ባለፉት 20 እና 25 ዓመታት የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ባለፉት 20 እና 25 ዓመታት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የነበረው ቁልፍ ሚና ተሸርሽሮና በበርካታ ችግሮች ተተብትቦ በአሁኑ ወቅት ሽባ የሆነ የኢኮኖሚ ዘርፍ ወደመባል መቃረቡን መንግሥት ይፋ አደረገ።
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጳጉሜን 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ዘርፉን የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ያቀረቡት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ደኤታ ወንድሙ ሲታ (ኢንጂነር)፣ የኮንስትራክሸን ኢንዱስትሪው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ ወደ 19 በመቶ የደረሰ ቢሆንም፣ በርካታ ማነቆዎች ግን አብረውት እየተጓዙ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በጥናት አቅራቢው ማነቆ ተብሎ በመጀመርያ ደረጃ የተጠቀሰው የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከሚመራበት ፖሊሲ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ፖሊሲ በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣው 2006 ዓ.ም. ሲሆን፣ ነገር ግን ፖሊሲው ወደ ትግበራ ከገባ በኋላ ውጤታማነቱ በየጊዜው እየተመረመረ፣ እንደ አገሪቱ ተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታ እየታየ ፖሊሲው ባለመከለሱ ችግር መፈጠሩን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹በአንድ መልኩ ፖሊሲው የተረሳ ሆኗል፣ ሁለተኛ ደግሞ ውጤታማነቱ እየተለካ ማሻሻያዎች ያልተደረገበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚፈለገውን ውጤት አምጥቷል አንልም፤›› ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፣ ይህንን ፖሊሲ ለማስፈጸም የሚያስችል የሕግ ማዕቀፎች መዘርጋት የነበረበት ቢሆንም፣ ያለመዘርጋቱም ትልቅ ችግር እንደነበር አመልክተዋል፡፡ ያሉትም ቢሆኑ እነዚህ የአሠራር ሥርዓቶች እርስ በርስ የማይናበቡ በሆናቸው ችግሩን እንዳባሱት ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
ዘርፉን ለማሳደግ የውጭ ኮንትራክተሮች እንዲገቡ ከተወሰደው ዕርምጃ ጋር ተያይዞና ገጠመ ያሉንትም ተግዳሮች አብራርተዋል፡፡ መንግሥት የውጭ ኮንትራክተሮች ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የዕውቅና የቴክኖሎጂ ሽግግር ይጫወታሉ በሚል እንጂ፣ እነሱ የሚሠሩትን መሠረተ ልማት መርጦ እንዳልነበረ ገልጸዋል፡፡ የውጭ ኮንትራክተሮች መምጣት ጋር ተያይዞ ሌሎች የተፈጠሩ ክፍተቶችንና በአገር ውስጥና በውጭ ኮንትራክተሮች መካከል ያለውን ልዩነት በተመለከተም በሰጡት ማብራሪያ፣ በፋይናንስ ደረጃ የውጭ ኮንትራክተሮች ከኢትዮጵያውያ ኮንትራክተሮች የበለጠ መጠን ያለው ፕሮጀክቶች መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ሒደት ግን 79 በመቶ ፕሮጀክቶች በአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የተያዙ ቢሆንም፣ በፋይናንሻል አንፃር ሲታይ ግን በአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የተያዘው 45 በመቶ ብቻ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ሜጋ ፕሮጀክቶች ደግሞ የተያዙት በውጭ የሥራ ኮንትራክተሮች መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት 20 እና 25 ዓመታት በነበረው ሒደት መጀመርያ ላይ የውጭ አገር ኮንትራተሮች ተሳትፎ እንዳልነበር አስታውሰው፣ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ግን በስፋት የውጭ ኮንትራተሮች ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
እነዚህ የውጭ ኮንትራክተሮች በተሳተፉበት ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ይህ ነው የሚባል ሥራን እየሠሩ ያለመሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ደኤታው፣ በእነዚህ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥና የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሚና፣ በአብዛኛው አፈር ከመቆፈርና በጣም ትንንሽ ቴክኖሎጂ የሚጠይቁ ወይም የማይፈልጉ ሥራዎች ላይ ከመሰማራት ባሻገር፣ በተጨባጭ የኮንትራክተሮችን ባለሙያዎች ችሎታ የሚያሳድግ ሚና እየተወጡ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግሩ የታሰበውን ያህል ውጤት እንዳላመጣ ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ከውጭ ኮንትራክተሮች ጋር በተያያዘ ችግሮች እየታዩ እንደሆነ በምሳሌነት የጠቀሱት ሌላው ነጥብ፣ የውጭ ኮንትራክተሮች የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን መቅጠር ወደማቆም መድረሳቸውን ነው፡፡ ይህንንም ‹‹እስከነጭራሹ አሁን ላይ የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን ያለመያዝ አዝማሚያ እየታየ ነው፤›› በማለት ያለውን ችግር ጠቁመዋል፡፡
‹‹የመጀመሪያው የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት ሲቀረፅ አብዛኞቹ የውጭ ተቋራጭ የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን መቅጠር ግዴታቸው ነበር፤›› ያሉት ጥናት አቅራቢው፣ ትልልቅ ሜጋ መንገዶች በሚከፈቱበት ጊዜ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የሚተፉበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይህ ዕድል በነበረ ጊዜ እነዚህ ባለሙያዎች ከቅጥር ወጥተው የራሳቸውን ሥራ ይሠሩ እንደነበር በመግለጽ፣ አሁን ግን የአገር ውስጥ ባለሙያ ከሥራው እየወጣ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሩ አፈር ከመግፋት የዘለለ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እያደረገ አለመሆኑም ጉዳይ በዘርፉ አሳሳቢ ከሚባሉ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
‹‹የውጭ ኮንትራክተሮች አገር ውስጥ መጥተው ይሥሩ ሲባል፣ አንድ ፍላጎቱን መፈለግ ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ ሒደት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አቅም ይገነባል፣ ቴክኖሎጂው ይሸጋገራል፣ ዕውቀት እንካፈላለን የሚል ቢሆንም፣ ከዚህ አንፃር ውጤት አላመጣም፤›› በማለት ያለውን ችግር ጠቅሰዋል፡፡ ሚኒስትር ደኤታው ሌላው የኢንዱስትሪው ቁልፍ ችግር ብለው የጠቀሱት፣ ከተለያዩ ዘርፎች ያለው ቅንጅታዊ አሠራር ደካማ መሆኑን ነው፡፡ ፕሮጀክቶች ታቅደው በቂ በጀት አለመመደቡ፣ በቂ ግብዓት ያለመኖሩና የመሳሰሉ ችግሮች መታየታቸው ነው፡፡ እንዲህ ላሉ ችግሮች የኮንስትራሽን ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ውስጥ መጫወት የነበረበትን ሚና እንዳይጫወት ትልቅ እንቅፋት ፈጥሯል ይላሉ፡፡
ሌላው የማይካድ ብለው ያስቀመጡት የኢንዱስትሪው ተግዳሮት ደግሞ በግንባታው ባለቤት፣ በኮንትራክተርና በኮንሰልታንት መካከል ያለው መልካም ያልሆነ ግንኙነትን ነው፡፡ በሦስቱ አካላት መካከል ያለውን ግንኙነት ‹ያልተቀደሰ ጋብቻ› ያሉት ጥናት አቅራቢው፣ ‹‹ጥሩ ግንኙነት ቢኖራቸው ኖሮ ዘርፉ እንዲለወጥና ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉትን አብዛኛዎቹን ችግር ይፈታ ነበር፤›› ብለዋል፡፡
እነዚህ ተቋማት ለአንድ ዓላማ የቆሙ ሳይሆን አንዱ ሌላውን የሚጎትትበት፣ አቅም በተጨባጭ ያልተገነባበት፣ በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቶች እጅግ የተጋነነ ወጪ እንዲወጣባቸው ጭምር ምክንያት ሆነዋልም ብለዋል፡፡
የእዚህ ተቋማት ተናበው አለመሥራት የግንባታዎችን ጥራት ጥያቄ ውስጥ እስከ መክተት የደረሰ መሆኑንም ያመለከቱት ጥናት አቅራቢው፣ ‹‹ቅድመ አያቶቻችንና አያቶቻችን ከገነቧቸው ሕንፃዎች ያነሰ የጥራት ደረጃ ያላቸው መሠረተ ልማቶች የሚገነቡበት ሆኔታ ተፈጥሯል፤›› በማለት፣ ተናቦ ያለመሥራት የኮንስትራክሽን ዘርፉ ማነቆ እንደነበር አመልክተዋል፡፡
ለጥራት መጓደሉ ሌላ ምክንያት አቅም የሌላቸው ተቋራጮችና አማካሪዎች እንዲቀጠሩ መደረጋቸው ጭምር መሆኑንም አስታውሰው፣ የዘርፉ ማነቆ ነው የተባለው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ከባለሙያዎች ጋር ይያያዛል፡፡ በየዓመቱ 45 ሺሕ የሚበልጡ ከምሕንድስናና ከምሕንድስና ጋር ተያያዥነት ያላቸው ባለሙያዎች ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ቢሆንም፣ በአግባቡ ዲዛይን ፕሮዲውስ የሚያደርግ፣ ጥራት መቆጣጠርና ፕሮጀክት ማኔጅ ማድረግ የሚችል ባለሙያ ማጣቱ ነው፡፡ የሥራ ልምድ ብቻ እየታየ የባለሙያዎችን ደረጃ የምናወጣበት ሥርዓት ትልቅ ችግር መሆኑንና ይህ ሥርዓት ያስገኘው ነገር እንደሌለ አመልክተዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የኮንትራክተርና የአማካሪዎችን ሁኔታም ሲታይ ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
‹‹ይህ ዘርፍ ማንም የሚገባት ነው፡፡ መግባቱ ችግር የለውም፣ ግን ከዚያው ውስጥ ግን አበጥረን እናውጣ ቢባል፣ የተሻለውና ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ሊያሻግር የሚችለው እጅግ ጥቂት ነው፤›› ያሉት ወንድሙ (ኢንጂነር)፣ በአሁኑ ጊዜ ወደ 22 ሺሕ የተመዘገቡ ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች ያሉ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የተሻሉ የሚባሉት 2,000 ማግኘት እንኳን ከባድ መሆኑንም አክለዋል፡፡
አቅም ኖሮት ነገ ለልጅ ልጅ የሚተላለፈ ኩባንያ ያለው ስንት እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ‹‹ስለዚህ ፈቃድም ሲሰጥ ስንት ማሽን አለህ? የሌለውን ባለሙያ ስንት ባለሙያ አለህ? ብለን ብቻ ፈቃድ መስጠት ተገቢ እንዳልሆነም ያሰምሩበታል፡፡ ላለፉት አሥር ዓመታት ምንም ዓይነት ፕሮጀክት ሳይሠራ ፈቃዱ የሚታደስለት መኖሩንና ፈቃዱን ለምን እንደሚጠቀሙበት ዘርፉ ውስጥ ያላችሁ ታውቁታላችሁ ብለው አልፈውታል፡፡ ስለዚህ ያልተገሩ አካሄዶች ስላሉ ይህንን ማረቅ የሚገባት አሠራር መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያጠፋው የሚቀጣበት፣ ጥሩ የሠራው ሪዋርድ የሚደረግበት ሥርዓት ያልነበረበት ስለነበር፣ ይህንን ማስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡
‹‹የሚሻገሩ ኩባንያዎችን መፍጠር ካልቻልን፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከሚፈልገው እየተገሩ ካላደጉ በቀር ይህ ዘርፍ ተሻጋሪ አይሆንም፤›› ጥናት አቅራቢው እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው እምነት በቁርጠኝነት በርካታ ማስተካከያዎችን እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱም በአሥር ዓመታት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ላይ እንደርሳለን ከተባለ፣ ይህንን ለማሳካት ወይም መካከለኛ ገቢ አገር ላይ ለመድረስ የሚቻለው በኮንስትራሸን ዘርፉ ላይ ያለውን ችግር ስንፈታ ብቻ መሆኑንም አሳስበዋል፡፡
በሁሉም ዘርፉ ላይ ያሉት የልማት ግቦች በሙሉ የኮንስትራሽን ኢንዱስትሪውን ዲማንድ ያደርጋልና ኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ያለውን ማነቆ ካልተፈታ ዕቅዶችን ማሳካት ስለማይቻል እዚህ ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቃል፡፡ ለዚህም ዘርፉን የሚያሻግር ሥራ መሠራት አለብን ተብሎ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች እጥረትን በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የችግሩ ምንጭ ያሉትንም ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ በግብዓት እጥረትና በዋጋ ንረት ላይ ማብራሪያቸውን የጀመሩት፣ ‹‹ከኮንስትራክሸን ኢንዱስትው በግብዓት ዕጦት ምክንያት ታንቋል፤›› በማለት ነበር፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትው ብቻ ሳይሆን ዛሬ የፈረሰ ቤት ለመጠገን እንኳን አልተቻለም፡፡ ሲሚንቶ በችርቻሮ በኪሎ ሁሉ እየተሸጠ መሆኑንም ጠቅሰው፣ የሲሚንቶ ዋጋ የማይቀነስ ከመሆን አልፎ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሲሚንቶ ዋጋ በየትኛውም ዓለም የሌለ ዋጋ ስለመሆኑም ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ ይህ የተጋነነ ዋጋ መንስዔ አንዳንዶች የምርት እጥረት፣ አንዳንዶች ደግሞ ሰው ሠራሽ እጥረት ሲሉ፣ ሌሎች የፋብሪካዎች የማምረት አቅም ማነስ ነው ቢሉትም፣ ትክክለኛው ምክንያት ግን ይህ አለመሆኑን ያመላክታል፡፡
አንዱ የኢኮኖሚ ዕድገት መለኪያ የሲሚንቶ ‹ፐር ካፒታል› ፍጆታ ነው፡፡ የአሁን ባለንበት የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ የእያንዳንዶችን የሲሚንቶ ‹ፐር ካፒታል› ፍጆታ በአነስተኛ ግምት የእያንዳንዳችን የሲሚንቶ ፍጆታ 500 ኪሎ ግራም ‹ፐር ካፒታል› ነው፡፡ 100 ሚሊዮን ሕዝብ አለን ቢባል፣ 50 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ በዓመት ማምረት አለብን፡፡ አሁን ያለው የፋብሪካዎቻችን የማምረት አቅም ግን በዓመት ከ16 እስከ 18 ሚሊዮን ቶን ነው፡፡ የሚሠሩት ደግሞ በ50 በመቶ አቅም ነው፡፡ ስለዚህ ዓመታዊ የሲሚንቶ የማምረት አቅማችን ሰባት ሚሊዮን ቶን አካባቢ ነው፡፡ ይህ የምርት መጠን በነፍስ ወከፍ ሲታሰብ 75 ኪሎ ግራም በዓመት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢኮኖሚያችንን እናሳድጋለን ስንል ሲሚንቶ ላይ ያለውን ማነቆ፣ በአገር ውስጥ ያለውን የግብዓት ማነቆ ካልፈታን፣ ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በመተካት ካልፈታን ኢኮኖሚ ተንገራግጮ ይቆማል፡፡
በመሆኑም እንዲህ ያሉ ክፍተት ባለበት ሁኔታ የግሉ ዘርፍ ማንቀሳቀስ አይችልም፣ የመንግሥት ፕሮጀክቶች መሥራት አይቻሉም፡፡ ግለሰቦች የራሳቸውን ግንባታ እንኳን ለማከናውን የማይችሉበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ በአንፃሩ ግን ኢትዮጵያ ለሥራዋ ብቻ ሳይሆን በዙሪያዋ ላሉ አገሮችና ለመካለኛው ምሥራቅ ሲሚንቶ ኤክስፖርት ማድረግ የምትችልት ሁሉም ጥሬ ዕቃዎች አሏት፡፡ ለሲሚንቶ ምርት የሚሆን እስከ 98 በመቶ የሚሆን ጥሬ ዕቃ ያላት ነች፡፡ ነገር ግን ችግሩን የሚያብስ ነገር ተከሰተ፡፡ ይህም ሲሚንቶ አሁን የገጠመውን ችግር መነሻ ያደረገበትን ምክንያት ሲያስቀምጡ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት በመንግሥት የተወሰነን አንድ ውሳኔ ነው፡፡ ይህም በወቅቱ እየተመረተ ያለው ሲሚንቶ፣ ከአቅም በላይ ስለሆነ የሲሚንቶ ኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዳይሰጥ መደረጉ ነው፡፡
ነገር ግን 280 ብር የነበረው የሲሚንቶ ዋጋ አምስት ዓመት በኋላ 2,000 ብር ገባ፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረው ፐር ሰፕሸን የሆኑ ተዋንያን በዚያ ገበያ ውስጥ እንዲገቡ፣ ነገር ግን እነሱ ከገቡ በኋላ ሌላ ተዋንያኖች ወደ ገበያ እንዳይገቡ ብሎክ ማድረግ ነው እንጂ፣ በዚያን ወቅት ጂዲፒ1 እና ጂዲፒ2 ተብሎ የታቀደው ዕቅድ ሲሚንቶ ዲማንድ ማድረግ ማንም ጠፍቶ አይደለም በማለት የችግሩን ሥረ መሠረት አስረድተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን እየተመረተ ያለው የሲሚንቶ ምርት መልናመርት ከሚገባው አንድ አምስተኛ ብቻ ሊሆን ችሏል በማለት የችግሩን ሥረ መሠረተ አመላክተዋል፡፡
በመሆኑም አሁን የተፈጠረው እጥረትና ክፍተት የሚገርም እንዳልሆነ ያመለከቱት ወንድሙ (ኢንጂነር)፣ ይህ ችግር ምንም ምክንያት ይሰጠው ሊፈታ መቻል እንዳለበት አስምረውበታል፡፡ ሚኒስቴር ደኤታው በዘርፉ ያሉ በርካታ ችግሮች ውስጥ የመረጃ አደረጃጀት ችግር አንዱ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ ኮንትራክተሮች ምን ያህል ግንባታዎችን እንዳከናወኑና ያስገኘውን ውጤት የሚያመለከት መረጃ የለም ብለዋል፡፡ በመሆኑም እንዲህ ያሉ ችግችንም ለመፍታት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኮንስትራክሽን የመረጃ ቋት ሥርዓት እያዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
ጥናት አቅራቢው ያለፉት 20 ዓመታት ኢንዱስትሪውን በተመለከተ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ደግሞ፣ ችግሮችም ቢኖሩም ዘርፉ ዕድገት እያሳየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለምሳሌ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በ2001 ዓ.ም. በኢኮኖሚው ውስጥ የነበረው ድርሻ 4.93 በመቶ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን 19.8 በመቶ ደርሷል፡፡ ስለዚህ ኢንዱስትሪው ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ የነበረው አስተዋጽኦ ከአምስት እጥፍ በላይ ከፍ ብሏል፡፡ ይህ አኃዝ የሚያሳየው በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ቁልፍ ድርሻ ያለው መሆኑን ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ብዙ ዘርፎችን አቅፎ የሚይዝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ትልቁን የመንግሥት ካፒታል በጀት የማይዘውም ይሄው የኮንስትራክሽን ዘርፍ በመሆኑ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ዕገዛ ያደርጋል፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ሲንቀሳቀስ ሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች የሚነቃቁ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ አንዳንድ አገሮች ኢኮኖሚያቸው በተወሰነ ደረጃ መቀዛቀዝ ሲጀምር ኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ በተለይ የቤቶች ግንባታ ላይ ኢንቨስት ያደርጋሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉበት ዋናው ምክንያት አጠቃላይ በዚህ ዘርፍ ውስጥ ያለ የምርትና ንግድ ሰንሰለት አጠቃላይ ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃና የሚያንቀሳቅስ በመሆኑ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰዋል። ይህ ዘርፍ ከእነ ችግሮቹም ቢሆን ባለፉት 20 ዓመታት በአገር ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ነበረው ብለዋል።
የቤቶች ልማት ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ላይ የቆመ ቢሆንም፣ የቤት ልማት ፕሮጀክቱ እየተተገበረ በነበረበት ወቅት ኢኮኖሚው ውስጥ የነበረው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ነበር ብለዋል፡፡ ከእነ ችግሩም ቢሆን ለብዙ ኮንትራክተሮች አማካሪዎች መፈጠር ምክንያት የነበረ ፕሮጀክት እንደነበረም ጠቅሰዋል፡፡
የህዳሴ ግድብም የዚህ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውጤት ነው፡፡ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በአዲስ አበባ የተሠሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችም የዚህ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውጤቶች ናቸው፡፡ ‹‹አውት ፑቱን›› ሳይሆን በዚህ ፕሮሰስ ውስጥ የሚፈጠር የሥራ ዕድልና ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረው መነቃቃትን ነው፡፡
ይህንን ዘርፍ አሁንም ለማሻገር በመንግሥት ደረጃ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች መኖራቸውን፣ አዳዲስ አሠራሮች የሚተገበሩ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ ባለድርሻ አካላት ተናበው የሚሠሩበት ሥራ ትልቅ ቦታ የሚጠው እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ዘርፉ ከብዙ ዘርፎች ጋር የሚገናኝ በመሆኑም መፍትሔም ይህንን ታሳቢ ያደረገ ይሆናልም ተብሏል፡፡
በአጠቃላይ በዘርፉ አሁን ያሉትን ችግሮች ለመፍታትና ለመቅረፍ፣ እንዲሁም ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት እንዲፈጠር ለማድረግ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው እንደሚሠራ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ይህንን ለማሳካት ሁሉም የዘርፉ ተዋንያኖች ከመሥሪያ ቤታቸው ጋር አብረው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡