Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ጥድፊያ በበዛበት በዚህ ዘመን ብዙ ነገሮች እየተበላሹ ነው፡፡ ይህንን ገጠመኝ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ጓደኛዬ ባለፈው ሳምንት የደረሰበት ነገር ነው፡፡ ጓደኛዬ ወደ ሥራ ለመሄድ ይጣደፍ ስለነበር መያዝ የነበረበትን ትቶ ሌላ ነገር ኪሱ ከቶ ይወጣል፡፡ ሥራው ቦታ ደርሶ ከጃኬቱ የውስጥ ኪስ የእጅ ስልኩን ለማውጣት እጁን ይሰዳል፡፡ እጁም የሚፈለገው ቦታ ደርሶ ተፈላጊውን ዕቃ ሲያወጣ ጓደኛዬ ባየው ነገር ይደናገጣል፡፡ ሞባይል ስልክ እንዲያወጣ የተላከው እጅ የቴሌቪዥን ሪሞት ኮንትሮል ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ ጓደኛዬ ለዚህ የዳረገው ጥድፊያ እንደሆነ ተረድቷል፡፡ አንድ ነገር ለማከናወን ወይም ወደ ሆነ ቦታ ለመሄድ ስንጣደፍ፣ ለጓደኛዬ ዓይነት ዝንጋታ ብቻ ሳይሆን፣ ለአደገኛ ነገርም ልንጋለጥ እንችላለን፡፡

በ1997 ዓ.ም. በወርኃ የካቲት 1 እሑድ ቀን ማለዳ ቤቴ ውስጥ መጽሐፍ እያነበብኩ ሳለሁ የሞባይል ስልኬ ይጮሃል፡፡ ቁጥሩን የማውቀው አይደለም፡፡ ስልኩን አንስቼ መነጋገር ስጀምር ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ የሚል ሰው፣ ‹‹ዘመድህ. . . አደጋ ደርሶበት ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ስላለ ቶሎ ድረስ. . .›› ብሎ ስልኩን ዘጋው፡፡ እኔም በድንጋጤ ውስጥ ሆኜ ከሩጫ በማይተናነስ ፍጥነት አቅሌን ስቼ ስጣደፍ፣ ከየት መጣ ያላልኩት ሞተረኛ ከመንገዱ አፈናጥሮ ጣለኝ፡፡ የዘመዴን ሕይወት ለመታደግ ስካለብ እኔው ራሴ ድንገተኛ ክፍል ከዘመዴ ጎን ስትሬቸር አልጋ ላይ ተገኛሁ፡፡ ዘመዴ የዚያን ቀን ማለዳ በመኪና ተከልሎ ሲጣደፍ ነበር በሚኒባስ ታክሲ የተገጨው፡፡ እኔም የእሱን አደጋ ሰምቼ ስጣደፍ ነበር ሞተረኛው የገጨኝ፡፡ ሁለታችንም በሕይወት ብንተርፍም አሁንም ድረስ ጠባሳው አብሮን አለ፡፡

ከምርጫ 97 በኋላ በነበረው የመጀመርያ ብጥብጥ ጊዜ የዘመድ ለቅሶ ለመድረስ ፈረንሣይ ሌጋሲዮን እሄዳለሁ፡፡ በደረሰብኝ የሞተር አደጋ ምክንያት አነክስ ስለነበር ከዘራ እጠቀም ነበር፡፡ ከቤላ ወደ ፈረንሣይ ሌጋሲዮን የሚያሸጋግረው መንታ መንገድ ስደርስ የአንበሳ አውቶብስ 13 ቁጥር በድንጋይ መስታወቶቹ ረግፎ ቆሟል፡፡ ምን ተፈጠረ ብዬ የአውቶብሱን ዙሪያ እየተዟዟርኩ ስመለከት፣ ጠመንጃ ያነገተ የአካባቢው ጥበቃ ከኋላ በሰደፍ ሲመታኝ ወደቅኩ፡፡ በዚያ ቅጽበት በአውቶብሱ ላይ አደጋ መድረሱን የሰሙ ፌዴራል ፖሊሶች ይደርሳሉ፡፡ እኔም ከዘራዬን ተመርኩዤ እየተንገታገትኩ ከወደቅኩበት ስነሳ አንደኛው ፖሊስ፣ ‹‹ምን ሆነህ ነው?›› ይለኛል፡፡ እኔም የደረሰብኝን እነግረዋለሁ፡፡ ፖሊሱ የመታኝን መሣሪያ የያዘ ጥበቃ፣ ‹‹አካሉ ተጎድቶ በከዘራ የሚሄድ ሰው ይመታል እንዴ?›› ብሎ ሲጠይቀው ጥበቃው በተደናበረ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ፣ ‹‹እየተጣደፍኩ ስለደረስኩ ከዘራ መያዙን እንኳ አላየሁም. . .›› ብሎ ሲመልስ፣ እንኳንም በሰደፍ መታኝ እንጂ ጥይት ተኩሶ ቢሆን ኖሮ አልቆልኝ ነበር ብዬ ከአካባቢው ሹልክ አልኩ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የምናየው ጥድፊያ ያስፈራኛል፡፡ ልብ ብላችሁ ከሆነ የዘመናችን ሰው ሲናገር በጥድፊያ ነው፡፡ ከቁም ነገር ይልቅ ቀልድ በዝቷል፡፡ ምግብ እንኳን ሲበላ እያጣጣሙና በሚገባ እያላመጡ ሳይሆን፣ ዝም ብሎ እየጎረሱ መዋጥ ነው፡፡ ጓደኝነት በጥድፊያ ይመሠረታል፡፡ ጠቡም ፈጣን ነው፡፡ ገንዘብ ለማግኘት የሚደረገው ሩጫ ልጓም ስለሌለው ሁሉም ይከንፋል፡፡ ግጭቱም የዚያኑ ያህል ነው፡፡ መንገዱ ላይ ልምድ ያለውም የሌለውም፣ መንጃ ፈቃድ የያዘውም ያልያዘውም፣ እንዲሁም ሐሰተኛ የመንጃ ፈቃድ የያዘውም ጭምር በፍጥነት ይሮጡበታል፡፡ ከሞተር ብስክሌትና ከአነስተኛዋ ቪትዝ እስከ ትልልቆቹ ላንድክሩዙሮች፣ አርጅተው ከተንቋቁት እስከ ዘመናዊዎቹ መኪኖች ድረስ ሁሉም ፍሬን የሌላቸው ይመስል ይከንፉበታል፡፡ ካፌ በር ላይ አቁሞ ወሬ ከሚሰልቀው አጣዳፊ ጉዳይ እስካለው ድረስ መሮጥ ነው፡፡ ከወሰን በላይ ፍጥነት ግን አደጋው ከሚታገሱት በላይ እየሆነ ነው፡፡ በተለይ በተሽከርካሪዎች መሀልና ግራና ቀኝ እንደ አበደ ሰው ዘው የሚሉት ሞተረኞች ጉዳይ ችላ የተባለ ይመስላል፡፡ ምንም ዓይነት ኃላፊነት የማይሰማቸው ሞተረኞች መበራከት ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው፡፡ በተለይ የትራፊክ ፖሊሶች ለዚህ ችግር ልዩ ትኩረት ካልሰጡ የሰው ሕይወት በከንቱ መቀጠፉ ይቀጥላል፡፡ የእነሱ ጥድፊያ የሚያስከትለው መዘዝ በቀላሉ መታየት የለበትም፡፡

የዛሬ አራት ወር ገደማ ከመገናኛ ወደ አራት ኪሎ የሚወስደው መንገድ ቀበና አደባባይ ላይ ሁለት ተሽከርካሪዎች ተጋጭተው አካባቢው ተጨናንቋል፡፡ በአካባቢው የትራፊክ ፖሊሶች ስላልነበሩ ሁለቱን አቅጣጫዎች የሚያገናኘው መንገድ ተዘጋግቷል፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ አንድ የትራፊክ ፖሊስ ደረሰ፡፡ አስፈላጊውን ነገር ካደረገ በኋላ፣ ምልክት አድርጎ የተጋጩት ተሽከርካሪዎች ጥግ እንዲይዙ ያዛል፡፡ ገጪና ተገጪ በፕላኑ መሠረት የሚለዩ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አንደኛው በሌላኛው ላይ ወቀሳ ይሰነዝራል፡፡ አደባባዩን በመዞር ላይ የነበረው ተሽከርካሪ ቅድሚያ አለው በሚባለው ሕግ መሠረት ነው ተገጪው የሚቆጣው፡፡ የትራፊክ ፖሊሱ የተዘጋውን መንገድ እያስከፈተ ስለነበር አንድ መንገደኛ ገጪ ነው የተባለውን፣ ‹‹ሕጉን ሳታውቅ ነው እንዴ ዝም ብለህ የገባኸው?›› ሲለው፣ ‹‹ቸኩዬ ስለነበር ተዘናግቼ ነው. . .፤›› በማለት ሲመልስለት፣ ‹‹ኧረ ሰውየውን ብትገድለው ኖሮ እንዲህ ብለህ ነበር የምትመልሰው?›› አለው፡፡ አዎን ሰውየው አደጋ ቢደርስበት ወይም ቢሞት ኖሮ በጣም አሳዛኝ ነበር፡፡

በቅርቡ ከምሸቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ከምኖርበት ሠፈር በቅርብ ርቀት ጩኸት ይሰማል፡፡ ጩኸቱ በሚሰማበት አካባቢ ደግሞ የእሳት ፍንጣሪ ይታያል፡፡ ተሯሩጠን ስንደርስ ቤት እየተቃጠለ ነው፡፡ በሰዎች ርብርብ እሳቱ ቢጠፋም በቤቱ ነዋሪዎች ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ምንድነው ሲባል የቤት ሠራተኛ ማደሪያዋ ውስጥ የለኮሰችውን ሻማ ሳታጠፋ በመሄዷ ምክንያት ነው ይባላል፡፡ በሻማና በጧፍ ምክንያት በተለያዩ ሥፍራዎች በርካታ ቃጠሎዎች ደርሰዋል፡፡ ከንብረት ውድመት በላይ ሕይወትም ጠፍቷል፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ሲጠየቁ ግን ‹‹ቸኩዬ ነበር›› የሚል ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ከቀልብ አለመሆን ለአደጋ ያጋልጣል፡፡ ከቤት ጀምሮ እስከ አገር ድረስ ከቀልባችን ካልሆንን የከፋ አደጋ ይገጥመናል፡፡ ሁሌም ጠንቃቃ መሆን ይበጀናል፡፡ ‹‹የቸኮለች አፍስሳ ለቀመች›› ከሚባለው ተረት በላይ አርቀን እናስብ፡፡

(ቴዎድሮስ ካሳ፣ ከቀበና)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...