ለሦስት ዙሮች የተደረገው የባለልዩ ጣዕም ቡና ውድድር (ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ) የኢትዮጵያ ቡናን የሚገዙ ዓለም አቀፍ ተጫራቾችን ፉክክር እንዳጎላው ተገለጸ፡፡
ከ2012 ዓ.ም. አንስቶ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በተካሄደው የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር፣ የአገሪቱን የቡና ገበያ አድማስ ከማስፋት ባሻገር፣ ዓለም አቀፍ ተጫራቾች በሚያደርጉት ፉክክር ቡና በኪሎ ግራም የሚሸጥበት ዋጋ አርሶ አደሩንና አገሪቱን መጥቀሙን፣ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር፣ የኢትዮጵያ የቡና ቀንን መስከረም 4 እና 5 ቀን በሸራተን ሆቴል ሲያከብር፣ በሦስተኛው ዙር የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር አሸናፊ ለሆኑ አርሶ አደሮች ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡
በዕለቱ ንግግር ያደረጉት አዱኛ (ዶ/ር)፣ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ውድድር የአገሪቱን ገጽታ ከመገንባቱ ባሻገር መላው ዓለም የኢትዮጵያ ቡናን ለመግዛት ጉጉት ያሳደረበት አጋጣሚ ፈጥሯል ብለዋል፡፡ ይህ መሆኑ አገሪቱ ትከተል የነበረውን አሠራር መቀየሯ ቡና በጥራት እንዲመረት፣ እንዲሁም ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልጋት ያመላከተ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡
በዘንድሮው የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር በጥራቱ በአንደኝነት ከፍተኛ ነጥብ ያመጣው ቡና አንዱ ኪሎ ግራም 884.10 ዶላር (47,236.23 ብር) የተሸጠ ሲሆን፣ በውድድሩ አሸናፊ የሆነው አርሶ አደር በጠቅላላው ለውድድሩ ባቀረበው ቡና 22.6 ሚሊዮን ብር አግኝቶበታል፡፡
ከሲዳማ ክልል አርቤ ጎና ወረዳ ቡርሳ ቀበሌ የመጣውና የውድድሩ አሸናፊ የሆነው አቶ ለገሰ ቦቶሳ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ከዚህ ቀደም ቡናን አምርቶ በአካባቢው ለሚገኙ አቅራቢዎች ሲሸጥ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ከመጣ ወዲህ ሌሎች አርሶ አደሮች መሸለማቸውን ተመልክቶ ምርቱን ለውድድሩ ማቅረቡን ገልጿል፡፡
በውድድሩ አሸናፊ መሆኑ ልዩ ስሜት እንደፈጠረበት የተናገረው አቶ ለገሰ፣ ዓምና ከሠራበት በበለጠ አቅም የተሻለ ቡና በማቅረብ የአገሪቱን ስም ማስጠራት ፍላጎቱ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ለአሸናፊነት ያቀረበው ቡና የተለየ ይዘት ኖሮት ሳይሆን ለምርቱ ያደረገው ልዩ እንክብካቤና በተለይም የችግኝ መረጣና የቡና ለቀማው፣ አደራረቁና በመፍጨት ሒደት ውስጥ የተከተላቸው ዘዴዎች ጥንቃቄ የታከለባቸው መሆናቸውን አቶ ለገሰ ገልጿል፡፡
በሸራተን ሆቴል በተደረገው መድረክ ኢትዮጵያ ቡና ለዓለም ገበያ ማቅረብ ከጀመረች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ 300 ሺሕ ቶን ቡና በመላክ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘቷ፣ ለውጤቱ መገኘት ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው ከ200 በላይ ላኪዎችና የዘርፉ ተዋናዮች ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለውጤቱ መገኘት የጎላ ሚና የተጫወቱትን አርሶ አደሮች አድንቀው፣ በተለይም የግሉ ዘርፍ ሚና እንዲስፋፋ በር የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡ ለብዙ ዘመናት የግሉ ዘርፍ እንዳያድግ ተደርጎ የቆየ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ያለ ግሉ ዘርፍ የአገር ዕድገት የለም በማለት ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከቡና ኤክስፖርት የተገኘው ውጤት ታሪካዊ ነው ቢባልም፣ ኢትዮጵያ የዓረቢካ ቡና መገኛ እንደ መሆኗ እንደ ሌሎች ተወዳዳሪ ቡና አምራቾች ቡናን በብዛት በማምረትና ወደ ውጭ በመላክ የሕዝቡንና የአገሪቱን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሊታሰብ የሚገባ መሆኑን ርዕሰ ብሔሯ ገልጸዋል፡፡ ይህ ዕውን እንዲሆንና በቀጣይ ዓመት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ፣ እንዲሁም በብዛት ወደ ውጭ በመላክ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ሁሉም ባለድርሻ አካላት አቅማቸውንና ጉልበታቸውን መስዋዕት በማድረግ መረባረብ ይገባቸዋል ተብሏል፡፡