የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ኤሊት ኢንስትራክተርና የባህር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ ዋና አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ፣ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) የቴክኒክ ባለሙያ ሆነው ተሾሙ፡፡ ሹመቱ እንደ ሁኔታው የሚታደስ የሁለት ዓመታት ኮንትራት እንደሆነ ተነግሯል፡፡
211 አገሮችን በአባልነት የያዘው ፊፋ፣ በዚህ ዘርፍ ሙያተኞችን ከመምረጡ በፊት ባለሙያው ከታዳጊ ወጣቶች ጀምሮ ለእግር ኳሱ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከግምት ገብቶ ሲሆን፣ አሠልጣኝ አብርሃም በኤሊት ኢንስትራክተርነት፣ በአፍሪካ ዋንጫና በመሰል ትልልቅ አኅጉራዊ መድረኮች በተለይም በቴክኒክ ጥናት ቡድን አባልነት የሠሯቸው ሥራዎች ለቦታው እንዳሳጫቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
ኢንስትራክተሩ በእግር ኳሱ ለቴክኒክ ዳይሬክተሮች፣ ለኢንስትራክተሮችና ከዘርፉ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሥልጠናዎችን ማዘጋጀት፣ ለአባል አገሮችና አኅጉራዊ እግር ኳስ ልማት ላይ የቴክኒክ ማማከርና የተለያዩ የእግር ኳስ ልማት ፕሮግራሞችን መከታተል እንዲሁም ለአዲሱ የፊፋ ልማት ፕሮግራም አስፈላጊ ሰነዶችን ማዘጋጀት፣ በዓለም አቀፉ ተቋም የሚኖራቸው የሥራ ኃላፊነት እንደሆነም ተነግሯል፡፡
ኢንስትራክተሩ በአሁኑ ወቅት የባህር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ ዋና አሠልጣኝ ሆነው በማገልገል ላይ ሲሆኑ፣ የሁለት ዓመታት ኮንትራት መፈራረማቸው ይታወቃል፡፡
አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱና የባህር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ በኮንትራቱ ዙሪያ በቀጣይ የሚኖራቸውን የሥራ ግንኙነት በተመለከተ ምን አስተያየት እንዳላቸው ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
ይሁንና ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በፊፋ ያገኙት ሹመት፣ ለኢትዮጵያ እግር ኳስም ሆነ ለባለሙያዎች በአርዓያቱ የሚጠቀስ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ የሚናገሩ አልጠፉም፡፡