የታክስ ማሻሻያ በማድረግ የኤሌክትሪክ መኪና የሚያስመጡና በአገር ውስጥ በመገጣጠም የሚያመርቱ ድርጅቶችን ከተለያዩ የታክስ ዓይነቶች ነፃ እንዲሆኑ የሚያደርግ ትዕዘዝ ማስተላለፉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እስከዚህ ውሳኔ ድረስ በታክስ በኩል ይስተናገዱ የነበሩት እንደ መደበኛ ተሽከርካሪዎች ነበር፡፡
በዘርፉ ላይ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን ለማበረታታት በማቀድ ይህን ውሳኔ ማሳለፉን ባለፈው ዓርብ መስከረም 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ያሳወቀው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የቤት አውቶሞቢሎችና የዕቃ መጫኛ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ ወደ አገር ውስጥ ሲያስገቡና በአገር ውስጥ ሲገጣጥሙ ከሚከፍሏቸው የተለያዩ እንደ እሴት ታክስ፣ ኤክሳይዝ ታክስና ተጨማሪ (ሱር ታክስ) ነፃ የሚያደርግ ውሳኔ ነው፡፡
የቤት አውቶሞቢሎች ሙሉ በሙሉ የተበተኑና ወደ አገር ውስጥ በመግባት የሚገጣጠሙ ከሆነ ከጉምሩክ ቀረጥ፣ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ቴክስና ሱር ታክስ ነፃ ይሆናሉ፡፡ በከፊል የተበተኑና አገር ውስጥ የሚገጣጠሙ ከሆነ አምስት በመቶ ብቻ የጉምሩክ ቀረጥ ይጣልባቸዋል፡፡ ሙሉ በሙሉ የተገጣጠሙና ያለቀላቸው የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች ደግሞ ወደ አገር ቤት ሲገቡ 15 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ተጥሎባቸው ከሌሎች የታክስ ዓይነቶች ነፃ ይሆናሉ፡፡
ለኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት የውሳኔ ደብዳቤ በመላክ ገንዘብ ሚኒስቴር ያሳወቀ ሲሆን፣ በመግለጫው ለዚህ ውሳኔ ዋነኛ ዓላማ ያደረገው በአገሪቱ እያደገ ለመጣው የመኪኖች ቁጥርና በአየር ንብረትና በብዝኃ ሕይወት ላይ ተፅዕኖ የማያሳርፍ የኃይል ምንጭ በአግባቡ ለመጠቀም ነው፡፡
የኤሌክትሪክ መኪኖች የአገሪቱን የነዳጅ ፍጆታ በማስቀረት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በማስታወቅ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ለኤሌክትሪክ መኪና ያላቸውን ድጋፍ ይገልጹ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የዓለም አቀፉ ነዳጅ ዋጋ በመናር ምክንያት የአገሪቱ የነዳጅ ወጪ እያደገ የመጣ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት እስከ ሦስተኛው ሩብ ዓመት ድረስ 2.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን መጠን ያለው ነዳጅ ወደ አገሪቷ የገባ ሲሆን፣ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲወዳደር በአንድ መቶ ሺሕ ሜትሪክ ቶን ብቻ ነበር የበለጠው፡፡ ነገር ግን በወጪ በኩል ከእጥፍ በላይ በማደግ ለ2.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የወጣው ገንዘብ 105 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ከባለፈው ዓመት በፊት ሦስተኛው ሩብ ዓመት ድረስ የወጣው ወጪ ግን 48.3 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡
የትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ዘርፉን ለማሻሻልና እንዲስተካከሉ ከጠየቃቸው ጥያቄዎች ይህ አንደኛው እንደሆነ ለሪፖርተር የገለጹት የሚኒስትሩ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታጠቅ ነጋሽ በበኩላቸው፣ በመሥሪያ ቤታቸው የአሥር ዓመት ዕቅድ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ማስፋፋት አንደኛውና ዋነኛው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የዕቅዳቸውን ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርፀው ወደ ትግባር እየሄዱ እንደሆነ በመናገር፣ በአሥር ዓመት ውስጥ ወደ 4,800 የሚጠጉ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የኤሌክትሪክ መኪኖች ወደ አገር ለማስገባትና 148,000 የሚጠጉ የቤት አውቶሞቢሎችንም እንዲመጡ ለማድረግ እንዳቀደ አቶ ታጠቅ ተናግረዋል፡፡
‹‹ባለሀብቶችና አስመጪዎችን በዚህ ዘርፍ ተሰማርተው በርካታ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያስመጡ የመጋበዝ ሥራ እየሠራን እንገኛለን፤›› ሲሉ አክለው ተናግረዋል፡፡
የተወሰኑ የግል ድርጅቶች እንደ ማራቶን ሞተርስና ግሪንቴክ አፍሪካ የመሰሉ ድርጅቶች በዘርፉ ላይ ተሰማርተው የነበረ ሲሆን፣ ድርጅቶቹም ዘርፉ ከቀረጥ ነፃ እንዲሆን ይጠይቁ እንደነበርም አቶ ታጠቅ አስታውሰዋል፡፡