የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ቡድኑን (ዋሊያዎቹ) ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ኮንትራት ለማራዘም መወሰኑ ተገለጸ፡፡ አሠልጣኙ የሩዋንዳን ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ጨዋታ አሸንፈው፣ በአልጀሪያ አስተናጋጅነት ለሚካሔደው የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) ማለፋቸውን ካረጋገጡ አገሮች አንዱ ሆነዋል፡፡
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚሠለጥነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ በሚቀጥለው ዓመት አይቮሪኮስት ለምታስተናግደው የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ ማጣሪያ በግብፅ፣ ማላዊና ጊኒ ምድብ፣ ሦስት ነጥብ በመያዝ የደረጃ ሰንጠረዥን እየመራ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ ማጣሪያው ሁለተኛ ጨዋታ የግብፅ አቻውን ያሸነፈበት መንገድ፣ በእግር ኳሱ መድረክ ግብፃውያን በኢትዮጵያውያን ላይ ከሦስት አሠርታት በላይ ይዘውት የቆዩትን የበላይነት ያስረሳ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን ተክተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ በመሆን ኃላፊነቱን የተረከቡት አሠልጣኝ ውበቱ፣ ኮንትራቸው የሚያበቃው መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ነበር፡፡ አሠልጣኙ ይህንኑ ተከትሎ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ኮንትራታቸውን እንዲያድስላቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም፡፡
ፌዴሬሽኑ የአሠልጣኙን ኮንትራት በተመለከተ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ይፋ ባያደርግም፣ ነገር ግን አሠልጣኝ ውበቱ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ሆነው እንደሚቀጥሉ ከስምምነት መድረሳቸው ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡
አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ቀድሞ በነበራቸው ኮንትራት ሲከፈላቸው የነበረው የተጣራ 125,000 ብር፣ በአዲሱ ውል የሚሻሻል ከመሆኑ ባሻገር፣ አሠልጣኙ የአሠልጣኞችን ስብስብ ጨምሮ ሌሎችም በቅድመ ሁኔታነት ያቀረቧቸው ጥያቄዎች እንደሚሟሉላቸው ከስምምነት መድረሳቸውም ተነግሯል፡፡
አሠልጣኝ ውበቱ ከፌዴሬሽኑ ጋር ያላቸውን ውል በተመለከተ ከሰጧቸው አስተያየቶች፣ የብሔራዊ ቡድኑን ኃላፊነት እንደያዙ የሚቀጥሉበት ዕድል እንዳለ፣ ይሁንና ሕጋዊ ውሉ ገና ባይፈረምም ከፌዴሬሽኑ ኃላፊዎችም ጋር ግን መግባባት ላይ ስለመድረሳቸው ነው የተናገሩት፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ለሁለተኛ ጊዜ በፕሬዚዳንትነት ለመምራት በቅርቡ የተመረጡት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው፣ በኃላፊነታቸው የሚቀጥሉ ከሆነ አሠልጣኝ ውበቱ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሆነው የመቀጠላቸው ጉዳይ ለድርድር እንደማይቀርብ መግለጻቸው መዘገባችን አይዘነጋም፡፡