- ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ወንጀልን ለመሸፋፈን የማስጮህ ተግባር ነው ብሏል
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከውጭ አገሮች ሥራ ስምሪት ጋር በተገናኘ የውል ማፅደቅ አገልግሎት ለሳምንት ያህል በተቆራረጠ መንገድ በመስጠቱ፣ ሥራቸውን እንዳስተጓጎለው የውጭ አገር ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ገለጹ፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነት የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አገልግሎትን ለማዘመን የሚያደርገው ጥረትና የሥራ ሒደት ቢደነቅም፣ ነገር ግን ለአንድ ሳምንት ያህል የውል ማፅደቅ አገልግሎት እንደማይሰጥ እየታወቀ፣ ለተገልጋዮች በድንገት መገለጹ ኪሳራ እንዲሁም በተቀባይ አገሮች ካሉ ወኪሎችና ደንበኞቻቸው ቅሬታና አለመተማመን መፍጠሩን ኤጀንሲዎቹ ተናግረዋል፡፡
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አጠቃላይ የሠራተኞች መድረክ ከነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. እስከ ጳጉሜን 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በመካሄዱ ምክንያት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል ይሰጥ የነበረውን የውጭ አገሮች ሠራተኞች የውል ማፅደቅ አገልግሎት ሳያገኙ መቅረታቸውን የገለጹት ኤጀንሲዎቹ፣ ከመስከረም 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮም በቀጠለው አገልግሎት የሚስተናገዱ የውል ማፅደቅ አገልግሎቶች በጣም ውስን በመሆናቸው፣ በሥራቸው ላይ ጥላ ከማጥላቱ ባሻገር ከተቀባይ አገሮች ወኪሎች ጋር ቅሬታ መፍጠሩንና ሥራቸውን እንዳበላሸው አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰግድ ጌታቸው ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የቀረበው ቅሬታ ዘርፉ ላይ ያሉ አስቸጋሪ ሰዎች የሚያስጮሁት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የመዋቅርና የአደረጃጀት ሥራውን አከናውኖ ቀደም ሲል ስምንት የነበሩትን ተቋማት ወደ አንድ በማምጣት፣ የሠራተኛ ምደባና ሥልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አቶ አሰግድ ገልጸው፣ ባለፈው ሳምንትም (ከነሐሴ 30 እስከ ጳጉሜን 4 ቀን 2014 ዓ.ም.) የሆነው የሠራተኞች ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡ ያም ሆኖ በተባሉት ቀናት አገልግሎት እንዳይቆም መደረጉን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በየቀኑ ከ100 እስከ 1,000 የሚደርሱ ዜጎች ከአገር ውጪ ይሄዱ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
‹‹በተባለው ሳምንት የቆመ አገልግሎት አልነበረም›› ያሉት አቶ አሰግድ፣ ነገር ግን በመጨናነቁ ምክንያት የተጠራቀሙ ጉዳዮች እንደነበሩ ገልጸው፣ በመጠባበቅ ላይ ያሉ ሰዎች ጉዳይ በዚህ ሳምንት ውስጥ የሚያልቅ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ቅሬታውን የሚያቀርቡ አካላት ከወንጀል ጋር በተያያዘ በተለይም ከሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም ወደ ውጪ ሰው በመላክ ለአገር ሊውል የሚገባውን የውጪ ምንዛሪ ለመሸፋፈን ሲያደርጓቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች የተደረሰባቸው አካላት መሆናቸውን ሚኒስቴር ዴኤታው ገልጸው፣ በተለይም ከውስጥ ሠራተኞች ጋር በመመሳጠር ሲያደርጓቸው የነበሩ ሕገወጥ ሥራዎች ሲቆሙ፣ ያንን ለመሸፋፈንና ጉዳዩን የማስጮህ ሥራ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አዲስ ሲስተም ለመተግበር በዝግጅት ላይ መሆኑንና ይህም ንክኪ ሳይኖር ባለጉዳዮች ሰነድ ብቻ አስገብተው የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች በኦንላይን ብቻ ሒደቱን እንዲያከናውኑ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ይህ እንቅስቃሴም በሕገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩትን አካላት ለማስደሰትና የነበረውን ሒደት ወደኋላ ለመመለስ የሚደረግ ጥረት መሆኑን ሚኒስቴር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
ከውል ማፅደቅ ጋር ተያይዞ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በየቀኑ ሲሰጥ የነበረው አገልግሎት ተመሳሳይ ቁጥጥር የሚከናወንበት አይደለም የተባለ ሲሆን፣ ኤጀንሲዎቹ እንደሚያመጡት ዶክሜንትና የሥራ ትዕዛዝ በቀን ውስጥ ከ100 እስከ 1,500 ሰዎች የሚስተናገድበት አጋጣሚ መኖሩ ተገልጿል፡፡
አንዳንድ ኤጀንሲዎች ከዚህ ቀደም ተልካሻ ምክንያት በማቅረብ ለአገሪቱ ሊገባ የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ ሲያስቀሩ ቆይተዋል ያሉት አቶ አሰግድ፣ ሆኖም ቁጥጥሩ ከተጠናከረበት ጊዜ አንስቶ ለአብነትም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ኤጀንሲዎቹ ከሚያገኙት ኮሚሽን 68 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ተናግረዋል፡፡ ይህ መሆኑ ኤጀንሲዎቹን ያስደሰተ እንዳልሆነ ሚኒስቴር ዴኤታው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ከኤጀንሲዎቹ ጋር ተመሳጥረው ሲሠሩ የቆዩ የመስሪያ ቤቱን ሠራተኞች ከቦታቸው ከማንሳት በተጨማሪ 17 ሠራተኞች ከሥራ መታገዳቸውን የተናገሩት ሚኒስቴር ዴኤታው፣ እነዚህን የታገዱን ሠራተኞች በማስተባበር ቅሬታ ያሉትን ጉዳይ እያስጮሁ ይገኛሉ ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሕገወጥ ሥራ ላይ የተገኙ ኤጀንሲዎችን እስከማገድ የሚደርስ ዕርምጃ እየተወሰደባቸው ነው ያሉት አቶ አሰግድ፣ በተለይም የፎርጂድ ሰነዶች የሚያቀርቡት ከዚህ ውስጥ ተጠቃሾቹ መሆኑን ገልጸው፣ ለአገር ማስገባት የሚገባቸውን የውጭ ምንዛሪ ባላስገቡ 37 ኤጀንሲዎች ላይ ኦዲት ተደርጎ ዕግድ መተላለፉን አስረድተዋል፡፡ ሆኖም የሚጠበቅባቸውን ከተወጡ ዕግዱ ጊዜያዊ ስለሆነ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው የሚመለሱበት የጊዜ ገደብ መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ለአንድ ሳምንት በተከናወነው የሠራተኞች የሥልጠና ቀናት ውስጥ የተጠራቀሙ ሰነዶችን ጨምሮ ከሥር ከሥር የመጡ ጉዳዮችን ለማስተናገድ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ ተብሏል፡፡