በአዲስ ዓመት ማግሥት ከመገናኛ ወደ ገርጂ ልንሳፈር ነው። ድንገት ብልጭ የምትለውን ፀሐይ ሰሞነኛው ደመና ሸፍኗታል። ልክ አንዳንዱን እውነታ ሰሞነኛ ማስተባበያ እንደሚሸፍነው። መንገዱ ላይ ቆመን በትርምሱና በጫጫታው መሀል የማሰላስለው ከአድማስ ወዲህ ማዶ ስላለው ስለሰው ልጆች ትግል ነው። ሁሉም ነገር በትግል ሲባጎ ተጠፍንጎ የተሳሰረ ይመስላል። ሁሉን የሚችለው ብርቱው የሰው ልጅ በአልበገር ባይነት ፅናትና መንፈስ ለመኖር ግብግብ እንደገጠመ ነው። ነጩ ደመና ቶሎ የሚያባራ ዝናብ ቋጥሮ እኛ ላይ ሊለቀው ያስባል። ለታክሲ ሠልፍ የያዘው መንገደኛም ገልመጥ እያለ በደመናው ውስጥ አንድ ነገር ፈልጎ ያጣ ይመስላል። ‹‹በቃ ይህ ነው የእኛ ሕይወት?›› ትላለች አንዲት ቀጭን ጠይም ረዥም ወጣት። ያለ ዕድሜዋ የተሸበሸበ ቆዳዋን ለሚመለከት ብዙ ያልተኖሩ ልጅነቶች ይታወሳሉ። ‹‹አይ እናት አገሬ፣ ስንቱን ያለ ዕድሜው አገረጀፍሽው?›› ይላል ልጅቱን በትኩረት ሲያስተውላት የቆየ ጎልማሳ። ‹‹የቱ ነው የእኛ ሕይወት ማለት?›› ትላታለች ግራ የተጋባች ጓደኛዋ። ‹‹ያ ሩቅ ያለው ደመና ነዋ፣ ከደመናው ጀርባ ፀሐይ እንዳለች እርግጠኛ የሆንበት ደመና። የእኛም ሕይወት እንዲህ አይደል? ከችግሮች በስተጀርባ ዘላቂ መፍትሔዎች እንዳሉ እናውቃለን። ግን ከደመናው ጋር ፍቅር ይዞን ነው መሰል ወይም ሌላ ይሁን ብቻ አላውቅም፣ ይኼው በየሄድንበት ሠልፉና መጉላላት፣ ኧረ ተይኝ…›› ብላት በረጅሙ ተነፈሰች። ‹‹ለዳቦ፣ ለኤሌክትሪክ ክፍያ፣ ለታክሲ፣ ለአውቶቡስ፣ ወዘተ እንሠለፋለን፡፡ አቤቱታ ለማቅረብ ግን ሠልፍ አይፈቀድልንም…›› ስትል ወጣቱና ጎልማሳው ተያዩ። የገመትነው እውነት የልጅቷ ልጅነት ውስጥ ነበር። መንገድ ሲያገናኝ ግን ስንት እውነት ይታያል!
ወዲያው አንድ የገርጂ ታክሲ መጣ። የምንሞላው ሰዎች ብቻ ገብተን ቦታ ቦታችንን ስንይዝ ቀሪው ሠልፈኛ ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ይቁነጠነጥ ነበር። ‹‹እኔ እምለው ከመቼ ወዲህ ነው አዲስ አበባ እንዲህ ሰው የበዛው?›› ይላል አንድ ‹‹ዳያስፖራ›› መሰል ተሳፋሪ፡፡ ‹‹አልሰሜን ግባ በለው አሉ፣ መንግሥት አልሰማን አለ ብለን የምንጮኸው ዝም ብለን ነው፡፡ መጀመሪያ መቼ እርስ በርሳችን ችግራችንን አወቅነው ሲባል ማን ሰምቶ? ግን ይኼው…›› ብላ አንዲት ነገር ነገር የሚላት ሴት አጠገቡ እንደ ተቀመጠች ተንበለበለች። ‹‹ይቅርታ፣ እኔ እኮ እዚህ አገር ስለማልኖር ነው የጠየቅኩት?›› ሲላት፣ ‹‹ጭራሽ እናንተ አይደላችሁ እንዴ እኛ እናውቅላችኋለን እያላችሁ በየኢንተርኔቱ ጓዳ ስለአገሬና ስለሕዝቧ የምትወሸክቱት? እኔ እምለው ለመሆኑ ከውጭ የመጣኸው ለአገርህ ለመዋጋት ነው?›› ስትለው ደንግጦና ግራ ገብቶት ሁሉንም ተሳፋሪዎች ይቃኝ ጀመር። እኛም እንደ እሱ ደንግጠን መተያየት ጀመርን፡፡ ብዙም ሳይቆይ እየተንቀሳቀ የነበረውን ታክሲ አስቁሞ፣ ‹‹እባክህ ቦታ ቀይረኝ?›› አለ ወያላውን። ሊወርድ አስቦ የሠልፉ ነገር ሐሳቡን እንዳስቀየረው ያስታውቅበታል። አንድ ፈቃደኛ ተሳፋሪ ከኋላ መቀመጫ ተነስቶ ከቀየረው በኋላ ጉዟችን ቀጠለ። ‹‹አይ ታክሲ ስንቱን ያሳየናል?›› ይላል ከሾፌሩ ጀርባ ያለ ጎልማሳ። ሕይወት በውስብስብ ገጽታዋ ብዙ እያሳየችን የኖርነው ቢያንስ ግማሹ ታክሲ ውስጥ መሆን አለበት። ቀለበት መንገዱን ይዘን መምዘግዘግ እንደ ጀመርን፣ ‹‹ይኼ ቀለበት መንገድ የስንቱን ቀለበት አስወለቀ?›› አለ የማይናገር የሚመስለው ወያላ መንገዱ መሀል እየዘለለ የሚሻገር ትልቅ ሰው እያየ። ‹‹እንዴት?›› ሲሉት፣ ‹‹ድልድይ ፈልጎ መሻገር አላስችል ብሎት ስንቱ ነው ያለቀው?›› ከማለቱ በቅጡ ያላስተዋልናቸው አዛውንት፣ ‹‹ጊዜ ጠብቀህ ተናገር ውኃ ሲጎድል ተሻገር ነዋ ከጥንትም ብሂሉ፣ የዘንድሮ ሰው ምክር ጠላ እንጂ?›› ብለው እጃቸውን አመናጨቁ፡፡ መጥኔ ማለታቸው ነው!
የደመናው ገጽታ ከጨለማው በፊት ሌላ ዓይነት ጨለማ የፈጠረ ይመስላል። ወያላው ሒሳብ መቀበል ጀምሯል። በውል ፊቱን ማየት ያልቻልነው ተሳፋሪ መስኮት ከፍቶ አይዘጋም በማለት ጭቅጭቅ ብጤ ለመጀመር ዳር ዳር ይላል። ጭቅጭቁ ብዙ ሳይገፋ አንድ ስልክ ጮኸ። ስልኩን ያነሳው ወጣት ተሳፋሪ፣ ‹‹መጣሁ፣ መጣሁ፣ ሜክሲኮ ደርሻለሁ። እውነት፣ እውነት…›› ብሎ ይዋሻል። አባባሉ ጆሯችንን ሰቅጥጦታል። ይባስ ብሎ ነው መሰል ስልኳ ሲጮህ ሳንሰማው መነጋገር የጀመረችው ሌላ ወጣት ሴት፣ ‹‹አሁን… እ… ወደ ሲኤምሲ እየደረስኩ ነው…›› ትላለች። አዛውንቱ በጩኸት፣ ‹‹ኧረ ሾፌር መኪናውን አቁምልኝ…›› ካሉ በኋላ ወያላውን ይወርዱበት ጀመር። ‹‹ምን ነው አባት ምን አጠፋሁ?›› ሲላቸው፣ ‹‹ሞላጫ፣ ዋሽተኸኝ ለምን ገርጂ ነው የምሄደው ብለህ ጫንከኝ?›› ብለው አንባረቁበት። ወያላው ነገሩ ወዲያው ገብቶት፣ ‹‹አሁን ስልክ ሲነጋገሩ የሰሟቸው ሰዎች የቀጠሩትን ሰው ስላረፈዱበት የተናገሩት ውሸት ነው እንጂ የምንሄደው ገርጂ ነው…›› ብሎ አረጋጋቸው። ከተሳፋሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ሆዳቸውን ይዘው ሲስቁ አንዱ ጎልማሳ እያዘነ፣ ‹‹ሞባይል ከመጣ ዘመን ቅጡን ይጣ…›› ይላል። ወዲያው የአዛውንቱ ስልክ ሲያቃጭል አነሱት። ‹‹የት ደርሰዋል?›› ተብለው ነው መሰል፣ ‹‹ኧረ እኔም አላወቅኩት፣ አንዱ ሜክሲኮ ይላል ሌላዋ ሲኤምሲ እያለች ግራ ገብቶኛል…›› ሲሉ የተሳፋሪዎች ሳቅ አጀባቸው። በምሬት መሀል ሳቅ ሲደባለቅ ዘና ያደርጋል!
ጉዟችን እንደ ቀጠለ ነው። ኢምፔሪያል አካባቢ ሁለት ሰዎች ወርደው አራት ተሳፋሪዎች በምትካቸው ተጫኑ። ሾፌሩ በመስኮቱ አሻግሮ በተቃራኒ አቅጣጫ የሚመጣ ባለታክሲ ወዳጁን በመጣበት መንገድ ትራፊክ ፖሊስ መኖር አለመኖሩን ይጠይቀዋል። ያኛውም፣ ‹‹የለም…›› ብሎ ይመልሳል። ‹‹ጫን በደንብ…›› ይለዋል ሾፌሩ ወያላውን፡፡ እኛ ደግሞ ዝም። ‹‹ለማን አቤት ይባላል? ቢባልስ እስካሁን ያልነው አይበቃም ነበር?›› ይላል ጎልማሳው። ጠይሟ ቆንጆ ወጣት በበኩሏ፣ ‹‹አስተዳዳሪዎቻችን እንኳን ተነግሯቸው ላያቸው ላይ አስተዳደር ቢገነባባቸውም አይነቁ…›› ትላለች የሚስቅ ይስቃል። ‹‹ተስፋ መቁረጥ የለም…›› ብሎ አንድ ድምፅ ሲጮህ ሁላችንም ዞረን አየነው። ሙሉ ልብስ ነው የለበሰው። በእጁ የ‹‹ላፕቶፕ›› ቦርሳ ይዟል። ‹‹እኔን ከመረጣችሁኝ ችግራችሁን ሁሉ ገደል ነው የምሰደው…›› ብሎ ወሬውን ጀመረ። ወዲያው ወደፊት ለሚደረግ ምርጫ ዕጩ የግል ተወዳዳሪ ለመሆን ከአሁኑ እየተዘጋጀ እንደሆነ ነገረን። ‹‹ለመሆኑ…›› አለው አንድ አጠገቡ የተቀመጠ ተሳፋሪ። ‹‹…እንዴት ብለህ ነው የታክሲ ሠልፍንና እጥረትን ልታስወግድ ያቀድከው?›› ብሎ ጠየቀው። የምርጫ ቀስቃሹ ሙሉ ፈገግታ ፊቱን ወርሶት ‹‹ይኼማ ቀላል ነው፣ አያችሁ ብዙዎቻችን ከእንቅስቃሴ ጋር ተቆራርጠናል። ጠንካራና ጤናማ ዜጋ ለአንድ አገር ህልውና ወሳኝ ነው። ጠንካራና ጤነኛ ኅብረተሰብ የአገሩን ዳር ድንበር ከማስከበር አልፎ፣ በጥሩ ሁኔታ ሳይደክመው እየሠራ ጥሩ ግብር ከፋይ ይሆናል። ስለዚህ የታክሲ ችግርን መቅረፍ የሚቻለው በእግር ለመሄድ ስንወስን ነው። ጤናችሁንና ገንዘባችሁን ገና በብዙ ጉዳዮች ዙሪያ ስለማተርፍላችሁ ግድ የለም እኔን ለመምረጥ ከወዲሁ ዝግጁ ሁኑ፣ አመሠግናለሁ…›› ሲል ታክሲዋ ደም በለበሱ ዓይኖችና ንዴት በሚያቁነጠንጣቸው ተሳፋሪዎች ተሞላች። ደም የሚያፈላ ነገር አይጠፋ!
ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ወያላው ኮሪያ ሆስፒታል አካባቢ የጫነውን ተሳፋሪ ሒሳብ ሲቀበለው ተሳፋሪው፣ ‹‹ለመሆኑ መቼ ነው እናንተም የካሽ ሬጅስተር ማሽን የምታስገቡት?›› በማለት ጠየቀው። ወያላው እየሳቀ፣ ‹‹እንግዲህ መመርያው ወጥቶ ሲፀድቅ ነዋ። መቼም እዚህ አገር ሁሉ ነገር ላይ የአፈጻጸም ችግር ሲኖር ‹‹ቫት›› ላይ ቀልድ የሚባል ነገር የለም። ምናለበት ሌላውም ነገር ላይ ቀልድ አላውቅ ብንል?›› ብሎ ይመልስለታል። ‹‹ቀልድ ሲበዛ አገር ያበላሻል…›› ይላል ሌላው ከኋላ። ‹‹አሁንስ የሰለቸን የኋላቀር ርዝራዦችን ትንታኔ መስማት ነው…›› ይላል ከጎኑ የተቀመጠ ጎልማሳ። ሁሉም ተሳፋሪዎች የጎሪጥ መተያየት ጀመሩ። ውይይቱ በሁለት ጎራ ተከፍሎ አረፈው። ‹‹በለው! እውነተኛው የምርጫ ክርክርስ ይኼ ነው…›› ይላል አንድ ቀልቀል የሚል ልጅ እግር። ከአንደኛው ወገን በቀልድ መልክ አንዱ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ይገርማችኋል ከማጣቴ የተነሳ አንድ ሰሞን የማውቀውን ሰው ሁሉ ተበድሬ ተበድሬ የቀረኝ ራሱን ኑሮን መበደር ሆነ። በኋላ ኑሮ ዘንድ ሄጄ ኑሮ ሆይ! እባክህ ሲኖረኝ የምከፍልህ አሁን ልበደርህና ልኑርበት አልኩና ‹አድቫንስ› ጠየቅኩት። እንዲህ የሚባል ነገር የለም፣ እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም ብሎ አውጇል አለኝ። እኔም አውጇል ባለው ፈንታ ዘፍኗል ይለኛል ብዬ ጠብቄ ኖሮ ማን ነው ያወጀው ስለው፣ ‹አብዮታዊው መንግሥትህ ነዋ!› አይለኝ መሰላችሁ? እውነቴን እኮ ነው. . .›› እያለ አጠገቡ ያሉ ሰዎችን እጅ ይመታል። መሀላና ቀልድ እውነትና ውሸት የተሰባጠሩበት ዘመን ይብቃ!
‹‹እውነቱን እኮ ነው፣ ባይሆን ኑሮማ ሌብነት እንዲህ ሥር ይሰድ ነበር?›› ትላለች ከፊት አካባቢ የተቀመጠችው ወጣት። ‹‹የዘንድሮ ሰው ምሥጋና የለሽና ራስ ወዳድ ብቻ ነው። በማን ላይ ሆነሽ ማንን ታሚያለሽ አሉ፡፡ እንዲህም የልብን መናገር ያስቻላችሁ የለውጡ መንግሥታችን ነው…›› ብሎ አንዱ ሲመልስ፣ ከዚያኛው ወገን ሦስት ተሳፋሪዎች በሳቅ ታክሲዋን አናጉዋት። ሳቁ ያልገባን ግራ ተጋብተን ስናያቸው፣ ‹‹አይ! አይ! ዴሞክራሲ በስምሽ ስንት ግፍ ተሠራ፡፡ በአዲሱ ዓመት በዴሞክራሲ መነገድና መቆመር ካልቆመ ምኑን አሮጌው ዓመት ተለወጠ ይባላል…›› ሲል ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገር የሌለባቸው በርካታ አላስፈላጊ ነገሮች አሉን…›› ይላል። ወያላው ታክሲው ሲቆምለት በተጣደፈ ድምፅ ‹‹መጨረሻ!›› አለ፡፡ ልንወርድ ስንጋፋ አንዱ፣ ‹‹የሁሉም ችግሮች ባለቤት እኛው ስለሆንን አስተሳሰባችንን ካላሳደግን ምንም የሚለወጥ የለም…›› ሲል አዛውንቱ ቀበል አድርገው፣ ‹‹እውነት ነው እኛም እንለወጥ…›› ብለው የጉዟችንን ጭውውት ቋጩት፡፡ መልካም ጉዞ!