- መንግሥት አሁንም እጁን ለሰላም እንደዘረጋ ነው። ነገር ግን በዚያኛው ወገን ከጦርነት በቀር ሌላ ፍላጎት የለም።
- ከዚህ አዙሪት በቀላሉ መውጣት ይቻላል ብለህ ታምናለህ?
- አዲሱ ዓመት ሰላም ይዞ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ።
- ዝም ብለህ ነው ተስፋ ያደረግከው።
- እንዴት?
- አዲስ ዓመት ከየት ያመጣዋል?
- ተስፋ ማድረግ ጥሩ ነው!
- ለሰላም ዝግጅት ሳይኖር ተስፋ ማድረግ ሰላም ያመጣል?
- በእኛ በኩል ዝግጁ ነን። እነሱ ግን እንደምታውቂው ናቸው።
- በእናንተ በኩል ዝግጁ ስለመሆናችሁ እርግጠኛ ነህ?
- በይፋ ደጋግመን እየገለጽን አይደል እንዴ?
- ታዲያ ምነው የሰላም ጥሪ ሊያቀርቡ የነበሩትን ከለከላችሁ?
- እነሱን ተያቸው… ሰላም ፈላጊዎች አይደሉም።
- እና ምንድናቸው?
- ተላላኪዎች!
- ኧረ …ተው?
- ሰላም ፈላጊዎች ቢሆኑማ ሁሉም ሲጠቃ ድምጻቸውን እንሰማ ነበር። ተልከው እንደሆነ ብቻ ሳይሆን ማን እንደላካቸውም እናውቃለን።
- ማን ይልካቸዋል?
- በጀት የሚመድቡላቸው ልዩ መልዕክተኞች ናቸው።
- ቢሆንስ ምን ችግር አለው?
- የመልዕክተኞቹ ዓለማ ሰላም አይደለም።
- ታዲያ ምንድነው?
- በሰላም ስም ፋታ ሊገዙለት ነው።
- ለማን?
- እየተቀጠቀጠ ላለለው አማጺ ወዳጃቸው ነዋ።
- ኧረ… ተው?
- እንደዚያ ባይሆንማ ማጥቃት ከመጀመራችን በፊት በተደጋጋሚ ያቀረብነውን ሰላም ጥሪ ጆሮ ይሰጡት ነበር። ልክ ማጥቃት ስንጀምርና ስንገሰግስ ግን ስለ ሰላም መጮህ ጀመሩ።
- እናተም ሆነ እነሱ የምትፈልጉት የሰላም ጥሪ አልመሰለኝም።
- ከሰላም ሌላ የምን ጥሪ እንፈልጋለን?
- የክተት ጥሪ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የአውሮፓ አገር ዲፕሎማት ጋር ዳግመኛ ስለተቀሰቀሰው የሰሜኑ ጦርነትና ሰላም እንዴት ሊመጣ እንደሚችል እየተወያዩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር የሰሜኑ ጦርነት በሰላማዊ ድርድር ይፈታል ብለን ተስፋ ባደረግንበት ወቅት ዳግም ጦርነት መቀስቀሱ አሳዝኖናል።
- እውነት ነው እኛም ችግሩን በሰላም ለመፍታት ተስፋ አድርገን ሳለ ወደ ጦርነት በመግባታችን በጣም አዝነናል።
- የአፍሪካ ኅብረትም ሆነ ሌሎች የአውሮፓ አደራዳሪዎች የጀመሩት የሰላም ጥረት ሊሳካ ጫፍ ላይ መድረሱን ነበር የሰማነው።
- ግን አልሆነም። ምክንያቱም ይህ ቡድን ያለ ጦርነት መኖር አይችልም።
- ስለዚህ ጦርነት ለመረዳት በጣም እየተቸገርን ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት?
- ያኛው ወገንም በተመሳሳይ መንግሥትን ይከሳል። እናንተም ያኛውን ወገን ትከሳላችሁ። በዚህ ሁኔታ ግራ ተጋብተናል።
- አምባሳደር ያኛው ወገን ግራ ማጋባት ልማዱ ነው። ከዚህ ወገን እውነትን መጠበቅ ነው።
- እነሱ መንግሥት ነው ጦርነቱን የጀመረው። ለሰላም ዝግጁ ነን ይላሉ።
- ችግሩ እናንተ ዘንድ ነው ያለው።
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ምክንያቱም እውነቱን ለማወቅ ሳይሆን ግራ ለመጋባት ነው የምትፈልጉት።
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- መንግሥት ጦርነቱን የሚጀምርበት ምክንያት የለም። ጦርነቱን በመጀመር የሚጠቀመው ነገር የለም።
- ግን እነሱም ጦርነቱን አልጀመርንም ይላሉ።
- የእነሱ ጦር በአንድ ቀን ወስጥ የቆቦ ከተማ ተቆጣጥሩ በቀጣዩ ቀን ደግሞ ወልዲያ ከተማ ዙሪያ እንዴት ሊደርስ ቻለ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ከቻልክ ጦርነቱን ማን እንደጀመረ መረዳት ትችላለህ።
- እንዴት?
- በዚያ አቅጣጫ ጦርነት ለመክፈት ዝግጅት ካላደረክ ጦርህን ካላሰለፍክ በዚያ ፍጥነት ወልዲያ ዙሪያ ለመድረስ ፈጽሞ የሚቻል አይደለም።
- እህ…
- ይህንን ለመቀበል የምትቸገሩ ከሆነ ደግሞ በቀላሉ መረዳት የምትችሉበትን ሌላ መንገድ መጠቆም ይቻላል።
- እባክዎ ይንገሩኝ ክቡር ሚኒስትር?
- በዚሁ ግንባር የማረኩትን አንድ የእኛ ጦር ሠራዊት አባልን በራሳቸው ሚዲያ ቃለመጠይቅ አድርገውለት የነገራቸውን ፈልገህ አድምጥ።
- እባክዎ ምን አንዳላቸው በአጭሩ ይንገሩኝ?
- የአሁኑ ጦርነት የጀመረው እርሱ በነበረበት የቆቦ ግንባር እንደሆነና የእነሱ ጦር ከጀርባ ቆርጦ በመግባት በአራት አቅጣጫ እንዳጠቃቸው ነግሯቸዋል።
- እሺ…?
- የእነሱ ጦር በጀርባ ቆርጦ መግባቱን ለበላይ አመራር አሳውቆ ድጋፍ ሰጪ ኃይል እንደሚላክለት ተነግሮት ምሽግ ውስጥ እንደቆየ ሁሉ ያስረዳል።
- እሺ…
- ነገር ግን ሁኔታው ፈጣን እንደነበርና ከበባውን ሰብሮ መውጣት እንዳልቻለ በዚህም ምክንያት ቆስሎ መያዙን ገልጾላቸዋል። ግን…
- ይቀጥሉ ክቡር ሚኒስትር…
- ይህንን ቃለ ምልልስ በይፋ አስተላልፈውም ጦርነቱን የጀመረው መንግሥት ነው እያሉ ማደናገራቸው የሚጠበቅ ነው።
- ክቡር ሚኒስትር አሁንም ለሰላም አልረፈደም።
- እኛም ሰላም ነው የምንፈልገው አምባሳደር። ጦርነት ተከተፍቶብንም ቢሆን ሰላም ነው የምንሻው።
- እነሱም ሰላም እንደሚፈልጉ ገልጸውልናል።
- እናንተስ አምባሳደር?