Wednesday, September 27, 2023

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ከተማ አስተዳደሩ ሲወዛገቡበት የነበረው ይዞታ መፍትሔ አገኘ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር የተወዛገቡበት፣ በልደታ ክፍለ ከተማ ከጎማ ቁጠባ ወደ ተክለሃይማኖት በሚወስደው መንገድ በስተግራ በኩል የሚገኘው ይዞታ ሁለቱም ተቋማት የሚጠቀሙበት ሁኔታ በባለሙያዎች መፈጠሩና መፍትሔ ማግኘቱ ተገለጸ፡፡

የሁለቱ ተቋማት ውዝግብ መጀመሪያ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ፣ የባለሙያ አስተያየት እንዲቀርብበት በመደረጉና በአስተያየቱ መሠረት ይዞታውን ሁለቱም ተቋማት እንዲጠቀሙበት ውሳኔ መሰጠቱ ታውቋል፡፡ በመሆኑም ከይዞታው 9.2 ሔክታር የሚሆነው ቦታ ለአዲስ አበባ የመንግሥት ንብረት አስተዳደር ባለሥልጣን እንዲተላለፍ መደረጉን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

የባለሙያዎች የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብ ምክንያት የሆነው፣ ቀደም ብሎ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይዞታውን ተረክቦ ካጠረና ሕንፃ ለማሠራት ዲዛይን ካሠራ በኋላ፣ አስተዳደሩ 36 ሴክታር ተቋማትን በ9.2 ሔክታር ቦታ ላይ ለመገንባት በመፈለጉ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለአጥርና ለዲዛይን ያወጣውን ወጪ ለመክፈልም አስተዳደሩ ተስማምቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ቦታው የተቆራረጠ ስለነበር የዲዛይን ለውጥ እንዲደረግ የባለሙያዎች አስተያየት በማስፈለጉ (Expert Opinion) ከሁለቱም ወገኖች የተውጣጡ ባለሙያዎች ተመድበው ባደረጉት ጥናት፣ ሁለቱም ተቋማት በቦታው ላይ መገንባት የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩን በመግለጻቸው ችግሩ መፈታቱ ታውቋል፡፡

ይዞታው ከፍተኛ ክርክር የነበረበት በመሆኑ ረዥም ጊዜ ከፈጀ በኋላ አድሎዎ በሌለበት አካሄድ ባለሥልጣኑ ለሚያስገነባው ኮምፕሌክስ ሕንፃ 9.2 ሔክታር ቦታ እንዲወስድ መደረጉን አቶ የሱፍ ኢብራሂም የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል፡፡

‹‹የመብት ጉዳይ በሕጋዊ መንገድ መታየት አለበት፡፡ መሬቱን እንፈልገዋለን በማለት የመንጠቅ ሒደት ሳይሆን ለባለይዞታው ተለዋጭ ቦታ በመስጠት በውሳኔው እንዲስማሙ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፤›› ሲሉ አቶ የሱፍ ገልጸዋል፡፡

በይዞታው ላይ የነበረውን ውዝግብ ለመፍታት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣንና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ካደረጉ በኋላ የሁለቱንም ልማቶች በማያስተጓጉል ሁኔታ የመሬት አጠቃቀምን የማሸጋሸግ ሥራ መሠራቱን የአዲስ አበባ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ደቦ ቱንካ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡

ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተገለጸለት የባለሙያዎች አስተያየትና (Expert Opinion)  የውሳኔ ሐሳብ ተፈጻሚነት እንዲያገኝ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት መላኩን ደቦ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በሚረከበው 9.2 ሔክታር መሬት ላይ ከ36 በላይ የመንግሥት ሴክተር መሥሪያ ቤቶችን በአንድ ዲስትሪክት የሚያደርግ ሕንፃ ለመገንባት ዕቅድ መያዙን አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ የባለሥልጣኑ ሕንፃ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በመጋቢት 2014 ዓ.ም. ለመገንባት ዕቅድ ይዞ የነበረው የአንድ ዲስትሪክት ግንባታ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ መቆየቱን ያነሱት አቶ ይድነቃቸው፣ የዘገየበት ዋና ምክንያት ለግንባታው የተሰጠው ቦታ አመቺ ባለመሆኑ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በሜጋ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሚሠራው የሴክተር መሥሪያ ቤቶች ዲስትሪክት መጀመሪያ መገናኛ አካባቢ 6.2 ሔክታር መሬት አግኝተው ነበር፡፡ ነገር ግን የአዋጭነት ጥናት በሚሠራበት ጊዜ መገናኛ አካባቢ ሕንፃው ከተገነባ ቦታው ላይ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ያባብሰዋል በሚል የቦታ ለውጥ መደረጉን አቶ ይድነቃቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹በ2014 ዓ.ም. መገናኛ ሊገነባ ለነበረው ሕንፃ ማስጀመሪያ ብቻ አምስት ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦ የነበረ ሲሆን፣ በቀጣይ በተለዋጭ ቦታ ላይ ለሚሠራው ፕሮጀክት ግምታዊ በጀት ከአሥር አስከ አሥራ አምስት ቢሊዮን ብር ድረስ ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉ አቶ ይድነቃቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዲስትሪክት ተቋማት እንደሚሰጡት አገልግሎት ዓይነት በዘርፍ ተለይተው በአንድ መንደር በማደራጀት አገልግሎት ፈላጊው ሕዝብ በአንድ አካባቢ ሁሉንም ዓይነት አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው ሲሉ አቶ ይድነቃቸው ጠቅሰዋል፡፡

የሜጋ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የግንባታውን የሥራ ተቋራጭ ለመቅጠር የጨረታ ሒደት ላይ የሚገኝና ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ድርጅቶች የሚሳተፉበት ሁኔታ መመቻቸቱን ደቦ (ኢንጂነር) ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ንብረት አስተዳደር ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 64/2014  የመንግሥት ሕንፃና ንብረት አስተዳደር ባለሥልጣን ተብሎ ተጠሪነቱ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ ሆኖ፣ ለሁለት ዓመት ከሠራ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 74/2014 የመንግሥት ንብረት አስተዳደር ባለሥልጣን በሚል ተጠሪነቱ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሆኖ  የተቋቋመ መሥሪያ ቤት ነው፡፡

ተቋማትን በአንድ ዲስትሪክት ማድረግ በየዓመቱ ለኪራይ የሚወጣውን አንድ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ሀብት ማዳን እንደሚቻል አቶ ይድነቃቸው ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ተቋማት እየገነቡ ያሉት ሕንፃዎች አብዛኛዎቹ የሕፃናት ማቆያና ጂም ያላቸው ሲሆን እስካሁን 51 ተቋማት የሕፃናት ማቆያ ያላቸው ተቋማት ወደ ሥራ እየገቡ ይገኛሉ ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -