Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ስለሚፈቅደው የፖሊሲ ውሳኔ የዘርፉ ባለሙያዎች ምን አሉ?

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በላይ በተለያየ መንገድ አስተያየት ሲሰጥበት የቆየውና ከዛሬ ነገ ዕውን ይሆናል እየተባለ ሲጠበቅ የነበረው የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ የሚፈቅደው የፖሊሲ ውሳኔ በመንግሥት ተወስኗል፡፡ ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ያረፈበት የውጭ የፋይናንስ ተቋማት እንዲገቡ መፈቀድ ታሪካዊ የሚባል እንደሆነም እየገለጸ ነው፡፡ 

ይህ ውሳኔ የውጭ ባንኮች ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ዳግም እንዲገቡና የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት እንደሚሆን መንግስት በይፋ የገለጸበት የፖሊሲ ሰነድ ነው፡፡ 

የውጭ የፋይናንስ ተቋማት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የፖሊሲ ውሳኔ መተላለፉ ታሪካዊ የሚባል መሆኑን ከገለጹት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አሰግድ ገብረመድን የፖሊሲ ውሳኔው ከታሪካዊነቱ ባሻገር  ወቅቱን የጠበቀ ስለመሆኑም ያመለክታሉ፡፡ 

የውጭ የፋይናንስ ተቋማት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበት መንገድ ምንም ይሁን ምን በኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ አዲስና ጠቃሚ የሚባል አሠራር የሚፈጥር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው የሚገልጹት አቶ አሰግድ በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በርካታ ሥር ነቀል  ለውጦች የሚፈጥር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 

አቶ አሰግድ የሚኒስሮች ምክር ቤት የፋይናንስ ዘርፉ ክፍት እንዲሆን መወሰኑ ለአገሪቱ ቀጣይ ዕድገት አስፈላጊ ነው ብለዋል። ውሳኔው ወቅቱን የጠበቀ ስለመሆኑና የኢንዱስትሪውን አሠራር አደረጃጀትና አጠቃላይ ይዘት የሚለውጥ እንደሚሆን የገለጹት የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንትና የዳሸን ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ራሳቸውን እንደ አዲስ የሚያደራጁበትና ውድድሩን ለመወጣት ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚተልሙበት ወሳኝ ሰዓት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ በእርግጥም ይህ ውሳኔ ዝርዝር መረጃዎችን ያላመላከተ ቢሆንም ታሪካዊ ሊባል እንደሚችል የጠቀሱት አቶ አስፋው ለአገራዊ ኢኮኖሚው ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን እነዚህ የውጭ ባንኮች እንዴት ይገባሉ የሚለው ነገር በቶሎ መገለጽና መታወቅ ያለበት መሆኑን ነው፡፡ ይህ የመንግሥት ውሳኔ ዝርዝር መሰጃው ባይገለጽም እስከዛሬ ድረስ በቃል ሲነገር የነበረውን የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ክፍት የማድረግ ፍላጎት መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ በፖሊሲ ደረጃ በይፋ ያሳወቀበትና ሁሉም ተዋንያኖች እንዲያውቁት መልዕክት የተላለፈበት ነው ብለዋል፡፡ ይህ የፖሊሲ ውሳኔ 

የውጪ ባንኮች መግባት እርግጥ መሆኑንና እያንዳንዱ የአገር ውስጥ ባንክ የራሱን ዝግጅት ከወዲሁ በትኩረት እንዲሠራ ያደርጋል ብለዋል፡፡ 

የውጭ ባንኮች መግባት ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚ ይዛ እንድትወጣና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን ለማጉላት መንገድ የሚቀድ ነው ያሉት አቶ አሰግድ ፣ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበት መልክ የተገለጸ ባይሆንም የእነዚህ ተቋማት መግባት በእጅጉ ጠቃሚ እንደሆነ የምናሉ፡፡ 

የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ለመፍታት፣ በአነስተኛ ወለድ ብድር ለማግኘትና ከ50 እና 60 ዓመታት በላይ በተለምዶ ሲሠራበት የነበረው የባንክና የኢንሹራንስ አገልግሎት ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን ይዞ እንዲሠራ ጭምር ይህ ውሳኔ ትልቅ ዕገዛ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡ 

ይህ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ  ብቻ የታጠረውን አገልግሎታቸውን ድንበር ተሻግረው እንዲሠሩ ጭምር የሚያግዝ እንደሆነ አቶ አስፋውና አቶ አሰግድ የገለጹ ሲሆን ወደ ተግባር ለመግባት ግን አሁንም ተጨማሪ ሥራዎች የሚጠበቁ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡እነዚህ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት መልክ ምን ይሁን ምን በሊያመጣ የሚችለው ተፅዕኖ እንደሌለ አቶ አሰግድ ይገልጻሉ። አቶ አስፋው ግን የውጭ ባንኮች አገባብ ደረጃ በደረጃ ቢሆን ይመረጣል የሚል ምልከታ አላቸው፡፡ 

ሙሉ በሙሉ ቢገቡም ብዙዎች እንደሚሉት ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋር በመጣመር እንዲገቡ ቢፈቅድም ጠቀሜታው ለአገር ነው የሚል አስተያየታቸውን ያጎሉት አቶ አሰግድ የአገር ውስጥ ባንኮች ተወዳዳሪ ለመሆን ግን ከወዲሁ ሊዘጋጁባቸው ይገባል ሲሉ መክረዋል። ለአብነት ካነሱዋቸው መካከል በየትኛውም መንገድ የውጭ ባንኮች ቢገቡ ይዘውት የሚመጡት ካፒታል ከፍተኛ መጠን ያለው ስለሚሆን ይህንን የሚመጥን ካፒታል የአገር ውስጥ ባንኮች ማደራጀት ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህ አሁን ያሉት ባንኮች በያዙት ካፒታል ተወዳዳሪ ሊሆኑ ስለማይችሉ ትልልቅ የሚባሉት ባንኮች ሁለት ሦስት ሆነው፣ እንዲሁም አነስተኛ ካፒታል ያላቸው ደግሞ አምስት ስድስት ሆነው መዋሃድ ሊጠይቃቸው እንደሚችል ያምናሉ፡፡ ይህንን ማድረግ ግድ የሚል መሆኑንም የሚገልጹት አቶ አሰግድ የአገር ውስጥ ባንኮች ወህደት በመፍጠር ጠንካራ የኢትዮጵያ ባንክ በመመሥረት ከውጪዎቹ ጋር መወዳደር ወይም ተጣምረው በመሥራት ከኢትዮጵያ ውጪ በመውጣት ተወዳዳሪ ባንክ መፍጠር የሚያስችላቸው ዕድል ለመፍጠር ጭምር የሚረዳቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

አቶ አስፋው ግን የውጭ ባንኮች በአንድ ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንዲገቡ የሚፈቀድ ከሆነ ተፅዕኖ ሊያመጣ እንደሚችል በመጥቀስ ፣ የውጭ ባንኮች ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋር ተጣምረው እንዲሠሩ በማድረግ ውሳኔውን ማስጀመር ተገቢ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ 

ነገር ግን ከመደበኛው ባንክ አገልግሎት ሌላ በአንድ ዘርፍ ላይ ያተኮሩ (ስፔሻላይዝድ በሆኑ) ለምሳሌ እንደ እርሻ፣ ኢንቨስትመንትና በመሳሰሉ ዘርፎች ባንኮችን እንዲያቋቁሙ ቢፈቀድ የበለጠ ጠቀሜታ እንዳለውም አቶ አስፋው ይናገራሉ፡፡

በሰሞናዊው የመንግሥት ውሳኔ በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው  የፋይናንስ ተቋማት የውሳኔው ዝርዝር መረጃ ያልደረሳቸው ሲሆን ውሳኔው ግን በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የለተያዩ አስተያየቶች እየተሰጡበት ይገኛል፡፡ 

መንግሥት ገንዘብ ስለቸገረው የወሰነው ውሳኔ ነው የሚሉ ያሉትን ጨምሮ ፣ ውሳኔው ተገቢ ቢሆንም ፈጠነ የሚሉ ትችቶችም እየቀረቡበት ነው፡፡ አቶ አሰግድ እንዲህ ያለውን አስተያየት አይቀበሉም፡፡ እንደውም የዘገየ ውሳኔ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ አሁን ያለውን ችግር ለመፍታት ከተፈለገ ከዚህ ዕርምጃ ሌላ ሊወሰድ የሚችል የተሻለ ውሳኔ ያለመኖሩን ያሰምሩበታል፡፡ ስለአገር መበልፀግና ዕድገት ከታሰበ ከዚህ ውሳኔ በተፃራሪ መቆም ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ውሳኔ ዙሪያ የተለያዩ አመለካከት እንዳለ የጠቆሙት አቶ አስፋው ደግሞ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት አዲስ የሆነ አሠራር የሚፈጠር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ብዥታ በመኖሩ ነው ይላሉ፡፡ ሁሌም ወደ አዲስ አሠራር በሚገባበት ጊዜ እንዲህ ያለ ግርታ ይፈጠራል፡፡  

ውሳኔው ጉዳት ያመጣል ወይ? ተቋማት፣ ይጎዳሉ ወይ? የአገር ጥቅም ይጠበቃል? የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በማንሳት የተያዩ አስተሳሰቦች ሊመጡ እንደሚችሉ ነገር ግን መታወቅ ያለበት ጉዳይ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች ስለተከፈተ ብቻ የሚመጣ ችግር ይኖራል ብሎ ማሰብ ትክልል አይደለም ይላሉ፡፡ 

ምክንያቱም የውጪ ተቋማቱ የሚፈልጓቸው ነገሮች ስላሉ የሚወጣው ዝርዝር ሁኔታ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅ መሆኑን ፣ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት አዋጭነትን፣ የአገሪቱ ፖሊሲዎችና የምትከተላቸውን አሠራሮች መዝነው እንደሚስማማቸው ካረጋገጡ በኋላ የሚወስኑት ጉዳይ በመሆኑ እንዲገቡ ስለተፈቀደ ብቻ ይገባሉ ማለት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት ብለዋል፡፡ 

‹‹የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የሚፈቅደው ፖሊሲ ውሳኔ ፈጠነ የሚሉ ወገኖች ምናልባት አዲስ እየተፈጠሩ ካሉ ባንኮች ጋር ሊያያዙት ይችላሉ፡፡ መንግሥት እስከ ዛሬ ድረስ ቀስ በቀስ የሚባል አካሄድ ሲከተል ቆይቷል፡፡ ከዚህ በኋላ መቆየት አለበት ብዬ አላስብም፤›› ብለዋል፡፡ 

አቶ አሰግድም ሆኑ አቶ አስፋው ጉዳዩ እንዲሁ በቀላል የሚታይ እንዳልሆነ ያምናሉ፡፡ ብዙ ሥራዎች የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ እስካሁን ሲሠራባቸው የነበሩ የተለያዩ የአገሪቱ ሕጎች እንዲቀየሩ የሚያስገድድ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የብሔራዊ ባንክ አደረጃጀትና አወቃቀር የሚለውጥ ጭምር በመሆኑ ሒደቱ ቀላል አይሆንም ባይ ናቸው፡፡ ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ በበኩላቸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውሳኔው እንዴት ይተገበራል የሚለውን ዝርዝር ጉዳይ ከውሳኔው ጋር ያለማስተላለፉ አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል ብለው የጠቀሱት ከዚሁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተያዘ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ወደፊት የሚኖረው አደረጃጀትን ወይም እንደገና ማቋቋም አለበት ለሚለው ጉዳይ ሁነኛ ውሳኔ በማስፈለጉ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ 

ብሔራዊ ባንክ አሁን ባለው አወቃቀሩ ከውጭ የሚገቡ ኩባንያዎችን ለማስተናገድ የሚችልበት አቋምና ብቃት ስለሚያሻው የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የሚፈቅደው የፖሊሲ ውሳኔ ዝርዝር መረጃዎች እንዳይወጡ መደረጉንና ይህም ጉዳዩ ገና ብዙ ሥራ እንደሚቀረው ያሳያል ብለዋል፡፡ እንዲሁም የባንኩን የቁጥጥር ሥርዓት በተመለከተ ከውጪ ከሚመጡት ተቋማት ጋር ጭምር መደራደር የሚያስፈልግ ስለሆነ መንግሥት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፍቀዱን አሳወቀ እንጂ እንዴት ይግቡ የሚለው ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ ያለመጠናቀቁን ያሳያል በማለት እኚሁ የኢኮኖሚ ባለሙያ ጠቁመዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን ውሳኔው ነፃ ገበያ የሚለው በተግባር የሚታይበት አሠራርን የሚፈጥር በመሆኑ የውጭ ኩባንያዎች ከመግባታቸው በፊት የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገበያ በነፃ ገበያ እንዲመራ መደረግ የሚኖርበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 

አቶ አሰግድም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ ገበያን ነፃ በማድረግ የጥቁር ገበያን እንደሚያዳክም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያሉ አካላትም ከጥቁር ገበያ ይወጣሉ ወይም በዘመነው መንገድ ለመራመድ ራሳቸውን አስተካክለው ሕጋዊ ግብይት ውስጥ ለመግባት እንዲችሉ ያረዳቸዋል ብለዋል። በዘርፉ ያለውን ሌብነትም ለማስቀረት የእነዚህ የፋይናንስ ተቋማት መግባት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው አቶ አሰገድ ያምናሉ፡፡ 

የአገር ውስጥ ባንኮች ጠንካራ ካፒታል ከፈጠሩና ራሳቸውን ከጊዜው ጋር ሊያራምድ ወደሚችል ውሳኔ ከደረሱ ምንም ተፅዕኖ እንደማይገጥማቸው፣ ሰፊ ገበያ ያለበት አገር በመሆኑ እንደማይቸገሩ ገልጸዋል። ነገር ግን የአገሪቱ ባንኮች በቂ ካፒታል ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ ይህ ካልሆነ ግን አስቸጋሪ ሁኔታ ሊገጥማቸው እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡ 

ከውጪ የሚመጡ ባንኮች በአብዛኛው በብሔራዊ ባንክ መተዳደርን ያልለመዱ መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ አሰግድ፣ የውጪ ባንኮች ይግቡ ሲባል ገለልተኛ የፋይናንስ ዘርፍ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ እንዲፈጠር ሊያደርግ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ 

ምናልባት አሁን ያሉት ተቆጣጣሪ አካላት በቦርድ ሊሰየሙ እንደሚችሉ፣ ይህ ከሆነ የቁጥጥር ሥርዓቱን እንደሚቀይረውና የተለመደውን የቁጥጥር አስተዳደር መዋቅር ሊቀይረው እንደሚችል ይህምይህ ዋናው ተግዳሮት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 

ሌላው ትልቅ ተግዳሮት ከሰው ኃይል ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ሠራተኞች  በዘርፉ ያላቸውን ልምድ ሊያሳድጉ እንደሚገባ መክረዋል። ፋይናንስ ዘርፉን የሚደግፍ  ራሱን የቻለ  ማሠልጠኛ አለመኖሩ የፈጠረው ክፍተት ቀላል ባለመሆኑ በዚህ ላይ ብዙ መሠራት ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የውጭ ባንኮች መግባት ተግዳሮት ሊሆን የሚችለው የውጭ ባንኮቹ የቻርተርድ ባንኪንግ ተማሪዎችን ነው የምንቀጥረው ሊሉ እንደሚችሉና በኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ የበቃ የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያ ውስን በመሆኑ ችግር ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ አሁን ባለው ደረጃ የኢትዮጵያ ባንኮች ከዓለም የግብይት ቋንቋ ሥርዓት ጋር ራሳቸውን፣ ሠራተኞቻቸውን እያበቁ ባለመሆኑ የውጭ ባንኮች ሲገቡ ሊፈተኑበት ይችለሉ ብለው እንደሚያምኑ አቶ አሰግድ ይገልጻሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የሥራ መሪዎችንም ሊመለከት ይችላል የሚል ሥጋትም አላቸው፡፡ ይህም ቢሆን ግን አሁን ባለው አቅም በውህደትና በጥምረት የአገሪቱን ባንኮች ብቁ ሊያደርጉ የሚችሉ ዕድሎች ስላሉ በዚህ መጠቀሙ ተመራጭ እንደሚሆን መክረዋል፡፡

ሌላው ሥጋት የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መፈቀዱ አገሪቱን ለውጭ ተፅዕኖ ያጋልጣል የሚለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን ያሳጣል ለሚለውን አስተያየት አቶ አሰግድ አይቀበሉትም። ‹‹ይህ እኮ በቀላል ቋንቋ ግብይት እንደማለት ነው፡፡ ሱቅ ተኬዶ ስኳር እንደ  መግዛት ነው፤›› የሚሉት አቶ አሰግድ፣ አሠራሩ ሁሉ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የተከተለ ስለሚሆን ተጎጂ ያደርገናል ብለው አያምኑም፡፡ 

‹‹እንደ ባንክ የሚጠበቅብን እነዚህ ባንኮች በትክክል የሚገቡበት ሞዳሊቲ ምንድነው የሚለውን  ነገር ጠንቅቆ ማወቅ ይገባል›› ያሉት አቶ አስፋው ዝርዝር ጉዳዮቹ ቢታወቁ ባንኮች ያንን መነሻ አድርገው ዝግጅታቸውን አካሄዳቸውን በምን መልኩ ማድረግ እንደሚገባቸው እንዲወስኑ ይረዳቸው እንደነበር አመልክተዋል፡፡ ተፅዕኖውን መመዘን የሚቻለውም ዝርዝር መረጃው ሲቀርብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ለመንግሥት ሚዲያዎች እንደገለጹት ‹‹የውጭ ባንኮችም ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው መሥራት የሚያስችል የሕግ ማርቀቅ ሥራና የመሳሰለው እየተሠራ ነው፡፡ በቅርቡ ዕውን ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፤›› ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች