ኢትዮጵያ በአፍሪካ አኅጉር ሁለተኛዋ ሰፊ የሕዝብ ብዛት ያላት አገር ነች። የሕዝብ ብዛት ዕድልም ዕዳ በሆነበት የዓለም የፖለቲካ ኢኮኖሚ ዓውድ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚሰጣት የኢኮኖሚ ደረጃ ከግርጌ ያልራቀ መሆኑን ጉዳዩን የሚከታተሉት ምሁራን በቁጥር አጣቅሰው ያስረዳሉ፡፡
መንግሥት የአገሪቱ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሮችን ለማስተካከል ይረዳል ያለውን አገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም እንዲሁም የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ ነድፎ ወደ ሥራ ቢገባም፣ ዓለም አቀፋዊ፣ አገራዊና ተፈጥሯዊ ክስተቶች የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛኑን ስለማዛባታቸው በጥናት ጭምር የተመላከተ ጉዳይ ነው፡፡
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን አባል ምሁራን የአገሪቱ ፖለቲካ ኢኮኖሚ፣ የመሬት ፖሊሲ፣ ግጭትና የድኅረ ግጭት ኢኮኖሚ ማገገሚያ መንገዶች እንዲሁም ብሔራዊ መግባባት ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን ባቀረቡበት የፖሊሲ ውይይት መድረክ ላይ፣ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ዘርፈ ብዙ መሆናቸው ተመላክቷል።
በአገሪቱ እየተባባሰ የመጣ የዋጋ ንረት፣ ከፍተኛ የሆነ የውጭ አገር ብድር ጫና፣ አሳሳቢ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የፊስካል ብልሹነት ጉዳዮች በተለይም ከግጭት አለመቆም ጋር ተያይዞ የአገሩቱን ፖለቲካ ኢኮኖሚ አስከፊ ገፅታ እንዲላበስ አድርጎታል ተብሏል፡፡
የኢኮኖሚ ማኅበሩ በወቅታዊ አገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ያካሄደውን የጥናት ግኝት መሠረት በማድረግ ባቀረበው ገለጻ እንደተመለከተው፣ በአገሪቱ ለተከሰተው ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ግሽበት ዓበይት ምክንያቶቹ አገሪቱ ተግባራዊ ከምታደርገው የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር፣ የገንዘብ አቅርቦትና የወለድ ምጣኔዎች፣ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ፣ ኤክስፖርት፣ የገቢ ዕቃዎችና ታሪፍና የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት ጉዳዮች ጋር የሚያያዙ ችግሮች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ማኅበር የምርምርና የፖሊሲ ጥናት ዳይሬክተር ደግዬ ጎሹ (ዶ/ር) በፖሊሲ ውይይት መድረኩ ላይ፣ የዋጋ ግሽበት በኢትዮጵያ እንዲባባስ ያደረጉት ገፊ ምክንያቶች ምንድናቸው? ምን ያህልስ ዋጋ እያስከፈሉ ይገኛሉ? በሚለው ጉዳይ ላይ ያተኮረ ጥናት ውጤት አቅርበዋል፡፡
በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ እንደተመላከተው፣ የዋጋ ግሽበት በኢትዮጵያ ባለ ሁለት አኃዝ ሆኖ ከተመዘገበ ዘለግ ያሉ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዓለም ላይ ከሚገኙ አገሮች በዋጋ ግሽበት ኢትዮጵያ የመጀመሪዎቹ አሥር ዝርዝር ውስጥ የምተገኝ አገር ስትሆን፣ በአፍሪካ ደግሞ ከሱዳንና ዚምባቡዌ በመቀጠል ሦስተኛዋ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የሚገኝባት አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ በኢትዮጵያ የተመዘገበው ግሽበት ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገሮችም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አማካኝ ከሚባለው የግሽበት መጠን አብላጫ ያለው መሆኑን አኃዞች ያስረዳሉ፡፡
በተለይም ከስምንት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ የኑሮ ዕድገት (ዌልፌር) ወይም ከድህነት ወለል የመላቀቅ ደረጃ እያሽቆለቆለ ይገኛል ብለዋል፡፡ የኑሮ ዕድገት መመዘኛ ከሆኑት ዝርዝሮች ውስጥ መሠረታዊ የማኅበራዊ ደኅንነት ወይም ሴፍቲኔት የሚለው ይገኝበታል፡፡ ከዚህ መመዘኛ አንፃር ብዙኃኑ ሕዝብ በድህነት አፋፍ ላይ ስለመገኘቱም ተጠቅሷል፡፡ በዚህም ሳቢያ የዋጋ ግሽበት የዜጎችን ከድህነት የመላቀቅ ዕድል እየሸረሸረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የዜጎች የኑሮ ዕድገት (የዌልፌር ሪጅም) ኢንዴክስ ሲታይ እ.ኤ.አ. ከ2016 በኋላ በወጥነት እያሽቆለቆለ መሆኑና የዋጋ ግሽበት ደግሞ ይህንን የኑሮ ዕድገት (ዌልፌር) በእጅጉ እንዲሸረሸር ዓይነተኛ ሚና መጫወቱ ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል የአገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ለግሽበቱ አባባሽ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ ምንም እኳን የየግብርና ኢኮኖሚ ዘርፍ ከአጠቃላይ የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የነበረው ድርሻ እ.ኤ.አ. ከ2008 በኋላ እየቀነሰ ቢሄድም፣ የአምራቹ ዘርፍ ግን እስካሁን ድረስ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በሚፈልገው ልክ አላደገም፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ያለውን ግሽበት እያባባሰ የሚገኘው ምክንያት በኢኮኖሚው ውስጥ የተለቀቀ የገንዘብ መጠን ማሻቀብ ነው፡፡ የገንዘብ ልቀት ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የሚነፃፀር ሲሆን ይህም የገበያውን ባህሪ መሠረት በማድረግ የሚተገበር ነው፡፡
በኢትዮጵያ የገንዘብ አቅርቦቱ ከኢኮኖሚ ዕድገቱ በጣም የፈጠነ ነው የሚሉት የኢኮኖሚ ምሁራን፣ ከፍተኛ የሆነው የገንዘብ አቅርቦት (ልቀት) ዕድገት በአገሪቱ የገንዘብ አለመረጋጋትን ያስከትላል ባይ ናቸው፡፡
የውጭ ተፅዕኖ በተለይም ከኤክስፖርትና የብር የመግዛት አቅም መውረድ (ዲቫሉዬሽ) ጋር በተገናኘ የተሟላ መረጃ ባይኖርም ከፍተኛ ዲቫሉዬሽን ከተደረገበት እኤአ 2018 ወዲህ ለተከታታይ ዓመታት በኤክስፖርቱ ላይ ያመጣው ውጤት አሉታዊ እንጂ አዎንታ አለመሆኑ የሚናገሩት ደግዬ (ዶ/ር)፣ የብር የመግዛት አቅም እንዲወርድ የተደረገበት ምክንያት ኤክስፖርትንና የኢንዱስትሪ ዘረፉን ተወዳዳሪነት ለማጎልበት ከሆነም የተፈለገው ውጤት እየተገኘ መሆኑ በደንብ መገምገም አለበት ሲሉ መክረዋል፡፡ በተጨባጭ የአንድ ፖሊሲ ትግበራ (ኢንተርቬሽን) ተግባራዊ ተደርጎ ውጤታማ ካልሆነና፣ ውጤቱም አሉታዊ ከሆነ ክለሳ (ሪቫይዝ) ሊደረግበት ይገባል ይላሉ፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ የብር የመግዛት አቅምን ማዳከም የሚሰጠው ጥቅም ከተወሰነ ጊዜ እንደማያልፍ መረጋገጡን በመግለጽ፣ ምርቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋል በሚል የተወሰደ ዕርምጃ ቢሆንም፣ ተመልሶ ሌላ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ምሁራኑ ጠቁመዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፣ የብር የመግዛት አቅምን መቀነስ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የሚሸረሽር ነው፡፡
አገሪቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ ዕድገት ከዲቫሉዬሽኑ ጋር ተያይዞ የተገኘ ውጤት እንደሆነ የሚናገሩ አካላት አሉ፡፡ ደግዬ (ዶ/ር) በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ በበጀት ዓመቱ የወርቅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ700 በመቶ፣ የቡና ዋጋም እንዲሁ ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት እንደሆነ ጠቅሰው ፣ የተገኘው 4.1 ቢሊዮን ዶላር ለ100 እና ከዚያ በላይ ለሚሆን ሕዝብ ምንም ማለት አይደለም (ኢምንት) ነው ብለዋል፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ ግኝት መጠን ምን አልባት ለኤርትራ ወይም ለጂቡቲ ትልቅ ሊሆን ይችላል የሚሉት የኢኮኖሚ ምሁሩ፣ መለኪያው በመቶኛ የሚገለጽ (ስታንዳርዳይዝ) ሊሆን ይገባል ባይ ናቸው፡፡ አክለውም የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ላለፉት አሥር ዓመታት ከኢኮኖሚ አቅም (ሳይዝ) ጋር ሲነፃፀር እያሽቆለቆለ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው በአብዛኛው የምግብ ውጤቶች (የግብርና ውጤቶች) ሲሆኑ፣ አገሪቱ ወደ ውጭ የምግብ ውጤቶችን በላከች ቁጥር ከአገር ውስጥ ገበያው ጋር ውድድር እየተደረገ እንደሚገኝ የሚያመላክት ስለመሆኑ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶችና አገልግሎቶች ሲታዩ አገሪቱ ዝቅተኛ የሆነ ኤክስፖርት አፈጻጸም ያላት ስድስተኛዋ የአፍሪካ አገር መሆኗን ያሳያሉ፡፡ ኤክስፖርት በአገሪቱ የውስጥ ገበያ ላይ የአቅርቦት እጥረት መፍጠሩ የተገለጸ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2011 ከነበረበት የ17 በመቶ ዕድገት በ2020 ወደ ሰባት በመቶ መውረዱን በፖሊሲ የውይይት መድረኩ በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ተመላክቷል፡፡
አገሪቱ ትርፍ ምርት ኖሯት ወደ ውጭ የምትልክ ቢሆን ችግር የለውም የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ ይህ ባልሆነበት ወደ ውጭ የሚላከው ምርት የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት እንጂ ተወዳዳሪ የሚያደርግ አይደለም ይላሉ፡፡ ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች ከምግብ ጋር የተያያዙ ስለሆኑ፣ የአገር ውስጥ የምግብ ዋጋን አባብሷል የሚሉት ደግዬ (ዶ/ር)፣ ይህ ደግሞ የሆነው የአገሪቱ የምንዛሪ ክምችት እጥረት የከፋ በመሆኑ ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡
መንግሥት በበጀት ዓመቱ ስድስት በመቶ ዕድገት ይኖራል ብሎ ቢገልፅም ፣ይህ ዕድገት ከየት ነው የሚመጣው ብሎ መጠየቅ ተገቢ እንደሆነም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል። ከአገልግሎት ዘርፉ ከሆነ አሁንም ለዜጎች የሚያመጣው ነገር የለም የሚሉት የኢኮኖሚ ተመራማሪዎች፣ የአገልግሎት ዘርፍ ላይ ጥገኛ መሆን ግሽበትን መቆጣጠር የማያስችል፣ ብዙኃኑ ኅብረተሰብ ከውጭ የሚመጣውን ተጠቃሚ (ዲማንድ ሳይድ) እየሆነ እንዲሄድ የሚያደርግ፣ የአቅርቦት ዘርፉን ችግር እያባባሰው የሚሄድ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ሲባል የአገልግሎት ዘርፉን ማቆም ማለት ሳይሆን፣ የአምራች ዘርፉን በከፍተኛ ፍጥነት እንዲያድግ ማድረግን እንደ ዋና አማራጭ መወሰድ እንደሚገባው በመግለጽ ነው፡፡
የኑሮ ውድነትን ያረጋጋሉ የተባሉ መፍትሔዎች ላይ መንግሥት ትኩረት ማድረግ እንዳለበት፣ ኃላፊነት የሚሰማው የፖሊሲ መፍትሔ ማመንጨት እንደሚገባው የኢኮኖሚ ምሁራኑ ይናገራሉ፡፡ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት የሚወስዳቸውን ዕርምጃዎች ማጤንና የሚሰጠውን ውጤት መለካት እንደሚገባውም እንዲሁ፡፡
በኢኮኖሚ ምሁራኑ የቀረበው ጥናት ላይ እንደቀረበው፣ በጠቅላለው እ.ኤ.አ. ከ2006 እስከ ተያዘው 2022 ዓመት ድረስ የአገሪቱ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ጉዞና ቅደም ተከተል በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች አንፃር ሽግግሩ ያልተሳካ የሚባል ጎራ የከተተው ሲሆን፣ ይህም ከኢኮኖሚ ሽግግር ይልቅ ፖለቲካዊ ለውጦች ዕድገታቸው የተፋጠነበት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በጠቅላላው ከዋጋ ግሽበት እንዲሁም ከአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ጋር በተያያዘ ያለው የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ተገቢ ካልሆኑ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች የሚመነጭ ውጤት እንደመሆኑ መጠን መንግሥት የምርት፣ የኢንዱስትሪ፣ የመሬት፣ የገንዘብ፣ የበጀትና ታክስ፣ የኢንቨስትመንት፣ የንግድ፣ የምንዛሪ፣ የአስተዳደር መዋቅር ፖሊሲ ላይ አሻጋሪ የሆኑ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚገባው በፖሊሲ ውይይት መድረኩ ላይ ያቀረበው ማጠቃላያ ምክረ ሐሳብ ነው፡፡