ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም አዲስ ዓመት እንመኛለን፡፡ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የመልካም ነገሮች ጅማሮና በተስፋ የተሞላ እንዲሆንም ምኞታችንን እንገልጻለን፡፡ አዲሱ ዓመት በብሩህ ተስፋ እንዲጀመር ኢትዮጵያውያን በሁሉም መስኮች የሚፈለግባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም በአክብሮት እናሳስባለን፡፡ ኢትዮጵያ ከገባችበት አውዳሚ ጦርነት ውስጥ በፍጥነት እንድትወጣ፣ በየቦታው በሚከሰቱ ግጭቶች በሰብዓዊ ፍጡራንና በአገር ሀብት ላይ የሚደርሱ ዕልቂቶችና ውድመቶች እንዲያበቁ፣ በኢትዮጵያውያን መካከል ቅራኔ የሚፈጥሩ ችግሮች በሰከነ መንገድ እንዲፈቱና በአጠቃላይ ሰላም ሰፍኖ ፊትን ወደ ልማት ማዞር እንዲቻል ሁለገብ ርብርብ ይደረግ፡፡ ኢትዮጵያውያን በትውልዶች ቅብብል እዚህ ያደረሱዋቸውን ተምሳሌታዊ ማኅበራዊ እሴቶቻቸውን የበለጠ በማጎልበት፣ አብሮ የመብላት ብቻ ሳይሆን አብሮ የመሥራት ባህል ለማዳበር በጋራ መነሳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዘመናት የሚጠቀሙባቸውን መልካም ባህሎቻቸውን በማስቀጠል፣ የማይጠቅሙ ጎጂ ልማዶችን በተሻሉ መተካትም ይኖርባቸዋል፡፡ በዓላት ሲደርሱ የሚታወቀው የመተሳሰብና የመረዳዳት አኩሪ ተግባሮቻቸውን በማጠናከር፣ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ አደጋዎች የተጎዱ ወገኖቻቸውንም ማሰብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አዲሱ ዓመት በብሩህ ተስፋ የሚታጀበው ከጦረኝነት አስተሳሰብ በመውጣት ለጋራ ዕድገት መነሳት ሲቻል ነው፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተዋናይ የሆኑ ወገኖች በሙሉ በአዲሱ ዓመት መልካም ባህሪ ይላበሱ፡፡ ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪዎቹ በሙሉ ለኩሩውና ለጨዋው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመጥን ባህሪ ያሳዩ፡፡ እርስ በርስ ከመከባበር አልፈው ለተቀናቃኞቻቸው አክብሮት ያሳዩ፡፡ ለዓመታት ከሰለቸ ጠልፎ መጣል የሴራ ፖለቲካ ውስጥ በመውጣት፣ ሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር እንዲጠናከር ያድርጉ፡፡ የሥልጣኑ ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚከበረው፣ ለሰላማዊና ለሥልጡን ፖለቲካ ዝግጁ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምኅዳሩ ውስጥ በነፃነት ሲንቀሳቀሱ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ከጠቅላይነት አስተሳሰብ በመውጣት ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ቁርጠኝነት ማሳየት ይኖርበታል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በዚሁ መንፈስ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆናቸውን በተግባር ያሳዩ፡፡ በልዩነት ምክንያት ከሕጋዊና ከሰላማዊ ፖለቲካ ፉክክር ራሳቸውን አግልለው ነፍጥ ያነገቡትም፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮችን ለመፍታት ፈቃደኝነታቸውን ያሳዩ፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን እንደ ዘመነ መሣፍንት በነፍጥ ይዋጣልን ማለት የኋላቀርነት ምልክት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዘመናት ችግሮች የሚፈቱት በጉልበት አይደለም፡፡ በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ለውጥ ይታይበት፡፡
በአዲሱ ዓመት ከኢትዮጵያ ምድር ስግብግብነት ሥሩ መነቀል አለበት፡፡ ነጋዴው በገዛ ወገኑ ላይ የእጥፍ እጥፍ በማትረፍ የሚያገኘው ደስታ ቁሳዊ ነው፡፡ ነገር ግን ወገኑን ማሰብ ሲጀምር ከምንም በላይ የህሊና እርካታ ያተርፍበታል፡፡ የገዛ ወገንን እያራቆቱ ገንዘብ በመቆለል የሚገኝ ደስታ ያሰክር ይሆናል እንጂ፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ህሊናዊ ደስታ ሊያጎናፅፍ አይችልም፡፡ ህሊና ምቹ ትራስ ሆኖ ሰላማዊ እንቅልፍ የሚገኘው በንፅህና ሥራን ማከናወን ሲቻል ነው፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች የሚቀምሱት አጥተው የዕለት ደራሽ ዕርዳታ እየተለመነላቸው፣ በርካታ ሚሊዮኖች በሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበት ኑሮአቸው ተመሰቃቅሎና ግራ ተጋብተው በእነሱ ላይ ያልተገባ ትርፍ ማጋበስ ነውር ነው፡፡ በዚህ ዘመን ከተለመዱ ነውረኛ ድርጊቶች መካከል በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው “በአቋራጭ መክበር” የሚባለው ነው፡፡ ይህ ወጣቱን ትውልድ ሳይቀር እየበከለ ያለ አደገኛና አክሳሪ ድርጊት፣ በጊዜ መላ ካልተፈለገለት አገር አውዳሚ እንደሚሆን መጠራጠር አይገባም፡፡ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” ከሚባለው የዘመነ ፊውዳል አስተሳሰብ የተወረሰው የአቋራጭ ሌብነት በአዲሱ ዓመት ከኢትዮጵያ ምድር ይነቀል፡፡
የመንግሥት ሹማምንት የቀጠራችሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ በቅንነት ለማገልገል በአዲሱ ዓመት ቃል ግቡ፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይኛው የመንግሥት መዋቅር ድረስ የሚስተዋለውን ብልሹ አሠራር አስወግዱ፡፡ የመንግሥት መዋቅር የሌቦችና የደላሎች መናኸሪያ መሆኑ ያብቃ፡፡ ግብር ከፋዩን ሕዝብ ጉቦ መጠየቅ፣ ማባሪያ በሌለው ስብሰባ እያሳበቡ ከቢሮ መጥፋት፣ ተጋልጋዮችን ማመናጨቅ፣ የመንግሥት በጀት መዝረፍ፣ በኔትወርክ በመቧደን ሌብነትን ማስፋፋት፣ መሬት በጠራራ ፀሐይ መውረርና ማስወረር፣ ለዕርዳታ የሚቀርቡ ቁሳቁሶችንና ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋልና የመሳሰሉ አስነዋሪ ድርጊቶችን ማስቆም ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የረከሰ ድርጊት አይመለከተንም የምትሉም አጥፊዎችን በድፍረት አጋልጡ፡፡ ከአንድ ቦታ በሌብነት ወይም በብቃት አልባነት የሚነሳን ተሿሚ ሌላ ቦታ መሾም መቆም አለበት፡፡ በፓርቲ ወገናዊነት ብቻ ለአገር የማያስቡ ግለሰቦችን በሕዝብ ላይ እንዲቀልዱ ማድረግ ይብቃ፡፡ የመንግሥት ተቋማት በብቁ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ በትጉህ ሠራተኞችና በጠንካራ ሕጎች ይጠናከሩ፡፡ የአድርባዮችና የአስመሳዮች መሰባሰቢያ ከመሆን ነፃ ይውጡ፡፡ የመንግሥትና የፓርቲ ሥራዎች አይደባለቁ፡፡ በአዲሱ ዓመት የመንግሥት ተቋማት የሕዝብ አገልጋይ ይሁኑ፡፡ በነፃነትና በክብር ሥራቸውን ያከናውኑ፡፡
የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰቦች፣ የሙያና የጥቅም ማኅበራት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ የእምነት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአዲሱ ዓመት ለአገር ሰላም የሚፈለግባችሁን አስተዋፅኦ አበርክቱ፡፡ ከአገር በፊት ምንም የሚቀድም ነገር የለምና ለኢትዮጵያ ህልውና ስትሉ ሥራችሁን በአግባቡ ተወጡ፡፡ ከፖለቲካዊ ወገናዊነት ራሳችሁን ነፃና ገለልተኛ በማድረግ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዘለቄታዊ ጥቅም ሥሩ፡፡ ከውጭ ኃይሎች ጋር በሥራም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ግንኙነት ያላችሁ ጥንቃቄ አድርጉ፡፡ የውጭ ኃይሎችን ጥቅማቸውን ታሳቢ አድርገው ስለሚመጡ፣ በተቻለ መጠን የአገራችሁን ጥቅምና ደኅንነት አስከብሩ፡፡ ለጊዜያዊ ጥቅም ብላችሁ በውጭ ኃይሎች ድጎማ አገር አፍራሽ ድርጊት ውስጥ እንዳትገኙ ጥረት አድርጉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና ማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች እንዳይፈጸሙ ታገሉ፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙ ከግጭት ይልቅ ሰላማዊ መፍትሔዎች ላይ እንዲተኮር አስተምሩ፡፡ ወጣቱ ትውልድ መልካም አርዓያነት ያላቸው ተግባራት ላይ እንዲሰማራ በጎ ፈቃደኝነትን አለማምዱት፡፡ አገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎችን እንዲያውቅ አድርጉት፡፡ በአዲሱ ዓመት ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት አገር እንድትሆን አርዓያ ሁኑ፡፡
ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ደም የሚፈስባት ሳትሆን የተትረፈረፈ ምርት የሚታፈስባት እንድትሆን፣ በሁሉም መስኮች ለልማትና ለዕድገት የሚያግዙ ተግባራትን ማከናወን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ተቀዳሚ ዓላማ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በሕግና በሥርዓት መምራትና መመራት የአገር ባህል ሊሆን ይገባል፡፡ ተማሪዎች ጥራት ያለው ትምህርት አግኝተው ዘመኑን በሚመጥን ዕውቀት እንዲኮተኮቱ ማድረግ የቤተሰብና የትምህርት ቤቶች ኃላፊነት ቢሆንም፣ መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በእጅጉ ይመለከታቸዋል፡፡ የግብርናም ሆነ የኢንዱስትሪ ምርቶች የአቅርቦት ሰንሰለታቸው እንከን ሳይገጥመው በአግባቡ ለሸማቾች እንዲቀርቡ፣ ሕገወጥ ተዋናዮች የግብይት ሥርዓቱን እንዳያዛቡና ሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበት እንዳይፈጠር መንግሥት ኃላፊነቱን ይወጣ፡፡ ከበጋ ስንዴ በተጨማሪ ሁሉም የምግብ ሰብሎችና የእንስሳት ተዋፅኦዎች በገፍ ወደ ገበያ እንዲቀርቡ የሚያስችል በዕቅድ ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ ይጀመር፡፡ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከግጭትና ከአውዳሚ ጦርነት የሚያላቅቁ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ የምክክር መድረኮች ይዘጋጁ፡፡ ለሕግ የበላይነት መከበር የሚረዱ ሥራዎች ይከናወኑ፡፡ ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት በፍትሕ፣ በእኩልነትና በነፃነት ምድርነት ስሟ የሚጠራ ትሁን! መልካም አዲስ ዓመት!