መሰንበቻውን የተካሄደውን የኬንያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ምክትል ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ማሸነፋቸው ተከትሎ ተቀናቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋ የምርጫው ሒደት ተጭበርብሯል በማለት ያቀረቡትን ክስ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ሰባት አባላት የተሰየሙበት የፍርድ አካል ካደረገው ምርመራ በኋላ ፕሬዚዳንታዊው ምርጫ እንከን የለበትም በማለት ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ውሳኔውን ያስተላለፉት ሊቀመንበሯ ማርታ ኩሜ ናቸው፡፡ ‹‹የተመራጩ ፕሬዚዳንት [ዊልያም ሩቶ] ምርጫ ትክክለኛ እንደሆነ እናውጃለን፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የሩቶን የነሐሴ 9 ቀን ምርጫን አሸናፊነት ውጤትን ይፋ ያደረጉት የነፃ ምርጫ ኮሚሽን ኃላፊ ዋፉላ ቼቡካቲ ሲሆኑ፣ ሩቶ 50.4 በመቶ ድምፅ ማሸነፋቸውን ኦዲንጋ ደግሞ 48.8 በመቶ ድምፅ ማግኘታቸውን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው፣ ውጤቱ ከመገለጹ ጥቂት ቀደም ብሎ በተፈጠረ አስገራሚ መለያየት ከሰባቱ ኮሚሽነሮች አራቱ የምርጫውን ውጤት ውድቅ አድርገው ነበር፡፡
ነገር ግን ሊቀመንበሯ ኮሜ፣ በማረጋገጡ ሒደት አራቱ ኮሚሽነሮች ምርጫው ችግር እንደገጠመው የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ አላሳዩም ብለዋል፡፡
አያያዘውም በኦዲንጋ ወገን በኩል የቀረበው የምርጫ ኮሚሽኑ ሰርቨር ስለመጠለፉና ውጤቶቹ እንደተጣሱ የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ አለማግኘቱም ተናግረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የመጨረሻውን ውሳኔ ከትናንት በስቲያ ከመስጠቱ በፊት እስከ ነሐሴ 27 ቀን ድረስ የሁለቱን ተፎካካሪ ወገኖች ክርክር አዳምጧል፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ውሳኔው ይፋ ከመደረጉ በፊት ርዕሰ ከተማዋን ጨምሮ በአገሪቱ ከተሞች የፀጥታ ኃይሎች በተጠንቀቅ ቆመው ነበር፡፡ የዳኞች መማክርት ውሳኔያቸውን በሚገልጹበት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕንፃ መዳረሻ መንገዶች ሁሉ ለትራፊክ ዝግ ሆነው ነበር፡፡
ውሳኔው በመጪው ቀናት የ55 ዓመቱ ሩቶ የኬንያ አምስተኛ ፕሬዚዳንት ሆነው ቃለ መሐላ እንዲፈጽሙ መንገድ ይከፍታል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2013 እና 2017 ከተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ምክትል ሆነው የተመረጡት ሩቶ፣ በ2018 በፕሬዚዳንቱና በቀድሞው ተቀናቃኛቸው ኦዲንጋ መካከል ያልተጠበቀ ዕርቀ ሰላም ከወረደ በኋላ መፋጠጣቸው አልቀረም፡፡
በአሁኑ ምርጫ ኡሁሩ ከምክትላቸው ይልቅ ድጋፋቸውን የሰጡት ለኦዲንጋ ሲሆን፣ ምርጫችሁ በኦዲንጋ ላይ ይረፍ ማለታቸውም ተዘግቧል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ ሚስተር ሩቶ ለፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው የወዳጅነት እጃቸውን እንደሚዘረጉ ገልጸው የፍትሕ አካላትና ምርጫ ኮሚሽኑ ‹‹የሕዝቡን ፍላጎት›› በማንፀባረቃቸው አወድሰዋል፡፡
‹‹እኛ ጠላቶች አይደለንም፣ ኬንያውያን ነን፡፡ ኬንያን አገር ለማድረግ ሁሉም ሰው የሚኮራባት አገር ለማድረግ እንሥራ›› ሲሉም ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በድምፅ በተቀረፀ መልዕክታቸው ኡሁሩ ኬንያታ በጠቅላላው ምርጫ ለተመረጡት ‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ›› ቢሉም ሚስተር ሩቶን ግን በስም አልጠቀሱም፡፡
ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ከዳኝነት አካላት ጋር የተጋጩት ፕሬዚዳንቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔን በተመለከተ ቅሬታቸውን ቢገልጹም ለውሳኔው እንደሚገዙ ግን አልሸሸጉም፡፡ ‹‹ሥልጣንን ማስረከቡ በሒደት ላይ ነው፡፡ ለቀጣዩ አስተዳደር ሰላማዊ ሽግግር እንዲሆን እሻለሁ፤›› ብለዋል፡፡
በአምስት ተከታታይ ምርጫዎች የተሸነፉት ሚስተር ኦዲንጋ፣ በ77 ዓመት ዕድሜያቸው እንደገና ለመወዳደር ወይም በተቃዋሚ ፖለቲካ ጎራ ውስጥ ንቁ ሆነው እንደሚቀጥሉ ለማየት አስቸጋሪ ነው ይላል የቢቢሲ ዘገባ፡፡
በየምርጫ ዘመኑ ውዝግብ የማያጣው የኬንያ ጠቅላላ ምርጫ ደም እስከማፋሰስ ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ እንደ ዘንድሮው ሁሉ ከአምስት ዓመት በፊት በነበረው ምርጫ ተመሳሳይ ውዝግብ ተከስቶ ውጤት ያጡት ራይላ ኦዲንጋ አቤቱታቸውን ለኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማስገባታቸው ይታወሳል።
በዚያም ወቅት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያሁኑ ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን የአሸናፊነት ውጤትን ውድቅ አድርጎ ምርጫውን ማስደገሙና በድጋሚው ምርጫም ኬንያታ አሸንፈው ለሁለተኛ ዙር ሲመሩ ቆይተዋል።
ምክትላቸው እርሳቸውን እንዳይተኩ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉትን ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ኬንያታን በተመለከተ ግንኙነታቸው እንደሻከረ የሚቀጥል ከሆነ ትኩረት መሳቡ አይቀርም፡፡
እንደ ዘገባው፣ ከሁሉም በላይ ኬንያ ከዚህ ቀደም ያየችው ሁከት ሳይከሰት የምርጫ አለመግባባቶችን መፍታት እንደምትችል አሳይታለች፡፡
በተያያዘም የአፍሪካ ኅብረት ለዊልያም ሩቶ ለድል አድራጊነታቸው እንዲሁም የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለማክበር ለገቡት ቃል ‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ›› ብሏል፡፡
በተመሳሳይም የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅትም (ኢጋድ) የምርጫው ወቅት መጠናቀቁ ለሁሉም ኬንያውያንና ለቀጣናው ሕዝቦች ድል ነው ብሏል፡፡