Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መልካም ምኞት!

እነሆ በአዲስ ዓመት መዳረሻ ላይ ሆነን የምንጓዘው ከቦሌ ወደ ካዛንቺስ ነው። ወያላው ራቅ ብሎ ቆሟል። “የት ነው?” እያለ እርስ በርሱ ተጠያይቆ የሚሳፈረው ተሳፋሪ ብዙ ነው። “የመረጃ እጥረት ብሎ ብሎ ታክሲ ተራ ገባ?” ብሎ ቢል አንድ ወጣት ተሳፋሪ፣ “ከላይ ከተጀመረ ወደ ታች መውረዱ መቼ ይቀራል?” ሲል አዋዝቶ አንድ ጎልማሳ መለሰለት። “ሰው ምን እንደሚታየው እንጃ ታክሲዋን ሲሳፈር የአሜሪካን አፈር የረገጠ ይመስለዋል እኮ…” ይለዋል አንድ ጎልማሳ አብሮት ለሚጓዘው ጓደኛው። “እንዴት?” ሲለው፣ “አትታዘብም እንዴ ታክሲ ውስጥ በነፃነት ሰው እንዴት እንደሚጨዋወት?” በአግራሞት እያየ ጠየቀው። “መብት ያለው የተጻፈው ሕግ ላይ ብቻ ነው ቢባልም ከታክሲ በቀር ሌላው ቦታ ብርቅ ሆኗል። ይልቅ የሚገርመኝ ሰው ታክሲ ሲሳፈር የሚያመጣው የማውራት ድፍረት ነው…” እየተባባሉ ቀጠሉ። አዳማጭ ጆሮዎች ተቀስረዋል። ሰው የሚጥለውን እየጣለ፣ የመረጠውንና የፈለገውን የመቀበል መብቱ ታክሲ ውስጥ ይመስላል። አላምጦ የመብላትን ያህል አጥብቆ መስማት ሲያስቸግረን አልታወቅ ብሎናል። ታክሲ ውስጥ የማይሰማ ጉድ የለም፡፡ ከማጀት እስከ አደባባይ ድረስ ብዙ ይተረካል፡፡ ከዚያም በላይ!

“በዚህ ኑሮ እንጀራና ነገር እያነቀን ስንባክን ጉድ አይባልም? ብክነትና ብክለት ምነው ጎዳናውን ሞላው?” ሲል እንሰማለን ከኋላ ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ጎልማሳ። “መባከን እኮ የሕይወት አንድ ምልክት ነው መባሉን እየሰማችሁ፣ ሌላ ዙር ጦርነት ተጀምሮ ስንባክን አይታያችሁም?” ትላለች ከጎኔ የተቀመጠች ባለ ጉዳይ መሳይ ወይዘሮ። ታክሲያችን መቆሚያ አጠገብ ካለው የኤሌክትሪክ ምሰሶ ሥር አንዱ በእጁ የያዘውን ሙዝ እየበላ ልጣጩን ወደ መንገዱ ይጥላል። “እግዚኦ!” ይላሉ አንዳንድ ተሳፋሪዎች። የሰውየው ድርጊት ያበሳጨው፣ “እኔ እኮ የሚገርመኝ የእሱ እየላጠ መብላት ሳይሆን፣ ልጣጩ ለሌሎች አደጋ ያመጣል ብሎ አለማሰቡ ነው…” ሲል፣ “በወያኔዎቹና በዚህ ሰው መካከል ምንም ልዩነት አለመኖሩን ከዚህ ድርጊት መገንዘብ ይቻላል…” እያለ አንዱ ጎልማሳ በንዴት ተናገረ። “የእነሱን ነገርማ ፈጣሪ ከላይ ሆኖ እያየ ስለሆነ በቅርቡ የምናየው እንደሚኖር ምንም ጥርጥር የለኝም…” ብላ አንዲት ሴት የጎልማሳውን ንዴት ሌሎችም ላይ አጋባች፡፡ ተጀመረ ማለት ነው!

አሥራ ሁለታችንም ተሳፋሪዎች ቦታችንን ይዘን ጉዞ ጀምረናል። ከብዙ ዓይነት የሕይወት አቅጣጫ፣ አስተሳሰብና እምነት ያለቀጠሮ ታክሲያችን ውስጥ መሰባሰባችን እየቆየ የሚደንቀን ብዙ ሳንሆን እንቀራለን? “ማን ወዴት ይሆን የሚገሰግሰው?” እንዲሉ ጉዞ ሰበብ ሆኖ ሰው ከሰው እንዲህ ያለ ቀጠሮ ይገናኛል። አስተሳሰብና አመለካከትም እንዲሁ ቢገናኝ ምናለበት? ታዲያ የቀናው እስከ ጫፍ ይጓዛል። ማለትም ይፋቀራል፣ ይዛመዳል፣ ይወልዳል፣ ይከብዳል። ያላደለው ደግሞ በሰላም መለያየት ሳይቀናው ተጋጭቶና ተጣልቶ በገላጋይ ይሸኛል። ይህ ነው መንገድ ማለት። ንክኪ የሚባል የሕይወት ጥበብ እዚህ ውስጥ ነው ፈትሉ። የሚያውቀው ሲያውቀው ያላወቀው ሲያልፈው የሕይወት ፍሰትን የሚያስቆመው የለም። ትናንትና ዛሬን እንዳደረሰ ዛሬ ነገን ሊያመጣ ከንፎ ያከንፈናል፡፡ የታወቀ ነው!

ሽበታሙ ሾፌራችን የመቀመጫ ቀበቷቸውን አጠባብቀው ሞተሩን አስነስተዋል። እሳቸውም የወያላውን ብቅ ማለት እንደ ሎተሪ ዕጣ በጉጉት የሚጠባበቁ መስለዋል። ወያላው በበኩሉ የቆመበት አልታይ የደረሰበት አልታወቅ ያለ ይመስላል። “የት ሄደ ደግሞ?” ይላሉ ሾፌሩ በለሆሳስ። ጥበቃችን ግን ሊከስትልን አልቻለም። “ወያላችን ቀረ ብለን እንዝፈን እንዴ? መቼም ሁሉም ነገር በዘፈን ካልታጀበ እንደማይሆንላቸው የማስታወቂያ ድርጅቶች እንሁን እንዴ?›› አለ ቀጠን የሚል ወጣት። አጠገቡ የተቀመጠ እሱን መሳይ፣ “ተው… ተው… ይቅርብን፡፡ በዚህ ጊዜ ዘፈን ሳይሆን ፀሎት ነው የሚያስፈልገው፡፡ አገራችን ጦርነት ተከፍቶባት ዘፈን ደግ አይደለም…” ብሎ ሲመልስለት፣ “አይዞህ ኢትዮጵያ ጠላቶቿ የፈለጉትን ያህል ቢሞክሩ አሳፍራ ስትመልስ እንጂ እጅ ስትሰጥ አትታወቅም…” ብሎ ከመሀል አንዱ ወሬውን ተቀላቀለ፡፡ የአገር ጉዳይ በአዲስ ዓመት መግቢያ ላይ ቢያሳስብም፣ ብዙዎች ግን አገራቸው አሸናፊ እንደሆነች ለአፍታ እንኳ የሚጠራጠሩ አይመስሉም፡፡ እንዲያ ነው!

ሽማግሌው ሾፌራችን እስከ ኋላኛው መቀመጫ ድረስ በሚሰማ ሳቃቸውና ድምፃቸው ጋቢና ከተቀመጡት ተሳፈሪዎች ጋር ሌላ ጨዋታ ጀመሩ። “አቤት ፀሐይ እንዴት እንደናፈቀችኝ… በዚህ ሽምግልና ላይ ቅዝቃዜ ሲደረብበት ደግ አይደለም፡፡ ወጣቶችማ ሙቀትም ይሁን ብርድ ለእናንተ ምንም ስሜት አይሰጣችሁም…” እያሉ ይስቃሉ ለራሳቸው። ድንገት ኮስተር ብለው በመሀል አንዱን ጎልማሳ መሳይ አስተዋሉት። “አንተ አገርህን እንዲህ የምትወዳት ከሆነ ከተማ ውስጥ ምን ትሠራለህ?” አሉት ልክ እንደሚያውቁት ሁሉ። አልፎ አልፎ መንገዱ ሲለቀቅ አንደኛ ማርሽ በጭንቅ ለማስገባት ካልሆነ በቀር ፊታቸውን ከሁለቱ ተሳፋሪዎች ላይ አይመልሱትም። “ከዚህ በፊት አለመዝመቴን እንዴት አወቁ?” ሲላቸው፣ “ወይ ጉድ ይህች መቼ ትጠፋናለች? እኔ ከቦቴ ሾፌርነቴ በፊት ወታደር ነበርኩ፡፡ ኦጋዴን፣ ኤርትራ፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ብቻ ምን አለፋህ ያረገጥኩት የኢትዮጵያ መሬት የለም፡፡ ስለዚህ የጦር ሰውና ሲቪል መለየት የሚያቅተኝ መሰለህ?” ብለው አሁንም ለብቻቸው ሳቁ። ቆየት ብለው ድምፃቸውን ቀነስ አድርገው በሹክሹክታ አንድ ወሬ አውርተው ሳቅ በሳቅ አደረጓቸው። እኛም ሳቅ አምሮን ባልሰማነው ጉዳይ ፈገግ አልን። ወይ የስበት ሕግ!

ሳናስበው መድረሻችን እየተቃረበ መጥቷል። ድካም የዘራብንን የዑራኤል ደጃፍ መቃረቢያ ትራፊክ መብራት ተንኳተን ካለፍነው በኋላ፣ ቅዝቃዜውን ክፉኛ የሰውን ምላስ ሸብቦት ስለነበር ጨዋታችን ቀዘቀዘ። ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ስንመጣ ታዲያ ቀልደኛው ሾፌራችን ጆሮ ኮርኳሪ የመደነቅ ፉጨት አፏጭተው፣ “ሰሞኑን በተለያዩ ግንባሮች ወረራ የፈጸመብን ወንበዴ አይቀጡ እየተቀጣ እንደሆነ ታውቁታላችሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ከእኛ ብቻ ሳይሆን ከምስኪኑ የትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወርድ ካልተደረገ ነው የሚደንቀኝ…” አሉ ፉጨታቸውን እየቀጠሉ። ሌላው ጣልቃ ገብቶ፣ “ሐሳብዎት በጣም የሚደገፍ ነው፡፡ እኔም ይህ ሥጋት ውስጤ አለ፡፡ በጀግናው ሕዝባችን በሚገባ እንደሚደቆሱ ባልጠራጠርም የምፈራው ግን አልቆላቸዋል ተብለው አፈር ልሰው እንደገና ተነሱ የሚባለውን ነው፡፡ ለማንኛውም የአሁኑ አያያዛችን ካለፈው ስህተት የተማረ ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ ግን እንደ ተለመደው ከሆነ ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም…” አለ፡፡ አስተያየቱ የብዙዎችን ቀልብ በመሳቡ ነው መሰል አንገታቸውን በመስማማት ነቀነቁለት፡፡ ተደማጭ ሆነ ማለት ነው!

ታክሲያችን ካዛንቺስ ስትደርስ አራቱን መንገዶች የሚያገናኘው መስቀለኛ ተጨናንቆ ነበር፡፡ የሚያስተናብር የትራፊክ ፖሊስ ባለመኖሩ የትራፊክ ፍሰቱ ተስተጓጉሏል፡፡ ለሰከንድ መታገስ ያቃታቸው እየዘለሉ ለመቅደም ሲጣደፉ መቅሰፍት ይዘው የመጡ የዲያብሎስ መልዕክተኛ ይመስላሉ፡፡ ሾፌራችን አንገታቸውን አውጥተው፣ “ኧረ ጎበዝ እየተሳሰብን…” ቢሉ ማን ሰምቶ፡፡ ጭራሽ አንዱ እየሳቀ፣ “አባት በመጦሪያዎ ጊዜ እዚህ መገኘት አልነበረብዎትም…” እያለ ሲያላግጥ የሰማችው ያቺ ሴት መስኮቱን ከፍታ፣ “አንተ ደግሞ የእሳቸውን ግማሽ እንኳ አትኖራትም…” አለችው፡፡ ጎዳና ላይ ድንገት የሚቀሰቀሱ ግጭቶች ወደ አልተፈለገ ችግር ስለሚያመሩ ተረባርበን መስኮቱን ዘጋንባት፡፡ ተናዳ ስለነበር፣ “የሰው መብት ሲገፈፍ እያያችሁ እንዴት ዝም ትላላችሁ?” ስትለን ከማዳመጥ ውጭ ምንም አማራጭ አልነበረንም፡፡ ድንገት ሁለት ትራፊክ ፖሊሶች ደርሰው ሥርዓት ማስያዝ ሲጀምሩ ታክሲያችን መስቀለኛውን ተሻግራ ወደ መጨረሻዋ ተፈተለከች፡፡ መጨረሻ የሚባል አለ እንዴ!

እስካሁን ምንም ያልተነፈሰው ወያላ ሊያሰናብተን ሲንጠራራ፣ ምንም ያልተናገሩ አንዲት እናት፣ “ደረስን እንዴ?” አሉ፡፡ ወያላው፣ ”አዎ ደረስን መጨረሻ…” ሲለን፣ “እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሰን፡፡ ወጥቶ መግባት አጠራጣሪ በሆነበት በዚህ ጊዜ ከዓመት ወደ ዓመት ተሸጋግሮ መድረስን የመሰለ ነገር የለም፡፡ በከንቱ በነገር ከመለባለብ በሰላም አድርሰህ በሰላም መልሰን ማለቱ ይበልጣል…” እያሉ ሲናገሩ፣ ለካ ይኼም አልታሰበ ኖሮ ሁላችንም በመገረም እያየናቸው ወረድን፡፡ የባጥ የቆጡን ስንቀባጥር የደኅንነታችን ጉዳይ ለምን ይረሳን ይሆን? የባጥ የቆጡን አንስተን ስንጥል መሠረታዊውን ጉዳይ ባንረሳ፡፡ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ላይ ሆነን አገራችን ከገባችበት ጦርነት ውስጥ በፍጥነት ወጥታ ሰላም እንዲሰፍን፣ ሁላችንም ለአገራችን መልካሙን በመመኘት ተሰነባበትን፡፡ መልካም አዲስ ዓመት! መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት