Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተመድ አስታወቀ

በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተመድ አስታወቀ

ቀን:

የተባሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ጳጉሜ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ ያለው አጠቃላይ የሰብዓዊ ዕርዳት አቅርቦት ሁኔታ በግጭት፣ ጎርፍና ድርቅ ምክንያት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አስታውቋል፡፡

ሪፖርቱ እንደሚያመላክተው በጦርነት፣ በአየር ንብረት መለወጥና በጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት 20 ሚሊዮን ዜጎች እ.ኤ.ኤ. 2022 መጨረሻ የሰብዓዊ ዕርዳታ እርቦት ይጠብቃሉ ብሏል፡፡

የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት ለበርካታ ወራት ያክል ጦርነት አቁመው የነበረ ቢሆንም፣ እንደገና ባገረሸው ጦርነት በርካታ ዜጎች በተለይም በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልል የሚገኑ ዜጎች የሕይወት አድን ምግቦች ፍላጎት እንዳሻቀበ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ተመድ ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ጦርነት እንደ አዲስ ማገርሸቱን ተከትሎ፣ ወደ ትግራይ መግባት የነበረባቸው ዕርዳታ የጫኑ 228 የጭነት ተሽከርካሪዎች ከሰመራ አልፈው ወደ መቀሌ አለመግባታቸውን ያመላከተ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 196 የሚሆኑት ማዳበሪያ የጫኑ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በሐምሌ 2014 ዓ.ም. ብቻ የዕርዳታ እህል የጫኑ 1‚220 የጭነት ተሽከርካሪዎች መቀሌ መግባታቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፣ ወደ መቀሌ ሲደረጉ ከነበሩ ሦስት ሳምንታዊ የአየር በረራዎች መካከል ከነሐሴ 20 ቀን ጀምሮ በረራ መቋረጡ ተገልጿል፡፡

በአማራ ክልል ዋግህምራ አካባቢ በጦርነቱ ምክንያት የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት መቆሙን፣ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ጃሂ ጠናን ወራዳ 66 የቤተሰብ አባላት በጎርፍ መፈናቀላቸውንና ባለፉት ስድስት ወራት ከወልዲያ 50 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቆ በሚገኘውና ጃራ በተባለው ቦታ ሰፍረው የነበሩ 30 ሽሕ ተፈናቃዮች በሰሞነኛው ጦርነት ሥጋት ምክንት ቦታውን ለቀው መውጣታቸን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በምሥራቅ፣ ደቡብና ምዕራብ ኢትዮጵያ አልፎ አልፎ በሚነሱ ግጭቶች የተነሳ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት መስተጓጎሉን ያመላከተው ሪፖርቱ፣ በሶማሌ ክልል በቅርቡ በተፈጠረ የፀጥታ ችግር ምክንያት በርካታ መፈናቀል እንደተከሰተ አስታውቋል፡፡ በአካባቢው በተጨማሪም፣ በተከሰተው ድርቅ ሊደረጉ የሚገባቸውን ድጋፎች በተገቢው ሁኔታ እንዳይቀርቡ መሰናክል መፍጠሩን በተለይም አፍደርና ሸበሌ ዞኖች እንዲሁም፣ በተወሰነ መልኩ ሊበን ዞን ላይ ችግሩ መከሰቱን ተጠቁሟል፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ በክልሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 4.1 ሚሊዮን ዜጎች የሚደረገው የዕርዳታ አቅርቦት ላይ መሰናክል መፍጠሩን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

የተመድ ሪፖርት እንደሚያሳየው በምሥራቅና ደቡብ ኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያና የደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ ለአምስተኛ ጊዜ የማያገኙ መሆናቸውና በዚህም የተነሳ የሰብዓዊ ዕርደታ አቅርቦት ችግርን ሊያባብሰው እንደሚችል ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 16 ሚሊዮን ዜጎች በድርቅ የተጎዱ መሆኑን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ በዚህም በቀጣይ ወራት የሕይወት አድን ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል በድርቅ ምክንያት 3.5 ሚሊዮን የቤት እንስሳት መሞታቸውንና 25 ሚሊዮን የቤት እንስሳት አደጋ ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት በሆሮ ጉዱ ወለጋ 54 ሽሕ፣ ምዕራብ ወለጋ 101 ሽሕ በድምሩ 155 ሽሕ ዜጎች መፈናቀላቸውን እንዲሁም 13 የጤና ተቋማት መዘረፋቸውን፣ 28 ጤና ኬላና አምስት አምቡላንስ መቃጠላቸውን  ያብራራው ሪፖርቱ፣ በዚህ የተነሳ የሕዝቡን የጤና አጠባበቅ ሁኔታ አሳሳቢ እንዳደረገውና ባለፉት ወራት የጤና ተቋማት ባለማግኘታቸው ብቻ 84 እናቶች መሞታቸውን አስረድቷል፡፡

ሪፖርቱ በኦሮሚያ ክልል በአጠቃላይ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ ምሥራቅ ኦሮሚያ እንዲሁም ቄለም ወላጋ የሰብዓዊ ዕርዳታው አሳሳቢ ከመሆኑም በላይ፣ የረጂ ድርጅቶች ገንዘብ አለመልቀቅ ችግሩን ይበልጡን እንዳባባሰው ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...