Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ሃያ ሁለት አካባቢ ከሄድኩበት ጉዳይ ለመመለስ ስዘጋጅ የገባሁበት ሕንፃ መኪና ማቆሚያ ጋ አራት ለግላጋ ወጣቶች ሲጨቃጨቁ ደረስኩባቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ ምን ይሆን የሚያጨቃጭቃቸው ብዬ ጠጋ ስላቸው በእጃቸው ላይ ረዘም ረዘም ያሉ የካሽ ሬጂስተር ደረሰኞች ይዘዋል፡፡ ቀረብ ብዬ ምን እንደሚያጨቃጭቃቸው ስጠይቃቸው የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦችን ግጥሚያ ውጤት ለመተንበይ፣ ከአቋማሪ ድርጅት ጋር የተወዳደሩበትን በተመለከተ እየተጨቃጨቁ እንደሆነ ነገሩኝ፡፡ እከሌ የሚባለው ክለብ በእከሌ ይሸነፋል ወይም ያሸንፋል በሚለው ውርርድ አንተ ልክ አይደለህም፣ እኔ ልክ ነኝ እየተባባሉ እንደሆነም አከሉልኝ፡፡ ታዳጊ ወጣቶች ለትራንስፖርት ወይም ለሻይ ተብሎ የሚሰጣቸውን እየቆመሩበት ነው ማለት ነው፡፡ ካልሆነ ደግሞ ቤተሰብ እየዛቀ የሚሰጠው ገንዘብ ይኖረዋል፣ ወይም ታዳጊዎቹ ሕገወጥ ድርጊት ፈጽመው ይቆምራሉ ማለት ነው፡፡ የዚህ የስፖርት ቁማር ጉዳይ መላ ካልተፈለገለት አደጋው ከፊታችን እንደሆነ ለመረዳት አለመቻል የሚያስከፍለው ዋጋ አለ፡፡ በዚህ መነሻ እስኪ ወደኋላ ልመልሳችሁ፡፡

ጊዜው ራቅ ቢልም ከጓደኞቼ ጋር ቦሌ አካባቢ የሚገኝ አንድ ዘመናዊ ካፌ በረንዳውን አልፈን ወደ ውስጥ ስንዘልቅ፣ በርካታ ሰዎች ትልቁ የቴሌቪዥን ስክሪን ላይ ዓይኖቻቸውን ሰክተው በተመስጦ በቢቢሲ የሚተላለፈውን ዜና ያያሉ፡፡ እኛም ወንበራችንን ይዘን ፊታችንን ወደ ቴሌቪዥኑ መለስን፡፡ ጋዜጠኞቹ በአሜሪካ ምርጫ ውጤት ላይ እየተነጋገሩ ነው፡፡ አንደኛዋ ጓደኛችን እንደኛ ተባራሪ ወሬ ስላልሰማች ‹‹ማን አሸነፈ?›› ብላ ስትጠይቅ ቤቱ ውስጥ የነበሩት በሙሉ ‹‹ኦባማ›› አሉ፡፡ ጓደኛችን ‹‹እኔ አላምንም፡፡ ሲወራ እኮ የነበረው ሮምኒ እንደሚያሸንፍ ነበር…›› እያለች ስትደነቅ፣ አንድ ለግላጋ ወጣት፣ ‹‹እንግዲህ የአሜሪካ ሕዝብ ኦባማን እንደገና መርጧል…›› አለ፡፡ በእርግጥም በቴሌቪዥኑ ስክሪን ላይ እንዳየነው ኦባማ ማሸነፋቸው ተረጋግጧል፡፡

ቡናና ሻያችንን እየጠጣን ስለአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት የሚተላለፈውን የቴሌቪዥን ዘገባ ስንከታተል አንድ አሜሪካዊ የፖለቲካ ተንታኝ ቀረቡ፡፡ በዕድሜ የገፉት ተንታኝ፣ ‹‹ይህ ምርጫ ከፍተኛ ፉክክር የተካሄደበትና በጠባብ ልዩነት የተሸናነፉበት በመሆኑ፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወደፊትም የበለጠ የሚያጓጓ ይሆናል፤›› ሲሉ፣ ሌላ ተንታኝ ደግሞ፣ ‹‹ሪፐብሊካን ለምን የሕዝቡን ድጋፍ ማግኘት አልቻልንም ብለው ካሁን ጀምሮ ትልቅ ዝግጅት ያደርጋሉ…›› አሉ፡፡ ውይይቱ በየዓይነቱ ቀጥሏል፡፡ በምርጫው ውጤት መጥበብ ምክንያት የአሜሪካ ሕዝብ ለሁለት ተከፍሏል ከሚሉት፣ የምርጫውን ውጤት መተንበይ አልተቻለም እስከሚሉት ድረስ ብዙ ተባለ፡፡ ይህንን እያዳመጥን ሳለ ድንገት አንድ አስገራሚ ነገር ተከሰተ፡፡

ወደ ካፌው በመግባት ላይ የነበሩት ሦስት ወጣቶች በከፍተኛ ድምፅ እየተነጋገሩ ወደ ውስጥ ዘለቁ፡፡ አንደኛው ብስጭትጭት እያለ፣ ‹‹ድሮም እነዚህን ማመን አልነበረብንም፡፡ ሮምኒ ኦባማን አሸንፎ ሥልጣን ይይዛል ስንል እንዲህ ጉድ ይሥሩን?›› ሲል የሚቀልድ መስሎኝ ነበር፡፡ አብረውት የነበሩት አንድ ወንድና ሴት እንደ እሱ እየተናደዱ ስሜቱን ሲጋሩት ግራ ገባኝ፡፡ ካፌው ውስጥ የነበርነው በሙሉ እየገረመን ስናያቸውማ ባሰባቸው፡፡ አንደኛው፣ ‹‹አሜሪካ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እኮ በኦባማ ድል ይኼኔ ጮቤ እየረገጡ ነው…›› ሲል ወፈፌም መሰሉኝ፡፡ በዚህ መሀል ከማዶ የተቀመጠ አንድ ጎረምሳ፣ ‹‹እናንተን ያበሳጫችሁ ምንድነው?›› ብሎ ሲጠይቃቸው ሴቷ ጠረጴዛውን እየደቃች፣ ‹‹የሚዲያውን ወሬ ተማምነን ሮምኒ ያሸንፋል ብለን ሦስት ሺሕ ዶላር ተበላን እኮ… ›› እያለች ስትንጣጣ ደነገጥኩ፡፡ ልጅት ከአነጋገሯ በጊዜው ኢትዮጵያን እንደፈለጉ ይዘውሩ የነበሩ ወያኔዎች ቤተሰቦች ትመስላለች፡፡ እነሱ ነበሩ ዶላርና ዩሮ እንደፈለጉ ሲረጩ የነበሩት፡፡

የ320 ሚሊዮን አሜሪካውያን ዕጣ ፈንታ የሚወስነው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ፣ ጊዜ በሰጣቸው ዘራፊዎች ‹‹እከሌ ያሸንፋል›› በሚል የዶላር መቆመርያ ሲሆን ከነከነኝ፡፡ በጊዜው አብዛኞቹ ወጣቶች ሥራ አጥተው፣ ተስፋ ቆርጠውና የጫት ሱሰኛ ሆነው በከንቱ መቅረታቸው ያንገበግበኝ ነበር፡፡ አብሮን የነበረው ጓደኛችን እንደኔ ከንክኖት ስለነበር፣ ‹‹ደህናው ነገር ሁሉ እኛ ዘንድ ሲደርስ ለምን ይበላሻል? የእነዚህ ወጣቶች ቤተሰቦች የዘረፉትን ሀብት ልጆቻቸው እንደፈለጋቸው ሲረጩት እንዴት ዝም ይላሉ? ድሆቹ ልጆቻችን በአርሰናልና በማንቸስተር ግጥሚያ፣ በባርሴሎናና በሪያል ማድሪድ ጨዋታ ሲጨቃጨቁ፣ ይህም አልፎ ደም የሚያፋስስ ችግር ውስጥ ሲገቡ፣ የወያኔዎቹ ልጆች ግን ከስፖርቱ አልፈው የፖለቲካ ቁማር ውስጥ ተዘፍቀው ነበር፡፡ ያውም ከኢትዮጵያ ሕዝብ በተዘረፈ ሀብት…›› ማለቱ አይረሳኝም፡፡

በአንድ ወቅት አሜሪካ ሄጄ በነበርኩበት ወቅት ያረፍኩበት አካባቢ የትግራይ ተወላጆች ይበዙበታል፡፡ በተለይ የጦርና የሲቪል አመራሮች የነበሩ ሰዎች ልጆች የሚነዷቸው ውድ መኪናዎች የሚያስገርሙ ነበሩ፡፡ አንድ ቀን ምሽት የሚያስተናግደኝ ዘመዴ እስኪ ይግረምህ ብሎ የሚዝናኑበት ክለብ ይዞኝ ሄደ፡፡ ዓይኔ ለማመን እስከሚያስቸግረው ድረስ እነዚያ በቅንጦት የሚኖሩ ወጣቶች ይህንን ዶላር እንደ ዓረብ ቱጃር ይረጩታል፡፡ እነዚህ የተመረጡ የገዥው መደብ ልጆች ናቸው አባቶቻቸውና እናቶቻቸው ከዝርፊያው ማዕድ ላይ ሲነሱ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በጠላትነት ተነስተው የወያኔን የከፋ ሥርዓት መልሰው ለማምጣት የጦረኝነት ፕሮፓጋንዳ ውስጥ በስፋት ተጠራርተው የተነሱት፡፡ በዶላርና በዩሮ የሚቆምሩበትን ሥርዓት ለማምጣት ደግሞ በትግራይ ሕፃናት ደም ይነግዳሉ፡፡

ወደ ጉዳዬ ስመለስ የኢትዮጵያ ወላጆች ለፍታችሁ የምታገኙ ከሆነ የልጆቻችሁን ውሎ ተከታተሉ፡፡ የልጆቻችሁ ወጣትነት በአጥፊው ቁማርተኝነት አይበላሽ፡፡ ልጆቻችሁ ከዚህ አደገኛ ቁማር ውስጥ ካልወጡ ለአገር አጥፊዎች ጭምር መሣሪያ ከመሆን አይመለሱም፡፡ ትናንት በእምዬ ኢትዮጵያ ሀብት ሲቆምሩ የነበሩ የወያኔ ጀሌዎች አገር ለማጥፋት ልጆቻችሁን ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ ተገንዘቡ፡፡ ሀብታሞችም ብትሆኑ ልጆቻችሁን ተቆጣጠሩ፡፡ እናንተ እዚህም እዚያም ብላችሁ ያመጣችሁት ሀብት ብርቱ ተተኪ ወራሽ ካላገኘ ለእሳት ነው የሚዳረገው፡፡ ቁማርተኛ እንኳንስ ገንዘቡንና ንብረቱን ሚስቱን ከማስያዝ አይመለስም፡፡ ለሚስቱ ያልሆነ ደግሞ አገሩን አሳልፎ ከመሸጥ ወደኋላ አይልም፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

(ጥበቡ አሥራት፣ ከሐና ማርያም)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...