ነው የሞከረው፡፡ በአጉል ጀብደኝነትና ከእኛ በላይ ላሳር ባይነት የትግራይን ወጣት አንድ ጊዜ ሳይሆን ደጋግሞ ወደ መማገድ ውስጥ የገባውም ለራሱ በሰጠው የተሳሳተ ግምት ነው፡፡ ግን አንድ ቦታ ላይ እልባት ማግኘት ያለበት የአገር ፈተና መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ሕወሓት ካለፉት ሳምንታት ወዲህ እያደረገው ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ እጅግ በተበታተነ መንገድ ታጣቂውን ለዘረፋ፣ ለማኅበራዊ ድረ ገጽ ውዥንብር፣ ለስለላና ለተኳሽነት በማሠለፍ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የሕወሓት የሽብር ቡድን በረገጠባቸው አካባቢዎች ሁሉ ከደሃ ጓዳና ሳጥን እስከ ሕዝብ ካዝናና የመንግሥት ድርጅቶች ድረስ ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት አድርሷል፡፡ በማኅበራዊ ድረ ገጾቹም ‹‹ይህን ያዝነው፣ ያኛውን አጠቃነው›› የሚል ውዥንብር በመንዛት የተሳካለት መስሎ ሰንብቷል፡፡ የውጊያው ነገር ግን “ጫት የሚያቃቅም” ሆኗል፡፡
ከዚህ ቀደም እንደታየውም በእርስ በርስ ጦርነቱ ትናንትም ሆነ ዛሬ የሕወሓት የሽብር ቡድን በረገጠባቸው አካባቢዎች ሁሉ፣ ከደሃ ጓዳና ሳጥን እስከ ሕዝብ ካዝናና የመንግሥት ድርጅቶች ድረስ ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት ሲያደርስ ነበር፡፡ ለተራበ ሕዝብ (ያውም የራሴ ወገን ለሚለው ሕዝብ) የመጣን የዕርዳታ እህል፣ አልባሳትና ነዳጅ እየዘረፈ ለጦርነት በማዋል ነውረኝነት ላይም ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡ እነዚህ አዋራጅ ተግባራትም ቢሆኑ ነገ በታሪክ ፊት ብቻ ሳይሆን በሕግና በሞራል ተጠያቂነት ረገድ የሚያስወቅሱት ናቸው፡፡
የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ቢያንስ በአሥርና በሃያ ዓመታት ውስጥ ጦርነት የማያጣው ያልታደለ ምድር ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብም ሕወሓትን የመሰለ ዕዳ ተሸክሟልና ከጦርነት አዝሪት ሊወጣ አልቻለም፡፡ አሁን ግን ሕወሓት በታሪኩ ገጥሞት በማያውቀው ደረጃ አንድ ሺሕ፣ ሁለት ሺሕ ጀሌና ታጣቂ በአንድ ዓውደ ውጊያ ማስገደልና ማስማረክ መገለጫው መሆኑ ሲታይ የፍፃሜውን መቃረብ ያረጋግጣል፡፡ በየዓውደ ውጊያው ተበታትኖ ሲሸሽ ንፁኃንን እየተበቀለ ቢሄድም፣ በገባበት እግሩም መውጣት አልቻለም፡፡ እንዳሻው መድፍና ታንክ እየተኮሰ፣ በጎዳና ላይ ተሠልፎ የሚዋጋበት ሁኔታም እየከሰመ ታይቷል፡፡
በዚህ ላይ በአሥር ሺዎች ሥልጠናውን አጠናቆ እየወጣ ያለ የመከላከያና የክልሎች ልዩ ኃይል ምልምል ብቻ ሳይሆን፣ በቁጭትና በተነሳሽነት የአገሩን ጥሪ የተቀበለው፣ እንደ ፋኖ፣ ሚሊሻና የወሰንተኛ አካባቢዎች ወጣት ዓይነቱ አደረጃጀት በሁለንተናዊ አቅሙ እየተፋለመው ይገኛል፡፡ ይህንን በከፍተኛ ቁጣ የተነሳ አዲስ ትውልድ ከ30 ዓመታት በፊት በወደቀ አስተሳሰብና በከሰረ አካሄድ ለመቋቋምና ለማስቆም መሞከር ደግሞ የሚቻል አይሆንም፡፡ እናም ሕወሓት ከሕዝብ አስጨራሽ ድርጊቱ የሚቀርበው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጥግ እንዲይዝ ሲደረግ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡