Wednesday, November 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ምንም ዓይነት ግብይት እንዳይደረግ ከለከለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የውጭ ዜጎች መያዝ የሚፈቀድላቸው የገንዘብ መጠን ከእጥፍ በላይ ከፍ ተደርጓል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአገሪቱ ድንበር ውስጥ መያዝ የሚቻለውን የውጭ ምንዛሪ መጠን የሚደነግገውን መመርያ በማሻሻል፣ በአገሪቱ ድንበር ውስጥ በውጭ ምንዛሪ ምንም ዓይነት ግብይት እንዳይደረግ ክልከላ አደረገ፡፡

በብሔራዊ ባንክ ‹‹ልዩ ፈቃድ›› ካልሆነ በስተቀር የውጭ ምንዛሪ ይዞ መገኘት የተከለከለ ሲሆን፣ በስጦታና በረድዔት መልክ ለሦስተኛ ወገን በጥሬ ገንዘብ ማስተላለፍም ተከልክሏል፡፡ ከስድስት ዓመታት በፊት በወጣው ነባሩ መመርያ ውስጥ እነዚህ ክልከላዎች አልነበሩም፡፡ በአዲሱ መመርያ ‹‹በልዩ ፈቃድ›› የተባለው ምናልባት ለአስጎብኚ ድርጅቶች፣ ለሆቴሎችና ለቀረጥ ነፃ መደብሮች ይሆናል የሚል ግምት ቢኖርም በመመርያው ላይ ግን አልተገለጸም፡፡

በብሔራዊ ባንክ ጋር አቶ ይናገር ደሴ ተፈርሞ የወጣውና ከሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ በሆነው አዲሱ መመርያ መሠረት፣ ማንኛውም የውጭ ምንዛሪ ይዞ ከውጭ አገር የሚመጣ ሰው በብር መመንዘር እንዳለበት ተገልጾ፣ ይህም ከተፈቀደው መጠን በላይ ከሆነና የውጭ ዜጋ ከሆነ ገንዘቡ በከፈተው ሒሳብ (አካውንት) ውስጥ እንደሚቀመጥ ተገልጿል፡፡

 በአዲሱ መመርያ መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚመጡና ለአጭር ጊዜ ለሚቆዩ ዜጎች የሚፈቀደው የገንዘብ መጠን ግን ከፍ ተደርጓል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡና ለሚወጡ ሰዎች መያዝ የሚፈቀድላቸውን የገንዘብ መጠን የሚደነግገውን መመርያ ከስድስት ዓመት በኋላ በማሻሻል፣ የገንዘቡን መጠን ከእጥፍ በላይ ከፍ አድርጓል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ዜጎችም፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን አሥር ሺሕ ዶላር ወይም በሌሎች የውጭ ምንዛሪዎች ተመጣጣኝ ይዘው ሲመጡ፣ በኢትዮጵያ ብር መንዝረው መጠቀም ይችላሉ፡፡ ከአሥር ሺሕ ዶላር የበለጠ ይዘው ከመጡ ግን፣ ለጉምሩክ በማሳወቅ በግላቸው የውጭ ምንዛሪ አካውንት ውስጥ ማስቀመጥ ይችላሉ፡፡ በነባሩ መመርያ ነዋሪ ላልሆኑ የውጭ ዜጎች መያዝ ይፈቀድ የነበረው አራት ሺሕ ዶላር ብቻ ነበር፡፡

ነዋሪነታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የሆኑ ሰዎች ግን ከውጭ ሲመጡ እስከ አራት ሺሕ ዶላር ወይም በሌሎች የውጭ ምንዛሪዎች ተመጣጣኙን ይዘው መምጣት የተፈቀደላቸው ሲሆን፣ ይህ በነባሩ መመርያ አንድ ሺሕ ዶላር ብቻ ነበር፡፡

የኤምባሲ ሠራተኞች፣ ጊዜያዊ ሠራተኞች፣ እንዲሁም ለስብሰባና ለተለያዩ ጊዜያዊ ጉዳዮች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ዜጎች የድጋፍ ደብዳቤ ማምጣት ከቻሉ ከአሥር ሺሕ ዶላር በላይ ይዘው እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል፡፡

ሌላው ለውጥ ደግሞ ማንኛውም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣም ሆነ ከኢትዮጵያ የሚወጣ ሰው ከሦስት ሺሕ ብር በላይ መያዝ አይፈቀድለትም፡፡ ይህም በነባሩ መመርያ አንድ ሺሕ ብር ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ ጂቡቲ የሚሄዱ ሰዎች በተለየ ሁኔታ እስከ አሥር ሺሕ ብር መያዝ የሚችሉ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት አራት ሺሕ ብር ብቻ ነበር፡፡

በመሠረታዊነት አዲሱ መመርያ ሁሉም የውጭ ምንዛሪ ይዘው የሚመጡ ሰዎች በሕጋዊ የምንዛሪ ቢሮዎች ወደ ብር መቀየር ሲኖርባቸው፣ ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ ከብር ውጪ ለመገበያያ ሌላ ገንዘብ መጠቀም ስለማይፈቀድ ነው፡፡ ምንዛሪ ማድረግ የሚችለውም ግለሰቡ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መግባቱን የኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠሩ 30 ቀናት ውስጥ ነው፡፡ በድንበር በኩል የሚገቡ ሰዎች 500 ዶላር ወይም በሌሎች ምንዛሪ ተመጣጣኙን ይዘው መግባት የሚችሉ ሲሆን፣ ነገር ግን በድንበር አካባቢ ለሚገኙ የኢትዮጵያ የጉምሩክ ጣቢያዎች ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል፡፡

‹‹በአዲሱ መመርያ ከአሥር ሺሕ ዶላር በታች (ኢትዮጵያዊ ላልሆኑት) እና ከአራት ሺሕ ዶላር በታች (ለኢትዮጵያውያን) ለያዙ በጉምሩክ ዴክላራሲዮን ማድረግ ግዴታ አይደለም፤›› ሲሉ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ፈቃዱ ድጋፌ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አዲሱ መመርያ በዋጋ ግሽበት ምክንያት ውጭ የመጡ ሰዎች ሊደርስባቸው የሚችለውን ጫና ለመቀነስ ይረዳል ተብሏል፡፡

ይህም ማለት አንድ የውጭ ዜጋ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሦስት ወራት ለመቆየት አሥር ሺሕ ዶላር ቢያስፈልገው፣ በሕጋዊ ባንኮች ከዘረዘረ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡

‹‹ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የትራንስፖርት፣ የሆቴል፣ የምግብና የሌሎች ወጪዎች ከፍ ብለዋል፡፡ ስለዚህ የውጭ ዜጎችም ሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለቆይታቸው የሚበቃቸው ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል፤›› የሚሉት የቀድሞ የቡና ባንክ ፕሬዚዳንትና አሁን የአሃዱ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ እሸቱ ፋንታዬ ናቸው፡፡

ሌላው የአዲሱ መመርያ ዓላማ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማሻሻል ነው፡፡ ይህም ይዘው የሚመጡት የውጭ ምንዛሪ በቀጥታ ለኢትዮጵያ ባንኮች ገቢ ስለሚሆን የሚፈቀደው መጠን ከፍ መደረጉ፣ መንገደኞች በርከት ያለ የውጭ ምንዛሪ ያለ ሥጋት ይዘው እንዲመጡ ያደርጋል ተብሎ እንደሚታሰብ ተጠቁሟል፡፡

ይሁን እንጂ አቶ እሸቱ መመርያው በሥርዓት ካልተተገበረ ጥቁር ገበያን ኢትዮጵያ ውስጥ ሊያባብስ ይችላል ይላሉ፡፡

‹‹በሕግ ደረጃ ማንኛውም ሰው ከውጭ ይዞ የሚመጣውን የውጭ ምንዛሪ ለጉምሩክ አስመዝግቦ ሕጋዊ ምንዛሪውን በብር መውሰድ አለበት ይላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሕግ ብዙውን ጊዜ አይተገበርም፡፡ በመሆኑም ብዙ ሰው ከውጭ ይዞ የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ በጥቁር ገበያ ውስጥ ነው የሚዘረዝረው፡፡ ለምሳሌ አሥር ሺሕ ዶላር ይዞ ቢመጣ ሁለት ሺውን ብቻ አስመዝግቦ የቀረውን ለጥቁር ገበያ ይሸጣል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የጥቁር ገበያውን እያጦዘ ያለው ዋነኛ ምክንያት የዚህ መመርያ አተገባበር የላላ መሆኑ ነው፤›› ሲሉ አቶ እሸቱ ያብራራሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በጥቁር ገበያ የዶላር ዋጋ 90 ብር አካባብ የደረሰ ሲሆን፣ በሕጋዊ መንገድ ግን 53 ብር ገደማ ነው፡፡

ሌላው የመመርያው ክፍተት ደግሞ በዲጂታል ባንኪንግ በኩል የሚመጡ የውጭ ምንዛሪዎችን አለማካተቱ ነው፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ካርዶች የውጭ ገንዘብ ይዘው ቢመጡና ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ባንኮች ቢጠቀሙ፣ አዲሱ መመርያ የሚለው የለም፡፡ አዲሱ መመርያ ሌሎችንም የገንዘብ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎችን አይጠቅስም፡፡

‹‹ድሮ ቁጥጥር ከባድ ነበር፡፡ አሁን ግን ቁጥጥር በመላላቱ ለጥቁር ገበያ መጋቢ በመሆን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ክፍተት እየፈጠረ ነው፡፡ ለውጭ ዜጎች ቤት ለሚያከራዩና ሌሎች አገልግሎቶች ለሚሰጡ በውጭ ምንዛሪ እንዲሆን ቢደረግ ጠቃሚ ይሆን ነበር፤›› ሲሉ አቶ እሸቱ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች