የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ ይዞታን ለማረጋገጥ በዕቅድ ይዟቸው ከነበሩ 22,339 ይዞታዎች ውስጥ 11,938 ይዞታዎች በካዳስተር ሥርዓት ለመመዝገብ ብቁ እንዳልሆኑ አስታወቀ፡፡
የከተማዋ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ፣ የካዳስተር ምዝገባና ዕወጃ ባደረገበት ከሚያዚያ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ባሉት አምስት ወራት ውስጥ፣ የይዞታ ማረጋገጫ ሠርተፍኬት ያዘጋጀው ለ10,401 ይዞታዎች ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ይኼም የዕቅዱ 46.5 በመቶ ነው፡፡
ኤጀንሲው የካዳስተር ምዝገባ ሥርዓቱን የሚያከናውነው ስለይዞታው ያሉትን ሰነዶች፣ ከአዲስ አበባ መሬት ልማት አስተዳደር ቢሮና ከባለሀብቱ በመውሰድ፣ ይኼንንም በመሬት ላይ ልኬት በማረጋገጥ መሆኑን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ገብሬ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ የሰነድና የመስክ የማመሳከር ሥራዎች ልዩነት የሌለባቸው ይዞታዎች፣ የይዞታ ማረጋገጫ ሠርተፍኬት እንደሚያገኙም አስረድተዋል፡፡
የማመሳከር ሥራው በሚሠራበት ጊዜ ልዩነት ሲፈጠር የሚታለፍበት የማቻቻል ገደብ “tolerance limit” እንዳለ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ ገደብ ያለፉ ይዞታዎች ‹‹መብት እንዲፈጠርላቸው›› ወደ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ እንደሚመለሱ ተናግረዋል፡፡
ከቀናት በፊት በተጠናቀቀው የካዳስተር ምዝገባና ዕወጃ ላይ፣ ምዝገባ ካልተካሄደባቸው 11,938 ይዞታዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ በሰነድ ላይ ካላቸው ስፋት እንደሚበልጡ አቶ ክፍሌ ተናግረዋል፡፡ የይዞታው ማነስ፣ መብት አለመፈጠርና የሰነድ ርክክብ መዘግየትም ይዞታዎቹ ብቁ ላለመሆናቸው በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡
አቶ ክፍሌ፣ ‹‹የእኛ ኤጀንሲ በይዞታዎቹ ላይ መብት ስለማይፈጥር፣ በይዞታው ላይ ልዩነት አግኝተናል፣ ብቁ እንዲሆን አስተካክሉና ላኩልን ብለን ሰነዱን ወደ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ እንመልሰዋለን፤›› ሲሉ ሒደቱን አስረድተዋል፡፡
‹‹በከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ አዋጅ መሠረት፣ ፋይሉ በተመለሰ በ15 ቀናት ውስጥ ምላሽ መስጠት አለባቸው፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ምላሽ አሰጣጡ ላይ ግን ‹‹መዘግየት›› እንዳለ ተናግረዋል፡፡ በተቋማቱ መካከል ያለው ቅንጅት የተሳለጠ ባለመሆኑ ምክንያትም፣ የኤጀንሲው ዕቅድ አፈጻጸም በሚፈለገው ልክ እንዳልሄደ አስረድተዋል፡፡
ቢሮው እነዚህን ይዞታዎች ብቁ ሲያደርግ የማረጋገጥና የመመዝገብ ሥራው እንደሚሠራም አክለዋል፡፡
ለአምስተኛ ጊዜ ከለሚ ኩራ ውጪ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች በተመረጡ 25 ቀጣናዎች ውስጥ በተካሄደው የካዳስተር ምዝገባ፣ አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ ከሆኑ ክፍላተ ከተሞች ውስጥ ልደታ፣ ኮልፌና የካ እንደሚጠቀሱ አቶ ክፍሌ ገልጸዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በሚቀጥሉት ቀናት በዚህ ዙር ለይዞታ ማረጋገጥ ብቁ ሆነው ሠርተፍኬት የተዘጋጀላቸውን 10,401 ይዞታዎች በሕጋዊ ካዳስተር ሥርዓት የመመዝገብና ዲጂታል ሠርተፍኬት የማዘጋጀት ሥራ ይሠራል፡፡
ዲጂታል ሠርተፊኬቱ የይዞታዎቹን የጂፒኤስ መገኛ፣ የይዞታውን ባለቤት፣ የቦታውን ስፋትና ሌሎች መረጃዎች የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አቶ ክፍሌ እንደሚያስረዱት ይኼንን ሠርቲፍኬት ያገኙ ይዞታዎች ከዚህ በኋላ ሁሉንም መሬት ነክ አገልግሎቶች የሚያገኙት ከተማዋ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹ይኼንን ሠርተፍኬት ሲያገኙ ይዞታው ላይ መብት ተፈጥሮ ተጠናቋል ማለት ነው፣ ስለዚህ አገልግሎት ሲፈልጉ መብት ፈጣሪ ወደ ሆነው መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የሚሄዱበት ምክንያት የለም፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡
በጊዜ ሒደት በከተማዋ በሚገኙ ሁሉም ይዞታዎች የካዳስተር ምዝገባ ተደርጎ ሲጠናቀቅ፣ ይዞታዎች በሙሉ መብት ስለሚፈጠርላቸው የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ፈርሶ አገልግሎቶች በሙሉ ወደ ኤጀንሲው እንደሚዞር ተናግረዋል፡፡
እስካሁን አምስት ጊዜ የካዳስተር ምዝገባ ያከናወነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ2008 ዓ.ም. እስከ 2011 ዓ.ም. ከ118 ሺሕ በላይ የመሬት ይዞታዎችንና ከ161 ሺሕ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ይዞታን አረጋግጧል፡፡
በአጠቃላይ በከተማዋ ውስጥ ከ600 ሺሕ በላይ ይዞታዎች ተረጋግጠው መመዝገብ ያለባቸው ሲሆን እስካሁን የተፈጸመው ከ25 በመቶ በታች ነው፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት 160 ሺሕ ይዞታዎችን አረጋግጦ ለመመዝገብ ዕቅድ መያዙን የተናገሩት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ፣ ለቀጣዩ ምዝገባ የሚደረገው ቅድመ ዝግጅት ሲጠናቀቅ ዕወጃ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡