Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትየታጠቀ ፓርቲ ይዞ ዴሞክራሲ የለም

የታጠቀ ፓርቲ ይዞ ዴሞክራሲ የለም

ቀን:

በገነት ዓለሙ

መንግሥትን በኃይል የመጣልና የመተካት ድርጊት በየትም አገር ወንጀል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተከታታይ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጎች በ1949 ዓ.ም.፣ በ1996 ዓ.ም. ይህንኑ ወንጀል ያደርጋሉ፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ማቋቋሚያም ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ የመንግሥት ለውጥን መቃወም/ማውገዝ የኅብረቱ መርህ (ፕሪንሲፕል) መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግም በረዥም የ17 ዓመታት ጦርነት ውስጥ በጉልበት አሸንፎ፣ ሥልጣን ይዞም፣ በጊዜያዊ መንግሥትነቱ ዘመንም ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መሠረትኩ ብሎ በምርጫ ሥልጣን ላይ ወጣሁ ይል በነበረበት ጊዜ ሁሉ፣ መንግሥትን በኃይል መጣልና መተካት ክልክል ነው ብቻ ሳይሆን፣ መቆምና ታሪክ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው ይል ነበር፡፡ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ቢሆን ጥሩ ነው የሚባል ብቻ ሳይሆን መሆን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

ይህ እንዲሆን ግን ‹‹ይሁን››፣ ‹‹አሜን›› ብቻ በቂ አይደለም፡፡ መንግሥትን በኃይል የመጣልና የመተካት ነገር የአፍሪካ ኅብረት እንደሚለው፣ የእያንዳንዱ አገር ሕገ መንግሥትም እንደሚደነግገው ነውርና ወንጀል ማድረግን አስተማማኝ ለማድረግ መንግሥት የመተካት፣ የመለወጥ ሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ መቋቋም፣ ዋስትናም ማግኘት አለበት፡፡ አገራችን ውስጥ በተለይም በመጨረሻው የሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን የነበረው ችግር መንግሥትን በኃይል ካልጣልኩ ሞቼ እገኛለሁ ባይነት አልነበረም፡፡ ወይም ‹‹ሳትዋጋ ንገሥ ቢሉት ግድ ተዋግቼ›› መርህ በልጦ አልነበረም፡፡ ዋናው የአገር ችግርና ሕመም ያለውን መንግሥት ራሱን ጨምሮ፣ ሕገ መንግሥቱን፣ የምርጫ ሥርዓቱን የመቀበልና ያለመቀበል ጉዳይ ሳይሆን፣ የተቀበለውም ሆነ መለወጡን የሚፈልግ ሁሉ ፍላጎቱን በይፋ ይዞ ለመታገልና ለመወዳደር ያስችላል ተብሎ የሚታመንበት ዴሞክራሲያዊ ሁኔታና መደላደል አለመኖሩ ጨርሶም መዘጋቱ ነው፡፡ ለውጡ የመጣው ዝም ብሎ ‹‹ምርጫ›› መቁጠርና በምርጫም ‹‹ቀጠሮ›› መያዝ የተቋረጠው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

- Advertisement -

በነገራችን ላይ የኢሕአዴግ መንግሥት ይባል የነበረው፣ ኢሕአዴግ ሲገዛ የኖረው በሕወሓት ቁጥጥር ሥር በኖረ መንግሥታዊ አውታር ላይ ስለመሆኑ አፍርጦ መናገር የመታገል ያህል በመሆኑ እንጂ፣ ነገሩ ሚስጥርና ሥውር ሆኖ አልነበረም፡፡ ሕወሓት የትግል/የጦርነት አከርካሪውን የአገር መከላከያ ከማድረግ የሽግግር ጊዜ ፕሮጀክት አንስቶ መላውን የመንግሥት አውታራት በራሱ አምሳል የሠራ፣ በሌሎች ተቋማትም ማኅበራትም እንደ ሠርዶ ውስጥ ለውስጥ ተሠረጫጭቶ ሥርና ጅማት ሆኖ የኖረ፣ ማሻሻያም ሲባል ያንኑ ሥርና ጅማት እንደሆነ ገለልተኛ የመምሰል ሥራን የ‹‹ማያስነቃ›› አድርጎ የመቀጠል ነገር እንደሆነ ዛሬ ሳይታለም የተፈታ መንግሥታቱ ድርጅት ድረስ የዘለቀ አባዜ መሆኑ ገና መድኃኒት ያላገኘ ‹‹ወረርሽኝ›› ነው፡፡ ዛሬ እኛ ብቻ ሳንሆን የሕወሓት መንግሥት የምንለው፣ ሕወሓት ራሱ ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው በዚህ ጦርነት ውስጥ ሌላው ‹‹ፓርቲ›› (ወገን) ሆኖ ‹‹የህዳሴውን ግድብ የጀመረውና ሰባ በመቶ ያደረሰው ሕወሓት ነው [ኢሕአዴግ አይደለም]›› ሲባል ሰምተናል፡፡

መጋቢት ላይ እንደነገሩ ፀና፣ ያዘ ሲባል የነበረውና ነሐሴ 18 ቀን የፈረሰው ግጭት የማቆም ‹‹መግባባት›› ከፈረሰና ጦርነቱ ከቀጠለ ወዲህ አዲሱ ዓመት ዕለቱ ላይ ሕወሓት ያወጣው መግለጫ/የጻፈው ደብዳቤ ዕውን ይኼ ‹‹የዘንባባ ዝንጣፊ›› ነው ወይ? ማለትንና በውስጡ የታጨቁ በርካታ ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለሰላም ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ ላለው መንግሥት በርካታ ቅድመ ሁኔታዎች ያቀረበው ሕወሓት አሁን ድንገት እነዚህን ሲያነሳ (እሱ አነሳሁ አይልም) መንግሥት ዝም ብሎ፣ ድሮም አንተ እንቢ አልክ እንጂ እኔማ ምን ገዶኝ ብሎ ለድርድር ይቀመጣል ወይስ የተለወጠ ነገር አለ? ወዘተ ማለት የአዲሱ ዓመት የመጀመርያ ቀናት የ‹ወገን› መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ሌሎችም በዚህ ውስጥ የሚካተቱ፣ ከዚህ ጋር የተያያዙ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህን ሁሉ ግን በትልቁ ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ፣ በሰላምና በዴሞክራሲ ግንባታ ጥረትና ግዳጃችን መቃን ክልል መመልከት አለብን፡፡ እዚህ አጠቃላይና መሠረታዊ ጉዳይ ውስጥ ዋናውን ጉዳይ የሚያስረሱና ከዚያ የሚያዘናጉ አንዳንድ ነገሮችን እግረ መንገዳችንን ማንሳትም ተገቢ ነው፡፡

ለምሳሌ አንዱ የትግራይ (ክልል መንግሥት፣ ወዘተ) የሚለው ስያሜ ነው፡፡ ሊጠራና በሰላሙ ጊዜም በራሱ ቢሆን ስታንዳርድ፣ ልክና መልክ ሊቀመጥበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ በሰላሙ ጊዜ በራሱ (ከጦርነቱ በፊት) ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ማለት፣ በተለይም ከሕገ መንግሥቱ መፅደቅ በኋላ ስህተት ተብሎ የማያውቅ ጉዳይ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአዋጅ ቁጥር ሰባት ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስቀርቶ ‹‹በክልል›› ብቻ እንደገደበው ብዙ ሰው (ባለሥልጣኖቻችን) ጭምር ‹‹አያውቁም››፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ብሔራዊ ወይም ‹National› ማለት አገራዊ፣ የአገር ማለት ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክን፣ ብሔራዊ ሎተሪን፣ የአገር መከላከያን የሚመለከቱ ነገሮች ስያሜ ነው፡፡ በ‹‹ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥታችን ማዕቀፍ ውስጥ በተለያየ ደረጃ የሚገኝ ሥልጣን፣ ሥልጣን ሁሉ፣ የ‹‹መንግሥት›› ቢሆንም የእንግሊዝኛው የሕገ መንግሥቱ ቅጂ ስለ የገቨርንመንት ቢናገርም፣ በዚህ ረገድ አማርኛው ‹‹መስተዳድርን›› ቢመርጥም የክልልን አስተዳደር የ… መንግሥት ማለት ነውርም ኢሕገ መንግሥታዊም አይደለም፡፡ ደግሞም በኢፌዴሪ ‹‹የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት መወሰኛ አዋጅ›› (ቁጥር 1231/2013) የሚባል ሕግ አለን፡፡

የትግራይን ክልል የሚመራውን ቡድን፣ ወይም ኃይል ‹‹መንግሥት›› አይደለህም ብሎ ለመከራከር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 479/2013፣ ለዚህ ደንብ መውጣት መነሻ የሆነውን የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ውሳኔ፣ በዚህ ውሳኔ ላይ ተመሥርቶ የተወሰዱትን ዕርምጃዎችና የሕግ ውጤታቸውን መጥቀስ ይበቃል፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ የትግራይ ክልል መንግሥት/መስተዳድር ብሎ ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡

ዋናው ጉዳይ ዋናው ማዕቀፋችንም በዚሁ ሕገ መንግሥታዊ መቃን ውስጥ ለውጡና ሽግግሩ ነው፡፡ ሽግግር ማለት ደግሞ ይህንን ሕገ መንግሥት ካስተጓጎለ፣ ይልቁንም ካሰነካከለ አምባገነንነት ወጥቶ ወደ ዴሞክራሲ መግባት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ደግሞ ሽርሽር አይደለም፣ ወይም ጫካ ውስጥ ተደግሶ የሚመጣ ‹‹ምርት›› አይደለም፡፡ የመንግሥት አውታራት ሕወሓታዊነት እስካለ ድረስ ዴሞክራሲ አይቋቁምም፡፡ ኢሕአዴግ ወይም ሕወሓት (ምክያቱም የኢሕአዴግ ይዘት ሕወሓት ነበርና) በየአምስት ዓመት ምርጫ መንግሥትነትን የሚሾም ፓርቲ ብቻ ሳይሆን፣ ሲጀመር ጦርነት አሸንፎ ሥልጣን ሲይዝ አንስቶ የኢትዮጵያ ዓምደ መንግሥት ሆኖ የተደራጀ ተቋም ነበር፡፡ ሕወሓት አገሪቷን ምርኮ ማስገባቴ፣ ግጬ መግዛቴ፣ ወርሬ መያዜ፣ ግዳይ መጣሌ ለምን ይነካል? ይህን ሁሉ ዘመን የተዋጋነው ታዲያ ለምንድነው? አለና ሥርና ጅማት ሆኖ በተንሠራፋባቸው ቦታዎችና አካላት ያለውን ኃይል ሁሉ አንቀሳቀሰ፣ የሰሜን ዕዝን አጠቃ፡፡ የውስጥ ወረራ ፈጸመ፡፡ መነሳት ያለብን፣ የጥበብ መጀመሪያችን ወይም ግራውንድ ዜሯችን (Ground Zero) የመንግሥት አካላትን ሕወሓታዊነት ማፅዳት ነው፡፡ ሕወሓትን ፓርቲና ፓርቲ ብቻ ማድረግ ነው፡፡

የምንመርጣቸው፣ ከዚያ በፊትም የምናቋቁማቸው ፓርቲዎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ በሕግ የተወሰነ፣ ቁርጡ፣ ልኩና መልኩ የታወቀ መንዕስ የዴሞክራሲያዊ ዕይታ፣ አመለካከትና ዴሞክራሲዊ የድርጅት ሕይወትንና አኗኗርን መለኪያ ተፈትነው ያለፉ እንዲሆኑ ማድረግ ግድ ነው፡፡ ፓርቲዎች ከጠመንጃ ጋር መገናኘት የለባቸውም፡፡ የታጠቀ ፓርቲ ብሎ ነገር ዴሞክራሲ አያውቅም፡፡ ፓርቲዎች ወደ ሥልጣን የሚወጡበት ብቸኛው መንገድ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ፣ እንዲሁም ሕጋዊ ትግል ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ (ይህ ለሰው ልጅ በሙሉ የሚሠራ እውነት ነው) ትልቁ ድል ይህ ወይም ያኛው ፓርቲ፣ ይህ ወይም ሌላው አማራጭ ወይም ባለ አማራጭ ማሸነፉ ሳይሆን፣ መጀመርያ አማራጮችን ማመንጨት፣ መቀመር የሚችሉ ነፃ ድርጅቶች መብዛታቸው፣ ማበባቸው፣ አማራጮችም በነፃ መቅረባቸው፣ ቀርበውም በነፃ፣ በእርጋታ ተገላብጠውና በደንብ ተመክሮባቸው በሕዝባዊ አወሳሰን ዕልባት ማግኘታቸው፣ በተግባር ሲውሉም ሊታረሙ፣ ሊነቀሱና ሊሻሻሉ የሚችበት ዴሞክራሲዊ ሁኔታና አሠራር አብሯቸው መኖሩና መዝለቁ ነው፡፡

ኢሕአዴግ (ኢሕአዴግ ማለት ሕወሓት ነው) ሥልጣን ላይ የወጣው በጦርነት ነው፣ የአገር መከላከያ የሆነውም የራሱ ተጋዳላይና አከርካሪ ነው፡፡ ትናንትም ዛሬም ሕወሓት የታጠቀ ፓርቲ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ይዘት ትናንት የሕወሓት የነበረ መሆኑ፣ ያራባቸውም ድርጅቶች ሁሉ የአንድ ይዘት ማለትም የራሱ ልዩ ልዩ መልክና ቅርፅ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ዛሬም ሕወሓት የኢትዮጵያ መከላከያ ላይና ሕገ መንግሥቱ ላይ አምፆና ተኩሶ ራሱን አስታጥቋል፡፡ ሲያስታጥቅም የኖረው በመላው የገዥ ፓርቲነት የሥልጣን ዘመኑ ሕገ መንግሥቱን ሸፍጦ በሕገ መንግሥት ላይ ሴራ ሠርቶና ሸፍቶ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አውታረ መንግሥት ሕወሓታዊነት እያለ ዴሞክራሲን ማደላደል አይቻልም በተባለ፣ ልዩነትን በውይይት፣ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ዴሞክራሲና ጨዋነት ከአንደበት ወግነትና ከማጭበርበሪያነት ወጥቶ እስትንፋሱ ያደረገ ሥርዓት ለማደላደል ፓርቲዎችን ከጠመንጃ ማፋታት ያስፈልጋል ማለትን የጥበብ መጀመርያ ክዶ፣ ስለዴሞክራሲና ወደ እዚህም ስለሚወስድ ድርድር መናገር በመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ላይ መቀለድ ነው፡፡ እዚህ ‹‹ሹፈት›› ውስጥ በርካታ ማፈሪያና መሳቂያ ነገሮች ይሰማሉ፡፡ አንዳንዶችን ለመጥቀስ መንግሥት ከሕወሓት ጋር ‹‹ድርድር›› ውስጥ ከመግባቱ በፊት ሕወሓት ትጥቅ መፍታት አለበት ሲባል፣ የፓርቲው አባላት/ደጋፊዎች በዚህ ወመኔነትና ትግል የጠራ መለኪያ ባላገኘበት ‹‹ፖለቲካ››ችን ውስጥ ጉዳዩ ከተነሳ አይቀር፣ በአንድ አገር ውስጥ የመንግሥት መከላከያ አንድ ብቻ ነው ማለት ላይ ተንጠልጥለው፣ ውይይቱ/ድርድሩ ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ‹‹TDF›› ይሁን ‹‹EDF›› መናጋገሪያ ሊሆን ይችላል አሉ፡፡ በዚህም አልተወሰኑም፡፡ መከላከያን የመሰለ የአገር አወታረ መንግሥት የመገንባት ታላቅ አደራ ‹‹የቁንጅና ውድድር›› አድርገው አሳንሰውና አዋርደው አቀረቡት፡፡

ለውጡ ይቀጥል፣ ከአምባገነንነት፣ ከሕወሓት አደራጊ ፈጣሪነት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር ይቀጥል፣ የዚህም አንድ ወሳኝ አካል የመንግሥት አውታራትን ሕወሓታዊነት ማፅዳት ነው ሲባል ዛሬም ‹‹ሆ ብዬ እገባለሁ!›› የሚሉት ከ‹‹ሠራዊታቸው›› ጋር ነው፡፡ እዚህ የፖለቲካ ‹‹ኩሸት›› ውስጥ የፌዴራሉ መንግሥት ደጋፊዎች ስለብቸኛ አንድ የመከላከያ ኃይል የሚያወሩት ስለጥምር ጦር፣ ‹‹ጥምር ጦር›› እያሉ ጭምር ነው ብለው ‹‹ይቀልዱብናልም››፡፡

ፓርቲዎች ሁሉ በዚህ ስም ለመጠራት በውስጣቸው ዴሞክራሲን የሚኖሩ፣ ዴሞክራሲን የሚተነፍሱ መሆን አለባቸው ብሎ የአገርን ‹‹አደራ›› ከባድነት ለማሳየት ምሳሌዎችንና ማስጠንቀቂያዎችን ታሪክ በገፍና በአደባባይ እያቀረበችልን ነው፡፡  የምንከተለው ‹‹ሥርዓተ መንግሥት›› ፓርላሜንታዊ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 45 መሠረት፣ የዚህ ሥርዓት እናትና ‹‹አናት›› በምትባለዋ በታላቋ ብሪታንያ መክረሚያችን እንዳየነው በሆነ ምክንያት ከምርጫ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ቦታ ክፍት ቢሆን ባለ ጉዳዩ፣ ‹‹አድራጊው ፈጣሪው›› በፓርላማ ውስጥ አብላጫ ድምፅ ያለው ፓርቲ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ቦሪስ ጆንሰንን የሚተካ ለአገር የመረጠው ሁለት ወር በወሰደ የገዛ ራሱ የውስጥ ደንብ መሠረት የፓርቲው የፓርላማ አባላትና የፓርቲው መዋጮ ከፋይ አባላት ድምፅ ነው፡፡ ፓርላማው እንደ ተቋምና እንደ እኛ ደግሞ ለወግ ያህል እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ይሰይማል አልተባለም፡፡ በዚህ ምክንያት እስከ ጃንዋሪ 24 ቀን 2025 ዓ.ም. ምርጫ ድረስ (ወይም ከዚያ በፊት ምርጫ ይደረግ ካልተባለ በቀር) የታላቋ ብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር በሕዝብ ያልተመረጠ ጠቅላይ ሚኒስትር ነው ማለት ነው፡፡ የምናቋቁማቸው፣ የምንመርጣቸው ፓርቲዎች ዴሞክራሲን ለራሳቸው የሚኖሩ መሆን አለባችው የምንለው ይህን የመሰለ አደራና ሥልጣንም ስላላቸው ነው፡፡

አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በሞት፣ በገዛ ፈቃዱ ወይም በሌላ ምክንያት ሥልጣኑን ቢለቅ፣ ተተኪ የሚመረጠው በዚህ የታላቋ ብሪታንያ የቅርብ ጊዜ ትኩስ ዜና እንዳየነው፣ በአጠቃላይ ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ በገዥው ፓርቲ የአመራር ምርጫ ሕግ መሠረት ነው፡፡ ቦሪስ ጆንሰንን የሚተኩት ጠቅላይ ሚኒስትር የተመረጡት በቶሪ/ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ አመራር የምርጫ ውድድር ውስጥ ነው፡፡ በጠቅላላው የ172,437 (አንድ መቶ ሰባ ሁለት ሺሕ አራት መቶ ሰላሳ ሰባት) የፓርቲ አባላት ድምፅ ሰጪዎች ጉዳይ ሆኖ የተከናወነ ምርጫ ነው፡፡ ይህን የመሰለ ሚናና ሥልጣን ያለው የትኛውም ፓርቲ በዴሞክራሲያዊ መርህ ተደራጅቷል ወይ? ብሎ መጠየቅና መረጋገጥ በየጊዜውም መፈተሽና መተማመኛ መስጠት አለበት፡፡

ፓርቲዎች ሁሉ ዴሞክራሲን ይኖሩታል ወይ? በዴሞክራሲ መርህ ተደራጅተዋል ወይ? ማለት ቢያንስ ቢያንስ የፓርቲው ተግባራት የሚከናወኑት በቀጥታም ሆነ በተወካዮቻቸው አማካይነት እኩል መብት ባላቸው በጠቅላላው የፓርቲ አባላት ነው፡፡ መሪዎቹ የአመራር አካላና የፓርቲው ተቋማት በሞላ በምርጫ የሚቋቋሙ፣ ለመራጫቸው ተጠያቂና በሌሎች ሊተኳቸው የሚችሉ ናቸው ማለት ጭምር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ውስጥ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ተካሄደ ተብሎ እነ ሱዛን ራይስ የመሰከሩለትን ተዓምር ለማመን ይቅርና ነፃና ፍትሐዊ የሚሉን ቃላት ለአፍ ለመጠቀም ቀናነት የሌለው፣ የእሱና ሴትየዋ ሱዛን ራይስ ‹‹የሳቁበት›› ዴሞክራሲ ዳኛው ከእኔ ሆኖ፣ እኔ በሰፊው ሜዳ አንተ በቀጭን ገመድ ላይ እንሽቀዳደም የሚል ዓይነት ነበር፡፡ በራሱ በውስጥም ቢሆን የተሻለ ሐሳብና የተሻለ ችሎታን በክርክርና በውድድር የማንጠር ወይም በድምፅ የመለየት እስትንፋስ ያልነበረው፣ ዛሬም የሌለው ተቋም ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሲመጣም፣ ሥልጣን ላይ እያለም አሁንም የታጠቀ ድርጅት ነው፡፡ የታጠቀ ፓርቲ ብሎ ዴሞክራሲ የለም፡፡

ደጋግመን እንዳልነው መንግሥትን በኃይል የመጣልና የመተካት ታሪክ መቆም አለበት፡፡ ይህ የሚጀምረው ያለውን መንግሥት፣ የምርጫ ሥርዓትና ሕገ መንግሥት ሁሉም መነሻው አድርጎ እንዲነሳ ከሚያደርግ ስምምነትና መግባባት ነው፡፡ ይህ መነሻ የፍቅርና የመውደድ ጉዳይ አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ መንግሥትንም፣ የምርጫ ሥርዓቱንም፣ ሕገ መንግሥቱንም በጭፍን ፍቅር ወይም ጥላቻ ወይም በሌላ የተሻለ ዘዴ የመውደድና የመጥላት ሳይሆን፣ የተቀበለውም ሆነ መለወጣቸውን የሚፈልግ ሁሉ ፍላጎቴን ይዤ ለመታገልና ለመወዳደር ያስችለኛል ብሎ የሚያምንበት የዴሞክራሲ ሁኔታ የመኖርና ያለ መኖር ጉዳይ ነው፡፡ በራሱ በሕወሓት/ኢሕአአዴግ ዘመን በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ሲጠየቅ የኖረው ይኼው ነው፡፡ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት ዋናው የአገር ሥራውና አደራው አድርጎ ሲዋጋው የኖረው የዚህ ሰላማዊ ትግል ዒላማ ገዥው ቡድን ሳይሆን እኔ ብቻ ልክና ትክክል ብሎ፣ ለብቻዬ ልገዛ ብሎ፣ በመንግሥታዊ ሥርዓቱ በአስተሳሰብና በአሠራር ባህል ላይ ሥራዬ ብሎ ያደረሰው ብልሽትና ምስቅልቅል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥታዊ አውታሩ ከየትኛውም ቡድን/ፓርቲ ይዞታነት እንዲላቀቅ የዴሞክራሲዊ መብቶችና ነፃነቶች ችሮታነት እንዲያከትም በመታገል ላይ ማተኮር ነው፡፡

ሕወሓት/ኢሕአዴግን ብቻ ሳይሆን የትኛውንም ፓርቲ ከባለ ጠመንጃነት፣ ከብረት ትግል የማላቀቅ ትግሉ የተጀመረው የመንግሥት አውታራት ኢሕአዴጋዊነት ይጥራ፣ አምባገነንነትንና የፓርቲ ወገናዊነትን እንዲያገለግሉ የተቀነባበሩ አውታራት ለሕዝብና ለሕግ ብቻ ታምነው ሊያገለግሉ አይችሉም ተብሎ ‹ለውጥ›› እና ሽግግሩ ሲካሄድ ነው፡፡ ሕወሓት ባለ በሌለ ኃይሉ የወጋው ይህንኑ ነው፡፡ የጦርነቱ መነሻም ይኼው ነው፡፡

ድርድሩ፣ የሰላም ውይይቱ ከሚነሳቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋናው ፓርቲዎችን/የፖለቲካ ቡድኖችን ከብረት፣ ከጠመንጃ ማገላገልና ማፋታት ነው ሲባል፣ አንዳንድ ጊዜና አንዳንዶቻችን ይህ አቋም አሁን ከነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በተለይም ከመስከረም አንዱ የሕወሓት/ደብዳቤ ወዲህ የመጣ ነገር ሊመስል ይችላል፡፡ ፓርቲዎች ከጦር ሠራዊትና ከጠመንጃ ይቆራርጣሉ ማለት ዴሞክራሲን የመገንባት፣ በገለልተኛ መደላደል ላይ ዴሞክራሲን የማቋቋም መነሻው ነው፡፡ በ1983 ዓ.ም. ግንቦት የጀመረው ሽግግር የከሸፈው የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ትግል ሁልጊዜም ያጎደለው፣ ገለልተለኛ ተቋም ላይ የመደላደል ነገር እዚህም ላይ እንደገና በመጋረጡ ነው፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ምርጫ፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እያለ ያጓራና በውጭም አዝማሪ ባዘፈነው ልክ የሕዝብን መተማመኛ አጣለሁ፣ ተጋልጬ እጠየቃለሁ የሚል ፍርኃት ሳያሠጋው ተቃውሞን፣ ለዚያውም ሰላማዊ ተቃውሞን በኃይል ለመደፍጠጥ የደፈረውና ሙያውም አድረጎ የኖረው፣ በመጨረሻም በመላው ዓለም በየኤምባሲው፣ በየትምህርት ተቋሙ፣ በመንግሥታቱ ድርጅት ተቋማትና በኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪዎች ውስጥ ሳይቀር  በግልጽም በሥውርም ‹‹Sleeper Cells›› (የክፉ ጊዜ ጥሪ ዘብ ቋሚዎች ተጋዳላዮች) አደራጅቶና አሠማርቶ የኖረው፣ መኖር የቻለው በዚህ የሥር የመሠረት ችግር ምክንያት ነው፡፡ እንኳንስ እዚህ ድረስ የገፋና የከፋ መበለሻሸትና መዝቀጥ ተደርሶ ይቅርና ፓርቲንና ጠመንጃን፣ የፖለቲካ ቡድንና ብረትን/መሣሪያን ማለያየት ብዙ ጥንቃቄና የመጠበቂያ መላ ሊበጅለት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የራሱ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ከዚህ ቀደሙ የ‹‹ሰላማዊ›› ጊዜው ገዥነቱ፣ በነፃና በፍትሐዊ ምርጫ ላይ የተንጠለጠለ ያልነበረበት ምክንያት ይኼው ነበር፡፡ ፓርቲና ጠመንጃ አለመለያየታቸው፣ የመንግሥት አውታራት በመላ (አሁንም ገና ትኩረት ያላገኘውን ሲቪል ሰርቪሱን ጨምሮ) ከፓርቲ ባለቤትነትና ወገንተኛነት ባለመላቀቃቸው ነው፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሺሕ ጊዜ ምርጫ ቢባል ምርጫ የማያንሸራትተውና የሚያናጋው ሆኖ ሥልጣንን በርስትነት ይዞ የኖረው፣ ራሱም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በውጭ አገር የኢትዮጵያ ጥቅሞች ውስጥ ሁሉ ጥገኛ ገዥ ሆኖ የተቋቋመው፣ እጁ የነካውን የመንግሥት ሥልጣን ባደረሰው ሁሉ፣ በመንግሥታዊ ቢሮክራሲውና ከዚያም ውጪ በሆኑ የኑሮ ዘርፎች በሙሉ ሳይቀር ለራሱ አገዛዝ የማጎንበስ አጠቃላይ እውነታ የፈጠረው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ተደጋግሞ አገራችን ስላመለጧት ዕድሎች ይነገራል፡፡ እኛም የ1983 ዓ.ም. ሙከራ አንስተናል፡፡ የ1983 ዓ.ም. የለውጥና የሽግግር ሙከራ ገና ከመነሻው የከሸፈው በጦር ሜዳው፣ በመሣሪያ ትግሉ ‹‹ድል›› ያደረገው ሕወሓት ካሸነፈው፣ የመንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ ወደ ተፎካካሪ ፓርቲነት፣ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ተፎካካሪነት መለወጥ ባለመቻሉ፣ ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብ፣ ምግባርና ኃላፊነት አልይዝም በማለቱ ነው፡፡ ከለመደው የጦርነትና እሱ ‹‹ፖለቲካ›› ከሚለው ሥልት መሸጋገር፣ መለወጥ ባለማወቁና ባለመቻሉ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን ለአሥራ ሰባት ዓመታት ሲገዛ የቆየው የወታደራዊው አምባገነን መንግሥት መገርሰስ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩንና መንግሥቱን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንደ አዲስ ለመገንባት የሚችልበት ዕድል የከፈተ ታሪካዊ ወቅት በመሆኑ…››  ብሎ የኢትዮጵያን የሽግግር ወቅት ቻርተር ያወጀው ሕወሓት ያለ ተቃዋሚ፣ ያለ ሌላ ፓርቲ ሥራውን ማካሄድ አለመቻሉን ልዩ ሴራና ተንኮል በእሱ ላይ የተጎነጎነበት አድርጎ አምኖ ተቀውሞን ማሳደዱ ዋናው የመንግሥት ሥራ አደረገ፡፡ እናም በኢትዮጵያ ለውጥና ሽግግር ውስጥ፣ ዴሞክራሲ እገነባለሁ፣ እሱንም እቀላቀላሁ የሚል ሁሉ መጀመርያ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት መለወጥ ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብ፣ ምግባርና ጨዋነት ይዞ መገኘት አለበት፡፡ ከትጥቁ መፋታትማ ለድርድር የማይቀርብ ዋናው ጉዳይ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...