በመታሰቢያ መላከ ሕይወት
በመጀመርያ ግሽበትና ግሽበቶች የሚለውን እንመልከት፡፡ ለምሳሌ በጦርነት ወይም በሌላ ምክንያት በድንገት የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ ቢጀምር፣ ይህ ግሽበት የተናጠል ግሽበት ልንለው እንችላለን፡፡ ከዚህ በመቀጠል ግን የምግብ፣ የትራንስፖርትና በአጠቃላይ ሌሎች በርካታ ግሽበቶች ይፈጠራሉ ማለት ነው፡፡ ይህንን ክስተት ግሽበቶች ልንለው እንችላለን፡፡
መንግሥት ሆነ ብሎ የሚፈጥረው ግሽበት ደግሞ የኢትዮጵያ ምርታማነት እየቀነሰ ባለበት ሁኔታ ባለ ፋብሪካዎች በጥሬ ዕቃ እጥረት፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እያቃታቸው, ምርታማነት እየቀነሰ ባለበት ወቅት መንግሥት ለብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ እየሰጠ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲታተም ካደረገና ይህ ገንዘብ በደመወዝና በሌሎችም የመንግሥት ወጪዎች ምክንያት ኢኮኖሚው ውስጥ የሚሠራጭ ከሆነ፣ ይህንን ዓይነትን ግሽበት መንግሥት ሆነ ብሎ የፈጠረው የዋጋ ግሽበት ልንለው እንችላለን፡፡
ይህ በደመወዝና በተለያዩ የመንግሥት ወጪዎች ምክንያት ወደ ኢኮኖሚው የተሠራጨው ገንዘብ ሊገዛው የሚችለው በቂ ምርት ሊኖር ስለማይችል, ሌሎች በርካታ ግሽበቶችን መፍጠር ይጀምራል፡፡ በዚህን ጊዜ ነው የዜጎች ሕይወት መመሰቃቀል የሚጀምረው፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ በቁጥር 2331 ነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው ዕትም፣ የመንግሥት የአገር ውስጥ ዕዳ 1.5 ትሪሊዮን ብር እንደደረሰ አንብበናል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው በአገሪቱ ውስጥ ባለው የፀጥታ መደፍረስ፣ የጦርነትና የሰላም ዕጦት ምክንያት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ምርታማነት እጅግ ከማሽቆልቆሉ በተጨማሪ አብዛኞቹ የማዕድን ልማቶች በመዘጋታቸው የመንግሥት ገቢ እጅግ አሳሳቢ ሆኖ ቀንሷል፡፡ መንግሥት ይህንን ችግር ለመለወጥ ሥር ነቀል ለውጦችን በማድረግና በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ዜጎች ያለ ችግር መሥራት የሚችሉበት ሥርዓት ለመፍጠር መሥራት ሲገባው፣ ምርታማነት በሌለበት ሁኔታ ገንዘብ በማተም የመንግሥትን ወጪ ለመሸፈን የሚደረግ ተግባር እጅግ ኃላፊነት የጎደለውና አገርን ወደ ከፋ አደጋ የሚወስድ ተግባር ነው፡፡
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ገንዘቡ እንዲታተም በቀጥታ ትዕዛዝ ያስተላለፉ የሙያተኞች ስብስብ ወይም የገንዘብ ሚኒስትሩ ሳይሆኑ፣ ይህ ትዕዛዝ በቀጥታ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ነው ብሎ ያምናል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ማንኛውም ዜጋ ለዕለት ፍጆታው የሚሆንን ገንዘብ ካልሆነ በስተቀር፣ የትኛውም ባለሀብት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ባንክ ውስጥ ማስቀመጥ የሚፈልግ የለም፡፡ ምክንያቶቹ ደግሞ ብዙ ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ባንክ የተቀመጠ ገንዘብ በየቀኑ የመግዛት አቅሙ እየቀነሰ ስለሚሄድ ለአስቀማጩ ከፍተኛ ኪሳራ ነው፡፡ ሁለተኛው ሌላው ምክንያት ደግሞ ገንዘብ ባንክ ከማስቀመጥ ይልቅ ዋጋ ሊጨምር የሚችል፣ ዕቃ ላይ ወይም ግንባታ ላይ ቢውል ባለ ገንዘቡን ወደፊት ተጠቃሚ ሊያደርገው ስለሚችል ገንዘብ ያላቸው ሰዎች እየተሯሯጡ አላቂ ያልሆኑ ምርቶችን መሸመት ይመርጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ ያለማቋረጥ አስፈሪ ግሽበት እየፈጠረ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ሲሚንቶ እጥረት የተፈጠረበት ምክንያት ቢታይ፣ ዜጎች ውድ የሆነውን ሲሚንቶ እንኳን በመግዛት ግንባታ ማካሄድ ይመርጣሉ እንጂ፣ ብሩን ባንክ ማስቀመጥ አይፈልጉም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በከተማችን በበቂ ሁኔታ መከራየት ያልቻሉ እጅግ በርካታ ሕንፃዎች አሉ፡፡ ባለቤቶቹ ‹‹ገንዘብ ከማስቀምጥ ፎቅ ገንብቼ ድንጋዩ ቆሞ ቢቀመጥ ይሻላል›› እያሉ በውድ ዋጋ ሲሚንቶና ብረት እየገዙ ግንባታ በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ 1,600 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ አንድ ኪሎ ግራም ብረት ደግሞ 120 ብር እየተሸጠ ነው፡፡
ሰዎች በዚህ ደረጃ ምንም አገራዊ ፋይዳ የሌላቸው ግንባታዎች ውስጥ እየተሰማሩ ገንዘብ ሲያባክኑ፣ ባንክ ውስጥ ያለው ገንዘብ መጠኑ እጅግ ስለሚያንስ የባንኮች የማበደር አቅም (Liquidity) በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ በተጨማሪ ዜጎች ለሚያስቀምጡት ገንዘብ ሰባት በመቶ ወለድ ቢያገኙም፣ ባንኮች ለባለሀብቶች ሲያበድሩ እስከ 18 በመቶ የሚደርስ ወለድ እያስከፈሉ ያበድራሉ፡፡ ዜጎች ገንዘብ ባንክ አስቀምጠው የሚያገኙት ሰባት በመቶ ወለድ ሲሆን፣ ነጋዴዎች ከባንክ ተበድረው ገዝተው በሚሸጡት ምርት ላይ ለባንክ የሚከፍሉትን 18 በመቶ ሲደመር ትርፋቸውን አስበው ይሸጣሉ፡፡ ዜጎች ባንክ ገንዘብ አስቀምጠው ከሚያገኙት ወለድ የበለጠ ለሚገዙት ምርት ወጪ ስለሚያደርጉ፣ ገንዘብ መቆጠብ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ ትርጉም አልባ ሆኗል፡፡
እንደሚታወቀው ብዙ ያደጉት አገሮች ዜጎች ገንዘብ እንዲቆጥቡ በማስተማርና በማበረታታት እንጂ ገንዘብ ባንክ ማስቀመጥ ሞኝነት ከሆነ፣ አገር (ዜጎች ገንዘብ የመቆጠብ ባህላቸውን ተጠቅማ ማግኘት የምትችለው ዕድገት) መቼም አታገኝም ማለት ነው፡፡
በቅርቡ ደግሞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የሚፈቅድ ውሳኔ እንዳሳለፈ ሰምተናል፡፡ ውሳኔው ቢዘገይ እንጂ ትክክለኛ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ውሳኔ ብቻውን ምንም የሚፈጥረው ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም አንድ አገር ኢኮኖሚዋን ለውጭ ባንኮች ከፈተች ማለት ዓለም አቀፋዊ ወይም ግሎባላይዝድ ሆነች ማለት ነው፡፡ ይህ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ግሎባላይዝድ ለመሆን ሁሉንም ዓይነት የግሎባላይዜሽን ሕግና ሥርዓቶችን መከተል ግድ ይላል፡፡
እንደሚታወቀው በየትም ዓለም የሌለ ሕገ መንግሥት ይዘን፣ ገና የመሬት ባለቤትነት መብት ለዜጎች የተከለከለ መብት ሆኖ ባለበት አገር፣ በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት መካከል በሁለት አገሮች መካከል እንዳለ ዓይነት ግንኙነት ባለበት ሁኔታ፣ የግል ባንኮች እንኳን በክልል ሕጎች ምክንያት ችግር ውስጥ ባሉበት ሁኔታ፣ የውጭ ባንኮች አገር ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱ በተዓምር ተግባራዊ አይሆንም፡፡ ወይም ውጤት አያመጣም፡፡ ምናልባት የኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ያልገባቸው ባንኮች ሊገቡ ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ገብተው ሥራ መሥራት የሚችሉበት ሁኔታ የለም፡፡ የውጭ ባንኮች ከእኛ ባንኮች በእጅጉ የሚለዩት ያላቸው የካፒታል አቅም፣ የዘመነ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትና ያላቸው ደንበኛን የማስተናገድ ሥርዓት ከእኛ ባንኮች በእጅጉ ይሻላሉ፡፡
ነገር ግን መጫወቻ ሜዳውን ሳናስተካክል፣ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ የቤት ሥራዎችን በአግባቡ ሳናከናውን፣ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስላለበት ብቻ ይህ ውሳኔ መወሰኑ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በእርግጠኝት ውጤት ያመጣል ብሎ አያምንም፡፡ መንግሥት መሥሪያ ቤት ሄዶ ጉዳይ ማስፈጸም በማይታሰብበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ የውጭ ባንኮች በዋናነት የምንፈልጋቸው አገራችን በተፈጥሮ ሀብት የተንበሸበሸች በመሆኗ ሲሆን፣ ይህንን ሀብት ወደ ጥቅም ለመለወጥ ገንዘብ ዋነኛ ግብዓት ስለሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እኮ ነዳጅ ሸጣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የማግኘት አቅም ቢኖራት፣ ምናልባት የውጭ ባንኮችን ላንፈልጋቸው እንችል ይሆን ነበር፡፡ በእርግጠኝነት የዓባይን ግድብ እንኳን ለመገደብ እያንዳንዱ ዜጋ የተቻለውን አዋጥቶና መንግሥት ገንዘብ ከያለበት አፈላልጎ የተደረገ ግንባታ እንጂ፣ እንዲህ በቀላሉ በተገኘ ገንዘብ የተገነባ አይደለም፡፡
የግል ባንኮች ደግሞ ወደ አገር ውስጥ መግባት ዓባይ ተገድቦ ሲያልቅ፣ በተጨማሪ እንደ ኮይሻ ያሉ ግድቦች ተገንብተው ሲያልቁ የሚፈጠረውን ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚገዙ ባለሀብቶች እንደልባቸው የሚበደሩት ገንዘብ እንዲኖር አስፈላጊ በመሆኑ፣ የውጭ ባንኮች በአሁኑ ጊዜ ወይም ቀደም ብለው መግባታቸው በእጅጉ አስፈላጊ ነው፣ ተገቢም ነበር፡፡ በተጨማሪ ባለሀብቶች ገንዘብ ተበድረው በመላው ኢትዮጵያ ተዘዋውረው ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ግብዓቶች ከሞላ ጎደል ተሟልተዋል፡፡ ለምሳሌ የመንገድ፣ የድልድይ፣ የቴሌ ኔትወርክ፣ በቂ የተማረ የሰው ኃይልና የኃይል አቅርቦት የመሳሰሉት ባለሀብቶች ብድር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ወደ ሥራ ገብተው አትራፊ መሆን እንዲችሉና ዕዳቸውን በጊዜ ከፍለው ውጤታማ መሆን እንዲችሉ መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በእኔ ግምገማ በአሁኑ ጊዜ ማንኛውም ኢንቨስተር በፈለገው የአገሪቱ ክፍል ሥራ መሥራት ቢፈልግ፣ ምርት ለማጓጓዝ ወይም ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ የሚያግደው የመሠረተ ልማት እምብዛም የለም፡፡ ያለው ችግር የፀጥታና የሥርዓት ዕጦት ነው፡፡ ስለሥርዓት ደግሞ ስናነሳ የሕገ መንግሥት ሥርዓትን፣ የመሬት አስተዳደርን፣ የፌዴራል አወቃቀርን በዋናነት ማለታችን ነው፡፡
ከዚህ በፊት በጻፍኳቸው በርካታ ጽሑፎች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 ላይ ያለኝን ምልከታ ለመግለጽ ሞክሬ ነበር፡፡ አንቀጽ 8 ቃል በቃል እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ነው፤›› ይላል፡፡
ክልሎች የሉዓላዊነት ሥልጣን (ማዕረግ) ሕገ መንግሥቱ ቢሰጣቸውም፣ በተግባር ግን መቼም የሉዓላዊ አገር ተግባር ፈጽመው አያውቁም፡፡ ሉዓላዊነት ማለት አንደኛ አንድ አገር ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ ጉዳይ የመወሰን መብት ሲሆን፣ አንዲት ሉዓላዊት አገር ገንዘብ ማተም፣ ፓስፖርት ማተም፣ ዓለም አቀፍ ውል መዋዋል፣ መክሰስና መክሰስ፣ በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ላይ መሳተፍ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና ማግኘትንና ሌሎችንም መብቶች የሚያጎናፅፍ ማዕረግ ነው፡፡
እስኪ የተከበራችሁ አንባቢያን ክልሎች፣ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ይህ ከላይ የተጠቀሰው መብት ላለፉት በርካታ ዓመታት ኖሯቸው ያውቃል? ኖሯቸው ካላወቀስ እስከ መቼ ነው ክልሎች ሉዓላዊ ናችሁ እያልን የምንሸነግላቸው? በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ መሠረት ክልሎች የራሳቸው ሕገ መንግሥት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ክልሎች ያወጧቸው ሕጎች ደግሞ በርካታ ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚፃረሩ የሕግ አንቀጾች አሏቸው፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ነው ወይ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ቤት መጥተው እነሱ ውጤታማ ሆነው አገራችንን የሚጠቅሙት?
በኦሮሚያ ክልል የበርካታ ባለሀብቶች ፋብሪካዎች፣ ሆቴሎች፣ የሕክምናና የጤና ተቋማት የባለሥልጣናት ድጋፍ በነበራቸው ሕገወጦች የመቃጠልና የመውደም አደጋ ደርሶባቸው፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ምንም ዓይነት የካሳ ክፍያ ባላደረገበት ሁኔታ የትኛው ባለሀብት ነው ከውጭ ባንኮች ብር ተበድሮ ኦሮሚያ ክልል ሄዶ ኢንቨስት የሚያደርገው?
በተጨማሪ ይህ ሁሉ ውድመት ደርሶ በነበረበት ወቅት ሥልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች እስካሁን ሥልጣን ላይ እያሉ ባሉበት ሁኔታ፣ መንግሥት ከውድመቱ በኋላ ምንም ዓይነት ዕርምጃ ባልወሰደበት ሁኔታ፣ አገራችንን እስካሁን ባለው ሁኔታ እጅግ የሚያስፈራ የውጭ ብድር ውስጥ ከተናት፣ አሁን ደግሞ ባንኮቹ አገር ውስጥ ገብተው ለባለሀብቶች ገንዘብ እንዲያበድሩ የታሰበው ዕርምጃ በምን ተዓምር ነው አገራችንን ውጤታማ የሚያደርጋት? በአሁኑ ወቅት ማንም ፊደል የቆጠረ ሰው ሊመሰክረው የሚችለው ጉዳይ፣ አገር ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ከተቋማዊ አመራር ወጥታ ሁሉም ሥልጣን በአንድ ሰው እጅ ገብቷል፡፡
በሕወሓት ዘመንም ይህ ሁኔታ የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ ደረጃ ተቋማት ሙሉ በሙሉ አቅማቸው አልጠፋም ነበር፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አዘጋጅ ከዛሬ አምስት ዓመታት ጀምሮ የውጭ ባንኮች ወደ አገር መግባት አስፈላጊነቱን ደጋግሜ ለማሳሰብ ሞክሬያለሁ፡፡ በዚሁ በሪፖርተር ጋዜጣ በቁጥር 1761፣ 2009 ዓ.ም. የውጭ ባንኮች አገራችን ካላት የተፈጥሮ ሀብትና የሥራ ፈላጊው ወጣት ቁጥር አኳያ የውጭ ባንኮች ይዘውት የሚመጡት ካፒታል በእጅጉ እንደሚጠቅማት፣ ይህንን ከማድረጋችን በፊት መሥራት ያለብን የቤት ሥራ በተገቢ መንገድ ሠርተን በዓለማችን በተትረፈረፈ መልኩ ያለን የዕውቀትና የገንዘብ ሀብት ወደ አገራችን ማስገባት ብልህነት እንደነበር ለማሳሰብ ሞክሬ ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚህ ጊዜ በኋላ የመንግሥት ለውጥ ከመደረጉ በዘለለ የአስተሳሰብና የሥርዓት ለውጥ አልተደረገም፡፡
በአሁኑ ጊዜ በማዕከላዊ መንግሥትና በደብረ ጽዮን በሚመራው ሕወሓት መካከል ጦርነት እየተካሄደ ነው፡፡ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሆኑ ደብረ ጽዮንም የሚመሩት በተመሳሳይ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መጡ እንጂ ምንም ዓይነት (ሕወሓት የተከለውን የተበላሸ ሥርዓት) ለመለወጥ ሙከራ አላደረጉም፡፡ ታዲያ ለምንድነው እነዚህ ሁለቱ ኃይሎች የሚፋለሙት? ለአራት ኪሎ ወንበር ነው ወይስ ለሥርዓት ለውጥ? ሁኔታው በእጅጉ የሚገርም ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሠራዊት በጦር ሜዳ የሚረግፍበት አጀንዳ ምንድነው? በወልቃይት ጉዳይ ነው እንዳይባል እኔ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በውጭ ጸሐፊዎች የተጻፉ መጻሕፍት አሉኝ ወይም መረጃውን ለማሳሰብ ሠርቻለሁ፡፡
አንደኛውም የታሪክ ጸሐፊ ሰሜን በጌምድር ሰሜን ጎንደር በትግሬ ራስ ወይም ንጉሥ ተገዝቶ ያውቃል ብሎ የጻፈ የለም፡፡ ሁሉም ጸሐፊዎች የትግሬና የአማራ ድንበር ተከዜ ነው ብለው የጻፉት በዚህ ታሪካዊ ማስረጃ መሠረት የወልቃይትን አጀንዳ ሙሉ ለሙሉ መተው አለብን፡፡ በመጨረሻም መንግሥት የሙያተኞች ሥሌት ሳይኖር በባለሥልጣን ትዕዛዝ ብቻ ገንዘብ እያተሙ ኢኮኖሚ ውስጥ መርጨት የግድ መቆም ያለበት ተግባር ነው፡፡
የውጭ ባንኮች ወደ አገር ሲገቡ የአገር ውስጥ ባንኮች ይተናሉ እየተባለ በስፋት ሲነገር ሰምቻለሁ፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እስካሁን ያሉት ባንኮች አሉ ከሚባሉ የሉም ቢባል የተሻለ ነው እላለሁ፡፡ ምክንያቱም መቼም አንድ ባንክ ሊሰጠው የሚገባን ተግባር ከውነው አያውቁም፡፡ ፋብሪካ፣ ትልቅ ሕንፃ ወይም ሀብት ካለው ባለሀብት ኮሚሽን እየተቀበሉ ያበድሩ እንደነበር ሁላችንም ያጋጠመን ክስተት ነው፡፡ የውጭ ባንኮች በቂ ካፒታል ይዘው ስለሚመጡ የመበደር ብቃት ላላቸው ተበዳሪዎች እጅግ የተቀላጠፋ የብድር አገልግሎት እንደሚሰጡ እኔ በምዕራቡ ዓለም በኖርኩበት ወቅት መታዘብ ችያለሁ፡፡ በሌላ አነጋገር እስካሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ነበር፡፡ ነገር ግን አገልግሎቱ ፈጽሞ ኖሮ አያውቅም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው metasebyamelaku@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡