Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹ ምርጫው ተከናውኖ ውጤቱ እስኪታወቅ ከፍተኛ ውጥረት ነበር›› ወ/ሪት ሳምያ አብደላ፣ የኦሮሚያ...

‹‹[የፕሬዚዳንት] ምርጫው ተከናውኖ ውጤቱ እስኪታወቅ ከፍተኛ ውጥረት ነበር›› ወ/ሪት ሳምያ አብደላ፣ የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ

ቀን:

በአገር አቀፍ ውድድሮች በተለያዩ ስፖርቶች ተሳትፎ አድርጎ እንደ ክልል በበላይነት ያጠናቅቃል፡፡ ከታዳጊ እስከ አዋቂ ስፖርተኞችን በማሳተፍ ተፎካካሪ ነው፡፡ ክልሉ ከአገር አቀፍ ውድድሮች ባሻገር፣ ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም አቀፍ መድረክ የሚካፈሉ ስፖርተኞችን ከማበርከት አንፃር የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በተለይ በዓለም አደባባይ የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብ የቻሉ በርካታ አትሌቶች መፍለቂያነት ይታወቃል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በተለይ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ያለው እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ታይቶበታል፡፡ በዚህም የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ቀድሞ የአትሌቲክስ መፍለቂያ ከሆኑ አካባቢዎች ባሻገር፣ በሌሎች የክልሉ ከተሞች ተተኪዎችን ለማፍራት ሰፊ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ በክልሉ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እየተገነቡ ቢሆንም፣ የጥራት ችግር እየተነሳባቸው መሆኑን ተከትሎ ዳግም በጥራት እንዲሠሩ ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡ ክልሉ በቅርቡ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት ዕጩ አቅርቦ ማስመረጥ ቢችልም፣ የተለያዩ ውዝግቦችን አስተናግዶ ማለፉ ይታወሳል፡፡ ሪፖርተር በክልሉ እየተደረጉ ስላሉት አጠቃላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ከኦሮሚያ ስፖርትና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ሳምያ አብደላ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡  

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ከሚገኙ ክልሎች ውስጥ የኦሮሚያ ክልል በርካታ ስፖርተኞች በማፍራት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ክልሉ ዓምና የነበረው የስፖርት እንቅስቃሴ እንዲሁም ተሳትፎ እንዴት ይገመገማል?

ወ/ሪት ሳምያ– በክልላችን ዓምና በስፖርቱ ታቅደው የነበሩ የተለያዩ ተግባሮች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም መካከል በዋነኛነት የማስ ስፖርት ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ማስ ስፖርት ከዞን አልፎ ወረዳ በሰፊው በኅብረተሰቡ ውስጥ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲደረግበት ነበር፡፡ ከዚያ በዘለለም ክልሉ በተለያዩ አገር አቀፍ ደረጃ በተሰናዱ ውድድሮች ላይ ተካፋይ ሆኖ አብዛኛው ሻምፒዮን ሆኖ ያጠናቀቀበት ዓመት ነበር፡፡ ሻምፒዮን ከመሆን ባሻገር በርካታ ተተኪ ስፖርተኞች የተገኙበትና ኢትዮጵያን በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ወክለው መወዳደር የሚችሉ ስፖርተኞች ማፍራት የተቻለበት ጊዜ ነበር፡፡ ከተሳትፎውም በዘለለ የተለያዩ የአሠልጣኞች ሥልጠና ለበርካታ ባለሙያዎች ሰጥተናል፡፡ በሌላ በኩል በክልሉ 834 ክለቦች፣ 6,574 የስፖርት ምክር ቤቶች፣ 327,889 ኮሚቴዎች፣ 38,930 የስፖርት ቡድኖች እንዲጠናከሩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ተቋማቱ ራሳቸውን ችለው፣ የማስፈጸም አቅማቸውን አጠናክረውና ዕቅዳቸውን እንዲፈጽሙ ማድረግ ተችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- በክልሉ ሲከናወን እንደነበር የተጠቀሰው የማስ ስፖርት እንቅስቃሴ ወጥነት የሌለውና እንዲሁ ለይስሙላ የተደረገ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህ ጉዳይ ስፖርት ቢሮው እንዴት ይመለከተዋል?

ወ/ሪት ሳምያ፡- እንደ ዕቅድ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ከተሞች ላይ ወር በገባ በሁለተኛ ሳምንት ማስ ስፖርት እንዲከናወን ነው የተቀመጠው፡፡ ሆኖም ተሳታፊነቱ ወጥ አይደለም እንጂ እንቅስቃሴ ይደረጋል፡፡ እኛም እንደ ቢሮ ሁሉም አካባቢዎች ላይ ተገኝተን እንዲከናወን ማነቃቃት ስለማንችል፣ በአንፃሩ አንዳንድ ወረዳዎች በተቀመጠላቸው መርሐ ግብር ያከናውናሉ፡፡ ገሚሱ ድግሞ ሲያከናውኑ አይስተዋልም፡፡ ስለዚህ ዘንድሮ በሁሉም ዞኖች፣ ወረዳዎችና የክፍላተ ከተሞች ሁሉም ኅብረተሰብ ተሳትፎ እንዲያደርግበት ጠበቅ አድርገን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ክልሉ የአገር አቀፍ ውድድሮችን በበላይነት ቢያጠናቅቅም፣ በተለይ በአትሌቲክስ መቀዛቀዝ ይስተዋልበታል፡፡ ችግሩ ምንድነው?

ወ/ሪት ሳምያ፡- መታወቅ ያለበት ስፖርት አንዳንድ ጊዜ በተፈለገው መንገድ ሊሄድ የማይችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ መቀዛቀዝ ይታየበት ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት ግን ዳግም እያንሰራራ ነው፡፡ በአትሌቲክስ በምንፈልገው ደረጃ ውጤት ማምጣት ባንችልም፣ ዘንድሮ ግን በተወሰነ ደረጃ መሻሻል አሳይቷል፡፡ ዓምና ባቀድነው መሠረት ግባችንን መተናል ማለት እንችላለን፡፡ በአገር አቀፍ ውድድር አሰላ ላይ በተከናወነው ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች ሻምፒዮና ላይ በሁለቱም ፆታ ክልሉ በበላይነት አጠናቆ አዳዲስ አትሌቶች ማግኘት ተችሏል፡፡ ሐዋሳ ላይ በተከናወነው የአዋቂዎች ውድድር ላይ አራተኛ ደረጃን ይዘን አጠናቀናል፡፡ ውጤቱ በርካታ ጉዳዮችን ወደ ውስጥ መመልከት እንድንችል ያስቻለን በመሆኑ፣ በታዳጊዎች ላይ በሰፊው ሠርተን ክልሉ የሚታወቅበትን የአትሌቲክስ ስኬት ዳግም እንዲያንሰራራ ለማድረግ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ችግሩ የነበረው ክልሉ ቀድሞ ያፈራቸውን አትሌቶች በታዳጊዎች ከሥር ከሥር መተካት አለመቻሉ ነው፡፡ አሁን ግን ከሥር ከሥር ተተኪዎችን ለማፍራት እየሠራን ችግሩን ለመፍታት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ በዚህም በአገር አቀፍ ውድድሮችን ብቻ በበላይነት ማጠናቀቅ ሳይሆን፣ ከሁለትና ከሦስት ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ወክለው የሚፎካከሩ አትሌቶችን ከወዲሁ ለማፍራት ግብ አድርገን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአትሌቲክስ ዕምቅ አቅም ያላቸውና በርካታ አትሌቶች ማፍራት የቻሉ ወ/ሪት ሳምያ– በእርግጥ እንደ ክልል ዕምቅ ኃይል ያላቸውን አካባቢዎች ካለመጠቀማችን በዘለለ፣ በትምህርት ውድድሮች ላይ ሊገኙ የሚችሉ አትሌቶችን ጭምር አጥተናል፡፡ ይህ ጥልቅ አቅም አሳጥቶናል፡፡ ሆኖም በ2015 ዓ.ም. በዕቅድ ከያዝናቸው ተቀዳሚ ግቦች ውስጥ የትምህርት ቤት ውድድሮችን እንደ ቀድሞ መመለስ ነው፡፡ የትምህርት ቤት ውድድሮችን ዳግም መመለስ በርካታ ችሎታ ያላቸውን ታዳጊዎች ለማግኘት ሁነኛ አማራጭ ነው፡፡ አሁን ላይ ቀድሞ በአትሌቲክስ ከሚታወቁ በቆጂና አሰላ ባሻገር፣ በሸዋ እንዲሁም ጉጂ ላይ ጥሩ ጥሩ አትሌቶችን እያገኘን እንገኛለን፡፡ ስለዚህ አትሌት የማፍራት አቅም ያላቸው አካባቢዎች ላይ ብቻ ትኩረት አድርገን መሥራት ሳይሆን፣ በሌሎችም አካባቢዎች ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተገንዝበናል፡፡ ስለዚህ ያሉትን ፕሮጀክቶችና አካዴሚዎችን የበለጠ አጠናክረን ተተኪዎችን የማፍራት ሥራችንን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከክልሉ የሚገኙ የእግር ኳስ ክለቦች በተለያዩ ውድድሮች ላይ እየተካፈሉ ይገኛሉ፡፡ በፕሪሚየር ሊግ ሲሳተፉ የነበሩ ክለቦች ወደ ሊጉ አድገው ወዲያው ደግሞ ሲወርዱ ይሰተዋላል፡፡ በሊጉ ወጥ አቋም ኖሯቸው መዝለቅ የማይችሉበት መንስዔ ምንድነው?

ወ/ሪት ሳምያ፡- በእግር ኳስ መሸነፍ፣ ማሸነፍ እንዲሁም ወደ ሊግ ማደግ፣ መውረድም የውድደር አካል ነው፡፡ ይህ በክልላችን የሚገኙ ክለቦች ላይ ብቻ የሚያጋጥም አይደለም፡፡ ዘንድሮ ከሊጉ ሁለት ወርዶብን አንድ ክለብ ደግሞ ወደ ሊጉ አድጓል፡፡ ይህ የተወሰኑ ችግሮች መከሰታቸውን ተከትሎ የሆነ ነው፡፡ እንደ ቢሮ ማድረግ የሚገባንን ቴክኒካል ድጋፍ እያደረግንና ከክለቦች ጋር እየተመካከርን እንቀጥላለን፡፡ ክለቦች የሚተዳደሩት በከተማ አስተዳደሮች ነው፡፡ ስለዚህ ክለቦችን ከሚያስተዳድረው አካል ጋር እየተመካከርን በ2014 ዓ.ም. የተከሰቱ ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ መፍትሔ እያበጀን እንቀጥላለን፡፡ ወደ ፕሪየሚር ሊግ ካደጉ ክለቦች ባሻገር ሱፐር ሊግ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ጠንካራ ክለቦች አሉን፡፡ ዘንድሮም የማይጠበቁ ክለቦች ማለትም ሮቤ ከተማና ሻኪሶ የመሳሰሉ ያደጉ ክለቦች አሉ፡፡ ስለዚህ በ2015 ዓ.ም. በርካታ ክለቦች ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲያድጉ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለን አቅደናል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የሚገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እንዲሁም የስታዲየም ግንባታዎች ጋር ተያይዞ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ክልሉ ከስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ግንባታ ጋር በተያያዘ ምን እየሠራ ነው?

ወ/ሪት ሳምያ፡- ከዚህ ቀደም በአገር አቀፍ ደረጃ ስታዲየሞች ቢገነቡም፣ ግንባታቸው በፈሰሰባቸው መጠን አልነበረም ሲገነቡ የነበሩት፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ብሔራዊ ቡድናችን ጨዋታ የሚያስተናግድበት ስታዲየም ያጣው፡፡ ችግሩ እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን እንደ አገር የገጠመ ነው፡፡ እኛ በክልላችን ያደረግነው ግን ያሉትን ስታዲየሞች ለየን፡፡ አንዳንዱ በደፈናው የተገነቡ እንጂ የባለቤትነት ወረቀት የሌላቸውና ዝግ ስታዲየሞች ነበሩ፡፡ ዝግ የነበሩትን ለውድድር ክፍት ማድረግና ባለቤት የሌላቸውን ባለቤት እንዲኖራቸው አድርገናል፡፡ ጥራታቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ባይኖሩንም የተለያዩ ውድድሮችን እንዲያከናውኑ አድርገናል፡፡ ስለዚህ እንደ አገር ያለውን ችግር ተገንዝበን፣ የሚታደሱትን አድሰን እንዲሁም አዲስ የሚገነቡትን በትኩረት ተከታትለን ውድድሮችን እናከናውናልን፡፡

ሪፖርተር፡- ከአምቦ ጎል ፕሮጄክትና ከሱሉልታ ደራርቱ ስፖርት አካዴሚ ግንባታ ጥራት እንዲሁም የአፈጻጸም ችግሮች ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ምን ምላሽ አላችሁ?

ወ/ሪት ሳምያ፡- የሱሉልታው 98 በመቶ ቢጠናቀቅም ግንባታው ግን በጣም ዘግይቷል፡፡ የዘገየው በኦሮሚያ ስፖርት ቢሮ ችግር አይደለም፡፡ የዘገየበት ምክንያት ግንባታው በተጀመረበት ወቅት በነበረው የፖሊቲካ አለመረጋጋት መኖሩን ተከትሎ፣ ግንባታውን በአባትነት ይዞት የነበረው ተቋራጭ አገር ጥሎ በመሄዱ ነው፡፡ ሥራውን ዳግም የጀመረው ባለፉት ሦስትና አራት ዓመት ውስጥ ነው፡፡ አሁን በጥራት እየተሠራ ነው፡፡ ቁሳቁሶች ከውጭ እየተገዙ ነው፡፡ ቀድሞ የግንባታው የተጀመረው መደበኛ ውድድር ብቻ እንዲያስተናግድ ታቅዶ ነበር፡፡ በሒደት ግን አካዴሚው መደበኛ ውድድር ከማሰናዳት በዘለለ ግንባታው እየሰፋና ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ እየተገነባ ነው፡፡ ለግንባታው የተለያዩ ቁሳቁሶች ግዥ ሲፈጸምና አገሪቱ የገጠማት የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት አዘግይቶታል፡፡ ቀድሞ የተሠራው የመሮጫ መም እንደ አዲስ እየተሠራ ነው፡፡ ያሉትን እንቅፋቶች ከተሻገርን 2015 ዓ.ም. ላይ ተጠናቆ ክፍት ይሆናል የሚል ግምት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- የዘንድሮ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ በውዝግብ የታጀበ ሆኖ ማለፉ ይታወሳል፡፡ ምርጫውን ያሸነፈውም የእናንተ ክልል ዕጩ ነው፡፡ ምርጫው እንዴት ነበር?

ወ/ሪት ሳምያ፡- ከባድ የምርጫ ጊዜ ነበር ያሳለፍነው፡፡ ምክንያቱም የእኛ ክልል ለፕሬዚዳንትነት ያቀረበው ሰው ስለነበር፡፡ ምርጫው ተከናውኖ ውጤቱ እስኪታወቅ ከፍተኛ ውጥረት ነበር፡፡ ምክንያቱም በምርጫው ዋዜማው የምርጫው ውጤት በገንዘብ ለማስቀየር ሲደረግ የነበረ ሩጫ ነበር፡፡ ውጤቱን ለማስቀየር ሲሯሯጡ የነበሩት ግለሰቦች ነበሩ፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ድርጊቱ እንዳይከሰት ከሆቴል ሆቴል ለመከላከል ስንንቀሳቀስ ነበር ያመሸነው፡፡ እኛ አቶ ኢሳያስ ጅራን እንደ ዕጩ ስናቀርባቸው በሥራቸው ነው የመዘናቸው፡፡ ሆኖም ጠቅላላ ጉባዔ ድምፁን በሀቅነት ላመነበት ሰጥቶ ምርጫው መጠናቀቅ ችሏል፡፡ ለዚህም የጠቅላላ ጉባዔው ተሳታፊዎች ምሥጋና ይገባቸዋል ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ምክያቱም ድምፃቸውን በብር ሳይለውጡ ያመኑበትን ስላደረጉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...