በነሐሴ ወር በአጠቃላይና በምግብ ዋጋ ግሽበቶች ላይ አንፃራዊ መሻሻል ቢመዘገብም፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት እንዳሻቀበ መሆኑን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
አገልግሎቱ ይፋ ያደረገው የነሐሴ ወር የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች ካለፉት ወራት ጋር ሲነፃፀሩ ጭማሪ ታይቶባቸዋል፡፡
የነሐሴ ወር ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር የ31.5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ የታወቀ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር ይህ አኃዝ 30.4 እንደነበር ይታወሳል፡፡
የምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በአልኮልና ትምባሆ፣ ልብስና ጫማ፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጂ፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች የሚባሉት ማለትም፣ የቤት ኪራይ፣ ሲሚንቶ፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ እንዲሁም የቤት ዕቃዎችና የቤት ማስጌጫዎች ላይ የታየው የዋጋ ጭምሪ መሆኑን ያመለከተው አገልግሎቱ፣ ነዳጅ፣ ሕክምናና ጌጣጌጥ (ወርቅ) ላይ የታየው ለውጥም የኢንዴክስ ክፍሉ የዋጋ ግሽበት እንዲያሻቅብ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች ተጠቃሹ ነው ብሏል፡፡
በዚህ ወቅት ካለው ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የኢኮኖሚ ሁኔታና ሌሎች ፈታኝ ሁኔታዎች አንፃር በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም. የታየው የዋጋ ግሽበት፣ በተለይም በምግብ ኢንዴክስ ክፍሎች ባለፉት ሁለት ወራት መጠነኛ መረጋጋት ማሳየቱ መልካም የሚባል መሆኑን ስታትስቲክስ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
በነሐሴ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር 32.5 በመቶ ሲሆን፣ ይህ አኃዝ በሐምሌ ወር 35.5 በመቶ ተመዝግቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳን ከቀደሙት ሁለት ወራት ጋር ሲነፃፀር መጠነኛ መሻሻል ቢታይበትም፣ በነሐሴ ወር በቀይ ሽንኩርትና በነጭ ሽንኩርት ላይ ፈጣን የዋጋ ዕድገት መታየቱን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
የዋጋ ግሽበት በኢትዮጵያ ባለሁለት አኃዝ ሆኖ ከተመዘገበ ዘለግ ያሉ ዓመታት መቆጠራቸውን ከሰሞኑ በኢኮኖሚክስ አሶሴሽን አዘጋጅነት በተካሄደ የፖሊሲ ውይይት መድረክ ላይ መገለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ በዓለም ላይ ከሚገኙ አገሮች በዋጋ ግሽበት ኢትዮጵያ የመጀመሪዎቹ አሥር ዝርዝር ውስጥ የምትገኝ እንደሆነች፣ በአፍሪካ ደግሞ ከሱዳንና ከዚምባቡዌ በመቀጠል ሦስተኛዋ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያለባት አገር መሆኗ ተጠቁሞ ነበር፡፡
ድህነት፣ የገቢ አለመመጣጠን፣ ሥራ አጥነት፣ የምርት መቀነስ፣ የጉልበት ብዝበዛና የሀብት ብክነት የዋጋ ግሽበት ከሚያስከትላቸው ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መካከል ተጠቃሾቹ መሆናቸውን የሚያስረዱት የኢኮኖሚ ምሁራን፣ ይህንን የዋጋ ግሽበትንና መዘዞቹን ለማስወገድ መንግሥት መሠረታዊ የሚባሉ ዕርምጃዎችን መውሰዱ እንዳለበት አሳስበዋል።
ለአብነትም የምግብ ነክ ምርቶች ላይ የሚስተዋለውን በአምራቹና በሸማቹ መካከል የአቅርቦት ሰንሰለቶችን ማጥበብ አንዱ በባለሙያዎች የሚቀርብ ምክረ ሐሳብ ሲሆን፣ ይህም በሁለቱ አካላት መካከል እዚህ ግባ የሚባል እሴት ሳይጨምሩ፣ ነገር ግን በርከት ያለ ትርፍ በማጋበስ የምርት ዋጋ እንዲንር ምክንያት የሚሆኑትን ደላሎች ከሒደቱ ለማውጣት የሚረዳ መሆኑን በማስረዳት ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገቡትን መተካት ዋጋን በማረጋጋት ረገድ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው በተደጋጋሚ ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል በመንግሥት በኩል በርካታ የውጭ ምንዛሪ ፈሰስ ተደርጎባቸው ከውጭ የሚገቡ ነገር ግን ለኢኮኖሚው ምንም የማይፈይዱ የቅንጦት ምርቶችን በመቀነስ ለምርቶቹ ግዥ የሚውለውን ምንዛሪ ለሌላ አስፈላጊ ዓላማ በማዋል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ብሎም የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ይቻላል የሚል መፍትሔ ይቀርባል።