‹‹እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰን!›› መጪው ዘመን የሰላም፣ የፍቅር፣ የብልፅግና ይሁንልን፡፡ የ2014 ዓ.ም. እንደ አገር ብዙ ፈተና ያሳለፍንበት በመሆኑ መጪው ዘመን ከዚህ አዙሪት የምንወጣበትም ይሁን፡፡ ለተከታታይ ዓመታት የገጠሙን ተግዳሮች እንደ አገር ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል። እንደ ሸማች ሆነን ስናስበው በ2014 ዓ.ም. እና ከዚያም ቀደም ባሉትን ዓመታት የፈተነን የዋጋ ንረት አልፈታ ያለ ቋጠሮ ሆኖብን ወደ አዲሱ ዓመት እየተሻገርን ነው፡፡
ሸማቾችና ገበያው ሊጣጣሙ አልቻሉም፣ ገበያው ግሏል፡፡ በየዕለቱ እየጨመረ የመጣውን የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ሊቋቋመው አልቻለም፡፡ በእርግጥ መንግሥትም ልጓም ያጣውን የዋጋ ንረት መቆጣጠር አልቻለም፡፡ ወቅታዊው የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት የቱንም ያህል ውጫዊና ውስጣዊ ተግዳሮቶች ጭምር ታክለው የፈጠሩት ቢሆንም፣ ቅጥ ያጣው የግብይት ሥርዓት ደግሞ ችግሩን አብሶታል፡፡ በተለይ በ2014 ዓ.ም. ብልሹ የግብይት አሠራሮች ጎልተው ታይተውበታል፡፡
በተለይ ዋጋ ጨመረ የሚለው ሮሮ ከልክ በላይ እየተስተጋባ ቢሆንም፣ የችግሩን ጥልቀት ያህል ለመፍትሔ እየተሠራ ባለመሆኑ ይህንኑ ብዥታና ምሬት ይዘን አዲሱን ዓመት ለመቀበል ተገደናል፡፡ ዓመቱን በሙሉ ‹እንዲህ ያለው ዕቃ ዋጋው ይህንን ያህል ደረሰ› እና ‹እንዲህ ያለው ምርት ደግሞ ዋጋው በዚህን ያህል ጨምሮ እየተሸጠ ነው› እያልን ለመጮህ ተገደናል፡፡ ምርቶች ተገማች ባልሆነ ሁኔታ ዋጋቸው ሰማይ እንዴት ወጣ የሚል ጠያቂ የለምና ሊጨምሩ አይችሉም የተባሉ ምርቶች ሁሉ ወደዚሁ መስመር እየገቡ የሸማቹን ምሬት አብሰውታል፡፡
ከሰሞኑ እንኳን አንድ ኪሎ ቲማቲም 75 ብር ሲሸጥ፣ ሙዝ በ60 እና 70 ብር በኪሎ ሲቸበቸብ፣ ብርቱካን 80 እና 90 ብር እስከመሸጥ ሲደርስ፣ ‹‹ኧረ ይኼ ነገር መጨረሻው ምን ሊሆን ነው?›› ብሎ በተቆርቋሪነት መፍትሔ ለመፈለግ የሚሞክር አልተገኘም፡፡ ከምርቶቹ መነሻ ቦታ የሚሰማው ግን የተለየ የዋጋ ለውጥ እንደሌለ ነው። በመሆኑም ችግሩ ሰው ሠራሽ ስለመሆኑ እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡ በእርግጥ ትክክለኛ ዋጋቸው ሆኖ ነው ወይ? ‹‹ኧረ የስኳር ጉዳይ ይታሰብበት!›› እየተባለ በኪሎ 40 ብር የሚሸጥ ስኳር፣ በአንድ ጊዜ 120 ብር የሚገባበት ሚስጥር ምንድነው? ሌሎች መሠረታዊ ሊባሉ የሚችሉ ምርቶችም እንዲሁ ዋጋቸው እየተሰቀለ አጀብ እያልን ዓመቱን አጠናቀናል፡፡
በሌሎች ግብዓቶች ላይ የሚታየው አስገራሚ የዋጋ ጭማሪና ብልሹ የግብይት ሥርዓት እንዲስተካከል ወይም ቢያንስ የዋጋ ጭማሪው ምክንያት ይህ ነው ብሎ የሚነግረን ማጣት በራሱ ሕመም ነው፡፡ ይህ ጉዳይ እንደ ዋዛ እየታለፈና ዝም እየተባለ የመቀጠሉ ነገር ደግሞ ካልቆመ፣ ሊፈጠር የሚችለው ቀውስ ልንቆጣጠረው ከምንችለው በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ብልሹ አሠራሮች ለችግሩ መባባስ ምክንያት ስለመሆናቸው የብረትና የሲሚንቶ ግብይትን ለማስተካከል ተወሰዱ የተባሉ ዕርምጃዎች መፍትሔ ያለማምጣታቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡
መንግሥት አንድ የተበላሸን የግብይት ሥርዓት ለማስተካከል በተደጋጋሚ እወስዳቸዋለሁ የሚላቸው ዕርምጃዎች ውጤት ሊያመጡ ካልቻሉ፣ ትልቅ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ገበያው የመንግሥት ሕግ በማይገድባቸው ጡንቸኛ አካላት የተያዘ ነው ወደሚለው አመለካከት ይወስደናል፡፡
ወይም ያልተገባ ንግድ ይካሄድበታል በተባሉ የቢዝነስ ዘርፎች ውስጥ የመንግሥት ባለሥልጣናት ራሳቸው አሉበት ብለን ድምዳሜ እንድንወስድ ያደርገናል፡፡
በዚህን ያህል ደረጃ ደፈር አድርገን ለመናገር የምንገደደውም፣ በቀላሉ ሊስተካከሉ የሚችሉ ብልሹ አሠራሮችን ወደ መስመር በመመለስ ገበያውን ማረጋጋት የሚቻል እየሆነ ሲታለፉ የምንመለከት በመሆኑ ነው፡፡
አገር በዋጋ ንረት እየታመሰ፣ የመፍትሔ ያለህ እያለ፣ ይህንን የብዙዎች ድምፅ በፀጥታ ማለፍ የብልሹ አሠራሩ ተባባሪ ከመሆን ውጪ ምን ይባላል? ባጠናቀቅነው 2014 ዓ.ም. በዚህ ረገድ ብዙ ግድፈቶች ታይተዋል፡፡ ሸማቹን ሊደግፉ የሚችሉ ውሳኔዎች በተገቢው መንገድ አልተተገበሩም፡፡ ስለዚህ አዲሱን ዓመት ስንቀበል ሸማች በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያለውን ብልሽት መንግሥት እንዳላየ መሆኑን እንዲያቆም ነው፡፡
አሁን ላይ በግብይት ውስጥ የሚፈጸም ዓይን ያወጣ ብልግና ቆንጠጥ የማይደረግ ከሆነ ችግሩ ለሁሉም የሚተርፍ ይሆናል፡፡ መንግሥት የዋጋ ንረቱን እንዳይብስ ‹ሠርቻለሁ ግን ውጤት አላመጣልኝም› ካለ፣ ለምን ብሎ ራሱን መጠየቅ የተሻለ አማራጮችን መውሰድ ግዴታው መሆን አለበት፡፡
በዚህ በችግር ወቅት ደግሞ ገበያው ዝም ብሎ አይለቀቅም፡፡ ባለፈው ዓመት ዋጋቸው ላይ የደረሱ ምርቶች መልሰው እንዲቀንሱ የሚያስችል አሠራር ወይም የቁጥጥር ሥርዓት ካልተበጀም የግብይት ሥርዓቱ እንደተፈገለ እንዲሆን ተፈልገዋል ማለት እንደሆነ መረዳቱ ጥሩ ነው፡፡
በአጠቃላይ ሥርዓት የሌለው ግብይትና እንዳሻቸው ለመሆን የሚሹ ነጋዴዎች መስመር እንዲይዙ ካልተደረገ ከዋጋ ንረት አዙሪት ውስጥ ለመውጣት እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን በግልጽ መናገር ያስፈልጋል፡፡
ስለዚህ በየዓመቱ እንደምንለው የሸማቹን ድምፅ የሚሰማ ጆሮ፣ ገበያውን የሚያረጋጋና ብልሹ የግብይት ሥርዓት የሚያስተካክል ፈጻሚና አስፈጻሚ ይሰጠን ነው፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!