አማራጭ አሠራሮች ላይ ተወያይቶ ለአገሪቱ መሪዎች ምክረ ሐሳብ አቅርቧል
የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን የተሽከረካሪ ባለንብረቶች ተሽከርካሪዎቻቸውን በዓይነትና የካፒታል መዋጮ ለንግድ ማኅበር እንዲያስረክቡ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሊገደዱ አይገባም ሲል ባለፈው ዓመት መጨረሻ ወር ላይ የፀደቀውን የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ ተቃወመ፡፡
በሐምሌ 2014 ዓ.ም. በፓርላማ ፀድቆ ወደ ሥራ የገባው የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ፣ ባለንብረቶች ተሽከርካሪያቸውን አሁን ካሉበት የትራንስፖርት ማኅበር፣ በአክሲዮን መዋጮነት ለንግድ ማኅበር እንዲያስረክቡ መደንገጉ፣ ባለንብረቶች በየበጀት ዓመቱ መጨረሻ የትርፍ ክፍፍል (ዲቪደንድ) ጠባቂ በመሆን በኑሯቸው ላይ ከፍተኛ ችግር ያስከትልባቸዋል ሲል ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
ተሻሽሎ በቀረበው የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ መሠረት በቀድሞው የትራንስፖርት ባለሥልጣን ተመዝግበው፣ ማንኛውም ዓይነት የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የትራንስፖርት ማኅበራት ፈርሰው፣ አዋጁ ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ንግድ አደረጃጀት ተቀይረው በሽርክና ወይም በግል የንግድ ድርጅት በድጋሚ እንዲመዘገቡ አስገዳጅ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡
የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን በውስጡ 66 የትራንስፖርት ማኅበራትና ከአሥር ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎችን ያቀፈ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ ባለንብረቶች መካከል 87 በመቶ የሚሆኑት በሠሩባቸው ቀናት በሚሰበስቡት ገቢ ብቻ የሚኖሩ መሆናቸውንና 70 በመቶ የሚሆኑት ተሽከርካሪዎች ደግሞ የባንክ ዕዳ እንዳለባቸው፣ የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሐፊ አቶ ደረጀ ለገሰ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በማኅበሩ ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ባለአንድ ተሽከርካሪ ባለቤት መሆናቸውን፣ ኑሯቸውን የሚመሩት በሚያገኙት አነስተኛ ገቢ በመሆኑ፣ ተሽከርካሪያችሁን አስረክባችሁ ዓመታዊ ትርፍ ጠብቁ ማለት የማያዋጣ አሠራር ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም በንግድ ሕጉ መሠረት ባለንብረቶች ተሽከርካሪያቸውን ወደ አክሲዮን ማኅበር አስገብተው የዓመት ትርፍ ብቻ እየጠበቁ ከሚኖሩ፣ ንብረቶቻቸውን ለሚያቋቋመው አክሲዮን ማኅበር አንድም በማከራየት፣ ተባባሪ በመሆን ወይም በሊዝ በመስጠት የአክሲዮን ባለቤት ሆነው እንዲሠሩ የሚል የግብዓት ሰነድ በፌዴሬሽኑ በኩል ተዘጋጅቶና ውይይት ተደርጎበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር፣ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ለንግድ ማኅበራት፣ ለአሠሪዎች ፌዴሬሽንና ለሌሎች የመንግሥት ተቋማት ማቅረቡን አቶ ደረጀ አክለው ገልጸዋል፡፡
በ2013 ዓ.ም. ተሻሽሎ በወጣው የንግድ ሕግ አዋጅ መሠረት የማኅበራት የንግድ ተቋም አደረጃጀቶች የኅብረት ሽርክና ማኅበር፣ ሁለት ዓይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማኅበር፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማኅበር፣ የእሽሙር ማኅበር፣ የአክሲዮን ማኅበር፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚሉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ፌዴሬሽኑ ባዘጋጀው ምክረ ሐሰብ ለማኅበራቱ የኅብረት ሽርክና ማኅበር፣ የአክሲዮን ማኅበር፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚሉት ለትራንስፖርት የንግድ ማኅበራት ተመራጭ አደረጃጀቶች መሆናቸውን ማስታወቁን ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል አሁን በሥራ ላይ ካሉት የትራንስፖርት ማኅበራት፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ ለትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪነት የሚቀመጡትን የተሽከርካሪዎች ብዛትና መሰል መሥፈርቶችን ሊያሟሉ የሚችሉት ጥቂቶች ብቻ መሆናቸውን አቶ ደረጀ አክለው ተናረዋል፡፡ በዚህም አዲስ በሚቋቋመው የንግድ ተቋም የሚመዘገቡ አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን መግዛት፣ ወይም የተሽከርካሪ ባለንብረትነትን ወደ አክሲዮን ኩባንያው የሚያዘዋውሩ ባለንብረቶችን ማግኘት ከባድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአዋጁ መሠረት በቀድሞው የትራንስፖርት ባለሥልጣን ተመዝግበው እየሠሩ የሚገኙት ማኅበራት ያፈሩትን ንብረት በሕግ አግባብ የሚለወጡበት የንግድ ማኅበር ማስተላለፍ አለባቸው፡፡
በአሁኑ ጊዜ የአገር ውስጥና የድንበር ዘለል የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የጭነት ተሽከርካሪዎች አብዛኞቹ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ የሆኑና የመጫን አቅማቸውም አነስተኛ መሆኑን የሚናገሩት ዋና ጸሐፊው፣ ይህ ሁኔታ በአገር ደረጃ ለሚጠበቀው አገራዊ የትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ዕድገት፣ ለአጎራባችና ለቀጣናው የትራንስፖርት አገልግሎት ብቁና ተወዳዳሪ ባለመሆናቸው፣ ለባለንብረቶች ከአገር ውስጥ፣ ወይም ከውጭ የፋይናንስ ተቋማት፣ ወይም ከተሽከርካሪ አምራቾችና አቅራቢዎች የሰፕላይ ክሬዲት (Supply Credit) አማራጭ በመጠቀም ይህን ስትራቴጂ ማሳካት እንደሚቻል አክለው ገልጸዋል፡፡
የትራንስፖርት ማኅበራቱ በመጪዎቹ ዘጠኝ ወራት ወደ አክሲዮን እንዲሸጋገሩ ቀነ ገድብ የተቀመጠላቸው ቢሆንም፣ ፌዴሬሽኑም ሆነ ማኅበራቱ ወደ አዲሱ አሠራር ለመግባት ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌላቸውና ሥራ ማቆምን ጨምሮ በርካታ አማራጮችን እንደቀረቡ አቶ ደረጀ አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም የአገሪቱ የጀርባ አጥንት የሆኑት ተሽከርካሪዎች ላይ የሚወስነው አዋጅ ላይ በነበረው ውይይት የቀረበው የማኅበራቱ ሐሳብ በምንም ሁኔታ አልተካተተም የሚሉት ዋና ጸሐፊው፣ በርካታ ዜጎችን ከሥራ የማፈናቀልና ተዛማጅ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች እንዳይደርስባቸው የታሰበውን የአደረጃጀት ለውጥ ሁሉንም በማይጎዳ መንገድ እንዲከናወን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከተባበሩት ድንበር ተሻጋሪዎች ባለንብረቶች ማኅበር ስለጉዳዩ የተናገሩ ግለሰብ፣ ‹‹ሁላችንም ግራ ገብቶናል፣ አዋጁ ቢፀድቅም ለመፈጸም የማይታሰብ ሆኖብናል፤›› ብለዋል፡፡
አክለውም አንድ ባለንብረት የሚያስተዳድረውን አንድ መኪና ወደ ንግድ ማኅበር አስገባና ዓመታዊ ትርፍ ጠብቅ ሲባል፣ ለሁሉም ባለንብረቶች የማይሆን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹አንድ መኪና ይዤ የማስተዳድረውን ንብረት ወደ ንግድ ማኅበር ለማስገባት፣ ልጆቼንና ሚስቴን ለማኖር አንድ ዓመት ትርፍ ጠብቄ እንዴት ልኖር እችላለሁ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡