Wednesday, November 29, 2023

ሰላምን የናፈቁ ድምፆች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መቀመጫውን በትግራይ ክልል ያደረገው የመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም. በሕወሓት ኃይሎች ከጀርባ መመታቱን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ቀስ በቀስ እየተስፋፋ፣ ዛሬ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የሚል ስያሜን አግኝቷል። እንደ ዋዛ የጀመረው ጦርነት ሁለተኛ ዓመቱን ሊደፍን የቀሩት ከሁለት ወራት ያነሰ ዕድሜ ብቻ ነው። በእነዚህ ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያውያን የገጠማቸው ሞት፣ የሴቶች መደፈር፣ የእናቶች ሥቃይና መከራ ሲታሰብ ግን የውጭ ወራሪ ወይም ባዕድ ኃይል የፈጸመባቸው እንጂ፣ በጊዜያዊ ፖለቲካ ፍላጎት እርስ በርሳቸው የተጫረሱበትና የተቋሰሉበት መሆኑን ለማመን ይከብዳል። የሰሜኑ ጦርነት ወታደሮችን ከማዋደቁ አልፎ ማኅበረሰቦች ደም የተራጩበትና የአገር ስምና ዝና የሟሽሽበት፣ እንዲሁም በቋፍ ያለው ኢኮኖሚ እንደ ሰው የደማበት ነው ማለት ይቻላል። በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የወደሙ የአገር መሠረተ ልማቶች የዜጎች መገልገያ ማኅበራዊ ተቋማት ቁጥር ሥፍር የለውም። በትግራይ ክልል ብቻ ከ1,300 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ሲወድሙ፣ 678 ያህሉ በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በአማራ ክልልም ከአንድ ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። በአጠቃላይ በጦርነት ሲናጡ በከረሙት የአማራ፣ የትግራይና የአፋር ክልሎች በዋናነት፣ እንዲሁም በሌሎች ክልሎች በነበሩ ግጭቶች የወደሙ የትምህርት ተቋማትን ለመገንባት 2.2 ቢሊዮን ዶላር (115 ቢሊዮን ብር) እንደሚያስፈልግ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል። ዘንድሮ ይገኛል ተብሎ የታሰበው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገትም በዚሁ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት እንደማይሳካ መንግሥት በይፋ አሳውቋል። በ2014 ዓ.ም. ብቻ መንግሥት ለዓመቱ ከተያዘው በጀት በተጨማሪ ለሰሜኑ ጦርነት 156 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመልክታል። በመሆኑም ጦርነቱ ኢኮኖሚውንም እያደማ ነው። ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ የፌዴራል መንግሥት በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም. ያወጀውን የተኩስ አቁም ተከትሎ፣ ‹‹አውዳሚው ጦርነት በሰላማዊ መንገድ በውይይት ሊፈታ ነው›› የሚል ተስፋ ለኢትዮጵያውያን ፈንጥቆ የነበረ ቢሆንም፣ የ2015 ዓ.ም. አዲስ ዓመት መቀበያ ዋዜማ ላይ ጦርነቱ ዳግም ተመልሷል። ይህም ገና ከወዲሁ ሞት፣ መከራ፣ ሥቃይና መፈናቀልን እየፈጠረ ነው። ነገር ግን በርካታ ኢትዮጵያውያን ይህ ደም መፋሰስ ይብቃ ማለት ጀምረዋል። የሪፖርተር ዘጋቢዎች ያነጋገሯቸው የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊያና ፖለቲካዊ ዘርፎችን የሚወክሉ ታዋቂ ግለሰቦችና ኢትዮጵያውያን አጥብቀው የናፈቁት ሰላም በአዲሱ ዓመት ይመጣ ዘንድ የተመኙት እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

“… ሕዝቡ እንዴት ልዋል? ምን ልብላ? ልጠጣ? የሚለው ነገር የማያሳስበው አገር ብትኖረው ደስ ይለኛል”

መንግሥቱ ከተማ (ፕሮፌሰር)፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የተገባደደው ዓመት ከአገሪቱ ኢኮኖሚ አንፃር ብንመዝነው ጥሩ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ጤናማ ያልሆነ ኢኮኖሚ ስናስተናግድ ቆይተናል ብዬ እገምታሁ፡፡ ያ የሆነበት ምክንያት የጦርነቱ ተፅዕኖ (የውስጥ ጦርነት) ከባድ ነበር፣ በእሱ ላይ ደግሞ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ተጨምሮበት የዋጋ ግሽበቱ በ30 በመቶ ቤቶች ውስጥ ለረዥም ጊዜ ቆይቷል፡፡ እንዲያውም የምግብ የዋጋ ግሽበት ሲታይ ደግሞ ከ40 በመቶ በላይ የዘለለባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ በዚያም የተነሳ ኅብረተሰቡ ተማሮ የቆየበት ነው፡፡ ዓመቱ ግጭት በየቦታው ሲካሄድ የነበረበት ነው፣ የአገሪቱ የዕዳ ጫና በጣም ከባድ ሆኗል (ለረዥም ጊዜ ተንከባልሎ የመጣ ቢሆንም)፡፡ አሁንም አገሪቱ ትልቅ ዕዳ ውስጥ ናት፡፡ የአገሪቱ የንግድ ሚዛን ክፍተቱ እየሰፋ ሄዷል (ወደ ውጭ የሚላከውና ከውጭ የሚገባው ሲተያይ)፣ ከውጭ ብዙ ምርቶችን የምታስገባው አገር የምትልከው ትንሽ ነው፡፡ የተለያዩ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት ብዙ ዶላር የሚፈለግ ሲሆን፣ ምርታችን ወደ ውጪ ተልኮ የሚገኘው ዶላር ደግሞ ትንሽ ነው፡፡ የመንግሥት የውስጥ ወጪና ገቢ የተራራቀ በመሆኑ ወጪ ይበዛል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁሉን ችግሮች ያስተናገድንበት ዓመት ነበር፡፡ ሌላው ጉዳይ ደግሞ በአገሪቱ ዝቅተኛ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ የእንስሳት ሀብታችንን በእጅጉ ጎድቷል፡፡ ያ ብቻም ሳይሆን በአካባቢዎቹ የሚኖረውን ማኅበረሰብ በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቷል፡፡ በአጠቃላይ ዓመቱ ጥሩ አልነበረም፡፡

በሌላ በኩል እነዚህን ችግሮች በመከሰታቸው ራሳችንንና አቅማችንን እንድናይ ለዚያም መፍትሔ መፈለጉ ግዴታ እንደሆነ የተገነዘብንበት ዓመትም ይመስለኛል፡፡ ለቀጣይ ዓመት ብዙ መሥራት እንዳለብን ያመላከተ ዓመት ስለሆነ ጥሩ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ በዓመቱ መንግሥት ሲሠራቸው የነበሩ ተግባራትን ተመልክተናል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ኢኮኖሚውንም ሆነ ዲፕሎማሲውን የተመለከቱ ናቸው፡፡ ከኢኮኖሚው ጋር በተገናኘ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ በስንዴ ምርት በአጭር ጊዜ ራስን ችሎ ወደ ውጪ ኤክስፖርት ይደረጋል የሚል ዕቅድ ተይዞ እየተሠራበት ያለ ይመስላል፡፡ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ ላይ እየተሠራ ነው፡፡ መንግሥት ዕቅዱን በተወሰነ ደረጃ ይከለሳል የሚል ሐሳብ አለው፡፡ አሶሴሽናችንም እነዚህ ዕቅዶች መከለስ አለባቸው የሚል አቋም ይዘን በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው አካላት ተነግሯቸዋል፡፡ ዕቅዱ ሲዘጋጅ አገሪቱ አሁን እያስተናገደቻቸው ያሉ ችግሮች ባልነበሩበት ወቅት ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ ኮቪድና ግጭት ዕቅዱ ሲዘጋጅ ያልነበሩ ጉዳዮች እንደ መሆናቸው፣ እንዲሁም ጦርነቱ በአገሪቱ ላይ ትልቅ ጠባሳ ጥሏል፡፡ ስለሆነም ያንን መከለስ (ሪቫይዝ) ያስፈልጋል፡፡ አብዛኛውን ትኩረት በማገገሚያ ስትራቴጂዎች ላይ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማልማት በራሱ ትልቅ ጥረት ስለሚጠይቅ በዚያ ላይ ትኩረት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የእኛን አሶሴሽን ጨምሮ ሌሎች የሙያ ማኅበራትም መረጃን የተመረኮዘ ጽሑፎችን ሲያወጡ፣ በመንግሥት በኩል የማየትና ከተቻለም የመተግበር አዝማሚያ ቢያሳይ፣ እንዲሁም የማሳተፉን ጉዳይ ቢጨምር ጥሩ ነው፡፡

ትንሽ ከበድ ቢልም እንደ ግለሰብ አዲሱ ዓመት ከ2014 ዓ.ም. የተሻለ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አንደኛው የሩሲያና የዩክሬን ግጭት ወይም ተፅዕኖ ብዙ የሚቀጥል አይመስለኝም፣ ወይ ራሳቸው መፍትሔ ይፈጥራሉ፡፡ ካልሆነም ሌሎች አገሮች በሚያደርጉት ትብብር ሌሎች አማራጮችን ልናገኝ ስለምንችል በአጭር ጊዜ እንደተጎዳነው ጉዳቱ ላይቀጥል ይችላል፡፡ ከዚያም ባሻገር በአገሪቱ ከላይ በገለጽኩት ሁኔታ በመንግሥት የተወሰዱት ዕርምጃዎች ኢኮኖሚው ላይ ጥሩ ተፅዕኖ ስለሚያስከትሉ 2015 ዓ.ም. የተሻለ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ለዚህ ሕዝብ ምን ትመኛለህ ብባል፣ ሕዝቡ ለረዥም ጊዜ ተሰቃይቷል ማለት ይቻላል፡፡ የአኗኗር ሁኔታውና የዋጋ ግሽበቱ ሰው መኖር የሚያቅተው ደረጃ ላይ የደረሰበት ጊዜ አሳልፈናል፡፡ ከዚህም የተነሳ የተለያዩ ወንጀሎች በተለይ ስርቆት እየተስፋፋ የሄደበት ነው፡፡ ሰው መኖር ሲያቅተው አንዱ እየበላ ሌላው ሳይበላ ሲቀር ዝርፊያና የመሳሰሉት ነገሮች እየተስፋፉ ሄደዋል፡፡ በዚህ ከቀጠለ በጣም የከፋም ሊሆን ስለሚችል ተስፋ የማደርገው ይህች አገር በኢኮኖሚ ራሷን የምትችልበት፣ ከሌሎች አገሮች ጥገኝነትን በተወሰነ ደረጃ የምትቀንስበት፣ የሕዝቡ አኗኗር እንዴት ልዋል? ምን ልብላ? ልጠጣ? የሚለው ነገር የማያሳስበው አገር ብትኖረን ደስ ይለኛል፡፡ ብዙ ሥራ ይጠይቃል፣ የሁሉንም አስተዋጽኦ፡፡ ማለትም የመንግሥትንም ሆነ የሕዝቡን፣ የተቋማትንም አስተዋጽኦ ይጠይቃል፡፡ ተባብሮ ከተሠራና ሁሉም የራሱን አስተዋጽኦ ካደረገ የማይሻሻልበት ምክንያት የለም፡፡

ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ካልወጣን ሁሌም እንደፈለጉ የሚያደርጉን አገሮች ይበዛሉ፡፡ የሆነ ዕርምጃ በወሰድን ቁጥር (ለምን ይህንን ትወስዳላችሁ? የሚል) በአብዛኛው የዓለም አገሮች የሚከሰቱ ግጭቶች መንስዔአቸው የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ አገር ለማደግ በሚፍጨረጨርበት ጊዜ ያንን የማይፈልጉ ብዙ አገሮች አሉ፡፡ በዚህ ዘመን ከዚህ ዓይነት ጉዳይ ማምለጥ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አገሮች ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግ ያን ያህል ፈተና አልነበረባቸውም በእኔ ዕይታ፡፡ አሁን አደጉ የሚባሉ አገሮች ትኩረት አድርገው ሠርተው ኢኮኖሚያቸውን አሳደጉ፡፡ ከዚያ በኋላ ወታደራዊ አቅማቸውን ወደ ማጠንከርና ሌሎች አገሮች ላይ ተፅዕኖ ወደ ማድረግ ሄዱ፡፡ በዚህ ዘመን መጀመርያ ኢኮኖሚያችንን እናሳድግ የሚባልበት ሁኔታ አማራጩ ዝቅተኛ ነው፡፡ በኢኮኖሚ እንደግ ሲባል ብዙ ተፅዕኖ የሚያስከትሉ ሌሎች አገሮች አሉ፡፡  ለምሳሌ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ያለውን ብንመለከት ‹‹ግድቡ የውኃ አቅርቦትን ይቀንሳል›› የሚለው ጉዳይ አይደለም ዋነኛ መነሻ ጉዳዩ፣ ከዚያ ጀርባ ያለው ሐሳብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ቀና እንዳትል የሚፈልጉ ብዙ አገሮች አሉ፡፡ የሚረዱ የማይመስሉ ያደጉ አገሮች ሳይቀሩ ይህን ነገር አይፈልጉም፡፡ በመሆኑም ከዚያ ለመውጣት ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ያንን ፈተና አልፈን ራሳችንን የምንችልበት ደረጃ ብንደርስ ደስ ይለኛል፡፡ በቀደመው ጊዜ ከላይ እንደገለጽኩት አንዳንድ አገሮች በኢኮኖሚ አድገው ከዚያ ወደ ወታደራዊው አቅም ገነቡ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ኢኮኖሚውን ትተው በወታደራዊው አቅም ጠንክረው ወጥተው በኢኮኖሚ ግን ሕዝባቸው ያልተንቀሳቀሰባቸው አገሮች አሉ፡፡ ዛሬ ኢኮኖሚውን ትተን በወታደራዊው አቅም ይጀመር ቢባልም አቅሙ የለም፡፡ በኢኮኖሚም ይጀመር ቢባል ተፅዕኖው ከባድ ነው፡፡ ስለሆነም ቀስ ብለው ሁለቱንም እያጠናከሩ የመሥራት ስትራቴጂን ተግባራዊ እንዳደረጉት ቻይናና መሰል አገሮች ካልተሄደ ከባድ ሁኔታ ውስጥ ያለን ይመስለኛል፡፡

‹‹በጠረጴዛ ዙሪያ ከተወያየን የማንፈታቸው ችግሮች የሉም››

መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር)፣ የምጣኔ ሀብት መምህርና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ

2014 ዓ.ም. ብዙ መንገራገጭ የነበረበት ዓመት ነበር፡፡ ብዙ  የፖለቲካ ትኩሳት ነበር፡፡ አሁን የቀጠለውን ጨምሮ የእርስ በርስ ጦርነት የተስተናገደበትና የኑሮ ውድነት ማኅበረሰቡን የጎዳበት ወቅት ነበር፡፡ ቀጣዩ ዓመት ሰላም የሰፈነበት፣ የፖለቲካ መቻቻል ባህላችን የሚያድግበት፣ ዴሞክራሲ የሚሰፍንበት፣ ሰላም የሚመጣት፣ የፖለቲካ መረጋጋት የሚታይበት፣ የኢኮኖሚ መረጋጋት የሚፈጠርበት፣ በአጠቃላይ በአገሪቱ ሰላም ወርዶ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዜግነቱ በእኩልነቱ የሚታይበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ የመጣንባቸው ብዙ መንገዶች የጦርነት ታሪኮች ናቸው፡፡ ከእነዚህ የጦርነት ታሪኮች ያተረፍነው ውድመት እንጂ ምንም የተለየ ትርፍ የለም፡፡ ስለዚህ በጦርነት የሚገኝ ነገር ከሌለ፣ በወንድማማችነትና በአንድነት ስሜት ይህች ብዙ ሀብት ያላትን አገር ማሳደግ እንችላለን፡፡ ለአብነት እንኳ የሰው ሀብት፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ ሌላውና ትልቁ ሀብት ደግሞ የማኅበራዊ ሀብት፣ መግባባትና አብሮ መኖር፣ ስለሰው መጨነቅና ማሰብ ጥሩ አገራዊ ሀብቶች በመሆናቸው ሕዝቡ ይህን ተላብሶ በመግባባት አብሮ መኖር እንዲችል እመኛለሁ፡፡ አንዲት አገር አለችን፡፡ ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ በጋራ እንድንጠብቃት ምኞቴ ነው፡፡ በመነጋገርና በመወያየት እኛ መግባባት ከቻልን አገራዊ መግባባት ላይ በመድረስ የኢትዮጵያን ችግር የምንፈታበት ዓመት ይሆናል ብዬ እመኛለሁ፡፡

በመጪው ዓመት እውነት ለመናገር ባለብዙ ተስፈኛ ነኝ፡፡ እንደ ፖለቲከኛ ባለፉት ወራት ያሳለፍናቸው የፖለቲካ ውይይቶች አሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ፖለቲከኞች በአንድ አዳራሽ ስንገናኝ ብዙ ሐሳቦች የሚለያዩን ቢኖሩም የሚያስማሙን ጉዳዮች ላይ ግን እንደርሳለን፡፡ ስለዚህ እነዚህን ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ ከተወያየን የማንፈታቸው ችግሮች የሉም፡፡ ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስተካከል አለብን፡፡ የዴሞክራሲ ምኅዳር ሲተካከል የሕግ የበላይነትን ማስፈንና ሰላምን ማምጣት ይቻላል፡፡ የሕግ የአስፈጻሚው አካል ደግሞ ሕግ የማስከበር ሥራውን መሥራትና ሁሉም ሰው ከሕግ በታች ሆኖ ባለሥልጣኑም ሆነ ተራው ሕዝብ በሕግ ተገዥ መሆን አለበት፡፡ የተጀመሩ ሥራዎች ሁሉ ሊጠናቀቁና ሕዝብን ሊጠቅሙ የሚችሉት ሰላም ሲመጣ በመሆኑ ይህ ከተስተካከለ ለውጥ ይመጣል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

‹‹የአገሪቱ ልሂቃን ከመገዳደር ፖለቲካ ወደ መደራደር ፖለቲካ መሄድ ነበረባቸው››

መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፣ የኦፌኮ ሊቀመንበር

2014 ዓ.ም. በአጭር ቋንቋ አገሪቱና ሕዝቦቿ እጅግ በጣም  አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የገቡበት ጊዜ ነበር፡፡ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ተፈጥሮ ሲያበቃ እንደና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ የገባንበት ወቅት ነበር፡፡ የአገሪቱንም ሆነ በአጠቃላይ የሕዝቦቿን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመወሰን የማንችልበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ያው እንግዲህ ለአገራችን የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጠርልን ከመጠበቅና ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደንወጣ ከመመኘት ባለፈ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ ሕዝቡ አቅም አጣ፣ እንጂ ለተፈጠረው ችግር ጥሮ ነበር፡፡ ሕዝብም አቅም አጣ መንግሥትም መቆጣጠር አልቻለም፣ የተሻለ አቅጣጫ ማምጣት አልቻለም፡፡ የአገሪቱ ልሂቃን ከመገዳደር ፖለቲካ ወደ መደራደር ፖለቲካ መሄድ ነበረባቸው፣ ነገር ግን መሄድ አልቻሉም፡፡ ይህ መፈታት አለበት፣ ይህ ካልተፈታ ወዴትም መሄድ አንችልም፡፡ እዚህ ላይ ነው ጧትና ማታ ስለሰላም፣ ስለልማት፣ ስለብልፅግናም ሆነ ሌላው ነገር ሲወራ ወደ ልቦናችን ተመልሰን እውነታውን መጋፈጥ፣ በሀቅና በሙሉ ልብ አገሪቱና ሕዝቦቿን ወደ ሰላምና ወደ መረጋጋት ማምጣት አለበት፡፡ ምኞት ብቻ፣ ህልም ብቻ ችግርን አይፈታም፡፡ ብዙ ጊዜ ችግርን ጧት ማታ እየፈጠርክ እግዚአብሔር ይረዳኛል ብለህ መፀለይ ፈረንጆች ይረዱኛል፣ ያግዙኛል ብሎ መመኘት የትም አያደርስም፡፡ ሀቁ ግን የችግሮች ፈጣሪ እኛው ነን፡፡ አገሪቱን ለመምራት ሁሉንም በእጃቸው ያስገቡ ኃይሎች በሰከነ አዕምሮ ሁኔታዎችን አስበው ወደ መነጋገር መምጣት ካልተቻለ ወዴትም መሄድ አይቻልም፡፡ ፈረንጆች የፖለቲካ አጣብቂኝ የሚሉት አለ፣ እኛም እጅግ አደገኛና መስቀለኛ የሆነ መንገድ ላይ ነን፡፡ በመሆኑም ይህን በመረዳት መሥራትና ከዚህ መውጣት ያስፈልገናል፡፡ ሃይማኖተኞች ‹‹ቂም ይዞ ፀሎት ሳል ይዞ ስርቆት›› እንደሚሉት፣ ከዚህ ለመውጣት ጧትና ማታ ከመፀለይና ከሰበካ ወጥተን መሥራትና ማሳየት ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ያሉት ሙከራዎች በእርግጠኝነት ወደ እዚህ ያመራሉ የምትላቸው ሳይሆን አደገኛና መስቀለኛ መንገድ ናቸው፡፡ አገሪቱ ያላየችው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡ ስለዚህ ጦርነቱ ከአጠቃላይ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውሱ ጋር ተደማምሮ ብዙ ቀውሶች እያየን ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ተዘፍቀናል፣ ከዚህ ለመውጣት ቀላል አይሆንም፡፡ ሰላም እንኳ ቢፈጠር የኢኮኖሚውና የፖለቲካ ሁኔታው መስተካከል አለበት፡፡ እነዚህ ካልተስተካከሉ የምንፈልገው ልማትና ብልፅግና በሰበካ ሊመጣ ስለማይችል፣ በቀጣዩ ዓመት ይህ ሁሉ ቀውስ ተፈቶ ብናይ አሸናፊ ያደርገናል፡፡ ነገር ግን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው፡፡

‹‹እኔ ወደፊት ጥሩ ነገር አለ ብለው ከሚያምኑና ከሚያስቡ ውስጥ ነኝ››

እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር)፣ ዋና ዕንባ ጠባቂ

2014 ዓ.ም. አብዛኛው ጊዜ መጀመሪያ በጦርነት፣ ከዚያም ጦርነት ቆሞ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ እንኳ የነበረው ሁኔታ ሲታይ ውስጣዊ ሰላም አልነበረንም፡፡ በዚህም ምክንያት መረጋጋት የለም፡፡ ተረጋግተህና አስበህ ሥራዎችህን  ለመሥራት የሚያግዝ ሁኔታ አልነበረም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ደግሞ የኑሮ ውድነቱ በጣም ጫፍ  የነካ ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ የፖለቲካ ቀውስና የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር ተደማምሮ የፀጥታ ችግሩ ተፈታትኖን ነበር፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የህዳሴው ግድብ ሦስተኛ ዙር ሙሌት የተሞላበት ጊዜ ስለነበር የሆነ የተስፋ ስሜት ነበር፡፡ ምንም እንኳ ፈተናዎች ቢኖሩም የውኃ ሙሌቱን ስታይ ለካ እንደዚህም አለ የሚል የተስፋ ጭላንጭል ሲታይ፣ መልካም ዕድሎች እንደነበሩ ማየት ትችላለህ፡፡ ስለዚህ ሁለቱንም  ዓይነት ስሜቶች ተሻግረናቸዋል ማለት ይቻላል፡፡

      በ2015 ዓ.ም. ላይ እንግዲህ በአጠቃላይ ለመላው ሕዝባችንና ለአገሪቱ ሰላም የሠፈነበትና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ጉሊት ከሚቸረችሩት እስከ ትልልቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች የተረጋጋ ሰላም አግኝተው ወደ ማምረት የሚገቡበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ይሆናል የሚልም ተስፋ አለኝ፡፡ ወደ እኛ የእንባ ጠባቂ ተቋም በምንመጣበት ጊዜ ዋነኛውና በተለይ ለኑሮ ውድነቱም ሆነ ለፀጥታው የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የዴሞክራሲ ሥርዓት በአግባቡ ሥር ስላልሰደደ በመሆኑ፣ በሚቀጥለው ዓመት እነዚህ ሁኔታዎች ሥር ሊሰዱ የሚችሉበት ሁኔታና መሠረት የሚጣልበት ጊዜ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ እኛም እንደ ተቋም ከ20 በላይ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት ከመልካም አስተዳደርና ከአገልግሎት አንፃር ምን ላይ ናቸው የሚለውን ነገር ደረጃ የምናወጣበትና የምንለይበት ጊዜ እንደሚሆን፣ በአጠቃላይ እንደ አገር ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለቅመን ለመንግሥት ምክረ ሐሳብ የምናወጣበት፣ ሕግና ፖሊሲ እንዲወጡ የሚያስፈልግ ከሆነ ሊወጡ የሚችሉበት ሁኔታ የሚመቻችበት ጊዜ ይፈጠራል የሚል አጠቃላይ ተስፋ አለን፡፡ እኔ ወደፊት ጥሩ ነገር አለ ብለው ከሚያምኑና ከሚያስቡ ሰዎች ውስጥ ነኝ፡፡ አብዛኛውን ፈተናዎች ባለፉት ጊዜ እየጨረስን እየመጣን ነውና የሚቀጥለው ዓመት በሰላምም ሆነ በኑሮ ሁኔታ በአጠቃላይ የተሻለ ነገር ይመጣል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

 

‹‹ባህላችን ሰላምን ትኩረት ካደረገ የምንፈልገውን ማግኘት እንችላለን››

ጣሰው ወልደሃና (ፕሮፌሰር)፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት

2014 ዓ.ም. በርካታ ችግሮች የነበሩበት ቢሆንም› የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉን መሻገር ችሏል፡፡ ከ2014 ዓ.ም. መማር ያለብን በችግር ጊዜ በፅናት መቆም፣ ሕይወትን መምራትና ለሰላም መታገልን ነው፡፡ ወደፊትም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሰላም እንዲወርድ ማድረግና የኢኮኖሚው ሁኔታ አሁን ካለበት ወደ ተሻለ ሁኔታ እንዲሸጋገር፣ ኅብረተሰቡ ካለበት የኑሮ ውድነት ተላቆና የሰላሙ ሁኔታ ተስተካክሎ ማየትን እመኛለሁ፡፡ ስለሆነም ሰላም በሕዝብ ተሳትፎ የሚመጣ በመሆኑ ኅብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት፡፡ ከግለሰቦች ጀምሮ ሰላም ከታሰበ እንደ አገርም ሰላም ሊመጣ ይችላል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ከሰሞኑ ጦርነት ጋር በተገናኘም ሁሉም ወገኖች ፊታቸውን ወደ ሰላም አዙረው በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሰላም ከእኛ ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ ጦርነት የምንፈጥረውም ሰላም የምንፈጥረውም ራሳችን በመሆናችን፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ሰላምን ትኩረት ካደረግን የምንፈልገውን ማግኘት እንችላለን፡፡

‹‹አዲሱ ዓመት ችግሮችና ጉድፎች ተወግደው ተስፋ የምንሰንቅበት ነው››

ኮሎኔል ጌትነት አዳነ፣ የመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር

እንደ አንድ ትልቅ የአገር መከላከያ ሠራዊት ያለፈውን ዓመት ስንዘጋጅ ነበር የቆየነው፡፡ ዝግጅቱም አንድ ትልቅ መደበኛ ሠራዊት መዘጋጀት እንዳለበት ይሆናል፡፡ ጠላትን አስበህ ትዘጋጃለህ፣ ግን ደግሞ ያልጠበቅከውም አደጋ ቢደርስ እሱን ለመመከት የአገር ሉዓላዊነት ለመጠበቅ አስበህ ትዘጋጃለህ፡፡ ዝግጅታችንና ልኬታችን በአንድ አገር ሠራዊት ልክ ነው እንጂ፣ አገር ውስጥ ላለ ቡድን ብቻ ታስቦ የሚደረግ አይደለም፡፡ ሠራዊቱ በ2013 ዓ.ም. የተጎዳው ከዚያ በፊት ሥልጣን ላይ የነበረው አካል ፖለቲካን ሠራዊቱ ውስጥ አስብቶ እንዴት እንዳደረገው ይታወቃል፡፡ እሱን ጠግኖ በርካታ ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል፡፡ አንደኛው ስኬትም እሱ ነው፡፡ በአንድና በሁለት ብቻ የማይታሰቡ በኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎች ሲመጡም ለመመከት የተቋቋመበት ሚስጥር እሱ ነው፡፡ የዘመኑ ጦርነት መልኩን ቀይሮ ግራጫ (ቅይጥ ዓይነት) መልክ ያለው ነው፡፡ አንደኛው በሚዲያ ሽብር ይሞግትሃል፣ ሌላው ደግሞ ሕዝባዊ የሆኑ እንቅስቃሴዎች፣ ተቃውሞዎችና ልዩነቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ ነው፡፡ የሠራዊቱን ሥራ ዘርፍ ብዙ የማድረግ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡ ስለዚህ እሱንም በመመከት ሥራ ላይ ነበር የእኛ ዝግጅት የነበረው፡፡ አሸባሪዎቹ ሕወሓት፣ ኦነግ ሸኔ፣ አልሸባብና የተለያዩ የህዳሴ ግድብን ለማደናቀፍ የሚመጡ በአጠቃላይ የሰርጎ ገቦችን ጥቃቶች በማምከን በጣም ውጤታማ ሥራ ላይ ነው መከላከያችን የሚገኘው፡፡

የኅብረተሰባችን ባህል እንደሆነው አዲሱ ዓመት ችግሮችና ጉድፎች ተወግደው ተስፋ የምንሰንቅበት ነው፡፡ ዓመት ሲቀየር በቴክኖሎጂም፣ በዕሳቤም ልዩነቶች የሚመጡ ስለሆነ፣ እንደ ሠራዊትም ዘመኑን የዋጁ ዝግጅቶች ያስፈልጉናል፡፡ 2015 ዓ.ም. እንደ ዓምናው አይሆንም፡፡ ፈተናዎች መልካቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ እንጂ፣ ለማደግ በምናደርገው ጥረት ምንጊዜም ፈተናዎች አያቋርጡም፡፡ እኛ ጦርነት እንዲኖር አንፈልግም፡፡ ነገር ግን ከተከሰተም አውዳሚነቱን በመቀነስ ለመመከት አሁንም ዝግጅት እናደርጋለን፡፡ በ2015 ዓ.ም. በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ካሉ ማኅበረሰቦች የሚጠበቀው አንድ መሠረታዊ ነገር ቢኖር፣ አሁን ኢትዮጵያ ብሔራዊ ኃይል የሚባለውን የታጠቀውንና የተደራጀውን ኃይል አሠልፋ እየሞገተች እንዳለች እንዲገነዘቡ ነው፡፡ አይበለውና ይህ ሠራዊት ቢሸነፍ ‹‹አገር የምትባል አለችን ወይ?›› በማለት አብረን ለምን አንነሳም ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ የመከላከያ ሠራዊት የመጨረሻ ምሽግ ነውና ይህ ታውቆ አንድ በመሆን ድጋፍ እንዳይለየን፡፡

‹‹በአዲሱ ዓመት ኢትዮጵያ ከጫና ነፃ ወጥታ ዴሞክራሲን መለማመድ አለብን››

ራሔል ባፌ (ዶ/ር)፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጸሐፊ

2014 ዓ.ም. በሰላም ማለፉ በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ዓመቱ ፈተናዎች የበዙበትና አገራችን ትልቅ ችግር ውስጥ የገባችበት ነበር፡፡ እዚህም እዚያም የንፁኃን ዜጎች ሞት፣ ጅምላ ግድያ፣ ማንነት ተኮር ጥቃቶችና ግጭቶች የበዙበት ነበር፡፡ ይህ መቼም እጅግ አሳዛኝ ጉዳይ ሲሆን ወንድማማችና እህትማማቾች የሆኑ የአንድ አገር ሕዝቦች በዚህ ውስጥ ማለፋቸው በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ልጆች፣ እናቶችና እህቶች በፆታቸው ሳቢያ የተጠቁበት ሁኔታ በጣም አሳዛኝ ነበር፡፡ ከሕወሓት ጋር የተደረገውም ጦርነት ቢሆን አግባብነት የሌለው ብቻ ሳይሆን፣ በሰውም ሆነ በንብረት እጅግ በጣም የጎዳን ጦርነት ነበር፡፡ ምንም ትርፍ ለሌለው ነገር አውዳሚ ጦርነት ነው የተካሄደው፡፡ በእነዚህ ሁሉ አስከፊ ሁኔታዎች ውስጥ አልፈን ፈጣሪ ረድቶን አንፃራዊ ሰላም አግኝተን ለአዲስ ዓመት መብቃታችን በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሁሉም ጊዜ አለው፡፡ አሁን የምንገኝበት ቀውስ የራሱን ጊዜ እየጨረሰ ነው ያለው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታትና በተለይ የሸኝነው 2014 ዓ.ም. የኖርንበት ፖለቲካ የፈጠረውን አስከፊ ቀውስ ያየንባቸው ነበሩ፡፡ እነዚህን ዓመታት በከፋ ሁኔታ ነው ያለፍነው፡፡ ከዚህ በኋላ እንደ አገር ሰከን ብለን የምናስብበት ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሕወሓትም ቢሆን ወደ ራሱ ተመልሶ ግጭት የሚያበቃበት ጊዜ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ አገራችን በሰላም ወደ ብሔራዊ ምክክሩ ገብታ ችግሮቿን የምትፈታበት ዓመት ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ እግዚአብሔርም ጣልቃ እንዲገባና ነገሮች እንዲስተካከሉ ፀሎቴ ነው፡፡

የመድበለ ፓርቲ ፖለቲካ መሠረት ይጣላል የሚል ብዙ ተስፋ ነበር፣ ብዙ ጥረቶችም ነበሩ፡፡ ሆኖም ብዙ መሻሻል በዚህ ዘርፍ አልመጣም፡፡ ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ ነፃ ይሆናል ብለን ገምተን ነበር፣ ነገር ግን እንደገመትነው ሳይሆን ነው የተጠናቀቀው፡፡ የተመኘነው ተሳክቶ ምርጫው ነፃ ሆኖ ቢጠናቀቅ ኖሮ ፖለቲካችንም ከጥሎ ማለፍ ጨዋታ የወጣ ይሆናል ብለን አስበን ነበር፡፡ ከግል ዕሳቤ ወጥቶ አገር የሚያክም ይሆናል ብለን ነበር፡፡ እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ እንዲሁም እንደ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አገርን እናስቀድም ብለን ስንነሳ፣ ከዚህ ከመጠላለፍና ከሴራ ፖለቲካ እንወጣለን ብለን ተስፋ በማድረግ ነበር፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ሥርዓቱ መውጣት አልቻለም፡፡ እንዲያውም ከነበረበት በከፋ ሁኔታ ሲሄድ ነው የታየው፡፡ የገዥው ፓርቲ አካሄድ ትንሽ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ተስፋ ያጨለመ ነበር፡፡ በፖለቲካችን በአጠቃላይ ብዙም መሻሻል አላየንም ነው የምለው፡፡

ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር መጀመሪያ እንዳለው ሁሉ ፍፃሜ አለውና ከኢሕአዴግ የተወረሰው የአንድ ፓርቲና የአንድ ወገን የበላይነትን የማስቀጠል የብልፅግና ፖለቲካ ፍፃሜው ጋ የደረሰ ይመስለኛል፡፡ አገርን እንደ ግል ንብረት አድርጎ በፍፁም የበላይነት የመዘወር የኢሕአዴግ ፖለቲካ ባልሆነ መንገድ ቢያልቅም መክሰሚያው ጋ የደረሰ ይመስለኛል፡፡ ይህ እንደሚሆን ደግሞ ብዙ መገለጫዎችና ምልክቶችን እያየን ነው፡፡ አገሪቱን በአንድ ፓርቲ የበላይነት መምራት የሚቻልበት ዕድል እየጠበበ ነውና መክሰሙ ግድ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያን ገንብተንና ለአገር በሚጠቅም መልኩ ወደ መድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት መሸጋገር የምንችለው እንዴት ነው ወይም ከሥርዓቱ መላቀቅ የምንችለው በምን መንገድ ነው የሚለው ላይ ማተኮር ጠቃሚ ነው፡፡ ሥርዓቱ ከነበረው የኢሕአዴግ ሥርዓት ምንም የተለየ ለውጥ ያላመጣ በመሆኑና እንዲያም ወደ ከፋ ጫፍ የሄደ በመሆኑ፣ በፖለቲካችን ብዙም መሻሻል ማምጣት አልተቻለም፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ከምንገኝበት ሁኔታ ተምረን የብሔራዊ ምክክሩን እንደ መፍትሔ እስካመንና እስከያዝነው ድረስ ከዚህ ውስጥ የምንወጣበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

አሁን ነፍጥ አንግበው የሚዋጉ ወንድሞቻችን እኮ ሰላማዊ መፍትሔ ለችግሮቻችን ባለመፈለጋችን ወደ እዚያ የገቡ ናቸው፡፡ በምክክር ለችግሮቻችን መፍትሔ የምናገኝ ከሆነ 2015 ዓ.ም. የመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት በኢትዮጵያ የምንገነባበት ነው የሚሆነው፡፡ እንደ አገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ነፃ መውጣት አለበት፡፡ የትግራይ ሕዝብም ቢሆን ከሕወሓት አፈና ነፃ መውጣት አለበት፡፡ ከአንድ ፓርቲ አፈና፣ ከካድሬዎች አፈና ነፃ መውጣት አለብን፡፡ የትግራይ ሕዝብ ብቻ አይደለም ጠቅላላ የኢትዮጵያ ሕዝብ አፈና ውስጥ ነው ያለው፡፡ በካድሬ ሥርዓት ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ በኃይልና በአፈሙዝ ተይዘን ነው የሚኖረው፡፡ ስለዚህ ነፃነቱ ለትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ አስፈላጊ ነው፡፡

ነፃነት ስንል ፍትሐዊ አስተዳደር መኖር ነው፡፡ ነፃነት ስንል መልካም አስተዳደርና ፍትሕን ፍለጋ ነው፡፡ በነፃነት የዴሞክራሲ ልምምድ መፍጠር ነው፡፡ ነፃ ምርጫ የሚኖርበትን ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው፡፡ የትግራይ ሕዝብም ፍላጎት ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ የሕወሓት አፈና ግን አልሰጠውም፡፡ በውስን ቦታ፣ ያውም አፈሙዝ ይዞ፣ በፖለቲካው ለ50 ዓመታት ያህል የመከፋፈልና የልዩነትን ዘር እየዘራ ሕወሓት ሕዝቡን ስለገዛው በትግራይ ውጤታማ የሆነ የአፈና ሥርዓት ፈጥሯል፡፡ የጫና ልዩነት ነው እንጂ ችግራችን እንደ አገር አንድ ዓይነት ነው፡፡ ስለዚህ በአዲሱ ዓመት ኢትዮጵያ ከጫና ነፃ ወጥታ ዴሞክራሲን መለማመድ መጀመር አለብን ነው የምለው፡፡ አዲሱ ዓመት ከነዚህ ችግሮች ተላቀን ብሔራዊ ምክክሩን የምናሳካበት ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሙሉ ለሙሉ በአንድ ዓመት ያሰብነውን ባንሠራ እንኳ ገሚሱን የምናሳካበት እንዲሆን ነው ተስፋ የማደርገው፡፡   

‹‹ከግትርነት ወጥተን መፍትሔ ለማግኘት ከጣርን ችግራችን ይቃለላል››

አረጋ ይርዳው (ዶ/ር)፣ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት

በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገራችንና በዩኒቨርሲቲያችን ዓመቱ ብዙ ፈተናዎች የበዛበት ነበር፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ነጥለን ካየነው የሰላም ችግር የነገሠበት፣ የኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖ የተስፋፋበት፣ የኑሮ ውድነት የተንሰራፋበት ነው እስካሁንም፡፡ የሰው ልጆች ለአካባቢ መራቆት ባደረጉት አስተዋጽኦ ዓለም በድርቅ፣ በጎርፍና በእሳት በመሳሰሉ ችግሮች ስትፈተን የቆየችበት ዓመት ነው፡፡ ዓለማችን ስትፈተን ኖራለች፡፡ የዓለም ፖለቲከኞች በዋናነት ለዓለም ሰላም መደፍረስ ምንጭ እየሆኑ ነው፡፡ በአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ትራምፕና የአሁኑን በሚመለከት የተነሳው ጭቅጭቅ አልለየለትም፡፡ በዩክሬንና በሩሲያ፣ በኢራቅ፣ በቱኒዚያ፣ በበምሥራቅ አፍሪካ፣ በማይንማርና በሌላው ሥፍራ ያለው ሁኔታ በሙሉ ሰው ሠራሽ የሰላም ዕጦት ነው፡፡ መሪዎች የሚጠበቅባቸውን ቢያደርጉ ይህ ሁሉ አይፈጠርም ብዬ አምናለሁ፡፡ መሪዎች ብዙ መጣር ነበረባቸው፡፡

በአገር ደረጃም ሲታይ የኮሮና ተፅዕኖና የኑሮ ውድነት ሲፈትነን ነው የኖርነው፡፡ ሰላምን በተመለከተ ግን እኛም ጋ ሰው ሠራሽ ችግሮች አሉ ነው የምለው፡፡ የሰላም ዕጦት ዋና ችግራችን ነበር፡፡ የሰው ልጆች ሕይወት ትንሽ የረከሰበት ዓመት ነበር፡፡ ሞት በመጠኑም ቢሆን የተለመደበት ዓመት ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ከመግባባት ይልቅ አለመግባባት የነገሠበት ዓመት ነው፡፡ የሰላም ጉዳይ በ20014 ዓ.ም. ብዙዎቻችንን ሲያስጨንቅ የቆየ ጉዳይ ነው እላለሁ፡፡ የሰላም ዕጦት መገለጫ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ደግሞ ጭንቀት ነው፡፡ ባትናገረውም ሁሉም ጋ ጭንቀት አለ፡፡ ለምሳሌ እኔ ወልዲያ ራሴ እየነዳሁ እሄድ ነበር፡፡ በለሊት ተነስቼ የነዳሁበት ጊዜ ሁሉ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህን ለማድረግ ጭንቀት አለ፡፡ በቅርቡ ወልዲያ ብሄድም ነገር ግን የአሁኑና የበፊቱ ጉዞዬ አንድ አይደለም፡፡ የቱ ጋር ነው ሥጋት ያለው እያሉ መጨነቅ ሁላችንም ዘንድ ካለ የሰላም ዕጦት አለ ማለት ነው፡፡

በአገራችን ብዙ ጥሩ ሥራዎች በዓመቱ ተሠርተዋል፡፡ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ያሳየው ዕድገትና ለውጥ በትልቅነቱ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ለእርሻ የተሰጠው ትኩረትም ቢሆን ጥሩ ነው ሊባል ይችላል፡፡ አካባቢ ጥበቃን በተመለከተ ደን ተከላው ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ያለውና መደነቅ ያለበት ነው፡፡ እኛ በተሰማራንበት በትምህርት ዘርፍ ኮቪድ-19 የትምህርት ፕሮግራሞችን በማጣበብና በማቋረጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ የሰላም ዕጦትም እንዲሁ ብዙ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ አፈናቅሏል፡፡ ሆኖም ደስ የሚሉ ሥራዎችም በዘርፉ የተሠሩበት ዓመት ነበር፡፡ የትምህርት ጥራትን በተመለከተ ከፍ ያለ ትኩረት ነው የተሰጠው፡፡ የድሮው ሂርካ የሚባለው ወደ ኢቲኤ ተለውጦ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰዎች መመደባቸው ጥሩ ነው፡፡ ጥራትን ለማስጠበቅ ብዙ ውይይቶችም ተደርገዋል ውሳኔዎችም ተወስነዋል፡፡ ለምሳሌ ከዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ይሰጥ መባሉ ትልቅ ውሳኔ ነው፡፡ እኛ ስለጥራት ያለንን ሐሳብ ከማጋራት በተጨማሪም ለመውጫ ፈተናው ራሱን የቻለ የከፍተኛ አመራሮች ቡድን አዋቅረናል፡፡ 

አዲሱ ዓመት 2015፣ እንዲህ ይሆናል ብሎ ለመተንበይ የዓለምንም ሆነ የአገራችንን ሁኔታ በሚገባ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ የዓለምን ሁኔታ አሁን ካለው በመነሳት ስገምተው ግን ወይ የተሻለ ዓመት፣ አለበለዚያም አሁን ካለው ሁኔታም እጅግ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ ዓለማችን ወይ ወደ ከፋ ሁኔታ ይገባል፣ አለዚያም ይሻሻላል፡፡ መካከል ላይ የሚቆም ነገር አይኖርም፣ ከሁለቱ አንዱ ነው የሚሆነው፡፡ አሁን ያለው የዓለም ኃይሎች መፋጠጥ የሚቀጥል ከሆነ፣ በምዕራባዊያንና በሩሲያ መካከል አለመግባባቱ ከቀጠለ አሁን ከምናየው በላይ አስከፊ ሁኔታ ይመጣል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ በሰላም ዕጦትም ቢሆን በኑሮ ውድነት ችግር ይፈጠራል፡፡ ላይ ያሉ ሰዎች ለሰላም ባለመሥራታቸውና የሚጠበቅባቸውን ባለማድረጋቸው በየአቅጣጫው የተፈጠሩ ግጭቶች ደሃውን የዓለም ሕዝብ እየጎዱ ነው፡፡ ችግሩን ፈጥነው ፖለቲከኞቹ ባለመፍታታቸው የበለጠ ችግር ሲፈጠር ነው የምናየው፡፡ የአሜሪካና የቻይና ፍጥጫ በታይዋን ላይ ከቀጠለ በተመሳሳይ ከታይዋን አልፎ ሌላ ጣጣ በዓለም ላይ ሊያመጣ ይችላል፡፡ የምጠብቀው ሰላም እንዲመጣ ቢሆንም ነገር ግን ዓለማችን ሌላም ችግር እንዳታይ እሰጋለሁ፡፡

በአገር ደረጃ ሦስት ነገሮችን ማየት አለብን፡፡ አንደኛውና ትልቁ ነገር ሰላም ነው፡፡ ሰላም ዝም ብሎ የሚገዛ ነገር ሳይሆን ተለፍቶ የሚገኝ ነው፡፡ አሁን የገጠመን የሰላም ዕጦት የፈጠረው ጭንቀትና ውጥረት ምን እናድርግ ብለን ወደ መፍትሔ የምናመራ ከሆነ ሰላም ይፈጠራል፡፡ በሆነው ባልሆነው መጋጨት የምንቀጥል ከሆነ ግን የከፋ ዓመት ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ አሁን ያለው ሞት፣ ረሃብና ሌላም ችግር እየባሰ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ሁላችንም እስካሁን ያየነው ይበቃናል ብለን ከግትርነት ወጥተን መፍትሔ ለማግኘት ከጣርን ችግራችን ይቃለላል፡፡ ፍኖተ ካርታ ቀርፆ፣ በየደረጃው ይህን ልሥራ ብሎ ዕቅድ አውጥቶ ለመሥራት የሚሞከር ከሆነ ሰላማችን ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሁለተኛው ትኩረት ያልተሰጠውና ሊወራለት የሚገባ ነገር ቢኖር የመልካም አስተዳደር ችግር ነው፡፡ እኔ ሙስና በኢትዮጵያ መስፋፋቱ በእጅጉ ያሳስበኛል፡፡ አገር ባልጠቅስም በምዕራብ አፍሪካ ሀብት እያላቸው በመሪዎቻቸው ስግብግብነትና ሙሰኝነት የተነሳ ነፃ ከወጡ ጊዜ ጀምሮ ሲዳክሩ የቆዩ የሙስና ምልክት የሆኑ አገሮች አሉ፡፡ ይህ ዝም ብሎ አልተጀመረም፡፡ በልሂቃን፣ በባለሥልጣናት፣ ከመንግሥት ጋር በሚገናኙ ሰዎች ተጀምሮ አገርም ሊቀለበስ ወደ የማይችል ንቅዘት ውስጥ የከተተ ችግር ነው፡፡

ሙስና በቀላሉ ነው የሚያድገው፡፡ እንደ ሱስ ነው፡፡ ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ ሰዎች ሱሳቸውን ለማስታገስ የበለጠ ስግብግብ እየሆኑ ይሄዳሉ፡፡ ሙስና እንደ ካንሰርም ነው፡፡ ሀብትና ንብረት የተወሰኑ ሰዎች ጋር ብቻ ገብቶ በትክክለኛው ቦታ ሊውል እንዳይችል ያደርጋል፡፡ ሰዎች በአንድ ላይ በጋራ እንዲያድጉ ከማድረግ ይልቅ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚያበለፅግ የሌሎች ነገሮችን ዕድገት የሚገታ ካንሰር ነው፡፡ ሙስና መንግሥት ቤት ብቻ አይደለም ያለው፡፡ ነጋዴውም ሆነ ባለሀብቱ ዘንድ አለ፡፡ ይህ የሙስና ባህል የሚንሰራፋ ከሆነ ደግሞ አገራችን በቀጣይ ችግር ይገጥማታል ነው የምለው፡፡ ዘንድሮ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ብዙ ተሠርቷል ብያለሁ፡፡ ነገር ግን ከትምህርት ቤት የሚወጡት የሥራ ኃይሎች ሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ሲገቡ በሥራ ዓለም የሚገጥማቸው ጥራት መመርመር አለበት፡፡ እኛ የፈለገ ጎበዝ ተማሪ ብናመርትም ሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ገብቶ በሙስናና በብልሹ አሠራር የሚደናቀፍ ከሆነ ምንም ዋጋ የለውም፡፡ ይህ ጉዳይ ከትምህርት ጥራት ማስጠበቅ እኩል ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡

‹‹የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ግጭትን በሚቀንስ መንገድ ቢሆን ዓመቱ በጣም ሰላማዊ ይሆናል››

ራኬብ መሰለ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር

ዓመቱን በሦስት ከፍዬ ነው የማየው፡፡ አንደኛው ኢሰመኮን በተቋማዊ ነፃነትና ብቃት ያለው ተቋም አድርገን ለመቅረፅ ግብ ይዘን የተነሳንበት ዓመት ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ ተደራሽነትን በማስፋት በኩል ውጤታማ ነበርን፡፡ በቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ ድረ ገጽና መገናኛዎቻችንን በማዘመን፣ ሚዲያዎችን በመጠቀም፣ ግኝትና ሪፖርቶቻችንን ተደራሽ በማድረግ፣ ለሴቶችና ለአረጋውያን ተደራሽ በመሆን ጥሩ ሥራ ሠርተናል ብለን እናምናለን፡፡ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የሚችል የተሻለ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ያሰባሰብንበት ዓመት ነው፡፡ የፋይናንስ አቅማችንን ከመገንባት በፊት መሥራት ያልቻልናቸውን ሥራዎች የሠራንበት ዓመት ነው፡፡ ሌላው በዓለም አቀፍ ትብብር በኩል በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ ጥሩ ሥራ የሠራንበት ዓመት ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ዕውቅናችንን ከነበረው የቢ ደረጃ መሥፈርቶችን በማሟላት ወደ ኤ ደረጃ ከፍ እንዲል ያደረግንበት ዓመት ነው፡፡ የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደኅንነት ኮሚቴን ተባባሪ ደረጃን በማግኘት በአፍሪካ ከጋናው ቀጥሎ ሁለተኛው ተቋም ለመሆን በቅተናል፡፡

በ2014 ዓ.ም. ባደረግነው የሥራ እንቅስቃሴ ከ300 በላይ ፖሊስ ጣቢያዎችን ጎብኝተናል፣ ማረሚያ ቤቶችን ጎብኝተናል፣ ያላግባብ ተይዘው የነበሩ ዜጎችን አስለቅቀናል፡፡ እንደሚታወቀው አገራችን ብዙ የመፈናቀል ችግር የሚገጥማት በመሆኑ፣ ወደ 1.5 ሚሊዮን ተፈናቃዮችን የሚወክሉ 52 አካባቢዎችን በመጎብኘት ክትትል አድርገናል፡፡ በሰሜኑ አካባቢ ያለውን ግጭት በተመለከተ ከትግራይ ክልል በተጨማሪ በአማራና በአፋር ክልሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የተመለከቱ ሪፖርቶችን አውጥተናል፡፡ ስድስተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ በተመለከተ ተፈናቃዮች እንዲሳተፉና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሳይፈጠሩ እንዲጠናቀቅ በጎ ሥራ ተሠርቷል፡፡ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙም በጣም ጥሩ ነው፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት ዓመት ስለነበር በርካታ የመብት ጥሰቶች ቢገጥሙም፣ አዋጁ ከጊዜው ቀድሞ መነሳቱና በርካታ የታሰሩ ሰዎች መፈታታቸው ጥሩ ነበር፡፡ ብዙ ሕጎች ሲወጡ ተቋማችን አስተያየትና ግብዓት መስጠቱም ጥሩ ነው እንላለን፡፡

ሆኖም ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችም አሉ፡፡ የሰሜኑ ጦርነት ቆሞ ወደ ድርድር ለመሄድ የነበረው ጥረት በጣም አበረታች የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን እንደምናየው ግጭቱ አገርሽቶ በሰዎች ላይ ጉዳትና ዕልቂት መድረስ መቀጠሉ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ከሰሜኑ ግጭት በተጨማሪ ደግሞ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን ተከትሎ፣ ከወሰንና ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ብዙ ችግሮች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ግጭቶችን ከማስቆምና የእርምት ዕርምጃ ከመውሰድ በተጨማሪ፣ ለእነዚህ ችግሮች መሠረታዊ ምንጭ የሆኑ ችግሮችን በ2015 ዓ.ም. በውይይት ለመፍታት ጥረት የሚደረግበት ዓመት ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ መንግሥት ተጎጂዎችን ለመርዳትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት እያደነቅን፣ ነገር ግን አሁን ያሉት ግጭቶች ተጨማሪ መፈናቀልና ጉዳት እያደረሱ ስለሆነ እነዚህን ሁኔታዎች መፍታት ላይ አተኩሮ መሥራት ይገባል እንላለን፡፡

ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ረገድና የሕግ የበላይነትን ከማስከበር አንፃር በ2014 ዓ.ም. በርካታ ክፍተቶች ዓይተናል፡፡ ለምሳሌ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች፣ ከመጠን ያለፉ የኃይል አጠቃቀሞች ይጨምራሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚፈጸሙ የኃይል አጠቃቀሞች፣ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ የሚፈጸሙ የዘፈቀደ እስር፣ የተራዘመ የቅድመ ክስ ሒደት፣ በጋዜጠኞችና በማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ የሚደረጉ አሁንም የምንሰማቸው ዓይነት እስራቶች፣ በሌላም በኩል አስገድዶ መሰወር፣ ከቤተሰብና ከጠበቃ ጋር እንዳይገናኙ የማድረግ ዕርምጃዎች በ2015 ዓ.ም. እንዳይከሰቱ ማድረግ ይገባል እንላለን፡፡ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለማክበርን በተመለከተ የዋስትና መብት ከተፈቀደ በኋላ በተለያዩ መንገዶች መከልከል የመሳሰሉ ችግሮች ወደ 2015 ዓ.ም. ስንሸጋገር የሚቀረፉበት ዓመት እንደሚሆን እንጠብቃለን፡፡ በድርቅ በተለይ በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተፈጥሯል፡፡ በተለያዩ ክልሎች ባጋጠሙ ግጭቶችም ተመሳሳይ ችግሮች ደርሰዋል፡፡ የማኅበራዊ አገልግሎቶች ተቆራርጠዋል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታትና አካባቢዎቹን መልሶ ለማረጋጋት መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሰጥበት ዓመት ይሆናል ብለንም እንጠብቃለን፡፡

ከቀበሌ መታወቂያ ማውጣትና ዕድሳት ጀምሮ የተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ለማግኘት የሚፈልጉ ዜጎች የሚገጥማቸው እንግልትና ሮሮ አስፈላጊውን የእርምት ዕርምጃ የሚወሰድበት ዓመትም ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡  ትልቁ ፈተና በእኛ ዘርፍ ሥራችንን እየሠራን ያለነው በግጭቶች ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ በሰላም ጊዜ ቢሆን ሥራችን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ አገልግሎትን ማስፋፋት ላይ ባተኮረ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን በአብዛኛው ምንሠራው ሥራ ጥፋቱ ከጠፋ በኋላ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰብ ላይ ነው፡፡ ግጭቶቹ በጣም በርካታ ስለሆኑ የሚጎዱትንና የሚሞቱትን ወይም የሚፈናቀሉትን ሰዎች ምን ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጉዳት ደረሰባቸው? ምን ዓይነት ዕርምጃ ሊወሰድስ ይችላል? የሚሉ ጉዳዮች ላይ ነው ያተኮርነው፡፡ እንደ እኛ ግን ሁኔታዎች ተረጋግተው እንደ ተቋም ሰብዓዊ መብቶችን ሁሉም ተረድቶ የሚተገብርበት አገር፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ባህል የሚሆንባት ኢትዮጵያን መፍጠር ነው ፍላጎታችን፡፡ ሆኖም ብዙ ችግሮች በአገራችን ስላሉ እዚያ ላይ ማተኮር አልቻልንም፡፡

አንዳንድ ጊዜ የክትትል ሥራ ስንሠራ አላስገባም የሚሉን ወይም ሊተባበሩን የማይፈልጉ የመንግሥት ባለሥልጣናት አሉ፡፡ እነዚህ አካላት የተቋማችንን ሥልጣንና ኃላፊነት ተረድተው ለሥራችን ተባባሪ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንጠይቃለን፡፡ በ2015 ዓ.ም. ሊለወጥ የሚችለው ውይይቱን፣ መነጋገሩን፣ ይቅርታ መባባሉን አስቀድመን ግጭቱን ማቆም የምንችል ከሆነ ነው፡፡ አሁንም እንደገና በግጭቶች መፈናቀሉና መጎዳዳቱ ነው የሚባባሰው፡፡ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ተፈናቃዮች ናቸው ያሉን፡፡ ለእነዚህ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ ካልሠራን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሚቀጥል ነው የሚሆነው፡፡ በ2014 ዓ.ም. የተወሰኑ ዕመርታዎች ቢኖሩም፣ ነገር ግን ብዙ ችግሮች የነበሩበት ዓመት ነው፡፡ ሆኖም ከእነዚህ ችግሮች ተምረን 2015 ዓ.ም. የተሻለ ለማድረግ የሁላችንም ትብብርና አስተዋጽኦ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ደግሞ የማኅበራዊ ሚዲያዎች አጠቃቀም ላይ ችግር አለ፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ግጭትን በሚቀንስ መንገድ ቢሆን ዓመቱ የበለጠ ሰላማዊ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ 

‹‹በአዲሱ ዓመት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ጦርነቱ መቋጫ አግኝቶ ይጠናቀቃል ብለን እንጠብቃለን

ዋሲሁን ተስፋዬ፣ የኢዜማ የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ

ተሰናባቹ ዓመት በኢትዮጵያ በርካታ የፖለቲካ ሁነቶች የተከሰቱበት ዓመት ነበር፣ እንደ ፓርቲ ኢዜማም ብዙ ሁነቶችን አስተናግዷል፡፡ ለምሳሌ በዓመቱ ሁለት ጉባዔዎችን ያካሄድን ሲሆን አንዱ መስከረም ላይ ከገዥው ፓርቲ ጋር በጋራ መሥራትን በተመለከተ ያስወሰንበት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በሰኔ ወር ያደረግነው፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት ፓርቲያችንን ሲመሩ የነበሩ አመራሮችን በምርጫ እንዲተኩ የማድረግ ሒደት ነው፡፡ በአገር ደረጃ ከብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋምና ሥራ መጀመር ጋር በተያያዘ የራሳችንን ግብረ ኃይል አቋቁመን ስንከታተለው የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ የምክክር ተነሳሽነት መኖሩ በጣም ጥሩ ቢሆንም ነገር ግን የኮሚሽኑ አወቃቀርም ሆነ የታለፈበት ሒደት አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ የኮሚሽኑ መቋቋም ገምቢ ሆኖ ሳለ፣ ነገር ግን ከኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጁ አወጣጥ ጀምሮ፣ የኮሚሽነሮች አመራረጥ ጭምር ባለድርሻ አካላትን ከማሳተፍ አንፃር ጉድለት የነበረ ሲሆን ሒደቱ ብዙ ጥድፊያና ችግሮች ነበሩበት፡፡

እኛ ይህ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላለፉት 20 እና 30 ዓመታት አገሪቱ የተጫኑባትን ችግሮች ሙሉ ለሙሉም ባይሆን እንኳን በተወሰነ ደረጃ ይፈታል ብለን እናስባለን፡፡ በትልቅ ጉጉት ሒደቱን የምንጠብቀው ሲሆን ራሱን የቻለ ኮሚቴ አዘጋጅተን ሒደቱን እየተከታተልን ነው የምንገኘው፡፡ ያኔ በኮሚሽኑ መቋቋምና በኮሚሽነሮች አመራረጥ ሒደት ያጋጠሙ ችግሮች ተገቢ እንዳልሆኑ ገምግመናል፡፡ ሆኖም ሒደቱ በ2014 ዓ.ም. መጀመሩ በራሱ በአጠቃላይ ጥሩ ሊባል ይችላል፡፡

ሌላው በአገር ደረጃ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ አሁንም ያላባራው አገሪቱን ወደ ቀውስ እየከተታት ያለው ችግር አሳሳቢ ነው፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያና በየቦታው የነበረው የዜጎች መገደልም ፈተና ነበር፡፡ ዜጎች በየቦታው ተንቀሳቅሰው መሥራት አለመቻልና የዜጎች በየቦታው መፈናቀል አሥጊ ሁኔታ ነው፡፡ በአጠቃላይ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ዋና ሥራውን በሚፈለገው ደረጃ ያልሠራበት፣ እንዲያውም ተፈትኖ የወደቀበት ዓመት ነበር፡፡ በየቦታው ንፁኃን በገፍ የተገደሉበትና ጅምላ ግድያ ያየንበት ዓመት ነበር፡፡

እኛ ጨለምተኛ ስላልሆንን አዲሱ ዓመት የተሻለ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን በ2014 ዓ.ም. የነበሩ ችግሮች ወደ ቀጣዩ ዓመት እየተሸጋገሩ ነው የሚገኘው፡፡ አሁን ከሰሞኑ ያገረሸው ጦርነት ወደ ቀጣዩ ዓመትም እየተሸጋገረ ነው፡፡ ነገር ግን በአዲሱ ዓመት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ጦርነቱ መቋጫ አግኝቶ ይጠናቀቃል ብለን እንጠብቃለን፡፡ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የምክክሩ ሒደት በኅዳር እንደሚጀመር አስታውቋል፡፡ ሒደቱ በመላው አገሪቱ ተከናውኖ ቢያንስ የተወሰኑ ችግሮችን የምንቀርፍበት ዓመት ይሆናል ብለን እናስባለን፡፡ ከአገራዊ ምክክሩ ጋር በተያያዘ 2015 ዓ.ም. ለእኛ በጣም ጠቃሚ ዓመት ነው፡፡ ማነቆ የሆኑብን የሕግና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ጭምር ለውይይት ቀርበው ሕዝቡ መክሮ አንድ መፍትሔ የሚያመጣበት ዓመት ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ብዙ ተስፋዎች አሉን፡፡ ሆኖም ብዙ ተስፋዎቻችንን ቀርጥፈን ስንበላ የኖርን አገር ነን፡፡ በመጪው ጊዜም ትልቅ ተስፋ የተጣለበትን አገራዊ የምክክር ተስፋ እንዳናጨልመው ሁላችንም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠይቀናል፡፡ በ2013 ዓ.ም. ሆነ በ2014 ዓ.ም. በጎ ነገሮች በፖለቲካው ዘርፍ ቢታዩም ወደኋላ የተመለስንባቸው ጉዳዮችም አሉ፡፡ አንደኛው ካቻምና የተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ጉልህ ተሳትፎ ያደረግንበት ምርጫ፣ እንደከዚህ ቀደሞቹ አይሆንም ብለን የገባንበት ነበር፡፡ ነገር ግን ምርጫውን ከሒደቱም ሆነ ከውጤቱ አንፃር ስንመዝነው ካለፉት ምርጫዎች ምንም የተለየ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ካለፉት አምስት ምርጫዎች የተለየ አልነበረም፡፡ ብዙ ጉድለቶች የነበሩት የምርጫ ሒደት ነበር፡፡ ይህ በአጠቃላይ እንደ አገር የወደቅንበት ጉዳይ ነው፡፡

በ2014 ዓ.ም. ድግሞ በአገር ደረጃ ከፍተኛ የሆነ የዜጎች መፈናቀልና የዜጎች ሞት የተከሰተበት ዓመት ነው፡፡ መንግሥት እንደ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ማስከበር ያልቻለበት ዓመት ነው ብለን መውሰድ እንችላለን፡፡ ይህንን ራሳቸው ገዥዎቹም የሚገመግሙት ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ በብልፅግና ውስጥ ታይቶ የነበረው ከብሔር ፖለቲካ የመላቀቅ ዝንባሌና ይደረጉ የነበሩ ፓርቲውን አገር አቀፍና ኅብረብሔራዊ የማድረግ እንቅስቃሴዎች ተስፋ ሰጪ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ብዙ መንገድና ብዙ ሥራ ይቀራቸዋል፡፡ ዋናው ችግር ግን የዜጎችን ደኅንነት የማስከበር ጉዳይ በመሆኑ በዚህ ላይ ብዙ ሥራ ይሠራል ብለን እንገምታለን፡፡

ኢኮኖሚው የፖለቲካው ተቀፅላ በመሆኑ የተረጋጋ ፖለቲካ በሌለበት ኢኮኖሚው ሊረጋጋ አይችልም፡፡ በኢትዮጵያ ከዕለት ዕለት ኢኮኖሚው መረጋጋት እያቃተው፣ ዜጎች በልቶ ማደር እያቃታቸው የመጣበትና የዋጋ ግሽበቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የኖረበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ የገንዘብ የመግዛት አቅም በ2014 ዓ.ም. እጅግ እየተዳከመ የመጣበት ዓመት ነበር፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በዋናነት በአገሪቱ የፀጥታ ችግር በመኖሩና የፖለቲካ ችግሩ ባለመፈታቱ የተነሳ ሰዎች ተንቀሳቅሶ መነገድና መገበያየት ባለመቻላቸው ነው፡፡ ይህ ችግር ደግሞ ወደአዲሱ ዓመት የሚሸጋገር ነው፡፡ በተሰናበተው ዓመት ከኢኮኖሚ አንፃር የዜጎች ሕይወት እጅግ ፈታኝ የሆነበት ነበር፡፡ የፖለቲካው ችግር በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ በቀጣዩ ዓመትም የኢኮኖሚው ሁኔታ ፈታኝ ሆኖ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡ የመሻሻል ተስፋዎች የነበሩ ቢሆንም መልሰው ሲጠወልጉ እያየን ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፉት አምስት ወራት የሰሜኑ ጦርነት በመቆሙ ኢኮኖሚው መነቃቃት አሳይቶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ደግሞ መልሶ ጦርነቱ በማገርሸቱ ኢኮኖሚውን ሊጎዳ ይችላል የሚል ሥጋት ይዘን ነው ወደ አዲሱ ዓመት የምንሸጋገረው፡፡ ጦርነቱን አጠናቀን ፊታችንን ወደ ልማት ካልመለስን ኢኮኖሚው የሚነቃቃ አይመስለኝም፡፡ 

‹‹አዲሱን ዓመት ስንቀበል በብርቱ መታሰብ ያለበት ሰላም ነው››

ወ/ሮ መሊካ በድሪ፣ የዘምዘም ባንክ ፕሬዚዳንት

2014 ዓ.ም. ከባንክ አንፃር ሲታይ ከውጪ ኮርስፖንደንት ባንክ ማግኘት ከባድ ነበር፡፡ በሰዎች ዘንድ አዲስ ነገር ለመሞከር ያለው ፍላጎት፣ እንዲሁም በአገር ውስጥም የሆነ በውጭ ያለው ተፅዕኖ ሥራውን በጀመሩበት ወቅት በጣም ተግዳሮት ነበረው፡፡ በዓመቱ መጠናቀቂያ ላይ ሆነን ስናየው ተግዳሮቶችን ተቋቁመን ያገኘነው ውጤት ተስፋ የሚሰጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ አዲሱ ዓመትን ደግሞ በተለይ በባንክ ዘርፍ ያለን ሰዎች በተለየ ሁኔታ የምንቀበለው ይሆናል፡፡ ይህም አዲሱ ዓመት ዘርፉን ሙሉ በሙሉ ለሚቀየሩ የሚችሉ አዳዲስ ነገሮች የሚመጡት ሆኖ ነው የምንቀበለው፡፡

ይህም ያልተሞከሩ ነገሮች የሚሞከሩበት ነው፡፡ ያልተሞከረ ነገር ሁልጊዜ ከሥጋት ጋር የምንቀበለው ነው፡፡ ግን ያ ያልተሞከረ ነገር ደግሞ ሥጋት ብቻ ሳይሆን ዕድልም ይዞ ይመጣል፡፡ ፈተና ሁልጊዜ ዕድል ይወልዳሉ፡፡ ሥጋቱን ግን አጨልሞ ከማየት የተሻለ ነገር ያመጣልኛል ብሎ፣ ከሥጋቱ ይልቅ ዕድሉን መውሰድ ስላለብን ለዚያ ዝግጁ ሆኜ  አዲሱን ዓመት እጠብቃለሁ፡፡ ዋናው ነገር ግን የአገር ሰላም መሆኑን ነው፡፡ በሰላም ዕጦት ያጣናቸውን ነገሮች ሁሉ በአዲሱ ዓመት ሰላም ወርዶ የምንካካስበት መሆን አለበት፡፡ አዲሱን ዓመት ስንቀበል በብርቱ መታሰብ ያለበት የአገር ሰላም ነው፡፡ ለሁሉም ነገር መሠረቱ ሰላም ነው፡፡ ሰሞኑን የውጭ ባንኮች ይመጣሉ ተብሎ ወሬው ይኸው ሆኗል፡፡ ወሬው የአዲስ ዓመት መቀበያ ሆኗል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች መሬት ላይ እንዲወርዱና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም ከፍ ለማለት ሰላም ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን መጪው ጊዜ ብሩህ ሆኖ ይታየኛል፡፡ ለሰላም መገኘት ግን ሁላችንም የየበኩላችንን ማበርከት ይኖርብናል፡፡

‹‹ሕዝባዊ ዕርቅ እርስ በርስ መደራደርና ይቅርታ መጠያየቅ ያስፈልገናል››

ስኂን ተፈራ (ዶ/ር)፣ የሴታዊት እንቅስቃሴ መሥራችና ዳይሬክተር

ያለፈው 2014 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ሕዝብ በአጠቃላይ በጣም ከባድ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ያለን ሰዎች በቀጥታ ላናየው እንችላለን፡፡ ነገር ግን ትንሽ ከአዲስ አበባ ከወጣን በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከባድ ጦርነት አስተናግደዋል፡፡ ብዙ ጉዳት ደርሷል፣ የንፁኃን ሕይወት ተቀጥፏል፡፡ ሴቶችና ሕፃናትም እስከ ዛሬ ዓይተነው በማናውቀው ሁኔታ ተጎድተዋል፡፡ ካለፉት ሦስት ዓመት ወዲህ እያየን ያለነውን ጉዳት ከዚህ ቀደም ዓይተነው አናውቅም፡፡ ሴቶች፣ ሕፃናትና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ አረጋውያን ጭምር ሲፈናቀሉ፣ ሲራቡና ሲጠሙ ነበር፡፡ ስለዚህ ከባድ ዓመት ነው ያሳለፍነው፡፡ እኛ ባለፈውም ዓመት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን የሰላም ጥሪ አድርገን ነበር፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ መስከረም ላይ ትግራይ ላይ የተደረገው ከበባ የሚባለው ተነስቶ፣ ድርድሩ ፍሬ አፍርቶ ወደ ዕርቅ፣ ካሳና ፍትሕ ፍለጋ ብለን ተስፋ ስናደርግ ለዚህም ስንዘጋጅ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ጦርነት ባልተጠበቀ ሁኔታ በድጋሚ ተነሳ፡፡ ውስጡ ያሉ ሰዎች ጠብቀውት ሊሆን ይችላል፡፡ ለእኛ ተራ ዜጎች ግን ቅስም የሚሰብርና ወደኋላ የሚመልሰን ነው፡፡ ጉዳቱ ደግሞ ጦርነቱ እንደ አዲስ ሲጀምር ሕዝብም መልሶ መፈናቀል ጀመረ፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው ጉዳት ጠባሳ ስላልሻረ፣ ያልተነኩ ጦርነት ያልደረሰባቸው አከባቢዎች ላይም ጭምር መፈናቀል ተጀምሯል፡፡

ሰዎች ከደረሰባቸው ጉዳት ገና ሳይገግሙ ስብራት እየጨመርንባቸው ነው፡፡ በአንድ ዓመት ጦርነት የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመገንባት አሥር ዓመት ይፈጃል ካልን፣ ጦርነቱ በቀጠለ ቁጥር ማገገሚያ መንገድ አይታየንም፡፡ ይኼም ብቻ ሳይሆን ማገገሚያውና መልሶ መቋቋሚያው እንደ ሕዝብ ዕርቁ እየራቀብን ይኼዳል፡፡ በ2015 ዓ.ም. ምኞቴ መጀመሪያ ጦርነቱ መቆም አለበት የሚል ነው፡፡ ይኼ ምንም አለሳልሰን የምንጠይቀው ነገር አይደለም፡፡ እኔ በበኩሌም እንደ ድርጅታችንም ያለን አቋም መንግሥት በትግራይ ላይ ያደረው ከበባ መነሳት አለበት የሚል ነው፡፡ ሕወሓት ጉልበት የሆነው የሕዝቡ መራብና መቸገር ነው፡፡ ምንም ነገር ለመጠየቅ መብት የሌለው ሕዝብ ከተገፋ ወደ ጦርነት ይሄዳል፡፡ ምንም አማራጭ የሌለበት ክልል እንደሆነ ስለማውቅ የትግራይ ወጣቶች በገፍ መውጣቸው አይገርመኝም፡፡ የእኛ መንግሥት የተሻለ ነገር አድርጎ፣ ትግራይ ላይ ያለውን ከበባ አንስቶ ወደ ድርድር መመለስ አለበት፡፡ ሕወሓትም ሕዝቡን መማገድ ማቆም አለበት፡፡ የእኛ መንግሥት የተመረጠና በዴሞክራሲ የሚያምን መሆኑን ተቀብለን እየኖርን ስለሆነ፣ ሁለቱም ወገኖች ለሕዝብ ከቃላት ያለፈ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣትና ለመደራደር ቁጭ ማለት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ጦርነቱ ከዚህም ከከፋ ግን መመለሻው ይጠፋናል፡፡ ጦርነት በእንዴ ባይቆምም ከዚህ እንዳይብስ ዕርምጃ መውሰድ ይቻላል፡፡ የጦርነት መጥፎ ባህሪው ከዚህ አይብስም ስንል ሁልጊዜ እንደሚብስ እናየዋለን፡፡ ለምደነው ምንም እንዳይመስለን ነው የምፈራው፡፡

የሴቶችም ጉዳት በተለየ ሁኔታ መታየት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም፣ ሕወሓትም ሌሎች ኃይሎችም መጠየቅ አለባቸው፡፡ ሴቶች ለምንድነው በዚህ ልክ የተጎዱት የሚለውን ቁጭ ብለው መነጋገር አለባቸው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ይኼንን ጦርነት የተፋለሙት በሴቶች ገላ ላይ ነው፡፡ በትግራይ ክልል ያሉ ሴቶች ላይ የተፈጸመውን ገና አላየንም፡፡ በአማራና በአፋር ክልሎች ከጦርነቱ በኋላ ሄጄ ነበር፡፡ የሴቶቹን ጉዳት መግለጽ ከምንችለው በላይ ነው፡፡ ተጠያቂነትና ካሳ ስንል ይኼ መታየት አለበት፡፡ ሕዝባዊ ዕርቅ ያስፈልገናል፡፡ ሁላችንም ላደረግነው ነገር እርስ በእርስ ይቅርታ መጠያየቅ አለብን፡፡ በቸልተኝነት ዝም ካልን፣ የሌላውን ሕመም ሳናይ ካለፍን፣ ምን አገባኝ ካልን፣ ወለጋ ውስጥ ንፁኃን ሲጨፈጨፉ ዝምታን ከመረጥን ነገ እኛም ጋ ይመጣል፡፡ እንደ ሕዝብ ረጋ ብለን፣ ንዴታችንን አብርደን፣  ትንሽም ቢሆን የእኔ ድርሻ ምንድነው ብለን ጠይቀን መወያየት ያስፈልገናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግሥት ኃላፊነት ምንም ጥያቄ የለውም፣ ሊመራን ይገባል፡፡ ከዚህ የባሰ አይምጣ፣ ግን ደግሞ ከዚህ ለመውጣት ዕርምጃዎች የምንወስድበት ይሁንልን የሚል ነው የእኔ የልቤ ምኞት፡፡

‹‹በግጭት ውስጥ የሚሳተፍ ማንኛውም አካል ሴቶችንና ሕፃናትን የመጠበቅ ግዴታ አለበት››

ወ/ሮ ሳባ ገብረ መድኅን፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዋና ዳይሬክተር

በተጠናቀቀው ዓመት ብዙ ሥራዎቻችን በአገሪቱ ባለው ሁኔታ ምክንያት የመደነቃቀፍ ሁኔታዎች የነበረባቸው ናቸው፡፡ ከእሱ በላይ ግን አሁን ባለው የግጭት ሁኔታ የሴቶች ተጠቂነት መብዛቱ በጣም የሚያሳስብ ዓመት ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ሳምንት ለሰላም በሚል እንዳካሄድነው የእግር ጉዞ ባሉ ተጎጂዎችን የመደገፍ ሥራዎች ላይ ሴቶች የነበራቸው ተሳትፎ ተስፋ የሚጣልበት ነበር፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ሥጋት የነበረበት ቢሆንም ድርድር ሲጀመር ደግሞ ተስፋን የጫረ ነበር፡፡ እንዲያውም በሰላም ድርድሩ ላይ የሴቶች ተሳትፎ አነሰ የሚል ነበር ስናነሳ የነበረው፡፡ በጦርነት ቀጣና ከሚንቀሳቀሱ ብዙ ማኅበራት ጋር አብረን ስለምንሠራ፣ ሴቶች ላይ የደረሱ ጉዳቶችን ሰምተናል፡፡ ሴቶች መፈናቀላቸው፣ በጦርነት ውስጥ መውለዳቸው፣ ልጃቸውን አዝለው ለመሸሽ መገደዳቸው፣ ከዚህም አልፎ ጥቃት መፈጸሙ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ጦርነቱ ከመጀመሩ አንስቶ በተለይ ሴቶችንና ሕፃናትን በተመለከተ ያለንን ሥጋት ስንገልጽ ነበር፡፡ ሰላምን እየተመኘን፣ በግጭት ውስጥም ቢሆን ደግሞ ለሴቶችን ሕፃናት አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግ የሚለው የሁልጊዜ መልዕክታችን ነበር፡፡ ግጭት ባይሆን እንመርጣለን፣ እንዳይሆንም ሲባል ድርድርና ንግግር ቢደረግ ፍላጎታችን ነው፡፡ ነገር ግን በማንኛውም ግጭት ውስጥ ሴቶችና ሕፃናት ተጠቂ እንዳይሆኑ ሁሉም ግዴታውን እንዲወጣ ስንገልጽ ቆይተናል፡፡ በግጭት ውስጥ የሚሳተፍ ማንኛውን አካል ይኼንን የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ ነገር ግን ይኼ ሳይሆን ስለቀረ፣ ብዙ ንፁኃን ሰዎችና ሴቶች ተጎጂ ሆነዋል፡፡ ይህ እጅግ ያሳዝነናል፡፡

አዲሱ ዓመት ለድርድርና ለሰላም ታይቶ የነበረው ተስፋ ተመልሶ የሚጫርበት፣ ሰላም የሚሆንበት እንዲሆን ነው ተስፋ የምናደርገው፡፡ ስለሞት፣ ስለመፈናቀል፣ ስለረሃብና ጥማት የማንሰማበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ እንደ ማኅበርም እንደ ሴት የሰብዓዊ መብት ተሟጋችም ለዚሁ እሠራለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ግን የሌሎች አካላት ጉዳይ ስለሆነ ከመመኘት ውጪ ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ የሰላም አካልና መሣሪያ ሆኖ ለመልካም ነገር ለሰላም ያለንን ፍላጎት መግለጽ ነው የምንችለው፡፡ ከዚህ አንፃር በአዲሱ ዓመት ሴቶች ድምፃችንን በደንብ የምናሰማበት፣ ልክ ያልሆነው ልክ አይደለም፣ ያሳሰበን አሳስቦናል የምንልበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ የመብት ተከራካሪዎችና የሰላም ወገኖች እንድንሆን ነው የምንጠብቀው፡፡ ባለፈው ዓመት ሴቶችና ሕፃናት ላይ ደርሶ ያየነው ነገር ሁሉ በ2015 ዓ.ም. እንዳይደገም፣ ከዚህም ባለፈ ጥበቃት እንዲደረግላቸው እንፈልጋለን፡፡ አሁንም ጉዳት የደረሰባቸው የመጠለያ፣ የሕክምና፣ የምክርና የኢኮኖሚ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ነው ምኞቴ፡፡

‹‹ሰብዓዊነት ሊሰማን ሲገባ ዝምታን መምረጣችን ትክክል አይደለም››

ወ/ሮ ፌቨን አርዓያ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች መሥራች

በ2014 ዓ.ም. እንደ አገር ብቻ ሳይሆን እንደ አንዲት ሴት ከባድ ዓመት ነበር፡፡ ጦርነት፣ የዜጎች ግድያና መፈናቀል በየአቅጣጫው የነበረበት ነው፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን ምንም ማድረግ አለመቻል ከሁሉም ይከብዳል፡፡ የሴቶች መብት ላይ ነው የምንሠራው የምንል ሰዎች ምንም መፍትሔ ጠብ ማድረግ አልቻልንም፡፡ ታጣቂ ኃይሎችን ማስቆም፣ ተቀራርበው እንዲነጋገሩና ነገሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ ፈታኝ ነበር፡፡ ይኼንን አስበን በዘርፋችን ያሳለፍነው ጊዜ ጥሩ ነበር ባንልም፣ ሴቶች በፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ የጨመርንበትና ወደፊት የመጡበት ጊዜም ነበር፡፡ ለሰላምም ተንቀሳቅሰናል፡፡ እነዚህ ስኬቶች ቢኖሩም የሚጎድሉንም አሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን እንደ ዘርፋችን በዙ አስተዋጽኦ አድርገናል ብለን አናስብም፡፡

የሚቀየረው አዲስ ዓመት ሳይሆን የሰው ሐሳቡ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሁላችንም ራሳችንን ማየት አለብን፡፡ ሁላችንም ለዚህ ነገር አስተዋጽኦ አለን፡፡ አብዛኛው ሰው ነገሮችን እንዳላየ የሚያልፍ ዝም ባይ (silent majority) መሆኑ ጉዳት አምጥቷል፡፡ ሁላችንም ሰብዓዊነት ሊሰማን ሲገባ ዝምታን መምረጣችን ትክክል አይደለም፡፡ ሁሉም የአቅሙን ማድረግ ቢችል መፍትሔ ማምጣት እንችል ነበር፡፡ ነገሮች በሙሉ ለተወሰኑ ተዋንያን መተዋችን ተገቢ አልነበረም፡፡ አገራችን እናየዋለን ብለን የማናስበውን ነገር ሁሉ ለማየታችን ለይተን የምንወቅሰው አካል የለም፡፡ ሁላችንም አስተዋፅኦ አድርገናል፡፡ እኩል ተጠያቂ ነን፣ የጋራ ኃላፊነት አለብን፡፡ እንደ ዜጋ መጫወት የሚገባንን ሚና አልተጫወትንም፡፡ ኃላፊነት ለመውሰድ የግድ ሥልጣን መያዝ አይጠበቅብንም፡፡ ፖለቲከኛው የወጣው ከእኛ ነው፡፡ የታጠቀውም ኃይል ከሌላ ፕላኔት አልመጣም፡፡ በጦርነቱ ውስጥ የተከሰቱ ፆታዊ ጥቃቶችን ስናይ በሰላማዊ ጊዜ ቢሆን እነዚያ ሰዎች የሚታለፉ ነበሩ? ዕድሉ ሲገኝ ግን ይኼ ተፈጽሟል፡፡ አሁን ለዚህ ማንን መውቀስ እንችላለን? እንደሚባለው ጨዋ ሕዝብ ነን ወይ? ወይስ ዕድልና አጋጣሚ እስከሚመቻችልን ነው የምንጠብቀው?

እንኳን በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ይቅርና መንገድ ላይ ለሚታይ ዝርፊያ እንኳን ሰዎች ፖሊስ ጣቢያ ላለመሄድ ሲሉ ገሸሽ ሲሉ ይታያሉ፡፡ እኔ የአንተ ጠባቂ እንተም ለእኔ የምትቆም ከሆንን ብዙ ነገሮችን ማሻሻል እንችላለን፡፡ ሌላ ሰው ላይ አንድ ነገር ሲደረግ እኔ የማልፍ ከሆነ ደግሞ ነገሮች አስቸጋሪ ይሆናሉ፡፡ ከሁሉም በፊት 2015 ዓ.ም. ሰላም የሚለውን ቃል ደጋግመን የምንሰማበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ምክንያቱም ሰላም ከሌለ እንኳን እኛ አየሩም ይበከላል፡፡ እግዚአብሔር ይኼንን እንዲሰጠን እመኛለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ሁሉም ድርሻውን የሚወጣበት ዓመት ቢሆን ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አገራችን ውስጥ ሴቶች ብዛታቸው 50 በመቶ ስለሆነ አስተዋጽኦ ማድረግ ያላበቸውም በዚያው ልክ መሆን አለበት፡፡ አሁን ግን ውሳኔ ሰጪነት ላይ፣ ተሳትፎ ላይ ስናይ አስተዋጽኦቸው ዝቅ ያለ ነው፡፡ በቅተው ተሳትፏቸው የሚጨምርበት ዓመት እንዲሆን ነው ምኞቴ፡፡ ወደፊት መጥተው የአገርም፣ የሰላምም ጉዳይ ላይ ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ እጠብቃለሁ፡፡

በዚህ ጦርነት ሴቶች ተደፍረው ‹‹የእኔስ ይሁን አገር ግን ትቀጥል…›› ሲሉ ዓይተናል፡፡ ማን ይኼንን መስዋዕትነት ለማን ይከፍላል? ለምንስ እዚህ ደረጃ እንደርሳለን?  ሕዝቡ በሌላው ጊዜ አብሮ በሰላም የሚኖር ነው፡፡ የሆነ ዓይነት ችግር ሲመጣ ነው ሕዝቡ ብትንትን ብሎ ጥጉን የሚይዘው፡፡ ለሌላው ነገር አንድ እንደምንሆነው ሁሉ ያለን ሰብዕና ላይ መሥራቱ ምንም አማራጭ የሌለው ነው፡፡ በምርቃት ይኼንን አገር ማሻገር የሚችሉ አረጋውያን ጧሪ አጥተው መንገድ ላይ ወድቀዋል፡፡ እንደ አገር ዋጋ የምንሰጣቸውን ባህሎችና እሴቶች ይበልጥ ማስቀጠል መቻል አለብን፡፡ ምን ነበር እንደ ሕዝብ አብሮ ሲያስቀጥለን የነበረው? ምንስ አንድ ያደርገናል? የሚለውን በደንብ መለየትና ማስቀጠል ይገባል፡፡ ምናልባት ወደ እዚህ ስንመለስ፣ ራሳችንን ስናገኝ እንደ ማኅበረሰብ ለጎደለብን ነገር መልስ መስጠት እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ከኅብረሰተቡ ውጪ ያሉ ባለድርሻ አካላትም ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ቢችሉ ምኞቴ ነው፡፡ የሚመለከታቸው አካላት ለመተላለፍ ሳይሆን፣ ተግባብተውና መፍትሔ አስቀምጠው እንደ አገር እንድንቀጥል የሚያደርግ ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት ዓመት እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡

‹‹ከጦርነት አትራፊው መሣሪያ የሚሸጠው ብቻ ነው››

አቶ ግርማ ዋቄ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቦርድ ሊቀመንበር

ያለፈው ዓመት ከሞላ ጎደል መልካም ዓመት የሚባል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ዓመቱ በራሱ ያጠፋው ጥፋት የለም፡፡ ኢትዮጵያ ግን ከባድ ሁኔታ ውስጥ ያለፈችበት ዓመት ነው፡፡ ይህንን ዓመት ወደ መጨረሻው ስንደርስ ደግሞ ተመልሰን ወደ ጦርነት ገብተናል፡፡ እርስ በርስ የመጨራረስ ግዴታ ውስጥ ሆነናል፡፡ እግዚአብሔር መልካም ፈቃዱ ሆኖ ይኼንን ዓመት ስንጨርስ መልካሙን እንዲያመጣልን መፀለይ ይኖርብናል፡፡ ከጦርነት የምናገኘው ምንም ነገር የለም፡፡ ከጦርነት አትራፊው መሣሪያ የሚሸጠው ብቻ ነው፡፡ ሌሎቻችን ዝም ብለን ነው፡፡ አገሪቱ ለምታደርገው የመሻሻል ሁኔታ ሰላም አስፈላጊ ነው፡፡ ያለ ሰላም መሻሻል አይመጣም፡፡ አሁን ያለንበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የዚህ ዓይነት የእርስ በርስ ችግር ወደፊት እንዳይፈጠር ሊሠራ የሚገባበት ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ስናየው ደግሞ ዓመቱ በጥሩ ሁኔታና ሥራ አልፏል፡፡ አየር መንገዱ ጥሩ ጥሩ ዓላማዎችና የተዘጋጁ ፕሮግራሞች አሉት፡፡ እነሱን ለማሳካት ይሠራል፡፡ እንደ ኮቪድ ዓይነትና ሌሎች ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ ግን አልፎ አልፎ እንቅፋት ያጋጥማል፡፡ ይኼንንም ቢሆን ጠንክሮ እስከተሠራ ድረስ ማለፍ ይቻላል፡፡ በዚህ ዓመት አየር መንገዱ ላይ ለውጦች ተደርገዋል፡፡ ለውጥ አስፈላጊ መሆኑ አይቀርም፡፡ በፊትም፣ ዛሬም ድርጅቱ በጠቅላላ በአንድነት የሚሠራ ነው፡፡ የእኔ ወይም የአቶ ተወልደ ጉዳይ አይደለም፡፡ አየር መንገዱ የቆመበት መሠረት ጥሩ ስለሆነ በጥሩ አካሄድ ይኼዳል፡፡ ደግሞም ሁሉም የተቻለውን አድርጓል፡፡ አቶ ተወልደም የተቻለውን ሁሉ አድርጎ ድርጅቱን መርቷል፡፡ አሁን ደግሞ አቶ መስፍን ጥሩ ይዞታል፡፡ ስለዚህ በጥሩ አኳኋን ይቀጥላል ብዬ አምናለሁ፡፡ መላው ሠራተኛና አስተዳደሩ በአንድነት ከሠራ ብዙ ማሳካት እንደሚቻል ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ተስፋዬ በጣም ብዙ ነው፡፡ አገራችን ደግሞ እንዲህ ዓይነት ጦርነት ውስጥ ተገፍታ ገብታለች፡፡ በአዲሱ ዓመት እንደ ምንም ተብሎና አንዳንድ ችግሮችን አስወግዶ ወደ እዚህ የማንመለስበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ጦርነት ሲባል ደግሞ የግድ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ብቻ አይደለም፡፡ በየቦታው የሚደረገው ግድያና መፈናቀል መቆም አለበት፡፡ ከባድ ጦርነት ውስጥ ስላልተገባ ብቻ ይኼ ጦርነት አይደለም ማለት አይቻልም፡፡

ጦርነቱ ለማስቆም የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ወጣቱ ‹‹ጦርነት አልጋፈጥም›› ማለት ይኖርበታል፡፡ ማንም በየመንደሩ ተነስቶ ወጣቱን ለጦርነት የሚያሠልፍበት ሁኔታ መቆም አለበት፡፡ ወጣቱ ቆም ብሎ ማሰብና መመከር አለበት፡፡ ወጣቱ በእንዲህ ዓይነቱ ችግር እንዳይጠለፍ የሥራ ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ የሥራ ዕድል መመቻቸት አለበት፡፡ ይኼንን ለማድረግ ደግሞ የግድ መንግሥት ሁሉንም ነገር መሥራት የለበትም፡፡ ኢኮኖሚውን ለቀቅ ቢያደርገው የሥራ ዕድል ይከፈታል፡፡ ሥራ ያለው ሰው ደግሞ የማይሆን ነገር ውስጥ አይገባም፡፡ ይኼንን መንግሥትም ቢያስብበት፡፡ አባትና እናቶችም ልጆቻቸውን መያዝ ይገባቸዋል፡፡ አጉል ፖለቲካ የሚያራምዱ ሰዎች በደሃ ልጅ ደም የራሳቸውን ዓላማ ማሳኪያ አለማድረግን ማሰብ አለባቸው፡፡ በዚህ አዲስ ዓመት የእኔ ትልቁ ምኞትና ይህች አገር ሰላማዊ ሆና፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አገሩ ውስጥ በደስታ የሚኖርበት ሁኔታ ሲፈጠር ማየት ነው፡፡ ተስፋ የሚያሳዩ አንዳንድ ጭላንጭሎች አሉ፡፡ በየቦታው ሰዎች ጥያቄ መጠየቅ መጀመራቸው፣ ይኼ ተገቢ አይደለም ማለት መጀመራቸው ጥሩ ነው፡፡ ግን ይህንን በደንብ መግፋት ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ሥራዬ ብሎ ለሰላም መግፋት ይጠበቅበታል፡፡ ሰላም ስለፈለጉት ብቻ አይመጣም፣ ከኋላው ሥራ ያስፈልገዋል፡፡

‹‹ለአዲስ ዓመት ምኞቴ አንድ ነገር ነው፣ ሰላም!››

ሮፍናን ኑሪ፣ ሙዚቃ አቀናባሪ፣ ዲጄና ድምፃዊ

ራስን በዓለም ውስጥ ሆኖ መመልከት ይገባል፡፡ በእነዚህም ያሉትን ሁነቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡ ራስንና ማኅበረሰብን ከፍ አድርጎ ማየትና እንዴት ከማኅበረሰቡ ጋር ማስተሳሰር፡፡ በተለያዩ ባህሎችና ቋንቋዎች ላይ ሙዚቃን ለመሥራት ሳጠና አንድ ነገር እገነዘባለሁ፡፡ ሁሉም ሰው በአንድ እውነታ የተሳሰረ መሆኑን፣ ይህም ፍቅርና እውነት ነው፡፡ የነፀብራቅ አልበም የእኔን ትውልድ ድምፅ የሚወክል አዲስ አገርኛ ድምፅ ለኢንዱስትሪው የተበረከተበት ነው፡፡ ሁሉም ሰው ከውግንና ተላቆ ሁሉንም ከማዳመጥ ይልቅ የእሱን እውነት፣ ሐሳብና አስተያየት የሚያጠናክርለትን ነው የሚፈልገው፣ ለዚያ ነው ቁጥብ ነኝ የምለው፡፡ ለዚያ ነው አድናቂዎቼ የማያውቁትና ከዚህ ቀደም ያልገለጽኩት ምንም ነገር የለም የምለው፡፡ ሌላውን የሚረብሸው  የሚያወዛግበው ጉዳይ እኔንም የሚያወዛግብኝ፣ ምንም ማድረግ ሲያቅተኝ የሰዎችን ችግሮች አዳምጬ ያላቸውን ሕመምና እውነታ መረዳትን ምርጫዬ የማደርገው፡፡ ለዚያም ነው ሙዚቃ ያንን እንዳደርግ የሚረዳኝ፡፡

እኔ ከማለት ይልቅ፣ ራስን ብቻ ከመውደድ ይልቅ፣ እኛ ማለት እንጀምራለን፣ የሰው ልጅ ለዚህች ዓለም ሁሉም ነገር መሆኑን መረዳት እንጀምራለን፡፡ የሰው ልጅ ከዓለም ጋር ያለውን ተዛምዶ በተረዳ ቁጥር ዓለምን መጠበቅ ይጀምራል፡፡ በአልበሜ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት የእኔ ትውልድ ነገሮችን በንስር ዓይን ሊመለከት ይገባል፡፡ ለአብነትም ዛሬ ላይ ሁላችንም የምንገለገልባቸው የእጅ ስልክ፣ ኮምፒዩተር፣ ኢንተርኔትና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶችና ዛሬ ላይ እንዲህ የሚያጋድሉን ወይም የምንጋደልባቸው የዓለም ዕሳቤ (ጭንቅላት) ውጤቶች ናቸው፡፡ የዓለምን ሁሉን አቀፍ ሁኔታ ያልተረዳ ሰው ዓለም ላይ ተዓምር የሚሠራበትን ስልክ እንዴት ለመሥራት ይቻለዋል? ስለሆነም ለራሳችንና ለምንኖርባት ምድር ያለን አመለካከት የተዛባ ስለሆነ ነው ወገንተኛና ዘረኛ የሆነው፡፡ ለራሳችንና ለምንኖርባት ዓለም ያለን አረዳድ መለስ ብለን ልናይ ይገባል፣ አሊያም መቀየር ይኖርበታል፡፡ እኔም ሦስት፣ ስድስትና ዘጠኝ የሚል ስያሜ በተሰጠው አልበሜ ራስንና ዓለምን በመመልከት ውስጥ የሚገኝውን ከፍ ያለ ዕይታ እንዴት ሊሆን ይገባል የሚለውን ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ ሁሉም ሰው ሁሉም ነገር ቀላል ይሆናል የሚለውን ከተረዳ፣ ሌላው ሰው በቀላሉ የሚረዳው ጉዳይ ሆኖ ይገኛል፡፡ ለአዲስ ዓመት ምኞቴ አንድ ነገር ነው፣ ሰላም ነው፡፡

‹‹ከጥፋቱና ከጉዳቱ በመማር ከጦርነት አዙሪት ውስጥ መውጣት እንችላለን››

አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ አንጋፋው የፋይናንስ ባለሙያ

2014 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በደንብ የተፈተነችበት ዓመት ነው፡፡ ከሁሉም አቅጣጫ አገር የተፈተነችበት ዓመት ነበር፡፡ ይህም ቢሆን ግን በግሌ ተስፋ የማልቆርጥ በመሆኔ መደምደሚያና መጨረሻው ያምራል ብዬ ተስፋ አድርጌ የምኖር ስለሆነ፣ መጪው አዲስ ዓመት የዚህች አገር ትንሳዔ ይሆናል፡፡ እኔ 2015 ዓ.ም. በአጠቃላይ መንገዳችን የሚለወጥበት ዓመት ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ እስካሁን ሰንፈተን ቆይተናል፡፡ እጅግ ከባድ ፈተና ስናስተናገድ ቆይተናል፡፡ በ2014 ዓ.ም. እጅግ ከባድ ፈተና ነው ስናስተናግድ የቆየነው፡፡ ነገር ግን ለመሻገር ከፈተናው በመማር እየጠነከርን የመጣንበት ዘመን ነውና 2015 ዓ.ም. ይህች አገር በደንብ ትሻገራለች፡፡

ይህንን ተስፋ ዕውን ለማድረግ ግን ከገባንበት ጦርነት መውጣት የግድ ነው፡፡ ጦርነት አስከፊ ነው፡፡ ጦርነት በሁሉም መልኩ መጥፎ ነው፡፡ አጥፊ ነው፡፡ ነገር ግን ከጥፋቱና ከጉዳቱ በመማር ከጦርነት አዙሪት ውስጥ መውጣት እንችላለን፡፡ ለሁሉም ነገር ሰላም ወሳኝ በመሆኑ በግላችሁ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ‹‹ኧረ በቃ በሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ›› በሚል መልዕክት ሳስተላልፍ ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ ሁሉም ነገር መጨረሻው ሰላም መሆንና መጨረሻውም ዕርቅ መሆን አለበት፡፡ በበኩሌ ከደቡብ አፍሪካ ልምድ ብንወስድ እላለሁ፡፡ ሁሉም ነገር የተሳካ ነው ባይባልም ከደቡብ አፍሪካ ልምዶች በመውሰድ ሰላም እንዲወርድ ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡ ለዚህም ኔልሰን ማንዴላና ዴክላርክ ያደረጉት ንግርር ያስገኘውን ጥቅም አስረጂ ነው፡፡ ስለዚህ እኛም አገር የሚያዋጣን መነጋገርና መወያየት ብቻ ነው፡፡ በጦርነት ብናሸንፍም ትልቁ ቁምነገር ሰላምን ማሸነፍ ነው፡፡ በመገዳደል አንዱን አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ አድርጎ  ሰላም አይመጣም፡፡ መወያየትና መደራደር ያስፈልጋል፡፡ እንደምናሸንፍም ብናውቅም ዞሮ ዞሮ መጨረሻው መደምደሚያው ተወያይቶ አብሮ ለመኖር መስማማትና እስክንስማማ ድረስ ደግሞ መጋደላችንን አቁመን፣ በዚያ መልክ ውይይት ብናደርግ ነው የሚያምርብን፡፡

አንዳንድ ጊዜ ቀንቶናል፣ ጥምር ጦር እዚህ ደርሷል እዚያ ደርሷልና ካላጠፋናቸው የሚባለው መጥፎ ነገር ነው፡፡ ሕወሓትም በአሁኑ ጊዜ ሸብረክ ማለት ነበረበት፡፡ ሕዝብን እያስጨረሰ መሄድ የለበትም፡፡ ሕዝብ እየተቀበለ አሁንም በዚያው ካልተገነጠልን፣ ብቻችንን ካልሆንን የሚለው ጽንፈኝነት በመሆኑ በምንም ሁኔታ ይህ ዕሳቤ ተቀባይነት የለውም፡፡ አሁን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ወደ ሰላም ለመምጣት ተስፋ አለው፡፡ ወደድንም ጠላንም በአሁኑ ጊዜ ሕወሓቶች እንደማያሸንፉ ተገንዝበው መምጣት አለባቸው፡፡ የአገሬውም ሕዝብ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሊረዳ ይገባዋል፡፡

እስከ መቼ ሕዝብ እንደዚህ ሆኖ ይቀጥላል? ስለዚህ የግድ አንድ ቦታ መቆም ይኖርበታል፡፡ እኛም ማሸነፋችን ከሆነ የአገሬ ሕዝበ ለመቀበል በጣም ያስቸግረዋል፡፡ ግን ሁላችሁንም ካልጨረስኳችሁ ማለትም ትክክል አይሆንም፡፡ ይህ ጦርነት የሚካሄደው ሁሉም የትግራይ ሕዝብ ደግፎ አይደለም፡፡ ብዙዎች እየተሰቃዩ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አማራጫችንን በጣም የጠበበበ ነው፡፡ ቢሆንም ግን የአምላክንም ተአምር እየጠበቅንና እየለመንን ለሰላም ማሰብ አለብን፡፡ መጪው ዘመን መልካም የሚሆነው በዚህ መንገድ ነው፡፡  

   

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -