Thursday, November 30, 2023

ኢምባሲዎች በግቢያቸው ስብሰባ ከማድረጋቸው በፊት ለመንግሥት እንዲያሳውቁ ትዕዛዝ ተላለፈ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገር ኢምባሲዎችና ሚሲዮኖች በቅጥር ግቢያቸው የሚያደርጓቸውን ስብሰባዎች ከማካሄዳቸው በፊት በቅደሚያ እንዲያሳውቁ ትዕዛዝ አስተላላፈ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጳጉሜ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሁሉም ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ በጻፈው ደብዳቤ፣ መንግሥት በአገሪቱ የሚገኙ የዲፕሎማቲክና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ደኅንነት ለማስጠበቅ ግዴታ ያለበት በመሆኑ፣ ተጨማሪ ጥንቃቄ ማድረግ ማስፈለጉን አስታውቋል፡፡

በዚህም በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁሉም ኢምባሲዎችና ቆንስላዎች በቅጥር ግቢያቸውም ሆነ በሌላ አካባቢ ለሚያደርጓቸው ስብሰባዎች፣ በጽሑፍ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀድመው ማሳወቅ እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡

የሚደረጉ ስብሰባዎችን አስመልክቶ፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚደረጉ የጽሑፍ ማሳወቂያዎች የተሳታፊዎች ቁጥር፣ የስብሰባው ዓላማ፣ የሚወስደውን ጊዜ በግልጽ የሚያሳይ መሆን እንዳለበትና ለሚደረጉ ስብሰባዎች ከመንግሥት ሊቀርቡ ስለሚገቡ የደኅንነት ዕገዛዎች አብረው መካተት እንዳለባቸው በደብዳቤው ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ስማቸው ሳይጠቀስ ሐሳባቸውን የሰጡ አንድ የአውሮፓ አገር የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባል እንደተናገሩት፣ የተላለፈው ማሳሰቢያ ከፀጥታ ችግር አንፃር ተብሎ ቢሆንም ለምናደርጋቸው ስብሰባዎች የማሳወቅ ችግር የለብንም ብለዋል፡፡ ‹‹ጉዳዩ ትንሽ የተወሳሰበ ቢሆንም ምን ማድረግ ይቻላል፣ አሜን ብሎ ከመቀበል ውጭ፤›› ነገር ግን ከባድ ጉዳይ አይደለም፣ ምንም እንኳ በጥያቄ ምልክት ውስጥ ሊገባ የሚችል አሠራር ቢሆንም ብለዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርተር ማብራሪያ የጠየቃቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም (አምባሳደር) እንደተናገሩት ‹‹ይህ የተለመደ የዲፕሎማሲ አሠራር ነው፣ በየትኛውም አገር ያለ ኢምባሲ ከከተማ ሲወጣ ወይም ስብሰባ ሲያደርግ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያሳውቃል፣ ይህ አሠራር ‹‹ጁባም ጀኔቫም›› እንደዚያው ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥም የተለመደ አሠራር መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ አዲስ አሠራር እንዳልተፈጠረ አስረድተዋል፡፡

በሌላ ዜና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዓርብ ጳጉሜን 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተቋም ከሥልጣኑ ውጭ የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ ማቅረቡን መንግሥት ውድቅ አድርጎታል፡፡

ኮሚሽኑ ጳጉሜን 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ እንደ አዲስ ያገረሸው ጦርነት ብሎም የኤርትራ ጣልቃ መግባት እንዳሳሰበው በመግለጽ፣ የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን በአስቸኳይ እንዲመለከተውና አፋጣኝ ዕርምጃ እንዲወስድ አስታውቆ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በመግለጫው፣ ኮሚሽኑ መንግሥት ለሰብዓዊነት ሲባል የወሰነውን የተኩስ አቁም በመተውና የሰላም አማራጭን ትቶ ወደ ጦርነት የገባውን ሕወሓት ለመውቀስ ያልደፈረ፣ ነገር ግን ለፀጥታው ምክር ቤተ ጥሪ ማቅረቡ ግዴለሽነት የታየበትና የኮሚሽኑን ፖለቲካዊ ዓላማ ያደላ ሥራ እንደሚሠራ ማሳያ መሆኑን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -