በነሐሴ አጋማሽ በዘ አፍሪካን ሪፖርት መጽሔት ላይ ‹‹Ethiopia፡ The African Union Cannot Deliver Peace to Tigray›› የሚል ጽሑፍ ያስነበቡት የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የአፍሪካ ኅብረትን ሚና አጣጣሉት፡፡ በተለይም የኅብረቱ የምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ልዑክ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን ሚና ጥያቄ ምልክት ውስጥ የከተቱት አቶ ጌታቸው፣ የአፍሪካ ኅብረት ለትግራይ ጉዳይ የሰላም መፍትሔ ለመስጠት እንደማይችል ነበር ለማሳየት የሞከሩት፡፡
በተለያዩ ጊዜያት የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪ እንዲቀይርላቸው ሲወተውቱ የቆዩት የሕወሓት ሰዎች፣ በስተመጨረሻ ከኅብረቱ ተስፋ አስቆራጭ ምላሽ ነበር የገጠማቸው፡፡ በአዲስ ዓመት ዋዜማ መግለጫ ያወጡት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሕማት የኦሉሴጉን ኦባሳንጆን የተልዕኮ ጊዜ ማራዘማቸውን ይፋ አደረጉ፡፡
ሊቀመንበሩ ከኦባሳንጆ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን በዚህ መግለጫቸው ገልጸዋል፡፡ በከፍተኛ ልዑኩ ሥራ እንደሚተማመኑ በመግለጽም፣ የአደራዳሪነቱን ሚናቸውን እንዲቀጥሉ መፍቀዳቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ይህ ሕወሓቶች ያልፈለጉትና ያልጠበቁት ውሳኔ እንደሆነ ብዙዎች ይገምታሉ፡፡
ሕወሓቶች የአፍሪካ ኅብረትን የአደራዳሪነት ሚና ሲቃወሙ ብዙም አልታየም፡፡ ከሰሞኑ ባደረጉት የድርድር ጥሪም በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ዋና አደራዳሪ በመሆናቸው ጉዳይ ላይ ተደጋጋሚ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደ ኡሁሩ ኬንያታ ያሉ መሪዎች ያደራድሩን ሲሉ የተደመጡት ሕወሓቶች በአዲሱ መግለጫቸው ግን፣ ‹‹ቢያንስ ሁለታችንንም የሚያግባባ ሰው ይመደብ፤›› በማለት ጥያቄያቸውን ለዘብ በማድረግ አቅርበዋል፡፡
ሕወሓቶች ‹‹በአፍረካ ኅብረት ጥላ ሥር እንደራደር፤›› ማለታቸው አዲስ ዜና ባይሆንም እንኳን፣ በርካታ ግብረ መልሶችን እያገኘ ያለ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ሕወሓቶች ቢያስተባብሉትም የመንግሥት ሚዲያዎች ሳይቀር ‹ሾልኮ የወጣ ሰነድ› ብለው በተቀባበሉት ዶክመንት፣ ሕወሓቶች የመጨረሻ ምዕራፍ ያሉትን የጥቃት ዘመቻ በቅርቡ እንደሚያውጁ ተጠቅሶ ነበር፡፡ በዚህ ሰነድ ላይ ደግሞ የመጨረሻው ምዕራፍ ዘመቻቸው አዲስ አበባ አራት ኪሎ፣ እንዲሁም አስመራ ቤተ መንግሥት የተቀመጡ መንግሥታትን የመገልበጥ ዓላማ ይዘው መነሳታቸውን የሚጠቅስ መረጃ ሠፍሯል፡፡
ሕወሓቶች በሰነዱ የተመለከተውን ዓይነት ዓላማና ግብ ባይኖራቸው ኖሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ዝግጁ ሆኖ ሳለ፣ በቅርቡ የጀመሩትን ዓይነት ጦርነት አይጀምሩም ነበር የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ‹‹ሕወሓቶች የተማመኑትን ባይተማመኑ ኖሮ ሦስተኛውን ዙር ጦርነት አይጀምሩም ነበር›› የሚሉት እነዚህ ወገኖች፣ ወዲያው ወደ ድርድር ካልገባን ሲሉ የታዩትም በአስገዳጅ ሁኔታዎች መሆኑን ይገምታሉ፡፡
ከዚህ ጋር አያይዘው በመንግሥት ኃይሎች ትግራይ ክልል ሊገባ ሲሞክር ተመትቶ ወደቀ ስለተባለው አንቶኖቭ አውሮፕላን ጉዳይ የሚያነሱት እነዚህ ወገኖች፣ ሕወሓቶች መሣሪያ ከየት አምጥተው ነው አዲሱን ጦርነት የከፈቱት? ሲሉ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡
ሕወሓቶች በምን ምክንያት ተገፋፍተው ጦርነቱን እንደጀመሩ ሁሉ፣ በአስገዳጅ ምክንያት እንደራደር ማለታቸው ብዙም ትርጉም እንደሌለው የሚናገሩም በርካቶች ናቸው፡፡፡ ዋናው ጉዳይ የሕወሓቶች አመክንዮ ሳይሆን ለድርድር ያላቸው ዝግጁነት ነው የሚሉት እነዚህ ወገኖች፣ ለሰላም ፍላጎት እስካላቸው ድረስ ዕድሉን መጠቀም ጠቃሚ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
ምንም ተባለ ግን የሕወሓቶች ሰሞነኛ የድርድር ጥሪ በአገር ቤትና በውጭ አገር በሰፊው መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ በቃል አቀባያቸው ስቴፋን ዱጃሪክ በኩል፣ የአፍሪካ ኅብረት መራሹን ድርድር ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አዲሱ ጦርነት ሲጀምር ሕወሓትንም መንግሥትንም እኩል የሚያወግዝ መግለጫ ስትሰጥ የታየችው አሜሪካ የሕወሓትን ጥሪ እደግፋለሁ ስትል ተሰምታለች፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የውጭ ጉዳይ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን፣ የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሀመር፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ የሕወሓትን የድርድር ጥሪ የሚቀበል መግለጫ አውጥተዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረትም ተመሳሳይ ስሜት ያንፀባረቀ ሲሆን፣ የኅብረቱ የውጭ ግንኙነት ከፍተኛ ተወካይና የደኅንነት ፖሊሲ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፕ ቦሬል የሕወሓትን የድርድር ጥሪ ‹‹ሁሉም ሊጠቀምበት የሚገባ ዕድል›› ብለውታል፡፡
ምዕራባውያኑ እንዳስተጋቡት የሕወሓት የድርድር ጥሪ ለሰላም መንገድ የሚጠርግ ዕድል ነው ወይ? የሚለው ጉዳይ ግን ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡ በተለይ በአገር ቤትና የኢትዮጵያን አቋም በሚደግፉ ወገኖች የሕወሓት ጥሪ በጥንቃቄ መመርመር እንደሚኖርበት የሚጠቁሙ አስተያየቶች በመሰጠት ላይ ናቸው፡፡
የሰላም ሚኒስትር ደኤታው አቶ ታዬ ደንደአ በፌስኩክ ገጻቸው የሕወሓት ጥሪ፣ ‹‹በጊዜ ካልደረሳችሁልን ሊያልቅልን ነው፤›› የሚል መልዕክት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ የመንግሥትን ለሰላም የተዘረጋ እጅ ነክሶ በአምስት ግንባሮች ጦርነት መክፈቱንና ገስግሶ አዲስ አበባ ለመግባት ሲናገር የቆየው ሕወሓት፣ የሰላም ድርድሩ መፍረሱንም በይፋ ማወጁን አቶ ታዬ አስታውሰዋል፡፡
ከዚህ በመነሳትም፣ ‹‹የሕወሓት የድረሱልኝ ጥሪ ኢትዮጵያን የማፍረሱ ጥረት በውክልና ስላልተሳካ፣ ራሳችሁ በቀጥታ ግቡና ፈጽሙት ብሎ ምዕራባውያኑን እንደ መጠየቅ ነው፤›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ሕወሓት ለሰላም ዝግጁ ከሆነ መጀመሪያ ትጥቁን እንዲፈታ የጠየቁት አቶ ታዬ፣ የመከላከያ ሠራዊት በየትኛውም አካባቢ ያለ ገደብ ተንቀሳቅሶ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ሥልጣን እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በትዊተር ገጻቸው ባሠፈሩት መልዕክት ደግሞ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ሕወሓት ሲጨንቀው በሚያወጣው የውሸት መግለጫ አይታለሉም፤›› በማለት፣ የሕወሓትን የድርድር ጥሪ አደናጋሪ መሆኑን ገልጸውታል፡፡ ለስድስት ወራት ሕወሓቶች ለሰላም ሲለመኑ መቆየታቸውን የጠቀሱት ሱሌማን (አምባሳደር)፣ ‹‹በጉልበት ተማምነው ጦርነት መጀመራቸው ገና የሁለት ሳምንታት ትዝታ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ በተመሳሳይ የሕወሓትን የድርድር ጥሪ በተመለከተ በፌስቡክ ገጻቸው ትዝብታቸውን አስነብበዋል፡፡ ‹‹ጥሪው ጥሩ ነው…›› ሲሉ የጀመሩት አቶ ዮናታን፣ ‹‹…ቀስ ብለው ደግሞ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መሣሪያ እናወርዳለን፡፡ የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎችም በትግራይ ክልል በሚያደርጉት ሥርዓት የማስከበር ሥራ እንቅፋት አንፈጥርም ለማለት እንዲያበቃቸው አያያዙን ጠበቅ ማድረግ ይበጃል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ አቶ ዮናታን ይህንን ሲሉም፣ መከላከያ በሰሞኑ ጦርነት ለሕወሓት የሰጠው የአፀፋ ጥቃት ከእስካሁኑ የበለጠ መጠንከር እንዳለበት እየጠቆሙ ይመስላል፡፡
አሁን ከጦር ሜዳ የሚሰሙ ዜናዎች የሕወሓት ኃይሎች የማይቋቋሙት ምት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ ሕወሓት አሁንም ቢሆን ይዟቸው በሚገኙ የራያ ቆቦ ግንባር አካባቢዎች በዜጎች ላይ እንግልት እያደረሰ መሆኑን ከሰሞኑ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ ይሁን እንጂ በወልቃይትና በሰቆጣ ግንባር በኩል ሕወሓት ተመቶ ማፈግፈጉ እየተነገረ ሲሆን፣ በኦፊሴላዊ የመረጃ ምንጮች ባይረጋገጥም በቁጥጥሩ ሥር የነበሩ አንዳንድ የትግራይ አካባቢዎችን ለጥምር ጦሩ አስረክቦ ማፈግፈጉም እየተነገረ ነው፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎነ ሕወሓት የድርድር ጥሪ ባደረገ በጥቂት ቀናት ልዩነት፣ ‹‹በሱዳን ድንበር በኩል ጦርነት ከፍቷል፤›› የሚሉ በይፋዊ መረጃ ምንጮች ያልተረጋገጡ ዘገባዎች ተደጋግመው በመሰማት ላይ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ‹ወትሮውንም ሕወሓት ጥሪውን ያደረገው ከልብ የሰላም ፍላጎት ኖሮት አይደለም› ለሚሉ ወገኖች፣ በሕወሓት ላይ ተጨማሪ ክስ ማቅረቢያ መነሻ እየሆናቸው ነው የሚገኘው፡፡
የምዕራባውያን አገሮችና ተቋማትን ብዙ ውዳሴ ቢያገኝም፣ የኢትዮጵያን አቋም በሚደግፉ ወገኖች በጥርጣሬ እየታየ ያለው የሕወሓት ሰሞነኛ የድርድር ጥሪ ከምን እንደ መነጨ መነሻውን እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም፡፡ አንዳንዶች በኢትዮጵያ ሰላም ለመፍጠር በጎ አጋጣሚ ቢሉትም፣ ብዙዎች ግን ጊዜ መግዣና በተንኮል የተተበተበ ነው ብለውታል፡፡ የሕወሓት የድርድር ጥሪ ለተጨማሪ ጦርነት ጊዜ መግዣ ነው የሚሉ ወገኖች፣ ቡድኑ ለአይቀሬ የሽንፈት አደጋ መጋለጡን ተከትሎ ፋታ ለማግኘት የዘየደው መሆኑን እየተናገሩ ነው፡፡ አንዳንዶች በበኩላቸው፣ ‹‹ጥሪው መንግሥትን ወጥመድ ውስጥ ለመጣል የተሸረበ ሴራ ነው፤›› ይላሉ፡፡
በቅርቡ የተፈጠሩ የዓለም ሁኔታዎችን ያጣቀሱ አንዳንድ ወገኖች በበኩላቸው፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም የምዕራባውያን ሚዲያዎች ሙሉ ትኩረት ኢትዮጵያ ላይ ማተኮሩ መቀነሱ ሕወሓትን አስፈርቶታል ይላሉ፡፡ የእንግሊዝ ንግሥት ሞትና የተራዘመ የሐዘን ሥነ ሥርዓት ከተጧጧፈው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ጋር ተደማምሮ፣ ሕወሓት ዓለም አቀፉን ትኩረትና ድጋፍ ሊያጣ በሚችልበት ወቅት ጦርነቱን መቀጠሉ አዋጪ እንደማይሆን ገምቶ የድርድር ጥሪውን አድርጓል ሲሉም ገምተዋል፡፡ ይህ በእርግጥ ለመንግሥትም የሚጠቅም አጋጣሚ እንደሆነ የሚያስረዱ አንዳንድ ወገኖች በበኩላቸው፣ ‹‹ጥምር ጦሩ ሕወሓትን ማሸነፊያ ዕድል ሊያደርገው ይችላል፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡
ይሁን እንጂ ከሚሰነዘሩ ግምቶችም በላይ በሕወሓት ላይ ዓለም አቀፍ ጫናዎች መደረጋቸው ለድርድር ጥሪው ተጨባጭ ግፊቶች ተብለው ሊነሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ በቅርቡ የሕወሓት ኃይሎች በመቀሌ የተከማቸ ነዳጅ ዘርፈዋል መባሉ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ አስነስቶባቸዋል፡፡ ጦርነቱን በአስቸኳይ አቁሙና ወደ ድርድር ፊታችሁን መልሱ ከሚለው ግፊት እኩል፣ ሕወሓቶች የወሰዱትን ነዳጅ እንዲመልሱና ለሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት የተመቸ ሁኔታ እንዲፈጥሩ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP)፣ ከተመድ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (UNOCHA)፣ ከአሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ከመሳሰሉ አካላት ያጋጠማቸው ዲፕሎማሲያዊ ጫና የድርድር ጥሪውን እንዲያደርጉ ገፋፍቷቸዋል ሲሉ የሚናገሩ አሉ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የተወሰኑ አባላት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲደረግ የሚያስችል ስብሰባ ቢጠሩም፣ ይህ ግን አለመሳካቱ ወይም ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ነው የተሰማው፡፡ በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ታዬ አፅቀ ሥላሴ (አምባሳደር) እንዳረጋገጡት፣ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጳጉሜን 3 ቀን 2014 ዓ.ም.፣ እንዲሁም ሰኞ መስከረም 2 ቀን 2015 ዓ.ም. የተጠራው የምክር ቤት ስብሰባ ተሰርዟል፡፡
ለአሥራ ሁለተኛ ጊዜ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የስብሰባ አጀንዳ ሆኖ የቆየው ኢትዮጵያ ጉዳይ፣ ‹‹አሁን በግልጽ የውይይት ጉዳይ ሊሆን አይገባም›› ተብሎ መቅረቱን ነው ታዬ (አምባሳደር) ያረጋገጡት፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ሕወሓት ለረዥም ጊዜ ሲተማመንበት የቆየው ዓለም አቀፉ፣ በተለይም የምዕራባውያን የዲፕሎማሲ ድጋፍ ቀስ በቀስ መሸርሸሩን ጠቋሚ ምልክት ተደርጎ በመቅረብ ላይ ነው፡፡
ከዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ድጋፍ ማጣት ጋር ተዳምሮ ጦርነቱን ለመቀጠል የሚያስችል ኃይል ሕወሓት እያጣ መምጣቱ ለድርድር ጥሪ ምክንያት ሆኗል የሚሉ ወገኖች፣ መንግሥት ሊሰጠው ይገባል ያሉትን ምላሽም ከወዲሁ በመተንበይ ላይ ናቸው፡፡ መንግሥት የሕወሓትን ጥሪ ተቀብሎ ወደ ድርድሩ መግባት ካለበት አስቀድሞ ትጥቅ ማስፈታት ይኖርበታል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ በሕግ ሊጠየቁ የሚገባቸውን የሕወሓት አመራሮች በሕግ ማስጠየቅ፣ እንዲሁም ሕወሓት ከትጥቅ በፀዳ ሁኔታ እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ የመንግሥት ግዴታ ነውም ይላሉ፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሕወሓት ራሱን እንደ አንድ ሉዓላዊ መንግሥት እየቆጠረ ካለበት ቁመና መውረድ እንዳለበት የሚያሳስቡት እነዚህ ወገኖች፣ ትግራይም ቢሆን እንደ አንድ የኢትዮጵያ ክልል እንጂ፣ ‹‹ዲፋክቶ አገር›› ሆኖ መቅረብ የለበትም ሲሉም ይደመጣሉ፡፡
‹‹አሁን የድርድር ጥሪው በመንግሥት ምን ምላሽ ያገኛል?›› የሚለው በጉጉት እየተጠበቀ ቢሆንም፣ መንግሥት ግን ባለፉት ጥቂት ቀናት በይፋ ያለው ነገር የለም፡፡
ድርድር ካለና እንደሚገመተው በቅርቡ የሚደረግ ከሆነ፣ ዋና የአደራዳሪነቱን ሚና እንደሚወጣ ከወዲሁ እርግጥ የሆነው የአፍሪካ ኅብረት ግን፣ ‹‹ለማደራደር ዝግጁ ነን ተደራዳሪዎችም ተዘጋጁ፤›› የሚል መግለጫ ከሰሞኑ አውጥቷል፡፡ የኅብረቱ ሰሞነኛ መግለጫ የዋና ሸምጋይነቱን ሚና ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ እንደሚቀጥሉ አረጋግጧል፡፡ የኅብረቱ መግለጫ ከዚህ ውጪ አዲስ ነገር ይዞ መጣ ከተባለ፣ ሁለቱ ተደራዳሪዎች ይሁንታ የሰጡት ታዛቢ ቡድን በድርድሩ ሊካፈል እንደሚችል መጠቆሙ ይገኝበታል፡፡