በአዲሱ ዓመት የመላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምና ደኅንነት የሚያስጠብቁ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መተኮር ይኖርበታል፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በወታደራዊና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ የሕዝባችንን ፍላጎት ማዕከል ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ሕዝብና መንግሥት ሲግባቡ ሁሉም ነገሮች በቅንነትና በመልካም መንፈስ ይከናወናሉ፡፡ በሕዝብና በመንግሥት መካከል መቃቃር የሚፈጠረው የሚደረስባቸው ውሳኔዎችም ሆኑ የሚከናወኑ ተግባራት፣ ከሕዝብ ፍላጎት ያፈነገጡና ዓላማቸውም አጥፊ ሲሆን ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ኢትዮጵያ እውነተኛ ሰላም ያስፈልጋታል፡፡ ሰላም በእውነተኛና በትክክለኛ መንገድ እንዲገኝ ከተፈለገ ከፖለቲከኞች በላይ የሕዝቡ ፍላጎት ነው መደመጥ ያለበት፡፡ ሰላምን በማጭበርበር ወይም በድብቅ ዓላማ ማጨናገፍ አይገባም፡፡ ጠንከር ሲባል ጉልበተኝነት ደከም ሲባል ሰላም ፈላጊ መስሎ መታየት የሴረኞች ማዘናጊያ ሲሆን፣ እውነተኛው ሰላም የሚገኘው ግን ከሕዝብ ጋር በሚደረግ ሁለንተናዊ ምክክር ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ተዋንያን መገንዘብ ያለባቸው፣ የሴራ ፖለቲካ የሕዝብን ሥቃይ ከማራዘም በዘለለ ለሰላም ፋይዳ እንደሌለው ነው፡፡ ለአገር ልማትና ዕድገት ሲባል ለእውነተኛ ሰላም ዕድል ሊሰጥ ይገባል፡፡ የሴራ ፖለቲካ ይብቃ፡፡
በአዲሱ ዓመት ሰላም ሰፍኖ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ከአሉታዊ ነገሮች መራቅ ያስፈልጋል፡፡ አሉታዊ ነገሮች ተስፋን የሚያጨልሙና ወደ ግጭት የሚያመሩ ስለሆነ፣ በተቻለ መጠን አዎንታዊ ነገሮች ላይ በማተኮር ለመግባባት መሞከር መልካም ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሕዝቡን ራዕይና ተስፋ ከሚያጨልሙ አሉታዊ ነገሮች መካከል አይሆንም፣ አይቻልም፣ አያስኬድም፣ አያዋጣምና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ጨለምተኛና ተስፋ አስቆራጭ ቃላት ከመጠን በላይ ከመለመዳቸው የተነሳ ለጭቅጭቅና ለፀብ ምክንያት ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ በንግግር ሊፈቱ የሚችሉ ልዩነቶችን ወደ መሠረታዊ ቅራኔ በመለወጥ አውዳሚ ግጭቶች ውስጥ ሲከቱ ተስተውለዋል፡፡ ብዙዎች ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች የተዳረጉት አሉታዊ ነገሮች በመብዛታቸውና ለሰላም ጠንቅ በመሆናቸው ነው፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙ በአገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች ከመጠቀም ይልቅ ወደ ባዕዳን ማንጋጠጥ በመለመዱ፣ ኢትዮጵያ ሌላው ቢቀር ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለሦስት ዙሮች ከባድ ጦርነቶች ተጋልጣለች፡፡ እንደሚታወቀው ባዕዳን ደግሞ ጥቅማቸውን ብቻ አስልተው ጣልቃ መግባት ይፈልጋሉ፡፡ ሴረኞች ደግሞ ይህንን ዓላማ ለማሳካት ሰላም ያደፈርሳሉ፡፡
አሁንም ቢሆን ለዘመናት አብሮ በኖረው ሕዝባችን ችግር አፈታት ዘዴዎች ጭምር በመጠቀም፣ ኢትዮጵያን ከገባችበት አዘቅት ውስጥ ጎትቶ ማውጣት የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው፡፡ ከእንግዲህ ሰላም ፈላጊ ሆኖ ማጭበርበርም ሆነ ጉልበት አለኝ ብሎ መመካት ዋጋ እንደሌለው በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም አግኝቶ ለዘመናት ከሚኖርበት የድህነት አዘቅት ውስጥ መውጣት ይኖርበታል፡፡ በአራቱም ማዕዘናት ውስጥ የሚኖረው ሕዝባችን በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትሐዊ መንገድ የአገሩ ባለቤት መሆን አለበት፡፡ የመንግሥት ሹማምንትም ሆኑ ፖለቲከኞች መገንዘብ ያለባቸው፣ የሥልጣኑ ሉዓላዊ ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ እንደሆነ ነው፡፡ ከእንግዲህ በኋላ በሕዝብ ስም መቀለድ ማብቃት አለበት፡፡ በነፃ አውጭነት ስም ፀረ ሕዝብ ድርጊቶችን መፈጸም ይበቃል፡፡ ሕዝብን አግቶ ሰብዓዊ ጋሻ ማድረግ የለየለት ወንጀል ነው፡፡ የጥቂት ግለሰቦችን ወይም ስብስቦችን ዓላማ ለማስፈጸም ሲባል በሕዝብ ስም ማጭበርበር ነውር ነው፡፡ ሕዝብን ማማለል የሚቻለው ለመብቱ፣ ለነፃነቱ፣ ለኑሮውና ለአገሩ ህልውና የሚበጅ ፕሮግራም ይዞ በመቅረብ እንጂ፣ የጥቂቶችን የሥልጣን ጥም ማርኪያ ሴረኝነት እንዳልሆነ ይታወቅ፡፡
ኢትዮጵያውያን የሰላም ዋጋው ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ በተለያዩ መንገዶች ከሚያንፀባርቋቸው መልዕክቶች መረዳት ይቻላል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች የተካሄዱ ጦርነቶች ያደረሱት ዕልቂትና ውድመት ዘግናኝ ከመሆናቸው የተነሳ የሰላምን ዋጋ ያሳያሉ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በንፁኃን ላይ በተፈጸሙ የጅምላ ጭፍጨፋዎች የደረሱ መሳቀቆች፣ የሰላም ዕጦት ለአገር ያለውን አጥፊነት ከመጠን በላይ የሚያስረዱ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው በሰላም ስም ማጭበርበርም ሆነ ማወናበድ አያስፈልግም የሚባለው ነው፡፡ ለሕዝብ ፋይዳ የሌለው ትግልም ሆነ መወራጨት የመጨረሻ ግቡ ለጥቂቶች ፍላጎት በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላ ለሕዝብ እናስባለን የምትሉ በሙሉ ለጠረጴዛ ዙሪያ ንግግርና ድርድር ራሳችሁን አስገዙ፡፡ ንግግርንና ድርድርን ለጊዜ መግዣ ወይም ራስን ለማዘጋጃ ለመጠቀም መሞከር አሳፋሪ ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ላይ ሆኖ ሕዝባችን ስለሰላም የተማፀነው የኢትዮጵያ ህልውና ስለሚያሳስበው ነው፡፡ “ባልበላውም ጭሬ ልድፋው” አለች እንደተባለችው ዶሮ “ለእኛ የማትሆን ኢትዮጵያ ትፍረስ” የሚሉ አገር አጥፊዎች፣ ከጥፋት መንገዳቸው ተመልሰው ሰላም ፈላጊነታቸውን በሀቅ ያሳዩ፡፡ በሕዝብ ስም እየቆመሩ በሴራ ፖለቲካ አገር ማፍረስ አይቻልም፡፡
በፖለቲካው ዙሪያ የሚገኙ ወገኖችም ሊያስቡበት የሚገባ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ አለ፡፡ ይህም ማንኛውም አስተያየትም ሆነ ተግባር የአገርን ዘለቄታዊ ጥቅምና ደኅንነት እንዳይጎዳ መጠንቀቅ ነው፡፡ የፖለቲካ ልዩነትን የበለጠ ከማጎን ይልቅ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት ሰላም ማስፈን እንደሚገባ መነጋገር ያዋጣል፡፡ እሳቱ ከሚንቀለቀልበት አካባቢ በጣም ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በከንቱ ከመፎከርና ከማጋጋል ይልቅ፣ እስከ ዛሬ የፈሰሰውን የንፁኃን ደም በማሰብ ሰላም የሚሰፍንበትን መንገድ ማመላከት ይበጃል፡፡ እንደ ዘመነ መሣፍንት ጀብደኞች ለዕልቂትና ለውድመት የሚያመቻቹ ጉራዎችን ከመንዛት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕፎይታ የሚያገኝበትን ቀና ጎዳና ማሳየት ያስከብራል፡፡ ወጣቶችን የሚያስፈጅ አውዳሚ ጦርነት መቼም እንደማያዋጣ ከበቂ በላይ የታየ ስለሆነ፣ አሁን ጊዜው የሴረኝነት ሳይሆን ፍፁም ሰላም ፈላጊነትን ይጠይቃል፡፡
ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት የሰላም አምባ መሆን ይኖርባታል፡፡ የጦረኝነት አባዜ ተወግዶ ሰላም የሚሰፍነው ለሕዝብ ሲታሰብ ነው፡፡ ጥቂቶች የሚያልሙት የሥልጣንና የጥቅም መንገድ ሳይሆን፣ ለብዙኃኑ ሕዝብ ዘለቄታዊ ጥቅምና ደኅንነት የሚበጀው ሰላም የሚሰፍነው በንግግር ብቻ ነው፡፡ ንግግር ለማድረግ ደግሞ ቅንነትና ሀቀኝነትን ይጠይቃል፡፡ ካለፈ የውድቀትና የጥፋት ታሪክ ሳይማሩ በቀላሉ ተገማች የሚሆን አመል ይዞ መቅረብ አያዋጣም፡፡ እውነተኛ ሰላም ፈላጊ የበፊት አመሉን ይዞ ለማጭበርበር ቢሞክር ማንም አይቀበለውም፡፡ ምክንያቱም ሰላም ፈላጊነቱን ለማሳየት የሚፈልገው የሚታወቅበትን ጦረኝነቱን ደብቆ እንደሆነ በቀላሉ ስለሚታወቅ ነው፡፡ ስለሰላም አስፈላጊነት ከመስበክ በላይ ኖሮ ለማሳየት የሚያስችል ተዓማኒነት ማግኘት መቅደም አለበት፡፡ “ቂም ይዞ ፀሎት ሳል ይዞ ስርቆት” እንደሚባለው፣ በሰላም ፈላጊነት ስም ለማጭበርበር መሞከር ጊዜው ያለፈበት ፋሽን ነው፡፡ በመሆኑም ለሕዝብ አክብሮት አለኝ የሚል ማንም አካል ሰላማዊ ሆኖ ይገኝ፡፡ ድብቅ ዓላማን ለማስፈጸም የሚደረግ አጉል ብልጣ ብልጥነት ጊዜው አልፎበታል፡፡ በዚህ እውነታ ላይ በመመሥረት ሰላም መፈለግ ያዋጣል፡፡ ሴረኝነት የሰላም ጠንቅ ነው!