Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየአዲስ አበባ ስታዲየም ዕድሳት ተጨማሪ በጀት ያስፈልገዋል ተባለ

የአዲስ አበባ ስታዲየም ዕድሳት ተጨማሪ በጀት ያስፈልገዋል ተባለ

ቀን:

  • ዕድሳቱ በበጀት ዕጥረት ተቋርጧል ቢባልም ሚኒስቴሩ አስተባብሏል

ዕድሜ ጠገቡ የአዲስ አበባ ስታዲየም በእርጅና ምክንያት አኅጉር አቀፍ ውድድሮች የማስተናገድ አቅም በማጣቱ ከዓመታት በላይ ጨዋታ ሳያስተናግድ ቆይቷል፡፡

የቀድሞ ስፖርት ኮሚሽንና ፍሬንድስ ኢንጂነሪንግ፣ ሰኔ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ስታዲየሙን ለማደስ ስምምነት ተፈራርመው ሥራውን የጀመሩ ሲሆን፣ በተቀመጠለት ቀነ ገድብ ግን መድረስ አልቻለም፡፡

ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ይጠናቀቃል የተባለለት የስታዲየሙ ዕድሳት 39 ሚሊዮን ብር ተበጅቶለት ቢጀምርም፣ የተወሰኑ ዕድሳቶች ብቻ እንደተደረጉለት ነው የተገለጸው፡፡ በምዕራፍ አንድ ዕድሳት የሳር ተከላ፣ የመፀዳጃ ቤትና የመልበሻ ክፍሎች ዕድሳት እንደተደረገላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ቀሪ ዕድሳቶች ግን ተጨማሪ በጀት እየተጠባበቁ እንደሆነና በሁለተኛ ምዕራፍ ላይ ዕድሳታቸው ለማከናወን መታቀዱን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መስፍን ቸርነት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ደኤታው አስተያየት ከሆነ፣ የመጀመሪያ ምዕራፍ ዕድሳት ቀድሞ በተያዘው በጀት መከናወኑንና ዘንድሮም የተያዘው ተጨማሪ በጀት ሲለቀቅ ሁለተኛው ምዕራፍ ለመጀመር ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡

ለሁለተኛ ምዕራፍ የተያዘው የገንዘብ መጠን ከመግለጽ የተቆጠቡት ሚኒስትሩ፣ የትሪቡን ጣሪያ፣ አጥር፣ የመሮጫ መም፣ የወንበር ገጠማና የእግረኛ መንገድ ዕድሳት ለማድረግ መታቀዱን አክለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በአፍሪካ ውስጥ ያሉትን የስታዲየሞች የሳር ዝርያ ዓይነት አጢኖ የሳር ተከላው እንደተከናወነና በየዕለቱ እንክብካቤ እየተደረገለት እንደሚገኝ አቶ መስፍን አስታውሰዋል፡፡

‹‹በቅርቡ የተጀመሩትን ዕድሳቶች አጠናቀን፣ ፊፋ እንዲሁም ካፍ የሚፈልጉት ዋነኛ መሥፈርቶች አሟልተን፣ ስታዲየሙን ለውድድር ዝግጁ እናደርጋለን፤›› በማለት አቶ መስፍን ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በአውሮፓ አገሮች ያሉትን የስታዲየም ደረጃዎች ላይ ለማድረስ ከፍተኛ በጀት እንደሚያስፈልግ የሚገልጹት ሚኒስትር ደኤታው፣ በአፍሪካ ከሚገኙት የስታዲየሞች ሳር ጋር ተመሳሳይነት ያለውን ዘር መጠቀማቸውን አብራርተዋል፡፡

ምንም እንኳን ሚኒስቴሩ ዕድሳቱ መቀጠሉን ቢያስረዳም፣ በተቋራጩና በሚኒስቴሩ መካከል የነበረው ስምምነት በበጀት ዕጥረት ሥራ መቆሙ እየተነገረ ይገኛል፡፡ በዚህም ሁለቱ ተቋማት ተስማምተው የነበረውን በጀት ሚኒስቴሩ በወቅቱ መልቀቅ ባለመቻሉ ዕድሳቱ ከተቋረጠ ሁለት ሳምንት መሻገሩ ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የትሪቡን፣ የሚዲያ ክፍሎች፣ ቪአይፒ ክፍሎችና ሌሎች በስታዲየሙ ዙሪያ ያሉ ዕድሳቶች መቆማቸው ተነግሯል፡፡

ሆኖም በሚኒስትር ዴኤታው አስተያየት ከሆነ፣ የስታዲየም ዕድሳት እንዳልተቋረጠና ይልቁንም ዕድሳቱ በተያዘለት መርሐ ግብር እየተከናወነ መሆኑን አስረድተው፣ ለዘንድሮ የተያዘለት በጀት ሲለቀቅ ወደ ሁለተኛው የዕድሳት ሥራ እንደሚገባ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የካፍን መሥፈርት ያሟላ ስታዲየም ማጣቷን ተከትሎ፣ ብሔራዊ ቡድኑ የማጣሪያ ጨዋታውን በተለያዩ አገሮች ስታዲየም ኪራይ እየከፈለ መጫወት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ለቀሪ የብሔራዊ ቡድኑ የማጣሪያ ጨዋታ ግንባታና ዕድሳት ላይ ያሉ ስታዲየሞች በወቅቱ የማይደርሱ ከሆነ፣ ብሔራዊ ቡድኑ በሰው አገር መንከራተቱ መቀጠሉ የማይቀር ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...