የበርካታ አገሮች የውስጥ አስተዳደር አወቃቀር ልምምድ መልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ልማት አመቺነት ላይ ያተኮረ ሲሆን የተፈጥሮ ሀብት ሥርጭት፣ የአየር ንብረት ፀባይ፣ የወንዝ ተፋሰስ፣ መልክዓ ምድር፣ የኮምፓስ አቅጣጫ፣ የባህልና የሥነ ልቦና ተጋሪነትን የመሳሰሉትን ተፈጥሯዊና ማኅበረሰባዊ ገጽታዎች በመሥፈርትነት እንደ ሁኔታው በመቀላቀል ይጠቀማል፡፡ በቋንቋ ተጋሪነት ላይ የተመሠረተ የአገር ውስጥ አስተዳደር አወቃቀር ከኢትዮጵያ በስተቀር የበዛ ብሔረሰቦች ባላቸው አገሮችም እንኳ ጭራሽ የተለመደ አይደለም፡፡ ጀምረው የነበሩ አንዳንድ አገሮችም የአስተዳደር መዋቅርን በቋንቋ ማደራጀት ለፍትሐዊ የሕዝብ አስተዳደር እንደማይበጅ ሲያውቁ አቋርጠውታል፡፡ ይልቁንም በነገድ መደራጀትን በሕግ ያገዱ አገሮች አሉ፡፡ አሁን ከገባችበት የብሔረሰበኝነት ቅርቃር በፊት አገራችን ኢትዮጵያ መልክዓ ምድርና የአስተዳደር አመቺነት መሥፈርትን የውስጥ አስተዳደር አሃዶችን ማዋቀሪያ አድርጋ ስለመጠቀሟና ሕዝቧን በፍቅር አስተሳስራ ስለመኖሯ ከታሪክ ሰነዶች መረዳት ይቻላል፡፡
ኢሕአዴግ የሕዝብን የመልካም አስተዳደር ችግር ብሶት ተጠቅሞ ደርግን በጠመንጃ አፈሙዝ ከቤተ መንግሥት አሽቀንጥሮ ከጣለ በኋላ አገር የማስተዳደር ኃላፊነት በእጁ ባስገባ ማግሥት፣ “ከፈረሱ በፊት ጋሪውን ማስቀደም” እንዲሉ ጫካ ውስጥ የነደፈውን የአገር አስተዳደር አወቃቀር ንድፍ መሬት ለማስነካት የሕገ መንግሥት ሰነድ አርቅቆ ዝርዝር ሕግ እስከሚያወጣ ድረስ ለመቆየት ትዕግሥት አልነበረውም፡፡ በጫካ ውስጥ ትልሙ መሠረት የአገሪቱን አካባቢዎች ካመሰቃቀለ በኋላ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” እንዲሉ፣ ለድርጊቱ የሕግ ማዕቀፍ ሽፋን ለመስጠት በማሰብ በጣም ዘግይቶ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በተባለ የይስሙላ ሰነድ አፅንቶታል፡፡
ይህ የሕዝብ ይሁንታ የጎደለው የአስተዳደር ክፍፍል ድርጅቱ ለዓመታት በጫካ ውስጥ ሆኖ ሲያልመው የቆየና “አገኘኋት እንደ ተመኘኋት” እንዲሉ፣ በረሃ የወጣበትን ታላቋን ትግራይ የመመሥረት ዓላማ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ተጠቅሞ አገርን ያፈረሰበት ትዕይንት ነው፡፡ በዚህ ትዕይንት ሰርጎ ገቦችንና ከአማራ አብራክ ወጣን የሚሉ ሆድ አደር ታዛቢዎችን መሣሪያ በማድረግ ከፊል የአማራ ተጎራባች ወረዳዎችን ወደ ትግራይ በማጠቃለል የታለመችውን ታላቋን ትግራይ ለመመሥረት ጥረት ያደረገ ሲሆን፣ ከፊሎቹን የአማራ ወረዳዎች ደግሞ ለአጎራባች ክልሎች በመቸርቸር “ጠጠር ሰማይ ደርሳ እስክትመለስ ድረስ ሹመት ስጠኝ” በሚመስል የደካማ ሰው ምኞት ለሁለት አሥርት ዓመታት የታገለበትን አማራን የማሳነስና የማኮሰስ ደባ በቆራጥነት ዕውን አድርጓል፡፡ ከዚህ ዕኩይ ድርጊት አንፃር ሲታይ ትሕነግ አንዱን የኢትዮጵያ ብሔረሰብ ሕዝብ በማኮሰስ ሌላውን በማኮፈስ የምትገነባ ኢትዮጵያ አለመኖሯን መገንዘብ ያቃተው ይመስላል፡፡
የብሔር/ብሔረሰበኝነት ፖለቲካ የነገድና ሃይማኖት ልዩነትን በማጦዝ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መቅሰፍት፣ ለአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች መንጠላጠያ መሰላል፣ ለእናት ጡት ነካሾች ደግሞ አቋራጭ የሕይወት ክህሎት አማራጭ በመሆን አገልግሏል፡፡ የብሔረሰበኝነት ፖለቲካ ጥቅምና ጉዳት ሲመዛዘን ፖለቲካው ለጠባብ የቡድን ዓላማ ከመዋሉና ዋጋ ካወጣችላቸው እናታቸውን ገበያ ነድተው ለመሸጥ የማያቅማሙ ኮንቱዎችን በመጠቀም፣ ለአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ህልም ስኬት ተስፋ ከመሆኑ በስተቀር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮ ዕድገት የፈየደው አንዲትም በጎ ነገር የለም፡፡ ብሔረሰበኝነት ሕዝብን በቋንቋ መሥፈርት በተዋቀሩ ክልሎች በማጎር የኢትዮጵያ ሕዝብ በነፃ እንዳይንቀሳቀስ አድርጎ የሕዝብ ወገብ ያጎበጠ፣ እግር ቀይዶ ያሰረ፣ ለዘመናት የዳበረ አብሮነትን ሸርሽሮ አንድነትን በማላላት አገርን ገፍቶ ከገደል አፋፍ ላይ ያደረሰ የባለ ቅንጭር አዕምሮዎች ምጡቅ አፍራሽ የአስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡
“ውሎ ውሎ ከቤት፣ ኑሮ ኑሮ ከሞት አይቀርም” ስለሚባል የአገር ዕድገትና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር መሰናክል የሆነው ብሔረሰበኝነት ከዚህ በላይ ርቀት ሊጓዝ እንደማይችል፣ የወቅቱ የአገራችን ፖለቲካ የግፊት መለኪያ መሣሪያ ጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ የቀድሞ ተማሪዎች ኅብረት የትግል አቅጣጫን በመቀየር ከአነሳሱ ጀምሮ የከሸፈ የጎጥ ፖለቲካ ንድፍ አውጭና ፈር ቀዳጅ የነበረው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ትሕነግ)፣ የትግራይን ሕዝብ የሕይወት ቀንዲል አጥፍቶ ኑሮውን በማጨለምና ከቀሪው የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ሕዝብ በማቆራረጥ ከ50 ዓመት የቡድን ብልፅግና የበረሃና የከተማ የኪራይ ሰብሳቢነት ትግል በኋላ ሩጫውን ጨርሷል፡፡ መጠነ ሰፊ መስዋዕትነት ቢከፈልም የትግራይ ሕዝብ ፀሐይ ሊወጣለት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም ዕፎይ ሊል ተቃርቧል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ያለንበት ወቅት አንድ ሌላ ክስተት ከሌላ ማዕዘን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ አገራችን ከብሔረሰበኝነት ደዌ ሳታገግም የዘመናት የባህልና ሥነ ልቦና ተጋሪነት የፈጠረው “ያልቀዘቀዘ እኛነት” ወይም የዘውጌነት ጥያቄ የብሔረሰበኝነት ተገዳዳሪ ሆኖ ወደፊት መጥቷል፡፡ የጠራ ዘውጌነት ብሔረሰበኝነትን ሊያስረሳ የሚችል ሕዝብን እርስ በርስ ያጋመደ የጋራ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን መልካም አሻራ የታተመበት የአብሮነት ድር፣ ከኋላቀሩ ብሔረሰበኝነት አስተሳሰብ የፀዳ ማኅበራዊ ገጽታ በመሆኑ የኢትዮጵያ አንድነት ዋልታና ማገር እንጂ ጠንቅ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን በዘውግ የመሰባሰብ ፍላጎትና ጥያቄ መነሻ ዓላማውና መዳረሻ ግቡ ገና ከጠዋቱ በግልጽ ካልታወቀ “በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንዲሉ፣ ሄዶ ሄዶ አገራዊ ችግር እንዲያስከትል ተደርጎ ስላለመቃኘቱ መተማመኛ አስቀድሞ ማግኘት ያስቸግራል፡፡
መነሻው ያልታወቀ የዘውጌነት ጥያቄ እንደ ብሔረሰበኝነት ሁሉ ለነፃነት የሚደረግ የፖለቲካ ትግል ወይም አንዱን አካባቢ ከአንዱ ነቅሎ ሌላው ላይ የመትከል የሌላ ዙር የተስፋፊነት የተደበቀ ዕቅድ ቢሆን፣ አገራችንን ከድጡ ወደ ማጡ መውሰዱ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ ከዘውግ ክልል ጥያቄ ጋር በተያያዘ በየአካባቢው አልፎ አልፎ እየተሰማ ያለው ጉምጉምታ ከዚህ ሥጋት የመነጨ ይመስላል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው ትልቁን የብሔረሰቦች ክላስተር ሸንሽኖ ትንንሽ የብሔረሰቦች ክላስተሮችን የማቋቋም ክስተትና የሥነ ልቦና ተጋሪነት ስሜትን በመቀስቀስ የሚቀርብ ምንጩ፣ በግልጽ ያልታወቀ የዘውጌነት ክልሎች ጥያቄ ጉዳይ የብሔር/ብሔረሰበኝነት ፖለቲካ ተፅዕኖ በአገርና ሕዝብ ላይ የፈጠረውን ጠባሳ ከሚያሰፋ በስተቀር አያጠበውም፡፡ ብሔር/ብሔረሰበኝነትን የሚቃወሙ ዜጎች እንዳሉ ሁሉ፣ ዘውጌነትንም የሚቃወሙ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የብሔረሰበኝነትን “ጨውና ስኳር መቃም” የለመዱ ቡድኖች “ሲጠባ ያደረ ጥጃ ሲያስሩት ይጓጉራል” እንዲሉ፣ የአባት እናታቸውን ዘውግ የእኛም ዘውግ ነው ብሎ ለመቀበል አንድም ላይዋጥላቸው ይችላል፡፡ ሁለትም መልሰው ሊገናኙበት የሚችሉበትን ያነገነገ ድልድይ ለማስጠገን ከባድ ዋጋ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ አንድ የነበረ ዘውግን በበርካታ ንዑስ ዘውጎች ለመለያየት እየተደረገ ያለው አጉል ፍጥጫ፣ የዚህ ችግር ተጨባጭ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ‹‹የብሔረሰቡ ሕዝብ ያገኘውን የዴሞክራሲ መብት አሀዳዊያን መልሰው ሊነጥቁት ነው›› የሚል ሕዝብን የማታለያ ግርግር ተሽቀዳድመው በማነሳሳት የለመዱት ጥቅም ከሚቋረጥ፣ የአገራችን የመከራ ጊዜ ቢራዘም የተሻለ ምርጫቸው አድርገው በመውሰድ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዘለዓለም በማይጠፋ የእሳት ረመጥ ውስጥ ማርመጥመጥ ትንሽ አይሰቀጥጣቸውም፡፡
የሚያስደንቀው ነገር ዘውጌነትን የሚያቀነቅኑ ቡድኖች እንደሚያቀነቅኑት ሁሉ፣ ይፈጸም ዘንድ በጥቂት ግለሰቦች ይሁንታ ብቻ የማይፈጸም ጉዳይን መቼና ምን ያህል የዘውጉን ሕዝብ አወያይተው በምን ዓይነት የሕዝብ ይሁንታ ማረጋገጫ ሥርዓት አሰባስበው እንደ ተነሱ የሚያሳይ መረጃ አለማቅረባቸው ነው፡፡ የአገራችን ሕዝብ የታመሰበት ብሔረሰበኝነት ከሕዝብ ይሁንታ እንዳልተነሳ ሁሉ፣ በአሁኑ ወቅት እየተነሳ ያለው የዘውግ ክልል ጥያቄም ከሕዝብ ይሁንታ እንዲነሳ አለመደረጉ አንድ ሳንካ ነው፡፡
የቀረበው ጥያቄ የሕዝብ ይሁንታ አለበት ለማለት የዘውጉ አጋር የሆነው ምልዓተ ሕዝብ በተደራጀ አኳኋን በጥያቄው ላይ በጋራ ተወያይቶ ካሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ መነሳት ቢቻል መልካም አቀራረብ ይሆን ነበር፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ አገራችንን ያጋጠማት ችግር ከጥቂት “አንቂዎች ነን ባዮች” ወይም “ታጋዮች ነን ባዮች” የሚነሳ ሐሳብ በአልነቃ ሕዝብ አዕምሮ ውስጥ ቀስ በቀስ በጉልበት እየተንቆረቆረ በጅምላ የሰፊው ሕዝብ ሐሳብ ተደርጎ መወሰዱ፣ ወይም ሐሳቡ በሒደት ወደ ሌላ አቅጣጫ መጠምዘዙ ነው፡፡
ከየትኛውም ጊዜ በላይ ዛሬ የአገራችንን ከችግር መውጫ መንገድ በጋራ ማሰብና ማሰላሰል የሚገባብን ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ለኢትዮጵያ የሚጠቅመው በገባንበት የብሔረሰበኝነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀን መንቦጫረቅ? ወይስ ዘውጌነትን እንደገና መሞከር? ወይስ ሌላ አማካይ መውጫ መንገድ ማበጀት? የሚል ጥያቄ አንስተን በሰፊ የውይይት ሁዳድ ማንሸራሸርና በጥናት ላይ የተመሠረተ ተጨባጭ የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ የሚገባን ወቅት ላይ የደረስን ይመስለኛል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ኢብሳ ጉተማ በ1962 ዓ.ም. በግጥም መልክ ላቀረበው “ማነው ኢትዮጵያዊ?” የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር፣ የፍትሕና እኩልነት ጥያቄ ተገቢ መልስ ማዘጋጀት ተስኖን እነሆ እሱ ያኔ እንዳለው ተንገዋልለን ቀርተናል፡፡ “ያልተማሩ ምሁራን ያቆሟትን አገር የተማሩ ማይማን” እንደ አሮጌ ቤት ገንብረው በመጣል አፈራረሷት ተብለን በታሪክ ዓምድ ላይ ለመዘከር “ትወድቃለች አትወድቅም” የሚል ትንቅንቅ ተያይዘናል፡፡
በዚያን ጊዜ የኢብሳ ጉተማ የግጥም ዳሰሳ በተማሪው ውስጥ ያቆጠቆጠውን ቅጥ ያጣ የተደበላለቀ የብሔረሰበኝነትና ዘውጌነት አስተሳሰብ ከገዥው መደብ የአገዛዝ ዘይቤ ጋር በንፅፅር ትዝብት ለማቅረብ እንጂ፣ ኢትዮጵያ አገሬ አይደለችም የሚል ብዥታ ስለአደረበት ወይም ኦሮሞነቱና ኢትዮጵዊነቱ ተምታቶበት ወይም ሁለቱ ከቄለም ወለጋነቱ ጋር ተጋጭተውበት አልነበረም፡፡ ለኢብሳ ጉተማ ጥያቄ ተገቢ መልስ ለማስገኘት መፍትሔው ኢትዮጵያን ማፍረስ ሳይሆን፣ ፍትሕና እኩልነት የተረጋገጠበት ተግባራዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲገነባ በማድረግ የአገራችንን አንድነትና የሕዝቡን አብሮነት ማስቀጠል ብቻ ነው፡፡ ከችግር ልንወጣ የምንችለው ቀድሞ የነበረ ሥርዓትን ሙሉ በሙሉ እያፈረስን በየጊዜው ከባዶ በመጀመር ሳይሆን፣ ክፍተቱን እያየን የጎደለውን እየሞላን በመሄድ ነው፡፡ የዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ ግንባታ ያለ መልካም አስተዳደርና አመቺ አስተዳደራዊ አወቃቀር ዕውን ሊሆን አይችልም፡፡
“እግር ወስዶ ወስዶ ከምን ላይ ይጥላል” እንዲሉ፣ በእኔ ዕይታ ብሔር/ብሔረሰበኝነት በስተመጨረሻ ከቆመ ግንድ ጋር አላግቶ ከመሬት የሚያንደባልል፣ ለኢትዮጵያዊነት የማይመጥን አውዳሚና ገዳይ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ስለመሆኑ ከትሕነግ የብሔር ፖለቲካ የውጤት ማጠቃለያ “ፖርትፎሊዮ” በቂ አስረጂ የተገኘ ይመስለኛል፡፡ የብሔረሰበኝነት የትግል ሥልትን ለመጨረሻ ጊዜ ሰርዘን ሌላ አማራጭ ገንቢ የትግል ሥልት መከተል የሚጠይቀን መሆኑን፣ የትሕነግ የፖለቲካ ትርፍና ኪሳራ ማመዛዘኛ የማጠቃለያ ትንተና በግልጽ ያመላክታል፡፡ ይሁን እንጂ የአሮጌዎቹ ብሔረሰበኞች አቅም ተዳክሞ እስትንፋሳቸው ሊያከትም ቢቃረብም እንኳ፣ ወራሴ ግልገል ብሔረሰበኞቹ የብሔር ትግሉን ዓርማ ተረክበው የትሕነግ ንድፍ ዘመን እንዲሻገር በዱላ ቅብብል ሩጫ ወደ ፊት ለመሸምጠጥ እንደ አዲስ ትንፋሻቸውን ለመዋጥና ሰውነታቸውን ለማሟሟቅ ዱብ ዱብ ሲሉ እታዘባቸዋለሁ፡፡
ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮነትና ለአገር አንድነት ፀርና ፅንፈኛ ያልሆነ ብሔረሰበኝነትና ዘውገኝነት በመርህ ደረጃ ክፉ ነገር ባለመሆኑ የአገር አስተዳደር መዋቅርን በዚህ መሥፈርት ማደራጀት ሊጤን የሚችል ተገቢ ጥያቄ ቢሆንም፣ ችግሩ የአፈጻጸም ብቻ ሳይሆን የገዛ አገራቸውን የማፍረስ አጀንዳ ለምንደኛ ዜጎቿ የሚሰጡ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጥረት የታከለበትና ብሔረሰበኝነት ከኢትዮጵያ ማኅበረሰባዊ ሥሪት ጋር በፍፁም መጣጣም የማይችል ገጽታ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡
እስካሁን በተገኘው ልምድ መሠረት በብሔረሰበኝነት መንፈስ በተቋቋሙ ክልሎች ብዝኃነትን ማስተናገድ አልተቻለም፡፡ የአገር ባለቤት ያደረጉንን የጋራ አያት ቅድመ አያቶቻችንን አፅም ያለምልምልን እያልን አብረን ሠርተን እየተጠቀምን፣ ያስረከቡንን አገር በተራችን በጋራ ጠብቀን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ድርሻችንን መወጣት ሲገባን በጋራ አገር ባለቤትነት አጀንዳ ላይ እንኳ መስማማት አቅቶን በጠላትነት ጎራ ለይተን እርስ በርስ በመጨራረስ ቂልነታችንን ለአገራችን ታሪካዊ ጠላቶች በግልጽ አሳይተናል፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች በሌሎች ባዕድ አገሮች ሀብት አፍርተውና ትዳር መሥርተው ልጅ ወልደው እያሳደጉ መኖር መቻላቸውን በሚገባ እያወቅን፣ በገዛ አገራቸው የእዚህ ፀጋ ባለቤት መሆን ያልቻሉ ዜጎች መኖራቸውን እየታዘብን ምንም እንዳልጎደለበት ሰው ተረጋግተን በቸልታ ተቀምጠናል፡፡
ለክልሉ ባዕድ ናቸው የተባሉ ዜጎች “መጤ” የሚል መለያ ታርጋ ተለጥፎባቸው፣ “ለነባር ብሔር/ብሔረሰብ ተወላጆች” አድልኦ በሚያደርግ የክልል ሕገ መንግሥት መብታቸው ተገድቦ በአገራቸው የመኖርና የመሥራት ዕድል ተነፍጓቸው፣ በኖሩበት አገራቸው ሲገደሉም እንኳ በሃይማኖታቸው ሥርዓተ አምልኮት በቀዬአቸው የመቀበር ዕድል አላገኙም፡፡ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ሳይሻሻል በዘውግና በክላስተር የሚደራጁ ክልሎችም ቢሆኑ የነባር ክልሎችን ፈለግ የሚከተሉ የሕዝብ ችግር ማስፋፊያ ተጨማሪ ምኅዳሮች ከመሆን አይዘሉም፡፡ ይህ ከሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁኔታው ‹‹ዝሆን አስቸገረን ብለው ለማመልከት ንጉሥ ፊት ቀርበው ተጨማሪ ዝሆን ጠይቀው እንደ ተመለሱት ጭቁን አርሶ አደሮች›› ዕድል ዓይነት ይሆናል፡፡ ይህ ከፋፋይና አድሎኛ ሕገ መንግሥት ሳይሻሻልና የብሔር/ብሔረሰብ ፖለቲከኞቻችን የአስተሳሰብ ቅኝት ሳይቀየር፣ መላው የኢትዮጵያም ሆነ የተወሰነ ክልል ሕዝብ ከብሔር/ብሔረሰበኝነትም ሆነ ከዘውጌነት የሚያገኘው ትርፍ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡
ብሔር/ብሔረሰበኝነትና ዘውጌነት የሚያስከትሉትን የአስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ የተሻለ አማራጭ መንገድ መፈለግ ጊዜው ያስገድዳል፡፡ ዜግነትን ማዕከል ያደረገ ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት የሚያስተናግድ የአገር ውስጥ አስተዳደርና አወቃቀር ሥርዓት በአስተዋይነት መፍጠር ያሻል፡፡ ባልተረጋገጠ መረጃ ላይ ተመሥርተን ብሔር/ብሔረሰበኞችና ዘውጌዎች በሚቀዱልን ቦይ በቀጥታ መፍሰስ ሳያስፈልገን የአገራችንን የዘመናት የመንግሥት አወቃቀር ልምድ፣ ወቅታዊውን ተጨባጭ ሁኔታና ለአገራችን የምንመኝላትን የወደፊት የዕድገት አቅጣጫን በጥልቀት በመገምገም ከአገራዊ የምክክር መድረክ የሚመነጭ የሕዝብ ተሳትፎን ያማከለ ዘመኑን የሚዋጅ አገራዊ የውስጥ አወቃቀር ሥርዓት ልንዘረጋ ይገባል፡፡
በዓለምም ሆነ በአፍሪካ አኅጉር በሚገኙ አገሮች ያለውን የአሠራር ልምድ በመቅሰም ለመልካም አስተዳደርና ለፈጣን የኢኮኖሚ ልማት ዕድገት የሚበጅ፣ ዘመኑን የሚዋጅ የአገር አስተዳደር አወቃቀር ሥርዓት በምክክር ማደራጀት ተገቢ ነው፡፡ ለሌሎች አገሮች የሠራ የተፈጥሮ ሀብት ሥርጭት፣ የአየር ንብረት ፀባይ፣ የወንዝ ተፋሰሶች፣ መልክዓ ምድር፣ የኮምፓስ አቅጣጫ፣ የባህልና የሥነ ልቦና ተጋሪነት የመሳሰሉ ተፈጥሯዊና ማኅበረሰባዊ ገጽታ መሥፈርቶች ለአገራችን ለኢትዮጵያ እንዴት አይስማሙም? ለአንዱ ዜጋ የበለጠ፣ ለሌላው የአነሰ ዕድል የማይሰጥ ፍትሐዊ የውስጥ አስተዳደር አወቃቀር መዘርጋት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
ብሔር/ብሔረሰበኝነትንና ዘውጌነትን መሠረት ባደረገ ክልል “ነባር” የተባለ ብሔረሰብ ወይም ዘውጉ የክልሉ መጠሪያ የሆነለት ዜጋ የክልል ባለቤት የሚሆንበት፣ ስም የለሹ ባይተዋር የሚደረግበት ኋላቀር ሥርዓት ባለቤቶች በመሆን የሉላዊነት አስተሳሰብ በሚናኝበት በእዚህ ዘመን የምንኖር ከንቱ ቆሞ ቀሮች መሆን በጣም ያስጠላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ በዕድገት ጎዳና በሰላም ወደፊት መራመድ ስለማይቻለን፣ የአገር አስተዳደር አወቃቀራችንን ከጊዜው አንፃር ማዘመን ያለብን ይመስለኛል፡፡ የአገር አንድነትና የሕዝብ አብሮነት አለርጂ ከሆነባቸው የብሔር/ብሔረሰብ ፖለቲከኞች መንደር ከሚነሳ “አሀዳዊያን ወደ ቀድሞው ሥርዓት ሊመልሱን ነው” ከሚል “የቁራ ጩኸት” በስተቀር፣ ከሕዝብ ወገን ሊነሳ የሚችል ቅሬታ እምብዛም ይኖራል ብዬ በግሌ አላስብም፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታ ከቀድሞው ሁኔታ ጋር አወዳድሮ በቂ ግንዛቤ በመጨበጥ ተሞክሮ ስላገኘ እንደ እስካሁኑ በነበረው “እኛ እናውቅልሃለን” ባዶ ስብከት በቀላሉ የሚጭበረበር አይመስልም፡፡ የኑሮ ዘይቤአቸውን የብሔር/ብሔረሰብ ፖለቲካ ኪራይ ያደረጉ ዜጎች የጋራ አገራችን የገባችበትን ውስብስብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ከግምት ውስጥ አስገብተው፣ የልቦና ውቅር ለውጥ በማድረግ የሕዝብ ወገን ለመሆን ቢዘጋጁ ረፈደ እንጂ መሸ አይባሉም፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የባዮሎጂ ዲፓርትመንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው adalhusm@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡