Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በንግድ ሕጉ የተናጠል ክሶችን ማቋረጥ አንዱ ዓላማ ብክነትን ለማስቀረት ነው›› አቶ ፍቃዱ ጴጥሮስ፣ የሕግ ባለሙያ

ኢትዮጵያ ከ60 ዓመታት በኋላ የንግድ ሕጓን አሻሽላለች፡፡ የተሻሻለው የንግድ ሕግ ሦስት መጻሕፍት ታትመው ሥራ ላይ ውለዋል፡፡ ይህ የንግድ ሕግ ኢትዮጵያ ከወቅቱ ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አብራ እንድትራመድ የሚያስችላት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከዓለም አቀፉ የንግድ አሠራር ጋር የተናበቡ ድንጋጌዎች በአዲሱ የንግድ ሕግ ውስጥ መካተታቸው፣ ለአገራዊ ኢኮኖሚው ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ከሚስማሙት የሕግ ባለሙያዎች መካከል በዚሁ ዘርፍ በመምህርነትና በጥብቅና ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ፍቃዱ ጴጥሮስ አንዱ ናቸው፡፡ አዲሱ የንግድ ሕግ ብዙ ማሻሻያዎች እንደተደረገበት የሚገልጹት አቶ ፍቃዱ፣ አተገባበሩ ላይ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ያመለክታሉ፡፡ የንግድ ሕጉ ጠቀሜታው የጎላ ቢሆንም፣ እንደ ባንክ ያሉ ዘርፎች ግን በንግድ ሕጉ ውስጥ የተካተተ አንድ አንቀጽ ሥጋት እየፈጠረባቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የባንኮችን ሥጋትና የአክሲዮን ኩባንያዎችን በተመለከተ በንግድ ሕጉ በተካተቱ ድንጋጌዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ አቶ ፍቃዱን አነጋግሯቸዋል፡፡   

ሪፖርተር፡- አዲሱ የንግድ ሕግ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳለው ተገልጿል፡፡ ይህ ሕግ ምን ያህል እየተተገበረ ነው?

አቶ ፍቃዱ፡- አዲሱ የንግድ ሕግ ለረዥም ጊዜ ዝግጅት ሲደርግበት ቆይቶ የወጣ ነው፡፡ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን አካትቷል፡፡ በድሮ የንግድ ሕግ ውስጥ ያልነበሩ ከጊዜው ጋር የሚሄዱ አዳዲስ ድንጋጌዎችን አካትቶ ይዟል፡፡ የንግድ እንቅስቃሴን ለማቀላጠፍ የሚረዱ ድንጋጌዎች አሉት፡፡ አንድ ኩባንያ ለማቋቋም በፊት እንደ ችግር የሚታዩ ነገሮችን አስወግዶ በአዲስ ተተክቷል፡፡ አንድ ግለሰብ ኃላፊነቱ የተወነ የግል ማኅበር ማቋቋም የሚችልበትን ዕድል ሁሉ ፈጥሯል፡፡ በአጠቃላይ ብዙ ኢኮኖሚዊ ጠቀሜታ ያላቸው ድንጋጌዎች እንዲኖሩት ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ ሕግ ግን አስፈጻሚውና ሠራተኞቹ ካልገባቸው ትልቅ ችግር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ የንግድ ሕግ በትክክል እንዲተገበር ምን ያህል እየተሠራበት ነው? እናንተም እንደ ሕግ ባለሙያ ምን አስተዋጽኦ እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ፍቃዱ፡- በግሌ መጽሐፍ የጻፍኩት ሕጉን ለማብራራትና ለማስረዳት ነው፡፡ ‹‹ይህ ሕግ በኩባንያዎች ላይ ምን ለውጥ አምጥቷል?›› የሚለውን ለማሳየት ነው፡፡ የተለዩ የሕግ ፎርሞች አሉ፡፡ አዳዲስ ነገሮች ሲከሰቱ ይህ እንዲህ ተቀይሯል በማለት በተወሰኑ ርዕሶች ላይ የሚጻፉም አሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን መንግሥት ወይም የመንግሥት ተቋማት ምን ያህል ለሠራተኞች እነዚህን አዳዲስ ሕጎች አስርፀዋል?  አስረድተዋል? ለሚለው ብዙ መረጃ የለኝም፡፡ እንዳልከው ግን የሚያሳስብ ነገር አለው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ሕጉን የመገንዘብና የመረዳት ችግር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ የንግድ ሕግ በርካታ አዳዲስ ሕግጋት እንዳሉት በተለያዩ መንገዶች ተጠቅሷል፡፡ የሕጉ መውጣት ጥቅም ይሰጣል ተብለው ከሚጠቀሱ ጉዳዮች አንዱ የአክሲዮን ከባንያዎችን በተመለከተ የተካተቱ አንቀጾች ናቸው፡፡ ይህንን ጉዳይ ያነሳሁት አክሲዮን ኩባንያዎችን በይበልጥ እንዲስፋፋ ዕድል ይሰጣል የሚል ትንተና ስላለ ነው፡፡ ይህም ምልከታ ምን ያህል እውነትነት አለው? ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ የተቋቋሙት ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውጤታማ ሆነው ቆይተዋል? ወይም ውጤታማ ሆነው ቀጥለዋል? በአንፃሩ በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ የሚቋቋሙ ሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች ግን በብዙም ውጤታማ ሲሆኑ አይታይም፡፡ በአዲሱ የንግድ ሕግ የአክሲዮን ኩባንያዎች ውጤታማ ሊሆኑበት የቻሉበት የተለየ ምክንያት ምንድነው? ስለአክሲዮን ኩባንያዎች አዲሱ ሕግ ምን ይላል? ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ ያሉ የቢዝነስ ዘርፎች በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ ተቋቁመው ውጤት ሳያመጡ የቀሩበት ምክንያት ምንድነው ብለው ያምናሉ?

አቶ ፍቃዱ፡- አዲሱ ሕግ በዚህ ረገድ ያሻሻላቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በአክሲዮን የተቋቋሙት ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውጤታማ ናቸው፡፡ በሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች የአክሲዮን ኩባንያዎች እንዳልከው ውጤታማ ሲሆኑ አይታይም፡፡ ለምሳሌ በትራንስፖርት፣ በማምረት ሥራ፣ በግብርናና በመሳለሱት ዘርፎች የአክሲዮን ኩባንያዎች ለምንድነው ያልተስፋፉትና ውጤታማ ያልሆኑት ለሚለው ጥያቄ አንዱና ቀላሉ መልስ እነዚህን የሚቆጣጠር አካል ስለሌለ ነው፡፡ ለምሳሌ በትራንስፖርት ዘርፍ የተቋቋሙ ብዙ አክሲዮን ማኅበራት ከስረው ወጥተዋል፡፡ በሥራ ላይ ያሉትም ቢሆኑ ያን ያህል አትራፊ አይደሉም፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው በግሉ አንድ ሚኒባስ ገዝቶ ሲሠራ በሦስትና በአራት ዓመታት ውስጥ አትርፎ የሚቀየር ከሆነ፣ የትራንስፖርት ቢዝነስ በአክሲዮን ኩባንያ ሲሠራ የማያተርፍበት ምክንያት የለም፡፡ ስለዚህ በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ ቢሠራ ሥራው ስለማያዋጣ አይደለም ማለት ነው፡፡ በአክሲዮን የተቋቋሙት የባንክና የኢንሹራንስ ዘርፍ ደግሞ በጣም አዋጭ ስለሆኑ አይደለም፡፡ ስለዚህ ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ የአክሲዮን ኩባንያዎች ውጤታማ ያልሆኑት ቁጥጥር ስለሌለ ወይም እነዚህን የሚቆጣጠር አካል ባለመኖሩ ነው፡፡ የብዙ ሰዎችን ሀብት አሰባስቦ የሚያስተዳድር ማንኛውም ተወካይ ወይም ባለአደራ ቦርድ የሚቆጣጠረው ሥርዓት ካልተዘረጋ ለመዘረፍ ወይም ለስርቆት በጣም የተመቻቸ ነው፡፡ በፋይናንስ ዘርፍ ብሔራዊ ባንክ ስለሚቆጣጠር ይህንን ጉዳይ ምን አደረሳችሁት እያለ በጥብቅ ስለሚከታተል ውጤት ተገኝቷል፡፡ አክሲዮን ኩባንያዎቹን የሚመሩ ሹሞችን ሳይቀር ያፀድቃል፡፡ ተሿሚው ማነው? የትምህርት ዝግጅቱና ልምዱ ምንድነው? ብሎ በጥልቀት ስለሚቆጣጠር በአክሲዮን የተቋቋሙ የባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጣም አድገዋል፣ አትራፊ ሆነዋል፡፡ በሌሎች ግን ተመሳሳይ ቁጥጥር ማድረግ የሚመከርም የሚቻልም አይደለም፡፡ ልክ እንደ ብሔራዊ ባንክ ሁሉንም የአክሲዮን ኩባንያዎች ልቆጣጠር ብትልም አቅም አይፈቅድም፣ ሥራውም አይሠራም፡፡ ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚያደርገውን 20 በመቶ እንኳን ቁጥጥር ማድረግ ቢቻል፣ ሌሎች የአክሲዮን ኩባንያዎችም ሊያድጉና ሊያብቡ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች ወደ 100፣ ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግሞ ወደ 50 የሚሆኑ መመርያዎች አሉት፡፡ ሌሎች የአክሲዮን ኩባንያዎችን ለመቆጣጠር ንግድ ሚኒስቴር አንድ መቶ መመርያ ባያወጣ እንኳ አሥር መመርያ ቢያወጣና ቢቆጣጠር፣ እንዲሁም ቢያስፈጽም ሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች ያድጋሉ ብዬ አስባለሁ፡፡    

ሪፖርተር፡- የአክሲዮን ኩባንያዎችን የተመለከቱ በአዲሱ ንግድ ሕግ ውስጥ የተካተቱት ድንጋጌዎቹ ያመጡት አዲስ ነገር ምንድነው? እንዴትስ ነው የሚተገበሩት?

አቶ ፍቃዱ፡- የንግድ ሕጉ በአዋጅ ደረጃ ያለ ትልቅ ሕግ ነው፡፡ ጠቅለል ያለ ሕግ ነው፡፡ የአፈጻጸም ዝርዝር መመርያዎች ሊያስፈልጉ ይችላሉ፡፡ ዝርዝር ስታንዳርዶች፣ መመርያዎችና መስመሮች ሊያስፈልጉት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በአዲሱ ሕግ የተሻሻሉ በርካታ ነገሮች አሉት፡፡ በተለይ ደግሞ አነስተኛ ድርሻ ያላቸውን ባለአክሲዮኖችን የሚጠብቁ ብዙ ድንጋጌዎች በአዲሱ የንግድ ሕግ ውስጥ ተካትተዋል፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህ ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ ያሉ የአክሲዮን ኩባንያዎች ውጤታማ ላለመሆናቸው ትልቁ ችግር ለስርቆት፣ ለዘረፋና ለምዝበራ ምቹ መሆናቸው ነው፡፡ ምዝበራውን ሁለት ቡድኖች ናቸው የሚፈጽሙት፡፡ አንደኛው በዚያ አክሲዮን ውስጥ በጣም ትልልቅ ድርሻ ያላቸው አካላት ናቸው፡፡ እነሱ አነስተኛ ድርሻ ያላቸውን ባለአክሲዮኖች በድምፅ ስለሚበልጡ የሚፈልጉትን የመሾም ሥልጣን ስላላቸው እነሱ ይመዘብራሉ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ትልልቅ አክሲዮን ያላቸው ጥቂት ባለአክሲዮኖች ሳይኖሩ ሲቀሩና የአክሲዮን ኩባንያው የተበታተኑ አባላት ካለው ደግሞ መዝባሪ የሚሆኑት ሥራ አስፈጻሚዎች ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ውጤታማ የማይሆኑት፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን የአክሲዮን ኩባንያዎች ውጤታማ የማይሆኑት እንዲህ ያሉ ችግሮች ስለሚጋጥሟቸው ነው ከተባለ፣ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አዲሱ የንግድ ሕግ ያስቀመጠው መፍትሔ አለ?

አቶ ፍቃዱ፡- አዲሱ የንግድ ሕግ እንዲህ ላሉ ችግሮች መፍትሔ ይሆናል ብሎ ያስቀመጠው ነገር አለ፡፡ አነስተኛ ድርሻ ያላቸው ባለአክሲዮኖችን ለመጠበቅና ለመደገፍ ብዙ ድንጋጌዎችን አካትቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ለግንዛቤ እንዲረዳ እንደ ምሳሌ ሊጠቀሱልኝ የሚችሉት አለ?

አቶ ፍቃዱ፡- ለምሳሌ በአክሲዮን ሕጉ ውስጥ የተቀመጠው ትልቁ ነገር በኩባንያውና በሚመሩት ሥራ አስፈጻሚዎች መካከል የሚደረግን ውል መቆጣጠር አንዱ ነው፡፡ እንዲሁም በኩባንያውና ትልልቅ የአክሲዮን ድርሻ ባላቸው አባላት መካከል የሚደረገውን ውል መቆጣጠር ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ በዋናነት ምዝበራ የሚፈጸመው በግብይት ሒደት ነው፡፡ አገልግሎት ያቀርብና ያልተመጣጠነ ዋጋ ያገኛል፡፡ ወይም ዝቅተኛ ደረጃ ያለው አገልግሎትና ዕቃ አቅርቦ ከፍተኛ የሚባል ክፍያ ይቀበላል፡፡ ባያቀርብ ላይከሰስ ይችላል፡፡ እንዲህ ያሉ ተዘዋዋሪ የሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ ወይም ደግሞ ይህ ሥራ አስፈጻሚ ወይም ትልቅ አክሲዮን ድርሻ ያለው አባል ሌላ ድርጅት ያቋቋምና ከዚያ ድርጅት ጋር የአክሲዮን ኩባንያው እንዲዋዋል በማድረግ፣ ሀብት ወደ እዚያ እንዲሄድና እንዲፈርስ ሊያደርግ ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን አዲሱ የንግድ ሕግ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ዝርዝር ጉዳዮችን አስቀምጦ ነው የሚቆጣጠረው፡፡   

ሪፖርተር፡- አሉ የተባሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ታስበው በንግድ ሕጉ የተቀመጡ አሁን የጠቀሱልኝን ድንጋጌዎችን መሠረት በማድረግ ቁጥጥሩን የሚያካሂደው ማነው? በምን መንገድ ነው የሚቆጣጠረው? ለዚህስ ዝግጅት አለ?

አቶ ፍቃዱ፡- አሁን ትልቁ ችግር እሱ ነው፡፡ ሕጉ እንደ ጠቀስኩልህ ያሉ ችግሮች እንዳይፈጸሙ ይከለክላል፡፡ ምን ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት እንዳለባቸው ዝርዝር ነገሮችን ያስቀምጣል፡፡ አሁን ችግሩ ይህንን የሚከታተልና የሚያስፈጸም ባለሥልጣን አለመኖሩ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ዝርዝር መመርዎችን እያወጣ ባንኮችን ይቆጣጠራል፡፡ ሪፖርት አምጡልኝ ይላል፡፡ ራሱ ሄዶ ይመረምራል፡፡ እዚህ ላይ ግን ተመሳሳይ ነገር የሚያደርግ የለም፡፡ ቢያንስ አዲሱ የንግድ ሕግ ከወጣ በኋላ ግን ምናልባት የተሻለ መረዳትና ዝግጁነት አለ ብዬ አገምታለሁ፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ንግድ ሚኒስቴር መቆጣጠር ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአዲሱ የንግድ ሕግ ውስጥ የካፒታል ገበያን የተመለከቱ የተለያዩ ድንጋጌዎች አስቀምጧል፡፡ ተቆጣጣሪ አካልም ይቋቋማል ተብሏል፡፡ ከአክሲዮን ገበያ ጋር የተያያዘ ስለሆነ በዚህ ላይ ያለዎት ምልከታ ምንድነው?

አቶ ፍቃዱ፡- ከዚህ የንግድ ሕግ ውጪ ቢሆንም፣ እሱ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጣም ከፍ ያለና ኃይለኛ ተቋም ነው፡፡ የፋይናንስ ተቋማትን ብቻ ሳይሆን ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ ያሉትንም ሊቆጣጠር የሚችል ነው፡፡ እሱ የሚቆጣጠራቸው እሱ ጋ ሲመዘገቡ ነው፡፡ በካፒታል ገበያ ውስጥ ያሉትን ተዋንያን ነው የሚቆጣጠረው፡፡ ዝርዝር መመርያዎች ገና አልወጡም፡፡ አሁን ‹‹ኢምፕሊመንቴሽን ቲም›› ተብሎ በብሔራዊ ባንክ ሥር የተቋቋመ አንድ የኤክስፐርቶች ቡድን አለ፡፡ ብዙ ነገር እየሠሩ ነው፡፡ ማነው በዚያ የሚካተተው የሚለውን ገና እያጠኑት ነው፡፡ መመርያ ከመውጣቱ በፊት ልንል የምንችለው አክሲዮን ወይም ሰነድ የሚሸጥ ማንኛውም ኩባንያ ይገደዳል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ተቋም በጣም ጠንካራ ቁጥጥር የመዘርጋት ሥልጣን በአዋጅ ተሰጥቶታል፡፡ እዚያ ውስጥ የሚመዘገቡ ተቋማት፣ ትልቅ ድርሻ ያላቸው ግለሰቦች ወይም ሥራ አስፈጻሚዎች እንደፈለጉ እንዳይፈነጩ ያደርጋል፡፡ ድርጅቶችን የሚመዘብሩበትን ቀዳዳዎች በሙሉ ያጠፋል ተብሎ ይታሰባል፡፡    

ሪፖርተር፡- የንግድ እንቅስቃሴዎች እየተለወጡ ነው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጦች ቴክኖሎጂ ቀመስ እየሆኑ ነው፡፡ የገንዘብ ዝውውሮችና ግብይቶችም በዚሁ መንገድ መከናወን ጀምረዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን እንደ ኤጀንት ባንኪንግ ያሉትን ጨምሮ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትን ሥራ የሚያከናውኑ ድርጅቶችና አገልግሎቶች እየተፈጠሩ ነው፡፡ እንደ ቴሌ ብር ያሉ አገልግሎቶች ገበያ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ስለዚህ በቴክኖሎጂ ቀመስ አገልግሎቶች በትሪሊዮን ብሮች ማዘዋወር ተጀምሯል፡፡ ይህ አሠራር የሆነ የመቆጣጠሪያ ዘዴና ሕግ ያስፈልገዋል የሚለው አስተያየት እንደተጠበቀ ሆኖ ለአደጋ የተጋለጠ ስለሚሆን በዚህ ላይ በንግድ ሕጉ ውስጥ የተቀመጠ ነገር ይኖር ይሆን? ቁጥጥር እንዴት ይደረግባቸዋል?

አቶ ፍቃዱ፡- ይህ ሌላ የክፍያ ሥርዓቱን የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ በአዲሱ የንግድ ሕግ ውስጥ ያልገባ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የድሮው የንግድ ሕግ አምስት የተለያዩ መጻሕፍት ነበሩት፡፡ ወይም የንግድ ሕጉ አምስት የተለያዩ መጻሕፍት ይይዝ ነበር፡፡ አንደኛው መጽሐፍ አጠቃላይ ስለንግድ ምዝገባና ነጋዴ ማነው? የሚለውን የሚመለከት ነው፡፡ ሁለተኛው ለንግድ ማኅበር ስለኩባንያዎች፣ ሦስተኛው ስለኢንሹራንስና ትራንስፖርት፣ አራተኛው ስለባንክ፣ አምስተኛው ደግሞ ስለኪሳራ ምንነት የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ አዲሱ የንግድ ሕግ ግን ሦስት መጻሕፍት ነው ያሉት፡፡ አንደኛው ስለንግድ ምዝገባ ፈቃድና ነጋዴ ማነው? የሚለውን የሚመለከት ሲሆን፣ ሁለተኛውና ሦስተኛው መጻሕፍት ደግሞ ስለንግድ ማኅበራትና ስለኪሳራ ምንነት የሚገልጹ ናቸው፡፡ ስለዚህ በአዲሱ የንግድ ሕግ ያልተካተቱ ቀሪ ሁለት መጻሕፍት አሉ፡፡ እነዚህ ወደፊት የሚወጡ ናቸው፡፡ እነሱም ስለኢንሹራንስ፣ ስለባንክ ሥራና በአጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፉን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ እነዚህ የንግድ ሕጉ ሁለት መጻሕፍት ወደፊት የሚወጡ ናቸው፡፡ አሁን ያነሳኸው ጥያቄ ከዚህ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ነገር ግን በአዋጅ መልክ ብዙ የወጡ ሕጎች አሉ፡፡ በዚህም ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ወጥቷል፡፡ ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ብዙ ሰው ስላልተረዳው ሳይተገበር ቆይቶ ነበር፡፡ በ2005 ዓ.ም. አካባቢ የወኪል ባንኪንግ መመርያ አወጣ፡፡ ከዚያ ውጪ ይህንን አዋጅ አልተገበረም ነበር፡፡ ብዙዎቹም አልተረዱትም፡፡

ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት የምንለው ራሱ ከፋይናንስ ሥራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ መደበኛ የባንክ ሥራ ገንዘብ መሰብሰብና ገንዘብ ማበደር ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ሦስተኛ ላይ የሚወጣው ክፍያውን ማመቻቸት ወይም ማሳለጥ ነው፡፡ ይህ የባንክ ሥራ ነው፡፡ ይህ የባንክ ሥራ ግን ለረዥም ጊዜ የሚሠራበት የሕግ ማዕቀፍ አልነበረውም፡፡ በተለይ ቴክኖሎጂ እያደገ ሲሄድ በሌላ አገር ላይ የተለያዩ የካርድ ዓይነቶች ሥራ ላይ ሲውሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከኤቲኤም ውጪ ብዙም የካርድ ሥርዓት አልነበረም፡፡ ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ይህንን የሚያስችል ነው፡፡ ነገር ግን መመርያ ስላልወጣለት ወደ ሥራ ሳይገባ ቆይቷል፡፡ አሁን የዛሬ ሁለት ዓመት እ.ኤ.አ. አፕሪል 2020 ላይ ሁለት መመርያዎች ወጥተዋል፡፡ አንደኛው የክፍያ ሰነድ አውጪ ‹‹ፔይመንት ኢሹ ዳይሬክቲቭ››፣ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹ፔይመንት ኦፕሬተር ዳይሬክቲቭ›› ነበሩ፡፡ የኤጀንት ባንኪንጉም በአዲስ መልክ ‹‹ዩዝ ኦፍ ኤጀንት›› በሚል በጣም ተሻሽሎ ወጥቷል፡፡ ስለዚህ ሦስት መመርያዎች ወጥተዋል፡፡ አሁን የምትለውን ነገር በጣም እያንቀሳቀሱ ያሉት እነዚህ መመርያዎች ናቸው፡፡ በተለይ ‹‹ፔይመንት›› የሚለው መመርያ ወጣ፡፡ ቴሌ ብር የመጣው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ‹‹ኤም ብር››፣ ‹‹ሄሎ ካሽ›› እና ‹‹ኢ ብር›› የሚባሉት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት በልማድ ነው፡፡ መመርያው ሳይወጣ በፊት ቴክኖሎጂን መሠረት አድርገው ሲሠሩ ነበር፡፡ ነገር ግን መመርዎቹ ግልጽ ሆነው ወጥተው ማን ምን ይሠራል? እንዴት መሥራት ይቻላል? በኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እንዴት መከላከል ይቻላል? ከደረሰስ ምንድነው የሚደረገው? የሚለውን ያብራራ መመርያ ነው የወጣው፡፡ እነ ‹‹ቴሌ ብር››፣ ‹‹ካቻ ሲቢ ብር›› እና ‹‹ኢ ብር›› ያሉት ሥራ ላይ የገቡትና እየተስፋፉ የመጡት ይህ መመርያ ከወጣ በኋላ ነው፡፡               

ሪፖርተር፡- አዲሱ የንግድ ሕግ ውስጥ ለባንኮች ያልተመቸ አንድ አንቀጽ ተካቷል በማለት በባንኮች አካባቢ ቅሬታዎች እየተደመጡ ነው፡፡ በአንቀጽ 654 ላይ ከኩባንያዎች ኪሳራ ጋር በተያዘ የተቀመጠውን ድንጋጌ ይመለከታል፡፡ ከዚህ ቀደም ባንኮች ሐራጅን (ፎርክሎዠር) በተመለከተ በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣን የሚጋፋ ነው እየተባለ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በንግድ ሕጉ ውስጥ ባንኮች በማስያዣ የያዙትን ንብረት በፈለጉት ጊዜ እንዳይሸጡ የሚገድብ በመሆኑ፣ በአሠራራቸው ላይ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር ነው ብለው ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡ በንግድ ሕጉ የባንኮችን መብት ያስጠብቅ ከነበረው ከ‹‹ፎርክሎዠር›› ሕጉ በተፃራሪ የተቀመጠው ድንጋጌ የማይሻሻል ከሆነ አደጋ ውስጥ እንወድቃለን ይላሉ፡፡ በዚህ የንግድ ሕጉ አንቀጽ ላይ እየተነሳ ስላለው ቅሬታስ ምን ይላሉ?

አቶ ፍቃዱ፡- እውነት ነው፡፡ ባንኮች ላይመቻቸው እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ዋናው ነገር የኪሳራ ሕግ ባህሪን መረዳት ነው፡፡ ምክንያቱም በሌላ አገር የሌለ ሕግ አይደለም ኢትዮጵያ ውስጥ የወጣው፡፡ እንዲያውም በዚህ ሕግ አወጣጥ ከተሳተፉ ሰዎች የሰማሁት፣ ንግድ ነክ ሕጎች ዩኒፎርም እንዲሆኑ ጥናቶች የሚያደርግና ሞዴሎችን የሚያዘጋጅ አንድ ዓለም አቀፍ ተቋም አለ፡፡ የኢትዮጵያ ሕግ ይህንን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ በዓለም ላይ የሌለ ነገር አይደለም የተፈጠረው፡፡ በሌላም አገር አለ፡፡ የኪሳራ ሕግ ባህሪን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሚባለው ጋር ልታገናኘው ትችላለህ፡፡ በመደበኛው ሕግ ማስከበርና የማስተዳደር ሊገዛና ሊመራ የማይችል ሲሆን፣ በመንግሥት ወይም በፖለቲካ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይታወጃል፡፡ በንግዱ ውስጥም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር አለ፡፡ በንግድ ድባብ ውስጥ የሚመሳሰል ነገር አለው፡፡ ዕዳን መክፈል አለመቻል ውስጥ አንድ ነጋዴ ሲገባ፣ በአዲሱ የንግድ ሕግ ሦስተኛው መጽሐፍ የሚያስቀምጠው ልክ እንደ አስቸኳይ ጊዜ ይታወጃል፡፡ በነገራችን ላይ ኪሳራ ይታወጃል፡፡ ውጤቱ ምንድነው? ሲባል የመጀመርያው ውጤቱ በተጠናጠል የሆነና ዕዳውን የማስመለስ እንቅስቃሴዎችን በሙሉ ማስቆም ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ነጋዴ ዕዳውን መክፈል የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ሲገባ፣ የተናጠል ክሶች ካልቆሙ በስተቀር ሁሉም ሊከስ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የባለዕዳው ሀብት ይባክናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በንግድ ሕጉ የተናጠል ክሶችን ማቋረጥ አንዱ ዓላማ ብክነትን ለማስቀረት ነው፡፡ ይህ አሠራር ለባንኮችም ይሠራል፡፡ ባንኮች ላይም ይሠራል ማለት ነው፡፡ ባንኮች ግን እኛን እዚህ ውስጥ መጨመር የለብንም ነው የሚሉት፡፡ ይህ እንግዲህ ትልቅ የፖሊሲ ውሳኔ ነው፡፡

የ‹‹ፎርክሎዠር››ን ሕግ ያወጣው ሕግ አውጪው ነው፡፡ ይህንንም የንግድ ሕግ ያወጣው ሕግ አውጪው ነው፡፡ አሁን አከራካሪ የሆነው አንቀጽ 654 መልሶ ማደራጀት በሚለው ክፍል ውስጥ ነው ያለው፡፡ በንግድ ሕጉ የኪሳራ ሕግ ሦስት አማራጮችን ነው የሚያስቀምጠው፡፡ አንድ ነጋዴ ዕዳ የመክፈል ችግር ውስጥ ሲገባ ሦስት አማራጮች አሉ፡፡ አንደኛ ለቅድመ ጥንቃቄ መልሶ የማዋቀር የሚባል ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ ሁለተኛው መልሶ የማደራጀት ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ እነዚህ የየራሳቸው ልዩነቶች አሏቸው፡፡ አንቀጽ 654 ሁለተኛው ሥነ ሥርዓት ውስጥ ነው ያለው፡፡ ሦስተኛው ሥነ ሥርዓት መልሶ የማደራጀት ሥነ ሥርዓት ሲሆን፣ ዋናው ዓላማው ተስፋ ያላቸው ነጋዴዎች ተመልሰው እንዲያንሠራሩ ማገዝ ነው፡፡ ይህ የማይቻል ከሆነ ሀብታቸው የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ በማድረግ፣ ለሁሉም የተናጠል ክስ የታገደባቸውን አንድ ላይ አስተባብሮ እንዲጠበቁ በማድረግ ነው፡፡ መልሶ ማንሠራራት የማይሆን ከሆነ፣ ያ ሀብት የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ መርዳት ነው፡፡ በተሻለ ዋጋ የሚገኝ ከሆነ ለባለገንዘቦቹ የሚከፋፈለውም የገንዘብ መጠን የተሻለ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ እንደ ባንክ ያሉ መያዣ ያላቸው አበዳሪዎች እነሱ ከያዙት ንብረት ተሸጦ ከሚገኝ ገንዘብ ላይ ቅድሚያ ዕዳቸውን የማስመለስ መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ ይህንን የኪሳራ ሕግ ወይም መልሶ የማደራጀት ሥነ ሥርዓት አይከለክላቸውም፡፡ የሚከለክለው ነገር ቢኖር ጊዜው ላይ ነው፡፡ ድሮ በፈለጉበት ጊዜ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው፣ ጨረታ ሁለት ጊዜ አውጥተው ካልተሸጠ ንብረቱን ወደ ራሳቸው መጠቅለል ይችላሉ፡፡ አሁን ግን አይቻልም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ንብረት ተነጣጥሎ ሲሸጥ ከሚያስገኘው ዋጋ ይልቅ አንድ ላይ ሲሸጥ የሚያስገኘው ዋጋ ይበልጣል፡፡ ለምሳሌ አንድ አምራች ድርጅት ቢኖር ያን አምራች ድርጅት ፋብሪካውን፣ ማሽኖቹንና መኪኖቹን ነጣጥሎ ከመሸጥ ከሚገኝ ዋጋ ይልቅ ፋብሪካው እንዳለ ቢሸጥ የሚያስገኘው ዋጋ የተሻለ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ለሁሉም ባለገንዘቦች የሚከፋፈለው መጠን ንብረቱን በአንድነት ቢሸጥ የተሻለ ይሆናል፡፡ ባንኮች ግን በመያዣ የያዙትን ንብረት ገንጥለው የሚሸጡ ከሆነ፣ የተቀረው ሀብት ወይም የተቀረው ንብረት ተሸጦ የሚያስገኘው ገንዘብ ያነሰ ይሆናል፡፡ ፈላጊ ያጣል፡፡ ስለዚህ ሌሎች ይጎዳሉ በሚል ነው ይህ ሕግ የወጣው፡፡ ግን አከራካሪ እየሆነ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በእርግጥም አከራካሪ እየሆነ ነው፡፡ ባንኮች ሥጋታቸው ትክክል የሚሆንበት ምክንያት እንዳለ አስረጂ ያቀርባሉ፡፡ ይህም ለብድር የሚያውሉትን ገንዘብ የሚያሰባስቡት ከኅብረተሰቡ ነው፡፡ የሕዝብን ገንዘብ ነው ለብድር የሚሰጡት፡፡ ይህ ገንዘብ በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ለዚህም ነው ሲያበድሩ ንብረት የሚይዙት፡፡ የሰጡት ብድር ካልተመለሰ የያዙትን ንብረት ሸጠው መመለስ አለባቸው፡፡ የተያዙ ንብረቶችን ሸጠው ገንዘባቸውን መመለስ እንዲችሉ ደግሞ የፎርክሎዠር አዋጁ ለእነሱ የበዛ መብት ሰጥቷቸው ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጎ እየተሠራበት ነው፡፡ በዚህ አዋጅ ያለ ችግር ንብረቱን ሸጠው ገንዘባቸውን ማግኘት ያስችላቸው ነበር፡፡ አሁን ግን በመያዣ የተያዘ ንብረትን ለመሸጥ በንግድ ሕጉ የተቀመጠው ድንጋጌ ገንዘባቸውን ለማግኘት ረዥም ጊዜ የሚጠይቃቸው መሆኑ እንቅፋት ሆኖብናል ይላሉ፡፡ ችግሩ ይህ ብቻ ሳይሆን በንግድ ሕጉ ውስጥ ያለው ድንጋጌ እንዲህ ባለው መንገድ እንቅፋት የሚሆንባቸው ከሆነ፣ ባንኮች ብድር ለመስጠት እንዲፈሩ እንደሚያደርጋቸውና ይህ ደግሞ ኢኮኖሚን እንደሚጎዳ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህ ይህ የንግድ ሕጉ ሲቀረፅ እንዲህ ያሉ ነገሮች ታሳቢ አልተደረጉም? ችግሩ ካልተፈታ በኢኮኖሚው ላይ ችግር አይፈጥርም?

አቶ ፍቃዱ፡- ችግር መፈጠሩ አይቀርም፣ ይፈጠራል፡፡ ሥጋታቸው ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሁለት ተፃራሪ ፖሊሲዎችን የማመዛዘን ሥራ የሚሠራበት ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ አሁን መልሶ ማደራጀት የሚለው የሕዝብን ጥቅም ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ባንኮችም እያሉ ያሉት እንደ ግል ወይም እንደ አንድ ኩባንያ አይደለም ይህንን ጉዳይ እያቀረብን ያለነው እያሉ ነው፡፡ የሕዝብ ገንዘብ ነው ሰብስበን የምናበድረው፡፡ ብድሩን ካልመለስን አደጋ ውስጥ እንወድቃለን፡፡ እናም አናበድርም፡፡ ለወደፊትም እንሠጋለን፡፡ ብድራችንን እንቀንሳለን የሚል ነው፡፡ በመሠረቱ በመያዣ የተያዘን ንብረት ባንኮች አይሽጡ የሚል አይደለም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው ያለው፡፡  

ሪፖርተር፡- ቢቆይም ንብረቱን ሸጠው ዕዳቸውን ሊመልሱ ይችላሉ? አንዱ ችግር መቆየቱ ነው፡፡ ነገር ግን ንብረቱን ሳይሸጡ ምን ያህል ጊዜ ነው ይቆዩ የሚባለው? የተቀመጠው ገደብ አለ? በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን ሕግ መሠረት አድርገው ተበዳሪዎች አውቀው ቀን የሚገዙበት ቢሆንስ?

አቶ ፍቃዱ፡- አዎ ጊዜ ተቀምጧል፡፡ መልሶ የማደራጀት ሥርዓት በአራት ወራት ማለቅ እንዳለበት ነው የተቀመጠው፡፡ እጅግ ቢበዛ በጣም አንገብጋቢ ነገር ካለና ፍርድ ቤት ካመነበት እስከ 12 ወራት ነው ሊራዘም የሚችለው፡፡ ስለዚህ ዓመታት ይወስዳል የሚለውን ሥጋት ሕጉ ያስወግዳል፡፡ ትልቁ ነገር ግን በዚህም በኩል ያለው የሕዝብ ጥቅም ነው፡፡ ድርጅቶች ተመልሰው እንዲያንሰራሩ ማድረግ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ ዞሮ ዞሮ የተቀጠሩ ሠራተኞች አሉ፡፡ ከድርጅቶች ጋር የሚሠሩ የተለያዩ አቅራቢዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ይህም ከአገር ጥቅም ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ለዚያም ነው እነዚህን ጥቅሞች ማመጣጠንና ሕግ አውጪው የቱ ይሻላል? የሚለውን አመዛዝኗል ብዬ የማምነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች ሊጠሉት ይችላሉ፡፡ ይህ የትም አገር አለ፡፡ አሜሪካ አገር በጣም የተለመደ ነገር አለ፡፡ ይህም አንድ ባለ ዕዳ፣ ዕዳህን ክፈል ተብሎ ተወጥሮ ሲያዝ ‹‹ኪሳራዬን አውጃለሁ›› ይላል፡፡

ምክንያቱም ኪሳራውን ካወጀ ሁሉም ነገር ቀጥ ይላል፡፡ ነገር ግን ይህንን በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው አገር የሚያስተናግድበት የራሱ ሕግ አለው፡፡ የኢትዮጵያን ሕግ ስታይ አንደኛ በማጭበርበር ወደ መልሶ ማደራጀት አቤቱታ የሚቀርብ ነጋዴ ይቀጣል፡፡ ሲጀመር አይፈቀድለትም፡፡ በማታለል ዕዳውን በማጋነን ከሆነ የሚቀርበው ባለገንዘቦቹ ዕዳቸውን እንዳይሰበስቡ ሆን ብሎ የሚደርገው ነገር ያስጠይቃል፡፡ ሒደቱን ለማስተጓጎል ሆን ብሎ የሚያደርገው ከሆነ አይፈቀድለትም፡፡ ካደረገውም ሪከርድ የሚያዝበትም ስለሚሆን፣ ራሱ ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ሁለተኛው መልሶ የማደራጀት ሥርዓት ውስጥ በተናጠል የማስፈጸም እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ፍርድ ቤት ሊፈቅድ ይችላል ማለት ነው፡፡ በተናጠል እየታየ ማለት ነው፡፡ ይህንንም አንቀጽ 654 ንዑስ አንቀጽ አምስት ላይ ራሱ ይጠቅሳል፡፡ የተወሰኑ ሁኔታዎች ከተሟሉ ሊፈቅድ ይችላል፡፡ ስለዚህ ባንኮች ይህንን መጠቀም አለባቸው ማለት ነው፡፡ እነሱን ታሳቢ ያደረገ ነውና ስለዚህ ያን ያን መጠቀም እንጂ፣ ባንክ መያዣ የያዘው ንብረት በሙሉ በፍፁም መልሶ ማደራጀት ሥነ ሥርዓት ውስጥ በተናጠል የማስፈጸም ዕድል መታገድ የለበትም የሚለው በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ባንኮች ገንዘባቸው ሳይመለስ ቆይቶ የመጨረሻ አማራጭ የሚሉትን ውሳኔ በመወሰን ንብረቱን ሸጦ ለመመለስ እስከ 12 ወራት የሚፈጅባቸው ከሆነ ተጎጂዎች መሆናቸው አይቀርም፡፡ በወቅቱ ገንዘባቸውን ቢያገኙ ገንዘቡን ምን ያህል ሊሠሩበት እንደሚቻል ይታወቃል፡፡ ዕዳው ላልተመለሰ ብድር ደግሞ መጠባበቂያ መያዝ ስለሚያስገድዳቸው ጉዳታቸው አይበዛም?

አቶ ፍቃዱ፡- ብድር ካልተመለሰ በመጠባበቂያ (ፕሮቪዥን) መያዝ አለበት ተብሎ የሚገደዱት ነገር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ባንክም ላልተመለሱ ብድሮች ባንኮች መጠባበቂያ መያዝ እንዳለባቸው የሚል ድንጋጌ ስላለው ከዚህም ጋር የሚጋጭ ነገር እንዳይፈጠር አያደርግም?

አቶ ፍቃዱ፡- ለዚህ እኮ ነው አጠቃላይ የኪሳራ ሥነ ሥርዓት በሙሉ ሲታይ እንደ አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ነው ያልኩህ፣ ሁሉንም ይነካል፡፡ ‹እኔ መነካት የለብኝም› የሚለውን የንግድ ሕጉ አልቀበልም እያለ ነው፡፡ ግን ባንኮችን የሚነካበት ሌሎችን በሚነካበት ጥልቀት አይደለም፡፡ ባንኮችን በተመለከተ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በመያዣነት የያዙት ንብረት የእነሱ ነው፡፡ ንብረቱ ሲሸጥ በመጀመርያ የሚከፈለው የባንኮች ዕዳ ነው፡፡ ንብረቱ ተሸጦ የእነሱን ገንዘብ መሸፈን ካልቻለ እንኳን እንደ መደበኛ ባለገንዘብ ሌላ ሀብት ተሸጦ መካፈል ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ይነካል፡፡ እኔን አይንካኝ ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያም ይህ ለነጋዴው እንደ አስቸኳይ ጊዜ ነው፡፡ የሚቻለው ቀነስ ማድረግ ነው፡፡ አንዱ ቀነስ ማድረጊያ ነጋዴዎች በሐሰት እንዲህ ያለ ነገር እንዳያቀርቡ መከላከል ነው፡፡ ባንኮች ሆን ብለው ነው፣ በማታለል ነው፣ ለማጭበርበር ነው ይህንን ያቀረቡት ብለው እንዳይፈቀድ ለፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ከተፈቀደም በኋላ ባንክ በመያዣነት የያዘው ንብረት ከዚህ ሥነ ሥርዓት ውጪ እንዲሆን መጠየቅ ይችላሉ፡፡ እዚህ አካባቢ መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ብሔራዊ ባንክም መመርያዎች ማውጣት፣ ዳኞችም አካባቢ በጉዳዩ ላይ በቂ አለመረዳት ካለ መሥራት ይሻላል፡፡ ነገር ግን ሕጉ በሌላም አገር የሚሠራበት የተለመደ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- በአዲሱ የንግድ ሕግ የግለሰብ ተበዳሪዎችስ መብት ምን ድረስ ነው? ግዴታቸውስ?

አቶ ፍቃዱ፡- በንግድ ውስጥ መክሰር፣ ውጤታማ ያለመሆን ያለ ነው፡፡ ንግድ የውድድርም ውጤት ስለሆነ ይህ መታሰብ አለበት፡፡ የድሮው ሕግ ተበዳሪን በጣም የሚበድልና የሚጨቁን ነበር፡፡ አዲሱ ሕግ ግን ለተበዳሪዎችም የተወሰነ መብት የሚሰጥ ነው፡፡ ተበዳሪዎችን በተመለከተ ሕጉ ካወጣቸው አንዱ ተበዳሪዎች ነፃ የመውጣት፣ ታማኝና ቅን ተበዳሪ (ባለዕዳ) ከሆኑ ሕጉ ነፃ እንዲወጡ ይፈቅዳል፡፡ ለምሳሌ ሙሉ ለሙሉ ወደ ኪሳራ፡፡ ስለዚህ ነፃ የመውጣት መብት የተሰጠው በአዲሱ የንግድ ሕግ ነው፡፡  በቅድመ ጥንቃቄና በመልሶ ማዋቀር ሥነ ሥርዓቶችም ነጋዴው ፋታ ተሰጥቶት አዲስ ዕቅድ አቅርቦ፣ ባለገንዘቦችም ከተስማሙና ከተቀበሉ ያን ዕቅድ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ በዕቅዱ መሠረት ጊዜ ተወስኖለት፣ ወይም የዕዳ ክፍያ ተቀንሶ፣ ወይም አዲስ አክሲዮን ሸጦ፣ የብድር ሰነድ ሸጦና አንሰራርቶ ዕዳውን እንዲመልስና ንግዱን እንዲቀጥል የሚያደርግ ግልጽ የሆነና ተገማች ሥርዓት በአዲሱ ሕግ ነው የተካተተው፡፡ ስለዚህ ለባለዕዳዎችም በአዲሱ የንግድ ሕግ ብዙ ለውጥ አለ፡፡  

ሪፖርተር፡- የሕግ አገልግሎት በምን ደረጃ ላይ ነው ማለት ይቻላል? እየተለወጠ ነው? አዳዲስ ነገሮች ይጠበቃሉ? የኢትዮጵያ የንግድ ኩባንያዎች የሕግ የባለሙያዎችን የመጠቀም ልምድስ ምን ይመስላል?

አቶ ፍቃዱ፡- ይህ በሒደት እየተሻሻለ የሚሄድ ይመስለኛል፡፡ እንደ ማንኛውም ዘርፍ ነው፡፡ ድሮ በአብዛኛው በልምድ አዋላጅ የሚሠራ ነበር፡፡ አሁን በጤናው ላይ መንግሥት ብዙ ሥራ እየሠራ ነውና ወሊድ በሆስፒታል ሆኗል፡፡ ሕጉም ላይ በደንብ እየተሠራ ነው፡፡ ያለ ትምህርት ዝግጅት በልምድ ራፖር ጸሐፊዎች ፍርድ ቤት አካባቢ የሕግ አገልግሎት የሚሰጡበት መንገድ አሁን እየቀረ መጥቶ፣ ቢያንስ በአብዛኛው የመጀመርያ ዲግሪ ያላቸው ናቸው ሥራውን የሚሠሩት፡፡ አሁን ደግሞ ከአንድ ዓመት ወዲህ የሕግ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች በተቋም መልክ እንዲቋቋሙ የሚፈቅድ ወይም ይህንን የሚያግዝ ራሱን የቻለ አዋጅ ተፈጥሯል፡፡ ራሱን የቻለ ነፃ የሆነ የጠበቆች የሙያ ማኅበር በአዋጅ እንዲቋቋም አዲስ ሕግ ወጥቶ ሁሉም ጠበቃ የግዴታ አባል የሆነበት ማኅበር ተቋቁሟል፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሙያውን በጣም ያሳድጋሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ እስካሁን በነበረው አንድ ሰው ሁሉንም ሥራ ሲሠራ ነበር፡፡ የውርስን፣ የወንጀልን፣ የቤተሰብን፣ የውልን፣ የኢንሹራስንና የባንክ ሥራዎችን አንድ ጠበቃ እችላለሁ ብሎ በድፍረት ገብቶ የሚሠራበትና ብዙ ነገሮችን የሚያበላሽበት ልማድ ይቀራል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ አንዱ ችግር ነበር፡፡ ስፔሻላይዝ ማድረግ አለበት፡፡ ይህ ለደንበኞች የአገልግሎት ጥራት ትልቅ ችግር ነበር፡፡ ሙያው እንዳያድግም አድርጎ ነበር፡፡ ምክንያቱም ድርጅት ሲሆን ድርጅቶች ሲስፋፉ የሚሆነው በአንድ ድርጅት ውስጥ አሥርና ሃያ ሰዎች ሊኖረው ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም የውል ክርክር ብቻ የሚመለከት አይሆንም፡፡ አንደኛው በኢንሹራንስ ላይ፣ አንዱ በጤና ሕግ ላይ፣ ሌላው ደግሞ በኮንስትራክሽን ላይ እያሉ መሥራታቸው ስፔሻላይዜሽን ያመጣል ተብሎ ይታሰባል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

ኢንቨስተሮች አደጋ ሲገጥማቸው ድጋፍ ማድረግ የሚያስችለው መመርያ ተሻረ

በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች በኢንቨስተሮች ንብረት ላይ አደጋ ቢከሰት፣...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሥጋቶች

ዘ ኮንቨርሴሽን ላይ ‹‹What Next for Ethiopia and its...