ሦስት ሳምንታት ያስቆጠረው ሦስተኛው ዙር የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሁንም ቀጥሏል፡፡ በቆቦ ግንባር የጀመረው ጦርነት ወደ ወልቃይትና ወደ ሰቆጣ ግንባር አቅጣጫውን አድርጎ ሲካሄድ ሰንብቷል፡፡ በሱዳን ድንበር አካባቢና በአፋር ክልል ጦርነቱ እንደነበር የተነገረ ሲሆን፣ የጦርነቱ ዋና ዓውደ ግንባር የሚባሉ ቦታዎች በትግራይ ክልል ሥር ያሉ መሬቶች እንደሆኑም ሲነገር ተሰምቷል፡፡
ከየጦር ግንባሩ የሚሰሙ መረጃዎች የአገር መከላከያ ሠራዊት የሚመራው ጥምር ጦር በርካታ ድሎችን በማስመዝገብ ላይ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በራያ ቆቦ ግንባር ጦርነቱ ማክሰኞ ጳጉሜን 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በረድ ማለቱ ቢነገርም፣ በሌሎች አካባቢዎች ግን ውጊያ መኖሩ ታውቋል፡፡
የወሎ ፋኖ የሚዲያ ኃላፊ ቴዎድሮስ አያሌው እንደተናገረው፣ በራያ ቆቦ ግንባር ውጊያው በረድ ብሏል፡፡ ‹‹ጠላት ከታጠቀው መሣሪያም ሆነ ካሠለፈው ኃይል በላይ ትልቁን ውጊያ እያካሄደ የሚገኘው በፕሮፓጋንዳ ነው፤›› ሲል የሚናገረው ቴዎድሮስ፣ እሱን መመከት እንደሚያስፈልግ አሳስቧል፡፡
ከዚህ ቀደም በሕዝቡና በመከላከያ ሠራዊት መካከል የተፈጠረውን መጠራጠር በመቅረፍ በከፍተኛ መናበብ ጭምር ጦሩ ውጊያውን እያካሄደ መሆኑን ቴዎድሮስ ይናገራል፡፡ ‹‹የጠላት የፕሮፓጋንዳ ጦር ተሰብሯል፡፡ በውጊያ ውስጥ ቦታ መያዝና መልቀቅ ያለ ነገር ነው፡፡ ጥምር ጦሩ በዚህ ቅንጅት መዋጋት ከቀጠለ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቀሌ ይገባል፤›› ሲልም ያክላል፡፡
በአፋር ግንባር በተለይም በሃራ ግንባር (አላውኃ) ያለውን ሁኔታ ያስረዱት የሃራ ከተማ ከንቲባ አቶ መሐመድ ሰኢድ፣ በአካባቢው ከመለስተኛ የከባድ መሣሪያ ድብደባ ውጪ ከባድ ውጊያ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡
‹‹ጥምር ጦሩ አስተማማኝ ቦታዎችን ይዞና በቂ ዝግጅት አድርጎ የጠላትን ኃይል ለመደምሰስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ ወደ ሕዝቡ መድፍ የተኮሱት ሕወሓቶች እንዳለፈው ጊዜ ነዋሪዎችን በማሸበር ከአካባቢው ሕዝቡን ለማሰደድ ቢያስቡም አልተሳካላቸውም፡፡ ከአምናው ትልቅ ትምህርት በመውሰድ ነዋሪዎች በእነሱ ወሬም ሆነ መድፍ እንዳይሸሹ አድርገናል፤›› ሲሉ ከንቲባ መሐመድ አስረድተዋል፡፡
የሃራ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች፣ ‹‹ለጥምር ጦሩ ስንቅ በማቀበል፣ መንገድ በመጠቆም፣ ገዥ መሬቶችን በማሳየት፣ ቁስለኛ በማውጣት፣ ተተኳሽ በማቀበልና በሌላም ነገር አስተማማኝ ደጀን በመሆኑ ጥምር ጦሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ግንባሩን በወኔና በጀግንነት እየጠበቀ ነው፤›› በማለት ከንቲባው የአካባቢውን የጦር አሠላለፍ አስረድተዋል፡፡
የወልቃይት ግንባርን የጦር አሠላለፍ ያስረዳው አቶ ፋኖ ኃይል በበኩሉ፣ ወልቃይት ሦስት ግንባሮች እንዳሉት ነው የተናገረው፡፡ ‹‹ከሱዳን ድንበር ጋር የሚዋሰነው የበረከት ግንባር አንዱ ሲሆን፣ በአዲረመጥ በኩል ያለው የቋራሪት ግንባር ሁለተኛው፣ እንዲሁም በደደቢት አቅጣጫ የሚገኘው አዲ ጎሹ ግንባር ሦስተኛው ነው፤›› በማለት ያስረዳል፡፡
በሱዳን አቅጣጫ የቀረው አንድ ምሽግ መሰበሩን የገለጸው አቶ ፋኖ ኃይል፣ በደደቢት በኩልም ጥምር ጦሩ ከቅዳሜ ጀምሮ ወሳኝ የሚባሉ ድሎችን ማስመዝገቡን ነው የተናገረው፡፡ በቋራሪት በኩልም ቢሆን የወገን ጦር ውጤታማ ጥቃቶችን ማድረጉን አቶ ነው ፋኖ ኃይል ያስረዳው፡፡
ከግንባር ከሚሰሙ መረጃዎች ጦርነቱ ጋብ ቢልም በተለያዩ አቅጣጫዎች መከላከያ መራሹ ጥምር ጦር ተስፋ ሰጪ ድሎችን አስመዝግቧል ወደሚለው ሚዛን የደፉ ናቸው፡፡
የግንባር መረጃ ምንጮች ጥምር ጦሩ አሁን ባለው ዝግጅትና አሠላለፍ ካጠቃ፣ የሕወሓት ኃይልን በጠባብ ቀለበት ውስጥ በማስገባት ወደ ማዕከላዊ ትግራይ እንዲሰበሰብ ያስገድደዋል የሚል ግምት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡
ይሁን እንጂ በተቃራኒው የተሠለፈው የሕወሓት መረጃ ምንጮች ጥምር ጦሩ በቀላሉ ወደመቀሌ መግባት እንደማይሳካለት የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ የሕወሓት ኃይል አመራሮች ከሰሞኑ በሚሰጧቸው ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ልጆችህን አታስጨርስ›› ከሚሉ መግለጫዎቻቸው፣ በጦርነቱ እናሸንፋለን የሚለው ተስፋቸው እንዳልተሟጠጠና ውጊያ ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው የሚጠቁሙ ይመስላሉ፡፡
ሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ባልተረጋጋ ስሜት ውስጥ ሆነው በደቡብ በዋግ፣ በፀለምት፣ በምዕራብ ትግራይ (ወልቃይት) አካባቢዎች በትግራይ ላይ ጥቃት ቢከፈትም ጥቃቱን በመመከት የመልሶ ማጥቃት መሰንዘር መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
የያዟቸውን መሬቶች ለመንጠቅና ትግራይን በተጠናከረ ከበባ ውስጥ ለመጣል ጥምር ጦሩ ጥቃት መክፈቱን የተናገሩት ቃል አቀባዩ፣ ‹‹ወልዲያንም ሆነ ሌላ አካባቢ ለመያዝ ሊያስቆመን የሚችል ኃይል አልነበረም፣ ማቆም በፈለግነው ቦታ ላይ ነው ያቆምነው፤›› ብለው ነበር፡፡
የጭፍራ ከተማ ከንቲባ አቶ ዘይኑ ዓሊ ግን ሕወሓቶች ‹‹ድል›› አደረግን የሚሉት ቅጥፈት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹አሳምረን እንተዋወቃለን፣ በቆቦ ጦርነቱን ሲጀምሩ በማግሥቱ ሰመራ ላይ ቡና እንጠጣለን ብለው አልመው ነበር፡፡ እንዳለፈው ጊዜ ድል በድል ነን ካሉ ዛሬ አዲስ አበባ በር ላይ በነበሩ፤›› ብለው፣ ‹‹የእነሱ ድል ከውጊያ ይልቅ በወሬ ነው፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡
በወሎ ራያና በአፋር ግንባር በአጠቃላይ በድምሩ እስከ 160 ሺሕ ጦር የሕወሓት ኃይል ማሠለፉን ‹‹አስተማማኝ መረጃ አለን›› ያሉት አቶ ዘይኑ፣ ሕፃን አዋቂ ሳይሉ ብዙ ሰው ወደ ጦርነት ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡ የሕወሓቶች ዋና ዓላማ የሥልጣን ዕድሜያቸውን ለማራዘም ጦርነት በየጊዜው መቀስቀስ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
‹‹የእነሱ ህልም አዲስ አበባን ወይም ራያን መያዝ ሳይሆን፣ በጎብዬና በአልውኃ ወደ ሰመራ በመውረድ የጂቡቲን መስመር መዝጋት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እየከሸፈ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ጥምር ጦሩን መደገፍና ማገዝ ነው ያለበት፤›› በማለት ነው የጭፍራ ከንቲባ አቶ ዘይኑ የአፋር ግንባር ጦርነት ገጽታን ያብራሩት፡፡
የግንባር መረጃዎች ጦርነቱ ጋብ አለ እንጂ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡ የጦርነቱ ሁኔታ በቀጣዮቹ ቀናት ምን ዓይነት ተለዋዋጭ ገጽታ ይኖረዋል የሚለው እያነጋገረ ይገኛል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ጦርነቱ እንዴት ይቋጫል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ግን፣ ‹‹ጦርነቱ ተመልሶ ባለበት ይቆማል›› የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ አሁን ምዕራባውያኑ ሁለቱ ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ ግፊት በማድረግ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ተንታኙ፣ በዚህ ሁኔታ ደግሞ ሁለቱ ኃይሎች ባሉበት ቆመው ግጭት ወደ ማቆም እንደሚገቡ ይገምታሉ፡፡
ጦርነቱ ባለበት ይቆማል የሚል ግምት ከሚያስቀምጡት በተቃራኒው ውጊያው የሕወሓት ኃይሎች እስኪሸነፉ (እጅ እስኪሰጡ) እንደሚቀጥል የሚተነብዩ በርካታ ናቸው፡፡ የጥምር ኃይሉን አሠላለፍና የጦርነቱን አካሄድ ከግንባር ሆነው ያስረዱት የመረጃ ምንጮች፣ መከላከያ የሚመራው ጥምር ኃይል ትዕዛዝ ከተሰጠው በሁሉም ቀጣናዎች ሕወሓትን የመደምሰስ አቅም እንዳለው ይናገራሉ፡፡
መንግሥት በዚህ ውጊያ እስከ መቀሌ የመገስገስ ወይም ሕወሓትን የመደምሰስ ዕቅድ ያለው መሆን አለመሆኑን እስካሁን በይፋ አልተናገረም፡፡ ይሁን እንጂ የዚህን ጦርነት ሒደት የሚከታተሉ አንዳንድ የፖለቲካ ሰዎች በየራሳቸው የጦርነቱ ግብ መሆን ይገባዋል ያሉትን ሐሳብ በመሰንዘር ላይ ናቸው፡፡
ከሁለተኛው ዙር ውጊያ በኋላ ሕወሓት ወደ ትግራይ ሲያፈገፍግ፣ ‹‹ሕዝቡን እንዳለ ጦር አድርጎታል›› ሲሉ የቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ከሰሞኑ ለአንድ የመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል፡፡ ሕወሓት በባህሪው ጦረኛ መሆኑንም ይናጋራሉ፡፡ ሕወሓት ራሱን ሲያዘጋጅ መቆየቱን የጠቀሱት የጦር መኮንኑ፣ ‹‹ወደ 12 ዕዝ፣ 36 ኮሮችና 109 ክፍለ ጦሮችን ገንብቷል፤›› ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
ሕወሓት ከዚህ ዝግጁቱና ከመሠረታዊ የጦረኝነት ባህሪው በመነሳት ወደ ጦርነት እንደሚገባ በሚገባ ያስታውቅ እንደነበር የተናገሩት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ፣ በድርድሩ መፍትሔ እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡
‹‹ሕወሓት ወደ ድርድር ለመግባት የሚያሳምንና የሚያስገድድ ምት ካልተመታ በስተቀር ወደ ሰላም ያመራል ማለት ዘበት ነው፤›› ሲሉም ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡
መንግሥት ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ ተደራዳሪ ኮሚቴ መሰየሙ ይታወሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሕወሓት ኃይሎች የሚያነሷቸው አጨቃጫቂ ጥያቄዎች በሕገ መንግሥታዊ መርሆዎች እንደሚፈቱ ቃል ገብቷል፡፡ ይህን ሁሉ ያለው መንግሥት መሠረት ልማት ለመጀመርና ወደ ድርድር ለመግባት አመቺ ይሆን ዘንድ የተኩስ አቁም ስምምነት አስቀድሞ ይፈረም የሚል ቅድመ ሁኔታ ብቻ አስቀምጧል፡፡ የሕወሓት አመራሮች ግን ይህን እንደማይፈልጉ በይፋ ሲናገሩ የተደመጠ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ለአሁኑ ጦርነት መቀስቀስ ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡
አሁን በመንግሥትም ሆነ በሕወሓት ወገን የሰላም አማራጭ ወይም የድርድር ዕድል መኖሩን ከመናገር ተቆጥበው አያውቁም፡፡ ይሁን እንጂ ውጊያው ሞቅ በረድ እያለ መቀጠሉ የሚታይ ሲሆን፣ አንዱ ሌላውን እንደሚደመስስ ሲያስጠነቅቅ ይታያል፡፡ ከዚህ በተረፈ የጦርነቱ ግብም ሆነ ግጭቱ ወዴት እንደሚያመራ አሁን እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር የሚቻል አይመስልም፡፡ ጦርነቱ ይሸጋገራል የሚለው አለመታወቁ ደግሞ፣ አገሪቱ በግጭት እሽክርክሪት ውስጥ ገብታ እንዳትቀር በብዙዎች ዘንድ ሥጋት ደቅኗል፡፡