Thursday, September 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሮ ዕዳሪሕክምና ግብዓትን ከጭላዳ ዝንጀ

የሮ ዕዳሪሕክምና ግብዓትን ከጭላዳ ዝንጀ

ቀን:

ኢትዮጵያ በርካታ የጄነቲክ ሀብት ካላቸው ጥቂት አገሮች መካከል በግንባር ቀደምነት እንደምትጠቀስ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሀብቷን ወደ ጥቅም የመቀየር ሥራ ቢከናወን ከሚገኘው ገቢ አገሪቷ ተጠቃሚ ልትሆን እንደምትችል ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፈለቀ ወልደየስ (ዶ/ር) ይህንኑ የብዙዎቹን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ለተግባራዊነቱም ኢንስቲትዩቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ በማከናወን ላይ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

እስካሁን በተከናወነው እንቅስቃሴ ከጭላዳ ዝንጀሮ የሚወጣው ፅዳጅ/ዕዳሪ (ድሮፒንግ) ላይ የሚገኘውን ልጋጋማ ነገር ለገቢ ማስገኛ እንዲውል የማድረጉ ሥራ ይገኝበታል፡፡

ከዚህም ልጋጋማ ነገር ለሕክምና የሚውል ግብዓት ለማውጣት ይቻላል የሚባል ሲሆን፣ በዚህም ሥራ ላይ የተሰማራው በአሜሪካ የሚገኘው ባዮ ማሪን ፋርማሲዩቲካል ኩባንያ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ለሦስት ቀናት የተካሄደውን የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት የማኅበረሰብ ቀንን አስመልክተው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ፈለቀ (ዶ/ር) በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው ወደ ሥራው የገባው በቅድሚያ ለኢንስቲትዩቱ ማመልከቻ ከጻፈና የሁለትዮሽ የውል ስምምነት ፊርማ ከተከናወነ በኋላ ነው፡፡

በስምምነቱም መሠረት ኩባንያው የቅድሚያ ክፍያ 50,000 ዶላር ገቢ አድርጎ ወደ መጀመርያው ዙር ሥራ መግባቱን ገልጸው፣ ቀዳሚው ዙር ሥራ ያተኮረውም በዳሰሳ ጥናት ላይ መሆኑን ጥናቱም ለአሥር ዓመታት ያህል እንደሚቆይ አስረድተዋል፡፡

ከምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው የጄነቲክ ሀብት ዋጋ የማይተመንለት፣ በአግባቡ ሊያዝና ከዘረፋም ሊድን ይገባል፡፡  በታቀደ መልኩም ሆነ ሳይታወቅ ከአገር ይወጣል፡፡ ይህ ደግሞ አገርን ተጎጂ ያደርጋል፡፡ ይህ እንዳይሆን የክትትል፣ የቁጥጥር፣ ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ ውል የመግባትና ፍትሐዊ ጥቅም የማጋራት ሥራ የማከናወን ኃላፊነት የተጣለበት የጄነቲክ ሀብት አቅርቦትና የጥቅም ተጋሪነት የሥራ ሒደት ተቋቁሟል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር መለሰ ማርዮ (ዶ/ር)፣ ‹‹ኢንስቲትዩቱ አጠቃላይ የጀነቲክ ሀብቶችን የመጠበቅ (ማንበር)፣ ብዝኃነት ኖሮት እንዲቀጥልና ከሀብቱም ማኅበረሰቡ ፍትሐዊ ጥቅም የሚያገኝበትን ሥርዓት ዘርግቶ እየሠራ ነው፡፡ የተለያዩ የአየር ጠባይ ባሉባቸው አካባቢዎችም አሥር ማዕከላት/ቅርንጫፎች ተቋቁመው ወደ መሬት የሚወርዱ ሥራዎችን እያከናወኑ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ የምርምር ተቋም እንደመሆኑ መጠን ምርምርን ለማሳለጥ የምርምር ሥርዓትና የፕሮጀክቶች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዘንድሮ እንደሚቋቋምና የብዝኃ ሕይወት መድረክ ተቋቁሞ ወደ ሥራ እንደሚገባ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከአገር ውጪ የሚመጡ የዛፍ ዝርያዎች ቶሎ እንደሚደርቁ፣ ረዥም ዕድሜም እንደማይኖራቸው፣ ሲሞቱና ሲጠፉ እንደሚስተዋሉ፣ ከዚህ አኳያ ኢንስቲትዩቱ ሁለት ሚሊዮን አገር በቀል ዛፎችን አፍልቶና አዘጋጅቶ እንዳሠራጨ ነው ያመለከቱት፡፡

በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ በብዝኃ ሕይወት ሀብት ላይ ጉዳት ማድረሱን፣ በዚህም በኦሮሚያ፣ በሶማሌና በአፋር ክልሎች ብዙ ከብቶች ማለቃቸው፣ ውኃ አዘል መሬቶች በመጤ አረሞች መወረራቸው፣ የእርሻ ሀብቶች መስፋፋት ለደን ሀብት መመናመን መንስዔ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ አባባል ኢንስቲትዩቱ ከ90,000 በላይ የሆኑ አዝርዕት፣ የሆርቲካልቸርና የደን ናሙናዎችን የያዙ ከ30 በላይ የጂን ባንክች አሉት፡፡ ከተጠቀሱት ባንኮች ውስጥ ከተያዙት ናሙናዎች መካከል 100 ያህሉ የአዝርዕት የቀሩት ደግሞ የደንና የሆርቲካልቸር ናሙናዎች ናቸው፡፡

ናሙናዎቹ ዝም ብለው የሚቀመጡ ብቻ ሳይሆን ከተመራማሪዎችና ከምርምር ተቋማት ጥያቄ በቀረበ ቁጥር እንደሚሰጥ ገልጸው፣ በዚህ ዓመትም የደቂቅ አካላትና የእንስሳት ሙዚየምና ቤተ ሙከራ እንደሚገነባ፣ እንዲሁም በብዙኃ ሕይወት ዙሪያ የሚወያይ ዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ጉባዔ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

ከዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ብዝኃ ሕይወትን አስመልክቶ ከፖሊሲ አውጪውና ውሳኔ ሰጪው የመንግሥት አካል ጀምሮ የግንዛቤ ችግር ይታያል፡፡ በእሳቤ ደረጃ ግን አርሶ አደሩ የተሻለ ግንዛቤ አለው፡፡

ይህም ሆኖ ግን ግንዛቤ ማስጨበጡ ላይ ኢንስቲትዩቱ የተቻለውን ያህል ቢጥርም ወደፊት ለመራመድ እንዳልተቻለ ገልጸው ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ በማስጨበጡ ላይ ሊረባረቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከጳጉሜን 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በተካሄደው በዚሁ የማኅበረሰብ ቀን ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ ጊዜያት ያከናወናቸው ልዩ ልዩ የሕይወታዊ ሀብት ጥበቃና ዘለቄታዊ አጠቃቀም ሥራዎችን ለታዳሚዎቹ አስተዋውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...