Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገሪቱ ኢኮኖሚ በዕጅጉ የተፈተነበት 2014

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተጠናቀቀው የ2014 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዕጅጉ የተፈተነበት ነው። በተለይም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለው ጦርነት ከፈጠረው ሞት፣ መከራና ስቃይ ባለፈ የአገሪቱ ኢኮኖሚንም ያደማበትና መልሶ ለማገገም ረዥም ዓመታትን የሚጠይቅ ውዝፍ ዕዳ የተወበት ነው። 

በያዝነው 2014 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ለ2014 ዓ.ም. የተጨማሪ በጀትን ሳይጨምር 542 ቢሊዮን ብር የወጪ በጀት በማጽደቅ ከሐምሌ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረ ሲሆን፣ ከዚህ የወጪ በጀት ውስጥ 436 ቢሊዮን ብሩ ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች እንዲሁም ከውጭ ዕርዳታ ለመሰብሰብ ታሳቢ ተደርጎ ነበር። የተቀረው ብር 106 ቢሊዮን ደግሞ በበጀት ጉድለትነት ተይዞ፣ ጉድለቱንም ከአገር ውስጥና ከውጭ ብድር ለመሸፈን ታቅዶ ነበር። በዚሁ መሠረት ከውጭ ብድር 38 ቢሊዮን ብርና 68 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ የተጣራ ብድር በመውሰድ የበጀት ጉድለቱ እንደሚሸፈን መታቀዱን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ይሁን እንጂ በዓመቱ መጨረሻ ላይ የታቀደው ሆኖ አልተገኘም። መንግሥት ከአገር ውስጥ ታክስና ግብር ለመሰብሰብ ያቀደውን ገቢ ለማግኘት አልቻለም። በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተከሰተው ጦርነት ከፍተኛ የሰብዓዊና የኢኮኖሚ ጉዳት ከማድረሱ ባሻገር መንግሥት ለመሰብሰብ ያቀደውን ገቢም እንዳያገኝ አድርጎታል። 

‹‹ጦርነቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን በማዳከሙና ጦርነቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ያሉ የኢኮኖሚ ተቋማት በመውደማቸውም ሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማቆማቸው ከእነዚህ ለመሰብሰብ የተያዘውን ገቢ መሰብሰብ የማይቻል በመሆኑ ከተያዘው ጠቅላላ ዓመታዊ የታክስ ዕቅድ ውስጥ እስከ ብር 40 ቢሊዮን የሚደርስ የታክስ ገቢ እንዳይሰበሰብ አድርጓል፤›› ሲል የገንዘብ ሚኒስቴር ዓመታዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሰነድ ገልጿል።

ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ በያዘው የተሳሳተ አቋም ዋና ዋና የአገሪቱ የልማት አጋሮች የሚሰጡትን የበጀት ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ አቋርጠዋል። በዚህም ምክንያት በ2014 ዓ.ም. ከእነዚህ የልማት አጋሮች ይገኛል ተብሎ የነበረ 64 ቢሊዮን ብር የቀጥታ በጀት ድጋፍ ገቢ ሊገኝ አልቻለም። 

በዚህና ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ምክንያት የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሚባል ተያይዞ የፊሲካል ኢኮኖሚ መዛባት እንደገጠመው መረጃው ያመለክታል። ይህንን ቀውስ ለመፍታትም ለካፒታል ፕሮጀክቶች ግንባታ የተያዘ በጀትን ለማጠፍ ተገዷል። 

‹‹ለገጠመን የፊስካል ጫና መፍትሔ ለመስጠት በበጀት ተይዘው ተግባራዊ ለማድረግ ታቅደው ከነበሩ የልማት ሥራዎች ቅድሚያ ማግኘት ያለባቸውን ቅድሚያ በመስጠት ቀሪዎቹን የወጪ ሽግሽግ ማድረግና ቀሪውን ጫና ደግሞ ከአገር ውስጥ ተጨማሪ ብድር በመውሰድ እንዲሸፈን ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ሆኗል፤›› ሲል ሰነዱ ይገልጻል። 

በዚህም መሠረት 31 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ፕሮጀክቶች ወጪ ታጥፎ ቅድሚያ ለተሰጠው የሰሜኑ ጦርነትና ተያይዥ ጉዳዮች እንዲውል ተደርጓል።

በአጠቃላይ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ በ2ዐ14 ዓ.ም. ለመከላከያ ሚኒስቴር ከተፈቀደው በጀት በተጨማሪ 156 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ሰነዱ አመልክቷል።

በመሆኑም ከሰሜኑ ጦርነቱ ጋር ተያያዞ የመጣውን ተጨማሪ የወጪ ለመሸፈን መንግሥት 210 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ተጨማሪ ብድር ከአገር ውስጥ ለመውሰድ የተገደደ ሲሆን፣ ይህም በበጀት ዓመቱ በአገር ውስጥ ብድር ይሸፈናል ተብሎ የታቀደውን የበጀት ጉድለት መጠን ቀድሞ ተይዞ ከነበረው 68 ቢሊዮን ብር ወደ 278 ቢሊዮን ብር አሻቅቦታል። በመሆኑም መንግሥት በዓመቱ ለበጀት መሸፈኛ ከአገር ውስጥ የወሰደው ብድር ከሦስት በመቶ ጣሪያ አልፎ አምስት በመቶ እንዲደርስ አድርጎታል። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳም የአገሪቱ ኢኮኖሚ በ2014 ዓ.ም. የ8.7 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ የተያዘው ዕቅድ እንደማይሳካ መንግሥት በይፋ አምኗል። የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ከስድስት እስከ ሰባት በመቶ ሊያድግ እንደሚችል ተተንብይዋል።

በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ አገሪቷ ገጠሟት የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች አንዱ ከአሜሪካ ነፃ የገበያ ዕድል አጎዋ ተጠቃሚነት እንድትታቀብ መደረጉ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ ከዘርፉ ታገኝ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እንድትጣ ብቻ ሳይሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሥራ አልባ አድርጓል፡፡ 

የአገሪቱ ዋነኛ ችግር ሆኖ የዘለቀው ሌላው ችግር የውጪ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ አምራች ድርጅቶች የጥሬ ዕቃ ለመግዛት የሚያስችላቸው የውጪ ምንዛሪ በማጣት አቅም በላይ እያመረቱ መሆናቸውን እያሳወቁ ዓመቱን አጠናቀዋል፡፡ የጥቁር ገበያ የምንዛሪ ዋጋ 80 ብር የደረሰና በመደበኛው የባንክ አገልግሎት የአንድ ዶላር መመንዘርያ ዋጋ 53 ብር መድረሱም የችግሩን  ግዝፈት ያሳያል፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ በ2014 ዓ.ም. በርካታ ፈተናዎች የገጠሙበት ቢሆንም ውጤታማ የሚባሉ ኢኮኖሚያዊ ክንውኖች የተስተናገዱበትም ነበር። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ እንደገለጹትም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ቢያልፍም ጥሩ አፈጻጸም ያሳየበት ዓመት ነው ይላሉ፡፡ አገሪቱ በብዙ ችግሮች ውስጥ ብትሆንም ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገቷ ከስድስት በመቶ በላይ መሆኑን ተጠቅሷል፡፡ ሁሉም የአገሪቱ ባንኮች ከታክስ በፊት ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ያተረፉበት ስኬታማ ዓመት ሆኖላቸዋል። የወጪ ንግድ ገቢ 4.1 ቢሊዮን ዶላር የደረሰበት ዓመትም ነበር፡፡ ቡና ለመጀመርያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘቱም ዓመቱ ኢኮኖሚያዊ ክዋኔዎች ተርታ የሚጠቀስ ነው፡፡ የሬሚታንስ ግኝትም ቢሆን ከቀደሙት ዓመታት በተሻለ የተገኘበት መሆኑ ታውቋል፡፡ 

የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ክዋኔዎች ያሳድጋሉ የተባሉ ትልልቅ ውሳኔዎች የተላለፉበት ነው ተብሎ የሚታመነው የ2014 በጀት ዓመት የአገሪቱን የንግድ ሕግ ከ60 ዓመታት በኋላ እንዲሻሻል መደረጉ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ በዓመቱ ማጠቃለያ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ከግማሽ ምዕት ዓመት በኋላ የባንክ ዘርፉን ለውጭ ክፍት ለማድረግ መወሰኗ ከኢኮኖሚ አንፃር ትልቅ ውሳኔ ተደርጎ ተወስዷል፡፡

ከባንክ ውጪ በአገሪቱ በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ትርፍ ተብሎ የሚጠቀሰው ሌላው ክዋኔ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያስመዘገበው የ5.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱና ከ937 ሚሊዮን ዶላር በላይ (ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ) ትርፍ ማስመዝገቡ በበጀት ዓመቱ የተሰጠ ትልቅ የትርፍ ምጣኔ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ከኪሳራ ዜናዎች ደግሞ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት 18 ቢሊዮን ብር ኪሳራ የደረሰበት እንደሆነ መገለጹ የተሰማው በዚሁ በጀት ዓመት ነው፡፡ 

ከብዙ በጥቂቱ የ2014 የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በወፍ በረር እንዲህ ባለ ሁኔታዎች የሚታወስ ቢሆንም የበጀት ዓመቱ ዋናና ቀዳሚ ችግር ግን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ነው፡፡ ዓመቱን በሙሉ በየወሩ የዋጋ ንረቱ እየጨመረ ሄዶ አሁንም መቆሚያው ሊታወቅ ያልቻለ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ 

ይህ ሥር የሰደደ ችግር ወደ ቀጣዩ ዓመት እየተሸጋገረ ስለመሆኑም በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ከዚህ የአገር ችግር የሆነና መንግሥትም የቻልኩትን ያህል ብጥርም ወቅታዊውን የዋጋ ንረት መግታት አለመቻሉን የገለጹበት ዓመት ነው፡፡ ነገር ግን የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር የወሰድኳቸው ዕርምጃዎች የዋጋ ንረቱን አሁን ካለው በላይ እንዳይሆን አስችሏል ብሏል፡፡ ከዚህ ትልቅ ተግዳሮት ባሻገር በ2014 በርካታ ኢኮኖሚያዊ ክዋኔዎች የታዩበት ሲሆን ከገበያ ሥርዓት ብልሽት ጋር ተያይዞ ቀላል የማይባሉ ችግሮች የታዩበት እንደነበር ይጠቀሳል፡፡ 

በ2014 ዓመቱን በሙሉ በኢኮኖሚ ውስጥ ያልተፈታ ችግር ሆኖ የዘለቀው እንደ ሲሚንቶና ብረት ያሉ ምርቶች ገበያ እንደተረባበሸና እንደተወነባበደ መቀጠሉን አንዱ ነው፡፡ 

በተለይ የሲሚንቶ ገበያን ለማረጋጋት በተከታታይ የተወሰዱ ዕርምጃዎች በሙሉ ውጤት ሳያገኙ ዓመቱ ተጠናቋል፡፡ ከማምረቻው ከ500 ብር ባልበለጠ የሚወጣው ሲሚንቶ ገበያ ላይ ከሦስት እጥፍ በላይ እስከ መዝለቅ ቀጥሏል፡፡ መስከረም 2014 ዓ.ም. በገበያ ውስጥ እስከ 700 ብር ሲሸጥ የነበረ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 1,800 ደርሷል፡፡ ይህ የተወነባበደ የሲሚንቶ ገበያ በፌዴራል መንግሥትም ሆነ በክልል መንግሥታት የእናስተካክላለን የሚሉ ውሳኔዎችን ቢወስኑም አልተቻላቸውም፡፡ መፍትሔ ያስገኛል የተባለ ውሳኔ ባሳለፉ ማግስት ጭራሽ ዋጋው እየጨመረ ቀጥሏል፡፡ 

ከግንባታ ግብዓቶች ጀምሮ በሁሉም ምርቶች ላይ ከታየው የዋጋ ጭማሪ ሁሉ የኅብረተሰቡ ራስ ምታት ሆኖ የቀጠለው የምግብ የዋጋ ንረት ነው፡፡ ከሌሎች ምርቶች በተለየ እያደገ መምጣቱ የብዙዎች ችግር እየሆነ ነው፡፡ የ2014 ኢኮኖሚያዊ ክዋኔን በተመለከተ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ተክለወልድ ለሪፖርተር እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ አገሪቱ ያስመዘገበችው የኢኮኖሚ ዕድገት በተለያዩ መለኪያዎች ሲታይ አበረታች የሚባል መሆኑን ነው፡፡ በግብርና በኢንዱስትሪ በአገልግሎት ዘርፎች የተገኙ ውጤቶች ለኢኮኖሚው ዕድገት አበርክቶ ነበራቸው ብለዋል፡፡ ነገር ግን የዋጋ ንረቱ የቱንም ያህል ቢሠራበት ዝቅ ለማድረግ አለመቻሉን ነው፡፡ ለዚህም ብዙ ምክንያቶች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ በዓለም ደረጃ የምርቶችና የሸቀጦች ዋጋ መጨመር አንዱ ሲሆን በአገር ውስጥም የምርትና አቅርቦት አለመጣጣም ለችግሩ በዋናነት የሚጠቀስ ምክንያት ነው፡፡ 

የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ቢያሳይም እያደገ ከመጣው ፍላጎት አንፃር ሊጣጣም ባለመቻሉ የዋጋ ንረቱ እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ 

ዓመታዊ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ግን እንደቀጠለ ስለመሆኑ የሚያመለክቱት አማካሪው በበጀት ዓመቱ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት እስከ ስምንት በመቶ ያድጋል ተብሎ ታስቦ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ አሁን ያሉት መረጃዎች የሚጠቀሱት ከ6.1 እስከ 6.6 በመቶ ሊያድግ የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ከሁሉም ዘርፎች የሚሰበሰቡት መረጃዎች ተጠናቅረው መስከረም ላይ የመጨረሻው ውጤት የሚገለጽ ቢሆንም እስካሁን ያሉት መረጃዎች ግን የሚያሳዩት እስከ 6.6 በመቶ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚመዘገብ መሆኑ ነው ይላሉ፡፡ ይህ በብዙ ፈተና ውስጥ ተኩኖ የተገኘ ውጤት በመሆኑ ዓመቱ ጥሩ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የተመዘገበበት እንደሆነ ያመለክታል ብለዋል፡፡ በተለይ እንደ አይኤፍ ያሉ አገሮች የአፍሪካ አገሮች አማካይ ዓመታዊ ዕድገት 3.3 በመቶ እንደሚሆን የኢትዮጵያ ደግሞ ወደ 3.8 በመቶ እንደሚሆን የተነበየ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ግን ከ6.1 በመቶ በላይ ዕድገት ማስመዝገቧ ትልቅ እመርታ ተደርጎ መወሰድ ያለበት መሆኑ ነው፡፡ 

ይህ ዕድገት ቢኖርም የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ ባለመቻሉ አሁንም ተጨማሪ ሥራዎች መሠራት እንዳለበት የሚያመለክት እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ተክለወልድ ከውጭ የሚፈጠረው ገፊ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ከባድ ቢሆንም በአገር ውስጥ ከግብይት ሥርዓት ብልሽት ጋር በተያያዘ የትርፍ ምጣኔን ያለመመጠን የዋጋ ንረቱን ከፍ ማድረጉንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በዓለም ላይ የትርፍ ህዳግ አነሰ ቢባል የ100 በመቶ ነው፡፡ በአብዛኛው ግን ከ200 እስከ 400 በመቶ የሚሰላ በመሆኑ ለዋጋ ንረቱ ቀላል አስተዋጽኦ ስለማበርከቱ ይገልጻሉ፡፡ 

የዋጋ ንረቱ በአብዛኛው ምግብ ነክ ምርቶች ላይ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ተክለወልድ ጫናው እንዲበረታ የሚያደርገውም በኢትዮጵያ አንድ ሰው ከወር ከሚያገኘው ከገቢው ወደ 54 በመቶ የሚሆነውን ለምግብ የሚያወጣ በመሆኑ ነው፡፡ 

ስለዚህ የምግቡ ዋጋ በተወደደ ቁጥር ለምግብ የሚያወጣው ወጪ ከ54 በመቶ በላይ እየሆነበት ሲሄድ የዋጋ ንረቱ እየከበደው እንዲሄድ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ በምግብ የዋጋ ንረት ሳቢያ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነትን ቢያንስ በተወሰነ ደረጃ ለመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው፡፡ በተለይ የምግብ ምርቶችን መጨመር ወሳኝ ነገር ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ 

እስካሁን የምግብ ፍላጎትን ለመሸፈን ከውጭ በማስመጣት ለመሙላት ሲሠራ መቆየቱንም አመልክተዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ ከምትፈልገው የምግብ ፍላጎት 75 በመቶውን ብቻ በአገር ውስጥ ምርት የሚሸፍን ሲሆን ቀሪው 25 በመቶ ከውጭ በሚገባ ምርት የሚሸፈን ነው፡፡ ይህንን ከውጭ መግባት ያለበት ምርት ለማስገባት ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልጋል፡፡ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ማስገባት ቢቻል የዋጋ ንረቱ ላይኖር ይችል ነበር የሚሉት አቶ ተክለወልድ ይህም ቢሆን ዘንድሮ ለምግብ ነክ ምርቶች ብቻ 3.8 ቢሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡ 

ስለዚህ የዋጋ ንረቱን ለማርገብ ብዙ ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም አሁንም የሚፈልገውን ለውጥ አላመጣም፡፡ ይህ የሚያሳየን አሁንም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ብቻ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

አሁን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ዘመናዊ የግብርና አሠራሮች ኩታ ገጠም የማምረት ስልቶችና የቆላ ስንዴ ምርትን ማስፋት ወሳኝ መሆኑን ነው፡፡ 

ከዚሁ ዕሳቤ አንፃር በአዲሱ ዓመትም እነዚህን ውጥኖች በማስፋት መሥራት ግድ መሆኑን በማመን የሚተገበሩና ለዚህም በቂ ዝግጅት እየተደረገ ስለሆነ ሌላ እንቅፋት ካልመጣና አሁን በተያዘው ዕቅድ ከተሠራ በቀጣዩ ዓመት የዋጋ ንረቱ ለዘብ የሚልበት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል እንዳለም አመልክተዋል፡፡ ይህ ማለት ግን አሁን ያለው የዋጋ ንረት በአንዴ ይወርዳል ማለት እንዳልሆነም የገለጹት አቶ ተክለወልድ በ2015 ከውጭ የሚገባ ስንዴን ማስቀረትና ወደ ውጭ የሚላክ ውጥንም መያዙም በአዲሱ ዓመት የተሻለ ነገር እንደሚኖር የሚያመለክት ነው በማለት ይገልጻሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች