Thursday, September 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየ12ኛ ክፍል ተፈታኞች የመጓጓዣና ሌሎች ወጪዎችን በመንግሥት እንደሚሸፈን ተገለጸ

የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች የመጓጓዣና ሌሎች ወጪዎችን በመንግሥት እንደሚሸፈን ተገለጸ

ቀን:

ከመስከረም 2015 ዓ.ም. መጨረሻ አንስቶ በሁለት ዙር የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱ አንድ ሚሊዮን ገደማ ተፈታኝ ተማሪዎች፣ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የሚጓጓዙበትን የትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎች በመንግሥት እንደሚሸፈኑ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ለተፈታኝ ተማሪዎች የሚያስፈልጉ የምገባና መኝታ አገልግሎቶችን ለመስጠት ቁሳቁሶችን እያሟሉ መሆኑን አስታውቆ፣ ፈተናውን በዩኒቨርሲቲዎች ለማከናወን የሚያስችለውን ወጪ ለመሸፈን ተጨማሪ በጀት እንዲፈቀድለት ንግግር ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡

የ12ኛ ክፍል ፈተናን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ከነበረው ልምድ የተለየ አሠራር ለመዘርጋት ያቀደው ትምህርት ሚኒስቴር፣ ፈተናው በትምህርት ቤቶች ሳይሆን በዩኒቨርስቲዎች እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡ ለዚህም ሲባል ተፈታኝ ተማሪዎችን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መመደቡን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ኃላፊ አቶ ይልቃል ወንድሜነህ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ምደባው ሲዘጋጅ በተቻለ መጠን ተማሪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲመደቡ መደረጉን ያስረዱት አቶ ይልቃል፣ ‹‹በአቅራቢያቸው ያለው ዩኒቨርሲቲ በመኝታ ወይም በመፈተኛ ክፍሎች ብዛት ውስንነት ካለበት ወደ ሌላ ዞንና ክልል የመሄድ ዕድል ይኖራል፤›› ብለዋል፡፡

በተለይ ገጠር አካባቢዎች ላይ ያሉ ተማሪዎች ወደ ተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ለመጓዝ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊገጥማቸው እንደሚችል ጠቅሰው፣ አገልግሎቱ ከክልል ትምህርት ቢሮዎች ጋር በመሆን ተማሪዎቹን ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደሚያጓጉዝ አስረድተዋል፡፡

‹ተማሪዎቹን እንዴት እናጓጉዛቸው?› የሚለው ላይ ውይይት እያደረግን ነው፡፡ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲዎች በመፈተናቸው ምክንያት ግን ወደ ተማሪዎችም ሆነ ወደ ወላጆች የሚሄድ ወጪ አይኖርም፤›› ብለዋል፡፡

ምክትል ኃላፊው፣ ተማሪዎቹ የተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ አካባቢ እንዲላመዱት ለማድረግ ሲባል ፈተናው ከሚጀመርበት ቀናት ቀደም ብለው ወደ ዩኒቨርሲቲው እንደሚጓዙ አስታውቀዋል፡፡ ወደ ዩኒቨርስቲ ሲገቡ ድምፅም ሆነ ምሥል የሚቀዳና የሚቀርፅ አሊያም ሌላ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ ይዘው መግባት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ የሚኖሩበት ከተማ ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ ተፈታኞችም ቢሆኑ በዩኒቨርስቲው ውስጥ እንዲያድሩ ለማድረግ መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡

ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በሁለት ዙር በሚሰጠው የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከ984,000 በላይ ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀመጡ ተገልጿል፡፡ መስከረም 30 ቀን በሚጀምረው የመጀመሪያው ዙር ፈተና ለፈተና የሚቀመጡት የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ ብዛታቸው 623 ሺሕ ገደማ ነው፡፡ ይህም ፈተናው የሚሰጥባቸው 42 ዩኒቨርሲቲዎች በመጀመሪያው ዙር በፈተና በአማካይ 14,827 ሺሕ ገደማ የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች በእያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይመደባሉ እንደማለት ነው፡፡

ይሁንና የዩኒቨርሲቲዎች ምደባ የተደረገላቸው ካላቸው ሀብትና አቅም አንፃር እየታየ መሆኑን የተናገሩት አቶ ይልቃል፣ ፈተናው በሁለት ዙር እንዲሰጥ የተወሰነው ዩኒቨርሲቲዎቹ ካላቸው አቅም አንፃር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ ለአንድ ዙር የተመደበላቸውን የተማሪ ብዛት ለማስተማገድ የሚጎድሏቸው ቁሳቁሶችን በመገምገም በግዥ እንዲያሟሉ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ፈተናውን ለማከናወን የሚያስፈልገው ወጪ ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ምክትል ኃላፊ፣ ‹‹ሐሳቡ ቀደም ብሎ ስለነበር ተጨማሪው በጀት ተጠይቋል፡፡ አሁን ያለው በጀት ግን ይህንን የሚሸፍን አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡ ክልሎችም የሚሸፍኑት ወጪ ሊኖር እንደሚችል የጠቆሙት አቶ ይልቃል፣ ፈተናውን ለማከነውን የሚያስፈልገውን አጠቃላይ ወጪ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት በ2015 በጀት ዓመት 1.1 ቢሊዮን ብር ገደማ የተበጀተለት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 943.8 ሚሊዮን ብሩ ወይም 85.9 በመቶው የተመደበው የፈተና ዝግጅት፣ ዕርማትና የውጤት ጥንቅርና የተማሪዎች ምደባ ነው፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር የ12ተኛ ክፍል ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰጥ የወሰነው፣ ከፈተና ስርቆት ጋር በተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚሠራጩ መረጃዎች የተማሪዎች ሥነ ልቦና ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመከላከል መሆኑን ገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ ዩኒቨርሲቲዎች ለፈተናው ለሚቀበሏቸው ተማሪዎች አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ያስተላለፈው ከአንድ ወር በፊት ነበር፡፡ የትምህርት ሚኒስትር ደኤታው ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ለ42 ዩኒቨርሲቲዎች በጻፉት ደብዳቤ፣ ከመስከረም 28 ቀን 2015 ዓ.ም. አንስቶ ምንም መደበኛ ተማሪ በግቢዎቻቸው ውስጥ እንዳይኖሩ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ በሚመደብላቸው የተማሪ ብዛት ልክ ምግብ ለማቅረብ እንዲዘጋጁና የፈተናውን አሰጣጥ ደኅንነት የሚቆጣጠር ግብረ ኃይል እንዲያዋቅሩ በደብዳቤው አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...