Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የቮልቮ ማሽነሪ መለዋወጫና ጥገና ማዕከል ሥራ ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • 200 የሕዝብ ማመላለሻ የቮልቮ አውቶቡሶች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ማስገባት አልተቻለም

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዱከም ከተማ በ3,000 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ፣ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የቮልቮ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ መለዋወጫ ማቅረቢያና ጥገና ማዕከል መስከረም 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ተመረቀ። ወረታ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ግሩፕ የቮልቮ ከባድ ተሽከርካሪዎችና የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች በኢትዮጵያ በብቸኝነት ለገበያ የሚያቀርብ ኩባንያ ሲሆን፣ በቀጣይ ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ ለመገጣጠም ዕቅድ መያዙን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዓለማየሁ ከበደ (ዶ/ር) ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በዓመት 100 የቮልቮ ከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎችን ለገበያ ለማቅረብ ዕቅድ እንዳለው ያስረዱት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው፣ የውጭ  ምንዛሪ ፈተና እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 200 የቮልቮ አውቶቡሶችን እንዲያቀርብ ቢያዘውም፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ማቅረብ እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

በዱከም ከተማ የተገነባውን የመለዋወጫና ጥገና ማዕከል ግንባታ ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመታት እንደፈጀ፣ በኢትዮጵያ የቮልቮ ተሽከርካሪዎችንና ማሽነሪዎችን ለገበያ ለማቅረብ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል መጠየቁን ዓለማየሁ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።

የስዊድን ሥሪት የሆኑት የቮልቮ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች፣ በጥራታቸው የሚታወቁ መሆናቸውን ገልጸው፣ በነዳጅ ቆጣቢነታቸው፣ ለደኅንነት ሲባል በተገጠሙላቸው ዘመናዊ መሣሪያዎች፣ በአገልግሎት ዘመናቸውና አነስተኛ ወጪ በመጠየቃቸው፣ እንዲሁም ከአየር ብክለት ነፃ በመሆናቸው፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችና መሣሪያዎች ያላቸው መሆናቸውን አስረድተዋል።

የአገልግሎት መስጫዎቹ በውስጣቸው መያዝ ያለባቸውን ለጥገናው የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች፣ ላፕቶፖች የዲያግኖስቲክ ሶፍትዌር በሙሉ የተሟሉላቸው እንደሆኑ፣ ማዕከሉን ለመገንባትና በውስጡ ያሉትን መገልገያዎች ለማሟላት ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መውጣቱ ተገልጿል።

ወረታ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ግሩፕ ከ20 ዓመታት በፊት በቤተሰብ የተቋቋመና በተለያዩ ሥራዎች ላይ የተሰማራ መሆኑ ታውቋል፡፡

ድርጅቱ አሁን በተለይ በአስመጪና ላኪነት ሥራ ላይ የተሰማራ ሲሆን፣ በእርሻ ልማት ተሰማርቶ የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ በመላክ፣ የተለያዩ ፋብሪካዎቹን በመትከል፣ የግራናይት፣ የዕምነ በረድና የቀለም ምርቶችን ፋብሪካ አጠናቆ ሥራ እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡

ከዚህም ባሻገር የታወቁ መሣሪያ አምራቾች ሕጋዊ ወኪል ሆኖ የኬዝ እርሻ መሣሪያዎች፣ የቮልቮ ትራክ፣ የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች፣ የአስኮት ጄኔሬተሮችና የቴኪንግ ጎማዎች በማቅረብ የኢትዮጵያ ብቸኛ ወኪል ነው ተብሏል፡፡ በግብርናው ዘርፍ ሩዝ፣ አኩሪ አተር፣ ቡና በሦስት የእርሻ አካባቢዎች ማለትም በአሶሳ፣ በአማራ ክልል ጃዊ አካባቢ፣ እንዲሁም በጋምቤላ ክልል ሜቲ አካባቢ እያለማ እንደሚገኝ ዓለማየሁ (ዶ/ር) አስረድተዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች