ከአሥር ወራት በፊት በቁጥጥር ሥር የዋሉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ኮማንደር ኢዶሳ ጎሹና በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. የታሰሩት የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ምሥጋናው ኢንጅፋታን ጨምሮ፣ በእስር ላይ የነበሩ የክልሉ የፀጥታ አመራሮች ከእስር ተፈቱ፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተፈቱት የፀጥታ አመራሮቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በክልሉ ከሚንቀሳቀሰው የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ጥርጣሬ ነበር፡፡ ይሁንና አሥር ወራት የታሰሩት ኮማንደር ኢዶሳም ሆኑ ከእስር የተለቀቁት ሌሎቹ ሰባት ግለሰቦች ክስ እንዳልተመሠረተባቸው ተገልጿል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ሀሩን ዑመር ስምንቱ ግለሰቦች መፈታታቸውን ለሪፖርተር አረጋግጠው፣ ‹‹እንዲፈቱ ብለን ጠይቀን በዚያ መሠረት ነው የተፈቱት፤›› ብለዋል፡፡ ግለሰቦቹ የተፈቱበትን ምክንያትና ሁኔታ ላይ ግን ዝርዝር መረጃ መስጠት እንደማይችሉ አስታውቀዋል፡፡
በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም. ከሥልጣናቸው ተነስተው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ኮማንደር ኢዶሳን ሪፖርተር አነጋግሮ ከእስር መፈታታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በልዩ ኃይል ውስጥ አመራር የነበሩት ዋና ኤንስፔክተር ሥዩም ገመዳና ዋና ኤንስፔክተር ጎበና ነመራ በእስር ቆይተው የተፈቱ ሌሎች የፀጥታ አመራሮች ናቸው፡፡
ከፀጥታ አመራሮቹ በተጨማሪ በእስር ላይ የነበሩት የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አማኑ ደሬሳ፣ የክልሉ ግብርና ኮሌጅ ምክትል ዲን አቶ ንጋቱ ቲልቱ፣ እንዲሁም ከዚህ ቀደም የክልሉ ከፍተኛ አመራር የነበሩና በግብርና ቢሮ ውስጥ ሲሠሩ የነበሩት መኮንን ጎላሳ (ዶ/ር) ከእስር ተፈተዋል፡፡
የፀጥታ አመራሮቹን ጨምሮ ስምንቱ ግለሰቦች ከእስር የተለቀቁት ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው፡፡ የፖሊስ ኮሚሽነሩ ሀሩን ግለሰቦቹ የተፈቱበትን ሁኔታ አስመልክቶ፣ ‹‹[ግለሰቦቹ የተፈቱት] ክስን በማቋረጥ ነው? በይቅርታ ነው? ወይስ በሌላ የሚለውን ከእነሱ ጋር እንነጋገራለን፤›› ብለዋል፡፡፡
ከተፈቱት ፀጥታ አመራሮች ውስጥ የሆኑና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብ በበኩላቸው፣ ከመፈታታቸው አንድ ቀን አስቀድሞ ፍርድ ቤት ቀርበው እንደነበርና ፍርድ ቤቱ በሰው ወይም በአራት ሺሕ ብር ዋስትና እንዲወጡ እንደፈደቀላቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ስምንቱ ግለሰቦች በአሶሳ ዞን ማረሚያ ቤት ታስረው እንደነበር የተናገሩት ግለሰቡ፣ በኮማንደር ኢዶሳ ጎሹ፣ በኮማንደር ምሥጋናው ኢንጅፋታና በዋና ኤንስፔክተር ጎበና ነመራ ስም በተከፈቱ ሦስት መዝገቦች ቀነ ቀጠሮ እየተጠየቀባቸው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ከፍተኛ የፀጥታ አመራር የነበሩት ግለሰቡ፣ ‹‹ከጉሕዴን ታጣቂዎች ጋር አብረሃል በሚል ምክንያት ነው መታሰሬ የተገለጸው፡፡ በምንድነው ዕገዛ ያደረገው የሚለው ዝርዝር ጉዳይ ላይ ሲገባ ግን ምንም ማስረዳት አልቻሉም፡፡ እስክንፈታ ድረስ ያቀረቡብኝ ማስረጃ የለም፤›› ሲሉ ስለተጠረጠሩበት ጉዳይ አስረድተዋል፡፡
እንደ ግለሰቡ ገለጻ ሰባቱ ግለሰቦች በሰኔ ወር የታሰሩት በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም. በካማሺ ዞን ዕርቅ ተፈጽሞ ወደ ከተማ የገቡ የጉሕዴን ታጣቂዎች፣ ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በዞኑ ምዥጋ ወረዳ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው፡፡
በካማሺ ዞን በተለይ በያሶ ወረዳ ጫካ ገብተው ከመንግሥት ጋር ሲዋጉ የነበሩት የጉሕዴን ታጣቂዎች ወደ ከተማ የገቡት፣ መንግሥትና ታጣቂዎች መጋቢት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ያደረጉትን ባህላዊና ሃይማኖታዊ የዕርቅ ሥነ ሥርዓት ተከትሎ ነው፡፡ ‹‹ከዕርቁ መፈጸም በኋላ ትጥቅ ይፈታሉ›› ተብለው ከእነ ትጥቃቸው ወደ ከተማ የገቡት ታጣቂዎቹ፣ ወደ ከተማ ከገቡ በኋላ ትጥቅ ለመፍታት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ኮሚሽነር ሀሩን ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር ተናግረው ነበር፡፡
ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በታጣቂዎቹና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብደኑ ጀርሞሳ፣ አንድ የአካባቢው ባለሀብትና ልጃቸው፣ እንዲሁም 16 የጉሕዴን ታጣቂዎች መገደላቸው ተገልጿል፡፡
ከዚህ ክስተት በኋላ የታሰሩት ሰባቱ ግለሰቦች የጊዜ ቀጠሮ እየተጠየቀባቸው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እንደነበር የገለጹት ግለሰቡ፣ በኮማንደር ምሥጋናው ኢንጅፋታ ስም በተከፈተው መዝገብ የተካተቱ አራት ሰዎች ዓርብ ነሐሴ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀጠሮ እንደነበራቸው ተናግረዋል፡፡ በዕለቱም ፍርድ ቤቱ ዋስትና እንደፈቀደ አስረድተዋል፡፡
በቀሪዎቹ ሁለት መዝገቦች የተካተቱ ሰዎች በዕለቱ ቀጠሮ ባይኖራቸውም፣ ፍርድ ቤት ቀርበው ዋስትና እንደፈቀደላቸው ገልጸዋል፡፡
ስምንቱም ግለሰቦች የተፈቱት በዋስ በመሆኑ ሒደቱ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል ብለው እንደማያምኑ የገለጹት ግለሰቡ፣ ይሁንና ተለዋጭ ቀጠሮ እንዳልተሰጠ አስረድተዋል፡፡