ሰላም! ሰላም! ሁላችሁንም እንኳን ወደ አዲሱ ዓመት በሰላም አሸጋገረን፡፡ መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን፡፡ አሮጌው ተሸኝቶ አዲሱ ሲገባ መልካም ምኞት መለዋወጥ ተገቢ ነው፡፡ እንደምታውቁት ብሶት ወልዶን ብሶት እያስረጀ ካስተዛዘበን በርካታ ዓመታት ተቆጠሩ። ይገርማል ዓመታትም እንደ ሞባይል ካርድና ከረሜላ ቶሎ ያልቃሉ ለካ? እያሉ ጎረቤቶቼ ሲጨቃጨቁ ሰነበቱ። እኔማ ከአሁን አሁን የኑሮ ውድነት አሰቃየን ማለት በለመደብን አፋችን፣ የጊዜ ውድነት ያመጣብን የዕድሜ ዋጋ ማጣት ውጤት ነው ብለው ይስማማሉ እያልኩ አዳምጥ ነበር። ከማዳመጥ ምን አጣን? እንኳን ከማዳመጥ ደም ከመፋሰስ የጎደለብን ያለ እንመስላለን እንዴ? እውነቴን እኮ ነው። እናም ለዘመናት አናታችን ላይ የሚያናጥረውን የደመኝነት ፖለቲካ ብዙዎቻችን ባንፀየፈው ኖሮ፣ ለማይረባ ነገር የምናባክነው ጉልበታችንና ዕውቀታችን ባክኖ ይቀር ነበር፡፡ ይኼን ጊዜ ነው እንግዲህ እኛ ማን ነን? የምንፈልገው ምንድነው? እየተባባልን ካልተነጋገርንና ለጋራ ጉዳያችን በአንድነት መሠለፍ ካልቻልን ዓለም ይንቀናል፡፡ ተባብረን ታሪክ ስንሠራ ግን ብዙ ይባልልናል፡፡ ሰሞኑን አዲሱን ዓመታችንን ደመቅና ሸብረቅ ብለን በሦስቱ ኅብረ ቀለማት አጊጠን ስናከብር ውስጣችን ተስፋ ይዘራል፡፡ ተስፋ ውስጣችሁ ሲዘራ የሚሰማችሁን መልካም ስሜት አጢኑት፡፡ ከዚያም ራሳችሁን በሚገባ መርምሩ፡፡ ማን ነን በሉ!
በሌላ በኩል ያው የወትሮ ነገራችን እንደተጠበቀ ነው። ጦርነቱ፣ በየሥርቻው የሚኖረው ግጭት፣ የመኪና አደጋው፣ ሥልጣንን የሀብት መዝረፊያ ማድረግ፣ ከሥራ ቦታ ጠፍቶ ተገልጋይን ማማረር፣ በሐሰተኛ ወሬዎች መስከር፣ የከሰዓት በኋላው ፍራሽ ላይ በጫት ተሟሙቆ በአበደ የምርቃና ወሬ የምናብ ዓለም ውስጥ መዋለል፣ ጎራ ለይቶ ለአገር ሳይሆን ለጥቅም ሲሉ ብቻ ጠላትነትን ማባዛትና የመሳሰሉት አስከፊ ነገሮች ሞልተዋል። ይህ ዓይነቱ መቅኖ ቢስነት በአዲሱ ዓመት ይቀጥላል ወይስ እጅጌን አጣጥፎ ለልማት መነሳት ይሻላል የሚለውን ለእናንተ ትቸዋለሁ። በነገራችን ላይ አብዛኛው የማውቃቸው ወዳጆቼ ካላንደር የሚዘጋቸው ብሔራዊና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ቅዳሜና እሑድ ላይ ሲያርፉ የማይወዱ ናቸው። የአዞበት ቀን ላይ ሲያርፉ ግን ስሜቱ ልዩ ነው። ሥራ የለም የተባለ ቀን ሰነፉ ቅልጥ ያለ አርበኛ ይሆናል። እንዲያውም እንደ ምሁሩ ባሻዬ ልጅ ሰላማዊ የፖለቲካ አተናተን ከሆነ፣ የዘንድሮ አዲስ ዓመት በዓል እሑድ ላይ ማረፉ ለነገረኛው ማጉረምረሚያ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ በመስኖ እርሻ ስንዴ ለማልማት ሚሊዮኖችን ማሠለፍ የሚገባት አገር ዝናብ መጣ ቀረ እያለች ከሥጋት የምትወጣበት ጊዜ ይናፍቃል፡፡ አዲሱን ዓመት ስንጀምር ከእረፍት ይልቅ ለሥራ፣ ከወሬ ይልቅ አምራች ለመሆን፣ በሌሎች ከመነዳት ይልቅ ራስን መምራት ላይ ብናተኩር የሚያዋጣን ይመስለኛል፡፡ ምንም ደላላ ብሆን ነገር ይገባኛል!
መቼም አንዳንድ ነገሮች ብዙ ያስብላሉ። ‹አንዳንድ ነገሮች ብዙ ያስገርሙኛል…› እንዲል ጥላሁን ገሠሠ። እናማ የሥራ ቀን ለበለጠ አገራዊ ዓላማ ዋለ ስንባል ጮቤ መርገጥ ሲኖርብን፣ ከግል ጥቅማችን አንፃር የአገርን ጉዳይ ስንቃኝ ግርም ይላል። መቼም ሰው ሥረ መሠረቱ ልጅነቱም አይደል? በቀደም ዕለት ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ “የአንድ ሙሉ ሰው አባት ወላጅ አባቱ ሳይሆን ልጅነቱ ነው…” ስላለው ዶስቶቪስኪ የሚባል የሩሲያ ጸሐፊ ሲያጫውተኝ ነበር። እሱ ምሁራዊ አተያዩን ከማስረጃ ጋር እያቀናበረ ሲያጫውተኝ እኔ የማስበው ልጅነቴን ነበር። አንዳንዴ ዛሬያችሁ ግራ ሲያጋባችሁ፣ እኔ እንዲህ ነኝ? ኧረ ማን ነኝ? ስትሉ ዝም ብላችሁ አስተዳደጋችሁ ዘንድ ወደኋላ ሂዱ። እመኑኝ መልሱ ያለው እዚያ ብቻ ነው። ማንነት ላይ ያለ ችግር ግራ አጋብቶ ስንቱን ሲያዛንፈው እያያችሁ አይደል? እስኪ ተጠያየቁ!
ታዲያ ምነው ሥራው ላይ ከመረባረብ በወሬና በአሉባልታ ተጠምደን እየዋልን መፍትሔ ከየት እናግኝ? የሚል ጥያቄ ያላችሁ ወሬውን ረግጣችሁ የመውጣት መብት አላችሁ። መልስ አልባ ሆኜ ብቻ ሳይሆን ዶስቶቪስኪ በሕይወት ስለሌለ ጭምር እንጂ፣ ቢያንስ እሱን ለማጠያየቅ መሞከሬ አይቀርም ነበር። እና ልጅነታችንን ስናጠና ትምህርት ቤት አርፍዶ የመግባት የአብዛኞቻችን አባዜ ትዝ ሲለኝ፣ ዛሬ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ‹ሥራ አስኪያጁ ገና አልገቡም› የሚባለው ነገር ውሉ ይገባኛል። ሠልፉና የባንዲራ ሥነ ሥርዓቱን አድምቀን ስናበቃ፣ አንደኛው ክፍለ ጊዜ ላይ የተሰጠንን የክፍል ሥራ በገዛ ስንፍናችን ወደ ሦስት ቀን የቤት ሥራነት ስንቀይረው ያደግን ልጆችን ሳስብ ዛሬ ስለአገር ክብር፣ ዕድገትና ልማት ደንታ በማጣታችን የቆለልነው ዕዳ እየታሰበኝ ተጠያቂው ይጠፋብኛል። ታዲያ እኛ ማን ነን ማለት አይገባም ትላላችሁ?
ለግርግርና ለሆታ ቅድሚያ በመስጠት ለሐሜትና ለአሉባልታ ትኩረት መድበን ስንጓዝ ብቻ እንጀራ እንደሚወጣልን እየነገሩ ያሳደጉንን ወላጆች የታዘዝን እኛ፣ ለሠርግና ለድግሱ የምንጨነቀውን ያህል ለፍቺው አለማሰባችን ምን ይገርማል? ተፈጥሮ ያላደለንን አብሾና ሥራ ሥር እየጋቱ ለአንደኝነት፣ ኮሌጅ ለመበጠስ፣ በልጦና ይዞ ተቆጣጥሮ ለመገኘት ካሳደጉን ወላጆቻችን የተገኘን እኛ፣ ዛሬ ከተማውን ተቆጣጥረን ወንበዴውንና ጨካኙን ብንረሳው ምን ያስተቻል? እውነት አይደለም? “በመበላለጥ የኑሮ ብልኃት የተቃኘ ልጅነት…” አለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ በቀደም ዶፍ ዘንቦ ከአንዱ ታዛ ተጠልለን ጎርፉ እስኪጎድል ቆመን ስናወራ። “…በመበላለጥ የተቃኘ ልጅነት በጉልምስና ዘመን እያነጣጠቀ፣ አገር ከመበጥበጥ ሌላ ውጤቱ ምን ሊሆን ኖሯል?” ሲለኝ፣ “ምን እኔን ትጠይቀኛለህ?” አልኩት አስፋልቱ ላይ የሚፈነጨውን ጎርፍ እያየሁ፡፡ ‘ጎርፍ ያመጣሽ እንደሁ ልጠብቅ ወንዙን’ ብዬ ለማንጠግቦሽ ያፏጨሁበትን ዘመን እያስታወስኩ። አሁንማ ጊዜው ነጉዶም ትዝታው ይወዘውዘኛል፡፡ እኔን አይባልም እንዴ!
ይኼን ጊዜ አንድ ወፈፌ ዶፉ እላዩ ላይ እየወረደ በጉያው ሦስት አራት የጫት እንጨቶች ሸጉጦ፣ “ጎርፉ ሳይጎድል አሥር ብር ስጡኝ…” አለን። ዝም ስንለው “ስለጎርፉ?” ብሎ ደገመው። የባሻዬ ልጅ አምስት ብር አውጥቶ ሰጠው። በቆመበት ቁጢጥ ብሎ ብሯን አጣጠፋት። አጥፎ አጥፎ ሲያቃናት ጀልባ ሆነች። “እኔን አልቀናኝም እስኪ አንቺ ሞክሪው…” ብሎ አንሳፈፋት። የባሻዬ ልጅ ተናዶ “አንተ፣ ወንጀል እኮ ነው…” እያለ የሚያደርገው ሲጠፋው ወፈፌው፣ “ለምን እኔን አላልክም?” አለው። የባሻዬ ልጅ ግራ ገባው። “እኔም እኮ ሥጋና ነፍስ ያለኝ የምራመድ ወንጀል ነኝ። ሲለምኑብኝ ለምን ዝም አልክ? ዋጋዬን ሲከለክሉኝ፣ ግዴታዬና መብቴ ላይ ሲጫወቱ፣ በድህነት ሲያጎሳቁሉኝ፣ የትም ሲጥሉኝና መልሰው ስሜን ብቻ እያነሱ በጥጋብ ሲሳከሩብኝ ለምን ዝም አልክ?” ቢለው ምን ይበል? ራሱን መጠየቅ መቼ ለመደና!
በቀደም አንድ ቅጥቅጥ አውቶቡስ ሳሻሽጥላችሁ ሻጩ ደንበኛዬ ትኩር ብሎ የጣት ቀለበቴን እየተመለከተ፣ “ትዳር እንዴት ነው?” ብሎ ጠየቀኝ። ‹‹አሸወይና ነው፣ ወርቅ ሚስት አለችኝ…›› አልኩት። አንዳንዴ ከጥያቄው በፊት የተዘጋጁ መልሶች ችግር ይፈጥራሉ እኮ። ለካስ ዕድሜው ከእኔ ከጎልማሳው የማያንሰው ደንበኛዬ አራተኛ ጣት ባዶ ኖሯል። ምን ብዬ ጨዋታዬን ልቀጥል። ‹‹ይገርምሃል ከጓደኞቼ ሁሉ ሳላገባ የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ…›› አለኝ፡፡ ‘ግድ የለም ሁሉም በጊዜው ይሆናል’ ብዬ ሌላ የተዘጋጀ መልስ ከመመለስ ለጥቂት ተረፍኩ፡፡ አንዳንዱ ባለማግባቱ የሚበሳጨውን ያህል ሌላ በምንም ሲበሳጭ አላየሁማ፡፡ “ምነው አልክ?” አልኩት ብዙም እንዳልደነቀኝ ሆኜ፡፡ ‹‹ዕድሜ ለጓደኞቼ መማሪያ ሆኑኛ፡፡ አንድ ሁለቱ ይሻላሉ እንጂ የሰባቱ ኑሮ ሲኦል በለው። ነጋ ጠባ ጭቅጭቅ ነው። ዘመኑ እንደምታየው ስለእኩልነት የሰበከውን ያህል ስለአንተ ትብስ አንቺ አይሰብክም። እናም እኔ ይኼን እያየሁ ምን ተማምኜ ላግባ? ያውስ በመሸበት ማደር በቀለለበት ዘመን?›› ሲለኝ ከልቤ አዘንኩ። እንዴት ነው ነገሩ? ተነጋግሮ ችግርን መፍታት ብርቅ በሆነበት አገር ውስጥ ሆነን ትዳራችን ቀርቶ ችግኙስ እንዴት ይፀድቃል? ጎበዝ! እስኪ በአዲሱ ዓመትም እንነጋገር!
ኋላ ሥራዬን ጨራርሼ ኮሚሽኔን ተቀብዬ ከአዛውንቱ ባሻዬ ጋር ስንጫወት ይኼው ደንበኛዬ ያለኝን ብነግራቸው፣ አንገታቸውን ወዝወዝ አድርገው ‘ዋ’ ብለው ቀሩ። “ምነው?” ስላቸው፣ ‹‹ያለ ሙያቸውና ፍጥረታቸው ገብተው የተደናገሩ ከበሮ መቺዎችን እያየ ስንቱ ከበሮውን ትራስ አደረገው? ስንቱ ዛሬ ታይተው በነጋታው በፈረሱ ትዳሮች ውጥኑ ፈረሰ? ለአገር ለወገኑ ስንት ዓላማና ዕቅድ ያለው ከእሱ በፊት የነበሩትን እያየ ስንቱ ሀሞቱ ፈሰሰ? ስንቱ ከሰላማዊ ትግል ሸሸ? ስንቱ ሕይወትን ተፀየፈ?›› ሲሉኝ አዝማቹን እየደጋገምኩ አጀብኳቸው። ‹እባብ ያየ በልብጥ በረየ› እንደሚባለው ሰው ግን በስንቱ ይንገፈገፋል? ያም ሆነ ይህ ‹ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም› እንደሚባለው፣ አንዳንድ ነገሮቻችንን ደፍረን ከላያችን ላይ ፈንቅለን መጣል አለብን፡፡ እየተንገፈገፍንማ መኖር የለብንም፡፡ አይመስላችሁም!
በሉ መሰነባበቻችን ደርሷል። እኔና የባሻዬ ልጅ ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ጎራ ብለን አንድ አንድ ማለት ጀምረናል። ‘ያም ሲያማ ያም ሲያማ፣ ወገኔ ለእኔ ብለህ ስማ’ ይላል በሚስረቀረቅ ድምፁ የሙዚቃው ንጉሥ። አንዱ ከመቀመጫው ተነስቶ፣ “ባለፉት ሦስት አሠርት ዓመታት ምን ተሠራ? መንገድ፣ ግድብ፣ የጋራ መኖሪያ ቤት፣ ወዘተ፣ ወዘተ፡፡ በእርግጥ ብዙ ለውጥ አየን ማለት አይቻልም፡፡ ጥያቄው መንገዱን እየፈነጨበት ያለው ማን ነው? ነው፡፡ መልሱ ደግሞ…” ሲል የግሮሰሪዋ ታዳሚዎች በአንድ ድምፅ “ሌባው!” ብለው አስተጋቡ። ድንግጥ አልኩ። ሌላው ተነስቶ፣ “ብሶትን ቀብረን መልሰን ብሶት የምናምጥ ከሆነ፣ ለምን አንደኛችን ድምፃችንን አዘግተን አንገላገልም?” ሲል ሰው አውካካ። ደግሞ ሌላው ተነስቶ፣ “ማሳሰቢያ አለኝ!” አለ። ‘ተናገር’ ሲባል፣ “ሳቃችሁን በቁጥጥር ሥር አውላችሁ ሳቁ ለማለት ነው። ምናልባት ከጣራ በላይ ስትስቁ ‘ፊውዝ’ ተቃጥሎ ለሳምንት መብራት እንዳይጠፋ። አመሠግናለሁ…” ብሎ ገና ሳይቀመጥ ሌላ ሳቅ። እኔ በመገረምና ግራ በመጋባት ድባቡን አስተውላለሁ። ሁሉም ተቺ ነው። ሁሉም ጥያቄ አለው። ሁሉም አንደበቱ ለነገርና ለሂስ የሰላ ነው። እንዲያው ከዚህ ልማድ መቼ ይሆን የምንገላገለው? እንጃ!
‘እኛስ ማን ነን? ሌባው የገዛ ዘመዴ፣ የገዛ ወገኔ፣ አብሬው የጠጣሁት፣ አብሬው የበላሁት አይዞህ አትፍራ ምን አባቱ ያልኩት አይደለም እንዴ?’ የሚል አንድ እንኳ የለም። ኋላ ውሎ አድሮ ለባሻዬ ትዝብቴን ስነግራቸው፣ “ንጉሥ ዳዊት ራሱን በአምላኩ ፊት ሲያይ ምን አለ መሰለህ?” አሉኝ፡፡ “ምን አለ?” ስላቸው፣ “‘እኔስ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድነው?’ ነው ያለው፡፡ አየህ ‘ጠቢብ ሰው ዓይኖቹ በገዛ መንገዱ ላይ ናቸው’ ያለንን ጠቢቡ ሰለሞንን የወለደው እንግዲህ እሱ ነበር…” አሉኝ። አላልኳችሁም? ዛሬያችሁ ላይ ጥያቄ ካላችሁ ልጅነታችሁን መርምሩት አላልኳችሁም? ታዲያ ተጠያቂው ማን ነው ጎበዝ? ጠያቂውስ? ‘ኧረ እኛስ ማን ነን? ጥያቄያችንስ የማን ነው?!’ ብለን ተለያየን፡፡ “አዲሱን ዓመት ራስን የማወቅ ያድርግልን’ ብለዋል ባሻዬ። አሜን አትሉም? እንዲህም ሲሉ ጨምረዋል፡፡ “አገራችሁን በጠላት አታስደፍሩ፡፡ አገራችሁ በምግብ የተትረፈረፈች እንድትሆን ታጥቃችሁ ተነሱ፡፡ ከጠላትነት ይልቅ ለወንድማማችነት ቅድሚያ ስጡ፡፡ እርስ በርስ ተከባበሩ፡፡ አብራችሁ መብላት እንደምትወዱት አብራችሁ ለመሥራት ጥረት አድርጉ፡፡ የተከላችሁትን ችግኝ ተንከባከቡ፣ ስትንከባከቡም ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ ማን ነኝ? ወዴትስ ነው የምሄደው በሉ፡፡ አደራ የተተከለው የሚበቅለው ንፁህ ልቦና ሲኖር ነው…” ብለዋል አዛውንቱ ባሻዬ፡፡ ከአጉል መካሪ የጠቢብ ተግሳጽ እንዲሉ ማን ነን ማለትስ አሁን ነው፡፡ መልካም አዲስ ዓመት! መልካም ሰንበት!