ኢትዮጵያ እግር ኳስን የሚወዱና የሚያዘወትሩ የኅብረተሰብ ክፍል ካላቸው አገሮች አንዷ ብትሆንም፣ ከውጤት አንፃር ሲታይ ግን ደካማ ተብለው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አገሮች ተርታ እንድትቀመጥ አድርጓቷል፡፡
ለዚህ በዋናነት እንደ ምክንያት የሚነሳው ደግሞ በየደረጃው የሚገኙ ሊጎች እንዲሁም መንግሥታዊ አካሉን ጨምሮ ስፖርቱን በበላይነት የሚመሩ ተቋማት፣ በተለይም ለታዳጊ ወጣቶች የሚሰጡት ትኩረት ማነስ እንደሆነ በትልቁ ይጠቀሳል፡፡
በኢትዮጵያ ለሚታየው የታዳጊ ወጣቶች እግር ኳስ እንቅስቃሴ መዳከም ሁለተኛው ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው ደግሞ፣ ከላይ ከፕሪሚየር ሊጉ እስከ ታችኛው ሊግ ድረስ ከፍተኛ ገንዘብ እየተከፈላቸው የሚጫወቱ በርካታ የሌሎች አገሮች ተጫዋቾች መበርከት፣ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በብዙ ልፋትና ጥረት እንዲሁም ውጣ ውረድ ለከፍተኛ ሊግ ቢበቁም፣ በውጭ ተጫዋቾች ያውም ረብ የለሽ ችሎታም ሆነ የቡድን ውጤት ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል አቅምና ብቃት ሳያሳዩ፣ ለኢትዮጵያ ምሰሶ የሆኑ ታዳጊዎችና ተተኪ ተጫዋቾች ተስፋ እንዳይኖራቸው አድርጎ ስለመቆየቱ ጭምር ይታመናል፡፡
ክለቦች ታዳጊ ወጣቶችን የሚጠቀሙት ያውም ዕድል የገጠማቸውን በአነስተኛ ክፍያ ካልሆነ ብዙም ዕድል ሲሰጧቸው አለመታየቱ፣ ለአገሪቱ እግር ኳስ በተለይም ለብሔራዊ ቡድኑ መዳከም ምክንያት እንደሆነ የሚናገሩ አልጠፉም፡፡ ምንም እንኳ ለውጭ ተጫዋቾች ዕድል መስጠት ተገቢና በየትኛውም ዓለም የተለመደ ቢሆንም፣ ገደብና ሥርዓት ሊበጅለት እንደሚገባ ግን ሙያተኞች ይመክራሉ፡፡
ይህ እውነታ ባለበት ነው ኢትዮጵያ በተያዘው የመስከረም ወር ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች (ሴካፋ) የእግር ኳስ ዋንጫ ለማስተናገድ ዕድሉን ያገኘችው፡፡
ይህም ሆኖ ግን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ለሁለተኛ ጊዜ በፕሬዚዳንትነት እንዲያስተዳድሩ በቅርቡ የተመረጡት አቶ ኢሳያስ ጅራና ስብስባቸው፣ ለዓመታት የተዘነጋውን የታዳጊ ወጣቶች ውድድሩ ዓይኑን እንዲገልጥና በውድድሩም ኢትዮጵያን የሚወክሉ ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እንዲቋቋም ማድረግ ብቻ ሳይሆን የአሠልጣኞች ቅጥርም እንዲፈጸም አድርገዋል፡፡
በዋና አሠልጣኝ ታዲዮስ ተክሉ ከረዳቶቻቸው ዓብይ ካሳሁንና ራህማቶ መሐመድ ጋር በመሆን ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የሆኑ 65 ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክልሎችና ክለቦች መልምለው ዝግጅት ጀምረዋል፡፡ ብዙዎቹ በምርጫው እንዲካተቱ የተደረገው ደግሞ አቶ ኢሳያስና ሥራ አስፈጻሚያቸው በመጀመሪያው የአገልግሎት ዘመናቸው በአገሪቱ ካስጀመሩት ዕድሜቸው ከ15 ዓመት በታች ፕሮጀክት መሆኑ ደግሞ ጅምሩን ‹‹ይበል›› አሰኝቶታል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እንደ ታዳጊ ወጣቶቹ ሁሉ ዕድሜቸው ከ23 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን በማቋቋም ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡ በዋና አሠልጣኝ አጥናፉ ዓለሙና ረዳቶቻቸው ሀብታሙ ዳዲና አዳሙ ኑሞሮ እየተዘጋጀ የሚገኘው ኦሊምፒክ ቡድኑ፣ ዝግጅቱ ደግሞ በቅርቡ ከዴሞክራክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ለሚጠብቀው የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ እንደሆነ ታውቋል፡፡
36 ተጫዋቾችን ያካተተው ቡድኑ ዝግጅቱን የሚያደርገው ሲኤምሲ አካባቢ በሚገኘው የምሥራቅ አፍሪካ የልቀት ማዕከል እንደሆነ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡