Wednesday, November 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ወጣቶችን ጥራት ባለው ትምህርት በመቀየር ሰብዓዊነት የተላበሳቸው እናድርጋቸው ክፍል ፩

በበላይ ወልደየስ (ፕሮፌሰር)

ሰሞኑን አንድ ወዳጄ ያካፈለኝ መጣጥፍ፣ የአገሬ ሁኔታ እየታየኝ ደነገጥኩኝ፡፡ ሰውነቴን ወረረኝ፡፡ ጽሑፉ የተገኘው በሁለተኛው ዓለም ጦርነት፣ ከአንድ የጀርመን ናዚ የሰው መግደያ ሠፈር (Concentration Camp) ከመሞት በተዓምር ተርፎ፣ ያየሁን ጨካኝ ክውነት አስደንግጦት፣ ‹‹መማር ማለት ምንድነው?›› በሚል ርዕስ ለመምህራን ጽፎ የተገኘውን ነው፡፡ ጽሑፉም እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ማንም ሰው ሊሠራው ቀርቶ፣ ሊያስብ የማይችለውን ዘግናኝ ነገር እኔ በእስር ላይ ከዛሬ ዛሬ ይገድሉኛል እያልኩ፣ በዓይኔ አየሁት፡፡ ከአየሁትም ውስጥ ሰው የሚገድሉበትን ጋስ ማውጫ፣ የፈበረኩት አዋቂ ኢንጂነሮች መሆናቸው፣ ለሕፃናት መርዝ አዘጋጅተው ሰጥተው የጨረሱዋቸው የተማሩ አዋቂ ነርሶች እንደነበሩ፣ ሴቶችና ሕፃናት በጥይት ተገድለው የተትረፈረፉት በሁለተኛ ደረጃ፣ በኮሌጅና በዩኒቨርሲቲ በተማሩ ምሁራን መሆኑ ወዘተ ይገኝበታል፡፡

ጸሐፊውም ይህንን ዘግናኝ ክውነት በማየቱ በጊዜው በነበረው መማር (ትምህርት) ላይ ጥርጣሬ እያነሳ፣ ይህ እንዳይደገም ለወደፊቱ መምህራን ሰብዓዊነት የተላበሳቸውን ተማሪዎች እንዲያወጡ ይለምናል፡፡ በመቀጠልም፣ ሲያስረዳ የመምህራን ጥረት መሆን ያለበት ያስተማሩዋቸው ተማሪዎች ሲወጡ በምንም ዓይነት የተማሩ ጨካኞች/አረመኔዎች (Cruel-Monsters)፣ የሠለጠነ አዕምሮአቸው ያልተረጋጋ (Psychopaths) እና የተማሩ መኃይም (illiterates) እንዳልሆኑ ማረጋገጥ አለባቸው ብሎ ይመክራል፡፡ ሲያጠቃልልም ማንበባቸው፣ ማወቃቸው፣ ልጆቻችንን ወደ ትሕትና የሚወስዳቸው መሆን ነበረበት እንጂ፤ አውሬ እንዲያደርጋቸው በፍጹም አልነበረበትም በማለት ቁጭቱን ይገልጻል፡፡

በአሁኑ ዘመን በኢትዮጵያ በተራቀቀ ሁኔታ በማንነት በመነሳት፣ የተረገዘን ልጅ ከእናቱ ሆድ አውጥተው በማያውቀው ማንነቱ የሚገድሉት፣ አሮጊቶችን የሚደፍሩና የሚያሰቃዩ፣ በሰው ላይ ቤት ዘግተው የሚያቃጥሉ፣ በአካባቢ ተሰባስበው፣ አንዱን መጤ ሌላውን የእኔ በማለት በደቦ ቁልቁል ሰቅለው በሬሳ የሚቀልዱት የአካባቢ ገበሬዎች ናቸው ሊባል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ቢባል፣ የኢትዮጵያ ገበሬ ከመንግሥት ይልቅ፣ አጠገቡ ያለውን ኅብረተሰብ በማክበር እግዚአብሔርን በማመን፣ በባህልና በአናኗር ሥርዓት የሚኖር ነው፡፡ ጦርነት እንኳን ቢያጋጥመው፣ በሕግና ሥርዓት ጦርነቱን የሚመራ ነው፡፡ ሴት፣ ሕፃን፣ ሽማግሌ፣ አሮጊት ወዘተ. በጦርነት እንዳይጎዱ ከለላ አድርጎ የሚዋጋ ነው፡፡ ታዲያ ማነው በአካባቢው ካለው፣ ይህን እኩይ ተግባር የፈጸሙት ብለን ከጠየቅን፣ በእየ ገበሬው አካባቢ ያሉት ተማርን የሚሉ ወጣቶች ብቻ ናቸው ሊሆኑ የሚችሉት፡፡ ይህንን በአንድ በኩል አምኜ በሌላ በኩል ከላይ የተገለጸውን ትርክት እያስታወስኩ በመምህርነቴ፣ ራሴን እንድጠይቅ አደረገኝ፡፡

ከ40 ዓመት በላይ በከፍተኛ ትምህርት በመምህርነት ያገለገልኩት፣ ‹‹የተማርን ነን የሚሉትን ወጣቶች፣ በተግባራቸው ግን መኃይምነትና የኋላ ቀርነት የተጠናወታቸውን ወዘተ. ለማፍራት ነው ወይ? ወይስ ያስተማርኳቸው ልጆች ‹‹ሰብዓዊነት ተላብሰው አንተ ትብስ፣ አንተ ትብስ በመባባል፣ የዓለም ሕዝቦች በሙሉ የአንድ መንደር ሰዎች ናቸው በማለት ተፈቃቅረው በአንድነት እንዲኖሩ ነው፡፡›› እንግዲህ ሰው የዘራውን እንደሚያጭደው ሁሉ፣ እኛም በሆነ ጊዜ እነዚህ እኩይ ተግባር የሚሠሩትን በማፍራታችን ዛሬ ዋጋ እየከፈልንበት እንገኛለን፡፡ የትጋ ነው ያበላሸነው ብዬ በጣቴ ልጠቁም አልፈልግም፡፡ ግን አበላሽተናል፡፡ አሁንም እየቀጠለ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ችግሮች ለይተን አውጥተን፣ ወደ ፊት የማይቀጥልበትን መፍትሔ መስጠት አለብን፡፡

በአብዛኛው ወጣቶች፣ ይህን እኩይ ሥራ የሚሠሩት በአስተዳደጋቸው ጊዜ በአጋጠማቸው፣ በአንድም ሆነ በሌላ ተፅዕኖ ወድቀው እንደሆነ የሚታመን ነው፡፡ በዘመናዊ አኗኗር ለልጆች አስተዳደግ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ወላጆች፣ ሃይማኖትና መንፈሳዊ ሕይወት፣ የአካባቢው ኅብረተሰብ፣ ትምህርት፣ ወዘተ. ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡ ከእነዚህ አንዱ ካልተሟሉ ሙሉ ሰብዕና ያለው ዜጋ ሊወጣ አይችልም፡፡ ስለዚህ ከላይ ያየነውን ዓይነት ሰቆቃ የሚያከናውኑት ምናልባት በአንዱ ወይም በሁሉም ነገር በመበላሸቱ ሊሆኑ ይችላል፡፡ በጽሑፌ መግቢያ ላይ ወደ ጠቀስኩት ትርክት ስመለስ፣ ተራኪው ለመምህራን ባስተላለፈው ጥሪ ትምህርት ላይ ጥንቃቄ እንድናደርግ ያሳስባል፡፡ እኔም ለአንድ ወጣት ከሰብዓዊ ውጭ ድርጊቶች ለመፈጸም የአስተዳደጉ ሁኔታ ወሳኝ ነው ብዬ ስለማምን፣ ከነዚህም አንዱ ትምህርት ስለሆነ፣ መምህርም ስለሆንኩ፣ በእሱ ላይ ላተኩር ፈለግሁ፡፡

ልጆች በትምህርት ቤት ማኅበራዊ ኑሮ አናኗርን፣ የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶችን፣ ያሉበትን አካባቢን፣ የዓለም አወቃቀርን፣ የተፈጥሮ ሀብትን፣ ወዘተ. ይማራሉ፡፡ ይህም ከመዋለ ሕፃን ጀምሮ አንደኛንና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃን፣ በሳይንሳዊ ሁኔታ ግብረ ገብን ጨምሮ እንዴት በኅብረተሰቡ መካከል አብሮ መኖር እንደሚቻል ይማራሉ፡፡ ከዚያም በመቀጠል በቴክኒክና ሙያ ወይም በዩኒቨርሲቲ፣ ለዘላቂ ኑሮዋቸው መሠረት የሚሆነውን ትምህርትን ያገኛሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በእየ ገጠሩ ይህንን እኩይ ተግባር የሚሠሩት፣ ከላይ እንደገለጽኩት ገበሬዎች አይደሉም፣ ሕፃናትም አይደሉም፣ ምናልባት ሁለተኛ ደረጃን ጨርሰው ወይም በቴክኒክና ሙያ ወይም በዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ናቸው ብንል ብዙም አንሳሳትም፡፡ እነዚህ በቴክኒክና ሙያ ወይም በዩኒቨርሲቲ የሚገባውን ትምህርት አግኝተው በመሥሪያቸው ጊዜ ሥራ ባለማግኘታቸው ተስፋ በመቁረጥ በየመንደሩ በሚንገላወዱበት ጊዜ በእሳት ላይ ቤንዚን ለማርከፍከፍ የተዘጋጁ፣ ልሂቃን ወይም እኩይ ተግባር የተፀናወታቸው በገንዘብ ወይም በሐሳብ ማርከዋቸው ለዚህ ጭካኔ ሥራ አሰማሩዋቸው ብንልም አንሳሳትም፡፡ እዚህ ላይም ደፍሮ መናገር የሚቻለው በአብዛኛው ወጣቶች ሥራ ቢኖራቸውና በራሳቸው እግር መኖር ቢጀምሩ ኖሮ ለኑሮአቸው ስለሚሯሯጡ ለእኩይ ተግባር ጊዜ አይኖራቸውም የሚለውም ቀልብ የሚገዛ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ለተማሩ ወጣቶች ሥራ አጥነት የሚበዛበት ምክንያት አንዱ ወላጆች ስለዘመናዊ ትምህርት ያላቸው ከንጉሡ ጀምሮ የተሳሳተ አመለካከት በመሆኑ ነው፡፡ ልክ ልጆች  በአካባቢያቸው የሥራ ልብስ ለብሶ ያዩትን እኔ ሳድግ ፖሊስ፣ ጦር ሠራዊት፣ ፓይለት ወዘተ. እሆናለሁ እንደሚሉት፣ ወላጆችም ልጃቸው ሲያድጉ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በዲግሪ ተመርቆ ለማየት ነው ጉጉታቸው፡፡ ይህም የሆነበት ምናልባት በንጉሡ ጊዜ የእጅ ሥራ የሚሠራ ብዙም ስለማይከበር፣ በዲግሪ ተመርቆ፣ ከረባት አጥልቆ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ሥራ ይዞ፣ በዚያን ጊዜ ጥሩ ደመወዝ ተቆርጦለት መታየት፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚያስከብር ሆነው ስላገኙት ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ እስካሁን ቀጥሎ ወላጆች ዲግሪ አምላኪ ሆነዋል፡፡ በተቃራኒው ግን ዲግሪ የያዘ ከሚፈለገው የሠራተኛው ቁጥር በጣም አናሳ ነው፡፡

በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ በዲግሪ የተመረቀው ሠራተኛ ቁጥር ከአራት በመቶ አይበልጥም፡፡ የተቀረው በሙያ (የቴክኒክና ሙያ ወዘተ.) የሠለጠነ ነው፡፡ በዚህም ነው በእነዚህ አገሮች ወላጆች ልጆቻቸው ሁለተኛ ደረጃን (በቴክኒክና ሙያ ትምህርት) ሲጨርሱ፣ ድል አድርገው ደግሰው፣ ዘመድና አዝማድ ጠርተው የሚደሰቱት፡፡ አሁንም በተቃራኒው በእኛ አገር ወላጆች ልጆቻቸው በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሠልጥነው ሲመረቁ ምንም የምርቃት ዝግጅት ሳይኖር በዲግሪ ሲያስመርቁ ግን (ሥራ የሚገኝለት መሆኑ ሳይታወቅ)፣ ድንኳን በመትከል ዘመድ አዝማድን በመጥራት የሚያከብሩት፡፡ በነገራችን ላይ፣ በንጉሡና በከፊል በወታደሩ አገዛዝ ጊዜ ለማናቸውም ምርቃት የወላጅ ድግስ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ አብዛኛው ተመራቂ በዚያን ጊዜ ገዋኑን ለብሶ ፎቶ ቤት ሄዶ ይነሳል እንጂ ቤቴ ድግስ አለ ብሎ አይቋምጥም፡፡

በኢሕአዴግ ጊዜ ነው ድግስ ተጠናክሮ የመጣው፡፡ እንግዲህ ወላጆች ሥራ በማይገኝለት የዲግሪ ትምህርት ልጆቻቸውን በመላክ ለሥራ አጥነት ዳርገዋቸዋል ብንል ብዙም አልተዳፈርንም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያም የዓለም ክፍል ስለሆነች የአገሪቱን የወጣት የሥራ አጥነት ለመቅረፍ፣ ጥራታቸውን የጠበቁ ከ90 በመቶ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥረውን የቴክኒክና ሙያ  ማሠልጠኛ ተቋምና እስከ አራት በመቶ የሚሆነውን የሠራተኛ ኃይል የሚያቅፉ ዩኒቨርሲቲዎችን በማደራጀት፣ በጥራት በማስተማር፣ በእኩይ ሥራ የተሠለፉትን ወጣቶች ቁጥራቸውን ልንቀንስ እንችላለን፡፡ ወደዚህ ግብም ለመድረስ በቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛና በዩኒቨርሲቲዎች  ያሉትን ጋሬጣዎች ነቅሰን አውጥተን መፍትሔ መስጠት ይኖርብናል፡፡ 

በቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛ ገብቶ የሚሠለጥነው ተማሪ የሚሠራው በማምረቻና በአገልግሎት ዘርፍ ነው፡፡ የሚያመርተውም ሆነ የሚሰጠው አገልግሎት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘት አለበት፡፡ ይህም ማለት የቴክኒክና ሙያ ተቋሙም ሆነ ተመራቂው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ሁኔታ ስናየው የአገራችን አብዛኞቹ የቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛ ተቋሞችና ተመራቂዎች እንኳን ዓለም አቀፉን፣ የአገሪቷን ብቃት አያረኩም፡፡ እዚህ ላይ እንደ አብነት እኔ የቆዳ ማሠልጠኛ ተቋምን በመንግሥት እንዳቋቁም ስጠይቅ በአገራችን በቆዳና ቆዳ ማምረት ላይ የነበረው፣ የሠራተኛ ውጤት ብቃት አነስተኛ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ቻይናዊው፣ በአንድ ቀን ሦስት ጃኬት ቆዳ ቆርጦ፣ ሰፍቶ፣ ለገበያ ያቀርባል፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጵያዊው ተመሳሳይ ምርት ለማምረት እስከ ሦስት ቀን ይፈጅበታል፡፡ እንግዲህ በዓለም አቀፍ ገበያ ሁለቱም ሲቀርቡ፣ ተመጣጣኝ ዋጋ ሰጥቶ ማን እንደሚያተርፍ ግልጽ ነው፡፡ ቻይናዊው ነው፡፡ በዚህም እኔ ያቋቋምኩት ማሠልጠኛ ተቋም፣ እንደ ግብ የወሰደው፣ ልክ እንደ ቻይናው የሚያመርት ኢትዮጵያዊ ማዘጋጀት ነበር፡፡ አብዛኞቹን ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋም ስንፈትሽ፣ የማሠልጠኛ መሣሪያ እጥረት ለሠልጣኞች ብቁ የተግባር ሥልጠና አለመስጠት፣ የአሠልጣኞች ብቃት አናሳ መሆን፣ ወዘተ. በችግርነት እናገኛለን፡፡

የሥልጠና መሣሪያ ብቁ ሆኖ አለመቅረቡ የሥልጠናውን ብቃትና ጥራት ሙሉ ለሙሉ ይገድለዋል፡፡ አብዛኛው የማሠልጠኛ ቦታ በሠልጣኞች ቁጥር እኩል መሣሪያ ባለመገኘቱ፣ አሠልጣኙ በተግባር ሠልጣኞቹ እንዲሠሩ ሳያደርግ፣ መሣሪያውን ብቻ በማሳየት፣ ሠልጥነዋል ተብሎ እንዲያልፍ ያደርጋል፡፡ ለዚህም ማስረጂያ ሠልጣኞች ተመርቀው ከወጡ በኋላ መሣሪያውን በእጃቸው እንዳልነኩት የሚያስረዱት ነው፡፡ ከዚሁ ጋራ የሚያያዘው በሥልጠና መርሐ ግብሩ ላይ የተነደፈው፣ ሠልጣኞች የተግባር ሥልጠና በኢንዱስትሪ እንዲያደርጉ የሚለው ነው፡፡ የተግባር ሥልጠና በኢንዱስትሪ ያግኙ የሚለው ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡ የመጣውም ‹‹በቃል ካስተማርከኝ ልረሳው እችላለሁ፣ በተግባር ካላሰየኸኝ ግን ዘወትር አልረሳውም፤›› ከሚለው አባባል ነው፡፡ ሌላው ችግር የሆነው የአሠልጣኞች ብቃት አናሳ መሆን ነው፡፡ የአገራችን አሠልጣኞች በአብዛኛው፣ ወይ የመነባንብ፣ ወይም የተግባር ብቻ ናቸው እንጂ ሁለቱንም አያሟሉም፡፡ ይህ ከፍተኛ ችግር ነው፡፡ ሌላው ችግር የቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛ ተቋማትን የሚቀላቀሉት ሠልጣኞች፣ መሄጃ በማጣት መቆያ በማድረግ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ሠልጣኞቹ የመጡት፣ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ያላሟሉ በመሆናቸው ፍላጎታቸው በጊዜ ብዛት የዩኒቨርሲቲን ማሟያ በሟሟላት ሙያውን ለመተው ነው፡፡ ስለዚህ በሥልጠና ተቋሙ ውስጥ ያሉት ያለፍላጎታቸው ነው፡፡

በእኩይ ሥራ የተሠለፉ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የሚገኙት ለዓመታት ሥራ አጥተው በገጠርም በከተማም በወላጆቻቸው ትከሻ ሥር ያሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ምሩቅ ወጣቶች፣ ወላጆቻቸው በአሁኑ ጊዜ በኑሮ ውድነት ትከሻቸው ጎብጦ እያነከሱ ባሉበት ጊዜ መርዳት ሲችሉ፣ ባለመርዳታቸው ልባቸው ተሰብሮ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ በወጣትነት ጊዜ ያሉ ምሩቃን  ደግሞ በእኩይ ሥራ ለተጠመዱ ልሂቃን የቅዳሜ ገበያን ነው የሚሆንላቸው፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሥራ ለምን አልያዙም የሚለውን ችግር ለማየት፣ በአምስት አቅጣጫ ማለትም የአገሪቱ የሥራ ዕድልና የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን አለመጣጣም፣ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትምህርት ወቅቱን የጠበቀ አለመሆኑና የሚሰጡትም ትምህርቶች ጥራት የጎደላቸው መሆናቸው፣ የዩኒቨርሲቲው ትምህርት ለሚፈለገው ሥራ ብቁ ሆኖ አለመገኘት፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲመጡ ይዘውት የሚመጡት ባህሪና አላስፈላጊ የመንግሥት ጣለቃ ገብነት፣ የሚሉትን ልንፈትሽ ይገባናል፡፡

ካለው የኢኮኖሚ ዕድገት (የሥራ ዕድል) በላይ ምሩቃን መብዛታቸው፣ ሥራ አጥ ምሩቃን እንዲበዙ ማድረጉ ዕሙን ነው፡፡ አንድ ምሳሌ በሲቪል ምህንድስና ትምህርት ለሚመረቁ ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ ብቸኛው በነበረው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥራ በሽ ነበር፡፡ ይህ ግን አሁን ብዙም የኢኮኖሚ ዕድገት ካለመኖሩም በላይ በ46 ዩኒቨርሲቲዎች ከሺሕ በላይ የሚመረቁ ሲቪል መሐንዲሶች በመመረቃቸው በአገሪቱ ከሥራ አጦች አንዱ ይህ ምህንድስና ክፍል ሆኗል፡፡ ይህም የሆነው ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስመርቁዋቸው የሲቪል ምህንድስና ምሩቃንና አገሪቱ የምትፈጥረው የሥራ ዕድል ሰማይና መሬት መሆኑ ነው፡፡ ሌሎቹ ችግሮች የሚወራረሱ ናቸው፡፡ ለዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ሥራ አጥነት በዋናነት የሚጠቀሰው፣ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰጡት ትምህርቶች፣ ጥራታቸው የጎደሉ መሆናቸው ነው፡፡ እነዚህም የመጡት በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው ከውጭ ማለት ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲመጡ ይዘውት የሚመጡት ዝግጅትና መጥፎ ባህሪ ናቸው፡፡ ሁለተኛው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያለው ትምህርቱ በጥራት አለመሰጠቱ ነው፡፡

ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲመጡ ይዘውት የሚመጡት ዝግጅት (ውድቀት) ለትምህርት ጥራት መውደቅ እንደ አንዱ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ይኸውም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚመጡት ከ12 ዓመት በላይ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አጠናቀው ሲሆን፣ በዩኒቨርሲቲ የሚቆዩት ደግሞ ከአራት አምስት ዓመት ስለማይበልጥ ከዩኒቨርሲቲው በፊት የሚሰጠው ትምህርት ጥራት የሌለው ከሆነ፣ በዩኒቨርሲቲው ትምህርት ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ይህንንም ለመግለጽ፣ አብዛኛው ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ራሱን በደንብ መግለጽ የማይችል ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ደግሞ በመማር፣ በማጥናት፣ በመመራመርና በመተንትን ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ለዚህ ብቁ ያልሆነ፣ በትምህርት ጥራቱ ላይ አሻራ ይጥላል፡፡

በሌላ በኩል ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲመጡ፣ ይዘውት የሚመጡት መጥፎ ባህሪ፣ ለዩኒቨርሲቲ ትምህርት መውደቅና ከዚሁም ተከትሎ የምሩቃን ሥራ ማጣት ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በደንብ ተምሮ ሥራ ከመያዝ ይልቅ፣ ኅብረተሰቡ ከሦስት ዲግሪ አንድ ሱቅ ሰርቆ ይዞ የተገኘ ወንድ ነው፣ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የሚሉት በወጣቱ ባህሪ ላይ ተቀርፃዋል፡፡ በዚህ የኖረ ተማሪ ከትምህርት ይልቅ፣ ሰርቆ መክበር እንደሚቻል፣ መማር ዋጋ እንደሌለው የሚለው ያይልበትና እንደምንም ብሎ ገልብጦ (ኮርጆ) አልፎ፣ ዲግሪ ለመያዝ ይሯሯጣል፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት በደንብ ተምረው የሚመረቁ የሉም ማለት አይደለም፡፡ እነዚህ በሥራው ዓለምም አሳይተው፣ ውጭ ሄደውም በማዕረግ የተመረቁ አሉ፡፡ ለማንሳት የተፈለገው፣ ዩኒቨርሲቲ ለመማር ገብተው፣ ሳይማሩ ዲግሪ፣ አየር በአየር ለማግኘት የሚጣጣሩትን ነው፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የገቡትን ተማሪዎች ለምሳሌ ብንጠቅስ፣ የአደጉበት ኅብረተሰብ ተፅዕኖ ምን ያህል፣ በወጣቶቹ ባህሪ ላይ አሻራ እንደሚጥል ማሳያ ይሆናል፡፡

እነዚህ አዲስ ገቢ ተማሪዎች የመጀመሪያውን ክፍለ ጊዜ (ሴምስተር) በሚፈተኑበት ጊዜ የሒሳብ ፈተና ተሰረቀ፡፡ ይህ እንደ ታወቀ ዩኒቨርሲቲው ሌላ ፈተና አውጥቶ እንደገና ተማሪዎቹን መፈተን ተገደደ፡፡ እንግዲህ ፈተና መስረቅ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ተለማመዱ እንዳይባል ወደ ዩኒቨርሲቲ የገቡበት ከሦስት ወራት በፊት የተመዘገቡበትም ቀለም ገና አልደረቀም፡፡ ሊሆን የሚችለው ከኅብረተሰቡ ይዘውት የመጡት ባህሪ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ራስ ማጥናት፣ መመራመርና መተንተን የሚጠይቅ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ተማሪዎች ለዚህ ጊዜውም ፍላጎትም ስለሌላቸው፣ ማለፍ ደግሞ ስለሚፈልጉ፣ ላልተገባ ሕገወጥ ይዳረጋሉ፡፡ ሌላ የሠራውን ማቅረብ፣ መኮረጅ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ተማሪው በዚህ ስለተለከፈ ለመሥራት አይፈልግም፡፡ ይህ የሚያሳዝናቸው መምህራን ከመደበኛ የትምህርት አሰጣጥ ሥራቸው ወጥተው ተማሪዎቹ ራሳቸው ማድረግ የሚገባቸውን ጽሑፎች በሙሉ በማዘጋጀትና በመስጠት ‹‹እባካችሁ ይህንን አንብቡ›› እያሉ ሲማፀኑ ይታያሉ፡፡

በሁለተኛ ማንሳት ያለብን፣ በራሳቸው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ወጣቱ የሚማረው ወቅቱን የጠበቀ አለመሆኑና የሚሰጡትም ትምህርቶች ጥራት የጎደላቸው መሆናቸው ነው፡፡ ይህንንም ለማየት ዩኒቨርሲቲዎቹን በሁለት እንከፍላቸዋለን፡፡ ማለትም አዲስ የተከፈቱትን ዩኒቨርሲቲዎችንና የአዲስ አበባ ነባር ዩኒቨርሲቲዎች (የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ቀድሞ በውስጡ የነበሩ የጎንደር፣ የሃረማያ፣ የባህር ዳር፣ የሐዋሳ፣ የጂማ ወዘተ. ኮሌጆችን ይጨምራል)፡፡ አብዛኛው ከአዲስ አበባ ራቅ ብለው የተከፈቱ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች (በትግራይ ያሉትን አይጨምርም)፣ ሲከፈቱ የፖለቲካ ውሳኔ በመስጠት ብቃት ያላቸው መምህራን፣ ቤተ ሙከራዎች፣ ወዘተ. መኖራቸው ሳይረጋገጥ ‹‹እየገነባን እናስተምራለን›› በሚል የተሳሳተ ፖሊሲ በመከፈታቸው ለብ ለብ ባለ የትምህርት ሥርዓት ተመርቀው ብዙዎቹ ሥራ በማጣት፣ ወይም የተማሩትን ቀይረው ሌላ ትምህርት በመማር፣ የበፊቱ ትምህርት ጥቅም ሳይሰጣቸው ቀርቷል፡፡

የትምህርቱ ጥራት በነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ለመውደቅ ከቻለበት አንደኛው ምክንያት የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን መምህራን ተማሪዎችን እንዲያስተምሩ በማድረጋቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ አንድን ትምህርት ለማስተማር መምህሩ በሦስተኛ ዲግሪ ተመርቆ ልምድ ያለው መሆን አለበት የሚለውን የሚፃረር ነበር፡፡ ይህንን መሥፈርት በአዲስ በተከፈቱት ዩኒቨርሲቲዎች ለማግኘት የሚያስቸግር ቢሆንም፣ ሲከፈቱ ቢያንስ የሚያስተምረው መምህር በሚያስተምረው ትምህርት በአንድ ዲግሪ ከፍ ብሎ ልምድ የያዘ መሆኑን መረጋገጥ ነበረበት፡፡ ይህን ለማሟላት ሳይሞከር በነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች መጀመሪያ ዲግሪ ያለውን መምህር የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪን እንዲያስተምር ተደረገ፡፡ በዚህ ብቻ ሳይበቃ በነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች በደንብ ያልተማሩትን የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸውን የእነሱን ምሩቃን ለመምህርነት በመቅጠር ሁለተኛ ዲግሪ እንዲያገኙ በማድረግ ብቃት ያላቸው  መምህራን አፍርተናል በማለት ተማሪዎች እየተቀበሉ በማስተማር ማስመረቅ ቀጠሉ፡፡

ይህም ምክንያት ሆኖ እስካሁን በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ምሩቃን አብዛኞቹ ሥራ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ይህንን ችግር የቀረፉ መስሎዋቸው፣ በአዳዲሶቹ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ መምህራን ድክመታቸውን ለመሸፈን፣ ከሥነ ምግባር ውጪ፣ በደንብ ላልተማሩ ተማሪዎች የተጋነነ (Inflated) ማርክ በመስጠት ምሩቃን የሚያስመዘግቡት ውጤትና የያዙት መካከለኛ ማርክ (Cumulative Grade Point Average, GPA) ባለመጣጣሙ በቀጣሪዎችና በዩኒቨርሲቲዎቹ መካከል ማርኩ ጥርጣሬ ጫረ፡፡ የሚያሳዝነው ከአዳዲሶቹ ዩኒቨርሲቲዎች ወጣት መምህራን ያደረጉትን የተጋነነ ማርክ መስጠት የእኛ ተመራቂዎች ይጎዳሉ በማለት በአዲስ አበባ ነባር ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ አንዳንድ ወጣት መምህራን ያልተሠራበትን ማርክ በመስጠት ሁሉም ደፋኝ ሆኖ እንዲገኝ በማድረግ፣ ጎበዙን ለመየት እንዲያስቸግር አደረጉት፡፡

ወደ አዲስ አበባ ነባር ዩኒቨርሲቲዎች ስንመጣ የተቋቋሙት በጠንካራ መሠረት ላይ ስለሆኑ የጥራት ችግር በአንፃራዊነት ይኖርባቸዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ለዚህም የሚሆነው፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው መምህራን በውስጣቸው ስለያዙ ነው፡፡ ይህም ሲባል ሙሉ በሙሉ በተለያዩ ኮሌጆች የጥራት ችግር አይስተዋልም ማለት አይደለም፡፡ የዚህንም ምንጩን በምናይበት ጊዜ በዋናነት በየዩኒቨርሲቲዎቹ የሚመደቡት የተማሪዎች ብዛት የተማሪዎቹ የመቀበል ብቃት አናሳ መሆን፣ የፍላጎት ዕጦት በዩኒቨርሲቲዎቹ ውስጥ ያለው የአስተዳደር ችግር አላስፈላጊ የመንግሥት ጣለቃ ገብነት ወዘተ. ጎልተው ይወጣሉ፡፡ በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ጎልቶ እየታየ ያለው የአስተዳደር ችግርን ብናይ የዩኒቨርሲቲው ኅብረተሰብ ብዙ ጊዜ የሚለውን ማወቅ ማለትም ‹‹ፖለቲካው አካዴሚውን መምራቱን ከአቆመና መምህራኑ አካዴሚውን መምራት ቢችሉ፣ አሁን ባለው የሰው ሀብት (መምህራን)፣ በዩኒቨርሲቲዎቹ ውስጥ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት መስጠት ይቻላል፤›› የሚለውን መቀበል አለብን፡፡ በእውነትም በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ አላስፈላጊ ከፍተኛ የፖለቲካ የአስተዳደር ጣልቃ ገብነት አለ፡፡

ፖለቲከኞች እስከ ቻሉ ድረስ የእኔ በሚሉት ፖለቲከኛ፣ ቀልደኛ በሆነ የይስሙላ ውድድርና ምርጫ በየኮሌጆቹ በኃላፊነት ያስቀምጣሉ፡፡ አሱም በተዋራጅ የራሱን ሰው በየትምህርት ክፍሉ በኃላፊነት ያስቀምጣል፡፡ የሚገርመው ደግሞ በአዋጅ እንደተደነገገ የሚቀመጡት ምንም ልምድ የሌላቸው ወጣቶች ከአካዴሚው ይልቅ ወደ ፖለቲካ ያደሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ደግሞ ‹‹የትምህርት አካዴሚ›› መምራት ምንም ልምድ ስለሌላቸው ሥራውን ራሳቸው እንደፈለጉት ይመሩታል፡፡ ሁሉም አስተማሪ ልምድ ቢኖረውም ባይኖረውም ‹‹ማስተማር (Course መያዝ)›› አለበት ብለው ይደለድላሉ፡፡ ለእነሱ ሥራ ለሁሉም መፍጠር ነው፡፡ ልምድ የሌለው ወጣት መምህራንን ከመደልደል ወደ ኋላ አይሉም፡፡

 በዩኒቨርሲቲ አሠራር አንድ የዩኒቨርሲቲ ሙያ ለምሳሌ በባዮሎጂ መሠረታዊ ትምህርት የሚገኘው በመጀመሪያ ዲግሪ ላይ ነው፡፡ በባዮሎጂ የመጀመርያ ዲግሪ አገኘሁ የሚል ሰው፣ የባዮሎጂን መሠረታዊ ንድፈ ሐሳብ በመማር፣ በማጥናት፣ በመተንትን ራሱን ብቁ የሚያደርግ ነው፡፡ ከዚያ በላይ ሲማር ዕውቀቱን ያስፋፋል እንጂ መሠረቱ በመጀመርያ ዲግሪ የተማረው ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ዋናው ግብ፣ በተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች መሠረታዊ ትምህርት በማስተማር በተወሰነ የሥራ ሥልጠና ለመሥራት ብቁ ዜጋ ማፍራት ነው፡፡ ስለዚህ በዩኒቨርሲቲዎች ይህንን የሙያ መጀመርያ መሠረታዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን ተባባሪና ሙሉ ፕሮፌሰሮች መሆን አለባቸው ተብሎ ነው የሚታመነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ነባር ዩኒቨርሲቲዎች ኮሌጆችና ኢንስቲትዩቶች ግን በወጣቶች አመራሮች ምክንያት ብዙ ልምድ ያላቸው መምህራን እያሉ በአብዛኛው መደበኛ የመጀመርያ ዲግሪ ትምህርት የሚሰጠው በሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች ነው፡፡

አንድ ምሳሌ ላቅርብ አንድ ባለፈው ዓመት የተመረቀ ተማሪ፣ በአምስት ዓመት ቆይታው አንድም በሦስተኛ ዲግሪ የተመረቀ አስተማሪ እንዳላስተማረው ሁሉም መምህራኑ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች እንደሆኑ ነግሮኛል፡፡ የሚገርመው ይህ ወጣት የሚለው የትምህርት ክፍል ውስጥ ብዙ በሦስተኛ ዲግሪ ተመርቀው ልምድ ያላቸው መምህራን እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ እንግዲህ በእንደዚህ ያሉ የትምህርት ክፍል የሚማሩ ወጣት መሪዎች እየሠሩ ያሉት ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ማለትም ‹‹መደበኛ የመጀመርያ ዲግሪን ማስተማር ያለባቸው ብቃትና ልምድ ያላቸው መምህራን መሆን አለባቸው፤›› ከሚለው ዓላማ ያፈነገጠ ነው፡፡ ወጣቶቹ የሚሰጡት ምክንያት ‹‹ብቃትና ልምድ ያላቸው መምህራን የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች እንዲያስተምሩልን ነው፤›› የሚል ነው፡፡ ይህ ግን ውኃ የሚቋጥር አይደለም፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሦስተኛ ዲግሪ የከፈተው ለማስተማር ብቃት አለኝ ብሎ ነው እንጂ መደበኛ የመጀመርያ ዲግሪን ትምህርት ለመተካት አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ላይ የሚሰጠው ትምህርት፣ ዕውቀትን ለማሳደግ (Advanced Courses) ነው እንጂ መሠረታዊ ትምህርት የሚማርበት አይደለም፡፡ ለዚህም ነው አብዛኛው የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎቹ፣ በመማር ማስተማሩ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ አጭር መግቢያ ይሰጣል፡፡ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎቹ ማጣቀሻን ዋቢ በማድረግ ግብረ መልስ ይሰጣሉ፡፡ ትምህርቱ የሚካሄደው ሰጥቶ በመቀበል ነው፡፡ መምህሩም ተማሪወ‹ም የሥራ ድርሻቸው እኩል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች፤ በተለይ የሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብርን የምርምር ሥራ ውጤት በማድረግ ኮርሶች (Course Work) የላቸውም፡፡ የቃል ትምህርቱን ራሱ ያጠናዋል በማለት ነው፡፡ ታዲያ ለምን እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች መደበኛ ሥራቸውን ወደ ጎን ትተው ‹‹ኮርስ ወርክ›› ለሦስተኛ ዲግሪ አካተቱ ለሚለው መልሱ በአገራችን የሚሰጠው የመጀመርያ ዲግሪ ትምህርትም ሆነ የሁለተኛ ዲግሪ ጥራታቸው የወደቁ ስለሆነ፣ እነሱን ለማካካስ አካተቱ እንጂ መደበኛውን ሥራ እንዲተካ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ሌላው መጠቀስ ያለበት ፕሮፌሰሮቹም የመጀመርያ ዲግሪ ተማሪዎችን አለማስተማራቸው ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡ ምክንያቱም ቢባል ላስተምር ሳይሉ ዝም በማለታቸው በራሱ የማይተማመን ትውልድ እየፈጠሩ መሆኑ ነው፡፡

በተያያዥ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት በአገራችን በቅርቡ እየተስፋፋ የመጣው፣ ዕውቀትና ልምድ ያለውን የዕድሜ ባለፀጋ ገፍትሮ፣ ዲግሪ ይዞ ምንም ልምድ በሌለው የመተካቱ ሁኔታ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ከመሪዎች ጀምሮ ‹‹ሽማግሌዎቹ በወጣት መተካት አለባቸው›› ብለው የት ቦታ እንደሆነ ሳይጠቅሱ የሚናገሩት ችግር እየፈጠረ መሆኑ ነው፡፡ ለተራ ወታደር በማምረቻ አካባቢ ወዘተ ከሆነ፣ ወጣት ቢይዘው አባባሉ ትክክል ነው፡፡ ወጣቱ ጉልበት ስላለው የበለጠ ሊሮጥ፣ ሊያመርት ወዘተ ይችላል፡፡ ከነዚህ ውጪ ግን ሽማግሌው በዕውቀት ላይ ልምዱ ተጨምሮ፣ አመርቂ ውጤት ያመጣል፡፡ ለዚህም ነው በብዙው ዓለም ፕሬዚዳንቶች፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ የንግድ ድርጅቶች ወዘተ. የሚሆኑት ብዙ ልምድ ያላቸው ዕድሜ ጠገብ ናቸው፡፡ እነዚህ መሪዎች ዲግሪያቸው ከወጣቱ እኩል ነው፡፡ አንድም ዓይነት ነው፡፡ ከወጣቱ የሚለያቸው ለዓመታት ያካበቱት ልምድ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ደግሞ ዕውቀትና ልምድ ያለው ይከበራል፡፡ ዕውቀትና ልምድ ያለው በአሠራር ላይ የሚታየው ልክ እንደ ወታደር ወይም እንደ ቤተክህነት ሥርዓት ነው፡፡ ወታደሮቹ ጄነራልን፣ ደቀ መዛሙርቱ ሊቃውንቱን፣ ወጣት መምህራን አንጋፋውን በመከተል የሚሠሩት ሥራ ስኬታቸው አስተማማኝ ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች አላስፈላጊ የመንግሥት ጣለቃ ገብነት ለትምህርት ጥራት መውደቅ ምክንያት እየሆነ መጥቷል፡፡ አዳዲሶቹ ዩኒቨርሲቲዎች የፌዴራል መሆናቸው ቀርቶ፣ ክልሎች በፖለቲካ መሥፈርት ነው የሚያስተዳድሯቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱን ብሎም መምህራኑ የሚመለመሉት በወንዜ ልጅነት ነው፡፡ እነዚህም ብቃት የሌላቸው አመራሮች እንዳለ እንደ ወረደ የፖለቲካ ሰዎች የሚሰጡዋቸውን መመርያዎች በመቀበል ለትምህርቱ ጥራት መውደቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርም በእነዚህ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ያለውን የአመራር ክፍተት እሸፍናለሁ በማለት፣ የአገራችንን የትምህርት ሥነ ልቦና ያላገናዘቡ መመርያዎች በመማር ማስተማሩ ላይ በማውጣት፣ ለትምህርት ጥራት መውደቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር በአንድ ወቅት አውርዶት ከነበራቸው አፍራሽ መመሪያዎች ከሆኑት፣ ‹‹የተቀበላችሁትን ሙሉ በሙሉ አስመርቁ›› የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ይህንንም ለማጠናከር ‹‹ተማሪን ያለማውደቅ ዘይቤ (Zero Attrition Rate)›› የሚል ፖሊሲ አውጥቶ ነበር፡፡ በደንብ አጥንተው ለመመረቅ የማይፈልጉ ተማሪዎቹ በዚህ ላይ የተሳሳተ ሐሳብ በመውሰዳቸው ማለትም መምህራኑ ተማሪዎችን እንዲይጥሉ መመርያ አለ በሚል፣ አብዛኛው ተማሪዎች ‹‹ባናጠናም እናልፋለን›› በሚል ሰበብ ሳይዘጋጁ ለፈተና መቅረብ የተለመደ እየሆነ ሄደ፡፡ ከዚህም ጋራ ተመሳሳይ የሆነ መመርያ፣ አነስተኛ ውጤት (የወደቀ ተማሪ) ያመጣውን ተማሪ፣ ‹‹መምህሩን ተማሪውን እንደገና አስተምረህ፣ በሳምንት በማይሞላ ጊዜ እንዲያልፍ አመቻች (Fx)›› የሚለው ሌላው፣ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያለው የማስተማር ብቃት ለትምህርት ጥራት ውድቀት መሆኑ ነው፡፡ እንደነዚህ ያሉ መመርያዎች ያላጠናን ተማሪን ‹‹እንደምንም ብለህ አሳልፈው›› የሚሉ ስለሆኑ ተጠራቅመው ‹‹ምንም የማያውቅ ሥራ አጥ ምሩቅ›› ማፍራት ነው፡፡ እንግዲህ በቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛና በዩኒቨርሲቲዎች ለእኩይ ተገባራት አነሳስተዋል ካልኩት ምክንያቶች አንዱ የሆነውን የትምህርት ጥራትና ይህንንም ተከትሎ የመጣውን የሥራ አጥነት ችግሮች አንዳንዶቹን ከዘረዘርኩ መፍትሔዎቹን በጥቅሉ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

ይቀጥላል…

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በላይ ወልደየስ (ዶ/ር-ኢንጂነር) የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ስፔሻላይዝድ ያደረጉት ደግሞ በፔትሮኬሚካል ኢንጂነሪንግ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2015/16 የአስተማሪነት ልዕልና ሽልማትን (Distinguished Teaching Award) ተቀብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ መሥራች አባልም ናቸው፡፡  ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው belay160@yahoo.com  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles