Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ሴት የሕግ ባለሙያዎችን ለአገራዊ ችግሮች መፍትሔነት

በ1980ዎቹ መጨረሻ የተመሠረተው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር በሦስት አሠርታት ውስጥ በዋናነነት ለሴቶች ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በመስጠት፣ አድሏዊ ሕጎችና ተግባራት እንዲስተካከሉ በመታገል ለኅብረተሰቡ አስተዋጽኦ ሲያደርግ የቆየ ድርጅት መሆኑን፣ ሕጎች እንዲሻሻሉ እንዲለወጡ በማድረግም ለአገር ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ይገልጻል፡፡ ማኅበሩን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩት ሌንሳ በየነ በማኅበሩ እንቅስቃሴ፣ በወቅታዊ የአገር ሁኔታና ቀጣይ ዕቅድን በተመለከተ ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ እስካሁን ለሴቶች ምን ያህል ነፃ የሕግ አገልግሎት ድጋፍ አድርጓል?

ሌንሳ፡- ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ከ200 ሺሕ በላይ ባለጉዳዮች የነፃ የሕግ አገልግሎት ድጋፍ አድርገናል፡፡ በተለይ በ2013 ዓ.ም. ደግሞ ከ8000 በላይ የሕግ ምክር፣ የፍርድ ቤት ጥብቅናና የተለያዩ ድጋፎች ሰጥተናል፡፡ በ2014 ከ2013 ይበልጥ የሕግ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው በርካታ ሴቶች አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች፣ ተግባራቶች በስምንቱ የክልል ቅርንጫፎች ላይ ከሴቶች መብት አኳያ ጥናቶች ሠርተናል፡፡ ከጥናቶች ባለፈ በርካታ በሕግ ባለሙያዎች ማለትም ለዓቃቤ ሕጎች፣ ለፖሊሶች፣ ለዳኞች ከሴቶች መብቶች አንፃር ሥልጠናዎችና ምክክሮችን ያደረግንበት ዓመት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ጦርነቱ ሴቶችና ሕፃናትን ለተለያዩ ችግሮች አጋልጧል፡፡ ማኅበሩ ለችግር የተጋለጡ ሴቶችና ሕፃናትን ከማገዝ አኳያ ምን ሠርቷል?

ሌንሳ፡- በአገራችን በተከሰተው ጦርነት በሥራችን ብዙ ተፅዕኖ አድርሶብናል፡፡ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭትና ጦርነት ሳቢያ ወጣ ያሉ የወንጀል ዓይነቶች ያየንበትና የተቀየረበት ጊዜ ነበር፡፡ በዚህም ሴቶች ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የነበሩበት ወቅት ነው፡፡ ማኅበሩ መልካቸውንና አካሄዳቸውን ቀይረው ብቅ ላሉ ወንጀሎች የአሠራርና የአመራር ሥራዎችን የቀየርንበት ዓመት ነው፡፡ ለምሳሌ ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ሴቶች ነፃ የሕግ ድጋፍ እንዲያገኙ ተንቀሳቃሽ የሕግ ባለሙያዎች አቋቁመናል፡፡ ውስንነት ቢኖርም ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ለሴቶች የሕግ ድጋፍ አገልግሎት መስጠትና ብዙ ተፈናቃዮች ባሉባቸው አካባቢዎች ማለትም አፋር፣ ወልዲያ፣ ቆቦ ላይ የሕግ ከለላ እንዲኖራቸው አድርገናል፡፡ የነፃ የሕግ አገልግሎት የሚያገኙበት የነፃ  ስልክ መስመር በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በትግሪኛ ቋንቋዎች በማዘጋጀት ችግሮች የሚገጥሟቸው ሴቶች አገልግሎት እንዲያገኙ ሠርተናል፡፡ ዓመቱ በአገራችን ከነበረው ሁኔታ አንፃር እኛ ከዚህ ቀደም ስንሠራቸው ከነበሩ ዘዴዎች በተጨማሪ ሌሎች አቅጣጫዎች እንድናይ አድርጎናል፡፡ በተለይ በጦርነትና በግጭት ቦታዎች የመጀመሪያ ተጋላጮች ሴቶች በመሆናቸው፣ የሥነ ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ ሙከራ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ በአጠቃላይ በ2014 ዓ.ም. ለመጡት ውስብስብ ችግሮች ምላሽ የምንሰጥበትን መንገድ እየቀረፅን ስንሠራ የቆየንበት ነው፡፡ እንደ ማኅበርና እንደ ሕግ ባለሙያዎችም ከሌሎች ማኅበራት ጋር በመሆን ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የሰላም አማራጮችን መያዝ እንደሚሻል ስናስገነዝብ ነበር፡፡ ጦርነቱ በተፋፋመበት ጊዜ ቢያንስ ለሴቶች፣ ለሕፃናትና ለአካል ጉዳተኞች እንዲሁም በይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች መንግሥት ከለላ የሚሰጥበትን መንገድ እንዲያስብ ግፊት ያደረግንበት ዓመት ነው፡፡ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች እንዲገቡ ግፊት ከማድረግ ጎን ለጎን ደግሞ፣ ለሴቶችና ሕፃናት የደኅንነት ከለላ እንዲያገኙ ግፊት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ የሕግ አገልግሎት የሚፈልጉ ሴቶች ቁጥር ከዚህ ቀደም ከነበረው ከፍተኛ ቁጥር የሆነበት ነበር፡፡ የነፃ የስልክ መስመር ስለዘረጋን ከተለያዩ አካባቢዎችም በርካታ ጥሪዎች ያስተናገድንበት ዓመት ነው፡፡ ባለጉዳዮቻችንን በይበልጥ ተደራሽ እንዲሆኑ ሠርተናል፡፡

ሪፖርተር፡- በተቋምና በተለያዩ ቦታዎች የነበረው የሴቶች ተሳትፎን እንዴት ታዩታላችሁ?

ሌንሳ፡- ባለፉት ዓመታት የሴቶችን ተሳትፎ በተለያዩ መንገድ ከማሳደግ አንፃር ጅማሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ነገር ግን በ2014 ዓ.ም. ግን እንቅስቃሴው ወደ ኋላ የተጎተተበት መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ በአንዳንድ ቦታ ምርጫዎች ሲደረጉ ሴቶችን ያላካተቱና ከነጭራሹም ያልገቡበትንም ያየንበት ነው፡፡ ለምሳሌ በሕወሓትና በፌደራል መንግሥት በኩል የአደራዳሪ ቡድን ሲቋቋም፣ አባላቱ በጠቅላላ ወንዶች ናቸው፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በነበረው ጦርነት ከወንዶች ይልቅ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የጉዳዩ ባለቤቶች ወደ ጠረጴዛ ማምጣትና ማሳተፍ ላይ በጣም አግላይ ውሳኔዎች ሲሰጥ የነበረበት ዓመት ነው፡፡ በእኛ ሙያ የነበረው ሌላኛው ደግሞ በኢትዮጵያ ጠበቆች ማኅበር የተስተዋለው ችግር ይታወሳል፡፡ ሕጋዊ የባለሙያ ማኅበር በመሆኑ የሴቶች ተሳትፎ እንዲጨምር ግፊት አድርገናል፡፡ በሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ሒደት ላይ የሴት የሕግ ባለሙያዎች እንዲካተቱና ሚዛኑን የጠበቀ እንዲሆን አድርገናል፡፡ ነገር ግን ዓመት በማኅበሩ የቦርዱ ምርጫ ላይ ሰባት ወንዶች የተመረጡበትና እንደ ማኅበርም ቅሬታችንን ለሁሉም አካላት ያቀረብንበትም ዓመት ነበር፡፡ ምክንያቱም በቦርድ ምርጫው ሴቶችን ያገለለና ልባችን የሰበረ ውሳኔ በመሆኑ ነው፡፡ ብዙ የሥራ ልምድና ብቃት ያላቸው የሕግ ባለሙያ ሴቶች እያሉ ይህንን መንፈግ አልነበረብንም፡፡ በአጠቃላይ እንደ ሕግ ባለሙያዎችም፣ በሙያችን በአገራችን ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጉልህ አስተዋጽኦ ስናደርግ የቆየንበትና የተፈጠሩ ችግሮችም እንደ ባለሙያ ተፅዕኖ ደርሶብናል፡፡ ማኅበራችን ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠራ ድርጅት እንደመሆኑ ትልቅ ጭንቀት ውስጥ ነበርን፡፡ አስቸኳይ መፍትሔ ለማምጣት የሚከብዱ ችግሮች ተወጥተናል፡፡ ለእያንዳንዱ ድምፅና የመፍትሔ አካል ለመሆን በጭንቀት ያሳለፍንበት ዓመት ነው፡፡ ማኅበሩና ለባለሙያዎቹ ፈታኝ ጊዜያትን አሳልፈናል፡፡ በአጠቃላይ በአገራችን የሴቶች እንባና ለቅሶና ዘግናኝ ጉዳዮችን የተመለከትንበት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በአዲሱ ዓመት በ2015 ዓ.ም. ማኅበራችሁ የነበሩትን ችግሮች ለመፍታት ምን አስቧል? እንደ ባለሙያ እንደ ሴትም አሁንም ያላባራው ጦርነትና ችግር ውስጥ የሚኖሩ ሴቶችን ለማገዝ ምን አቅዳችኋል? የአዲስ ዓመት ምኞታችሁ ቢገልጹልን?

ሌንሳ፡- የነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በምንችለው የቴክኖሎጂ አማራጮች ለመድረስ የምንሠራበትና ከክልሎች አልፎም በወረዳዎች በተቀናጀ ሁኔታ ለመሥራት አስበናል፡፡ ስለ ብሔራዊ ምክክር ከፌደራል እስከ ወረዳ ድረስ የሚገኙ ሴት የሕግ ባለሙያዎችን ግንዛቤ እንዲኖራቸው እየሠራን ነው፡፡ መሠረታዊ የሕግ አገልግሎት ዕውቀትና የአቅም ግንባታ ሥልጠና እስከ ታች ድረስ የመሥራት ትልም አንግበናል፡፡ የአገራችን የሴቶች ፖሊሲ፣ የፆታዊ ጥቃት ፖሊሲዎች የሚስተካከሉበት ዓመት እንዲሆን ተግተን እንሠራለን፡፡ ወደ ኋላ እየጎተቱን ያሉ የተለያዩ አሠራሮች በመታገል፣ ለመቀነስና ለማስቀረት ሙሉ አቅማችንን እንጠቀማለን፡፡ በአገራችን በተከሰተው ጦርነትና የተለያዩ ግጭቶች በበርካታ ሴቶች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመነጋገር ጥረት አድርገናል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶችን ለማገዝ ሙከራ ልናደርግ ብንፈልግም ጦርነቱ መልሶ አገርሽቷል፡፡ በአማራና በአፋር ክልሎችም ጉዳት የደረሰባቸው፣ የተፈናቀሉ ወገኖችን የሕግ ድጋፍ አገልግሎታችን በ2015 ዓ.ም. አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ሴት የሕግ ባለሙያዎች ለአገራቸው መፍትሔ እንዲሆኑ በርካታ ውይይቶችን በማድረግ ተሳታፊ እንዲሆኑ የምንጥርበት ነው፡፡ ችግር የደረሰባቸው ሴቶች በምን ዓይነት መንገድ ፍትሕ እንደሚያገኙ ወይም ምን ዓይነት ምላሽ ያገኛሉ የሚለው ላይ እስካሁን ውይይት ላይ ነን፡፡ ጥቃት ፈጻሚዎቹ እስካሁን አይታወቁም፡፡ ጥቃቱ ለደረሰባቸው ሴቶች ምላሾች እንዲሰጥ መንግሥት ላይ ጫናችንን የምንቀጥል ይሆናል፡፡ እንደ ግለሰብ ሴቶች ላይ ጥቃት የማልሰማበት ዓመት እንዲሆን የፌደራል መንግሥትና ሕወሓት በመወያየትና በመነጋገር ለሚመጣው ትውልድ ደኅንነቷ የተጠበቀና ተስፋ ያላት አገር እንድትሆን፣ ልባዊ ምኞቴ ነው፡፡ በሥራዎቻችን ደግሞ ከስሜታዊነት ተላቀን ውይይቶቻችን የሚያቀራርቡ፣ በሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የምንፀየፍበት፣ ዓመት እንዲሆንልን እንመኛለን፡፡   

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...