Tuesday, March 28, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ችግሮች መላ ይፈለግላቸው!

አዲሱ ዓመት ሊጀመር በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ቀርተዋል፡፡ በአዲስ ዓመት መልካሙን መመኘት ብቻ ሳይሆን፣ በዕቅድ ላይ የተመሠረቱ ተግባራትን ለማከናወን ቆራጥ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አገር ድረስ በዕቅድ ላይ የተመሠረተ ዝግጅት ከሌለ፣ ግጭቱም ሆነ ድህነቱ ተባብሶ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በአዲሱ ዓመት መግቢያ ዋዜማ ላይ ሆነው፣ ኢትዮጵያ ችግሮቿን በሙሉ ተራ በተራ የምታስወግድባቸውን መላዎች የማፈላለግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ በችግሮች ተከባ የመፍትሔ ያለህ እያለች እየተጣራች ነው፡፡ መንግሥት በራሱ በኩል የሚፈለጉበትን ግዴታዎችና ኃላፊነቶች መወጣት ሲኖርበት፣ በተለያዩ ሙያዎች የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ያላቸው ደግሞ ችግር ፈቺ ዘዴዎችን ማፍለቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተደጋጋሚ ለማሳሰብ እንደተሞከረው የአገር ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያውን ኃላፊነት በመሆኑ፣ በመደጋገፍ አዲሱ ዓመት የሰላምና የዕድገት እንዲሆን ድርሻን መወጣት ተገቢ ነው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ሦስተኛ ዙር ጦርነት ሕይወት እየተቀጠፈ ነው፡፡ በኢኮኖሚው መዛባት ምክንያት የኑሮ ውድነቱ ከዕለት ወደ ዕለት እያሻቀበ በልቶ ማደር እየከበደ ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ከዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ መውጣት የግድ መሆን አለበት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ መለወጥ ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ በመጀመሪያ መንግሥት ራሱን ይለውጥ፡፡ የሕዝቡን ሰላም ያስጠብቅ፡፡ ለዘመናት ድብርት ውስጥ ያሉ መንግሥታዊ ተቋማትን ዘመናዊ ማድረግ ይገባል፡፡ ከዘመኑ ጋር መራመድ አቅቷቸው አላሠራ የሚሉ ሕጎችንና አሠራሮችን በጥናት ላይ ተመሥርቶ መለወጥ፣ ለኢንቨስትመንት እንቅፋት የሚሆኑ ደንቦችንና መመርያዎችን መከለስ፣ አገሪቱ ከድህነት ጋር ተቆራኝታ እንድትኖር የሚያስገድዱ ሕገ መንግሥታዊም ሆኑ ሌሎች ሕጎችን በፍጥነት ማስተካከል፣ የአገርን ሀብት እንደ ነቀዝ የሚያወድሙ ብልሹ አሠራሮችንና የሌብነት ዘዴዎችን ቦታ ማሳጣት፣ ለአድልኦ በር የሚከፍቱ ድርጊቶች የሚንሰራፉበትን የመንግሥትና የፓርቲ መደበላለቅን ማስቆም፣ በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ ግብታዊ አሠራሮችን ማስወገድ፣ በሥልጣናቸው የሚባልጉ ሹማምንትን በሕግ አደብ ማስገዛት፣ በዜጎች መካከል አድልኦ የሚፈጥሩ የፓርቲና የመንግሥት ኃላፊዎችን ከያዙት ሥልጣን ላይ ማንሳትና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በስብሰባና በተለያዩ ሰበቦች ሕዝባዊ አገልግሎት የሚነፍጉና በግልጽ ጉቦ የሚጠይቁ ተበራክተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን ከንቱዎች የያዘ መንግሥታዊ መዋቅር መቼም አይሻሻልም፡፡ መንግሥት በአዲሱ ዓመት ራሱን ከምንጊዜውም በላይ ለሕዝብ አገልግሎት ያዘጋጅ፡፡

ኢትዮጵያ የዘመናት ችግሮቿ ሊወገዱላት የሚችሉት ሰላም ስታገኝ ነው፡፡ ሰላም የሚገኘው በአንድ ወገን ፍላጎት እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ የሰላም ጉዳይ ሲነሳ ከግለሰብ ጀምሮ ሁሉንም ወገኖች የሚመለከት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ የሚያጨካክኑ ወንጀሎች ሲበዙ ለምን መባል አለበት፡፡ የግለሰቦች ዕለታዊ ፀብ አድማሱን አስፍቶ የብሔር ወይም የሃይማኖት ግጭት እንዲመስል ጥረት ሲደረግ፣ ተባብሮ ማስቆምና አጥፊዎችን መገሰፅ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በተለያዩ ምክንያቶች ግጭት የሚቀሰቅሱም ሆኑ የሚያሟሙቁ፣ ራሳቸውን ከአገር በታች አድርገው ቢመለከቱ ኖሮ ኢትዮጵያ የማያባራ ዕልቂትና ውድመት ውስጥ አትገባም ነበር፡፡ በአዲሱ ዓመት ራስን ከአገር በታች የማድረግ ስክነት መፈጠር ይኖርበታል፡፡ ማንም ግለሰብ ሆነ ቡድን ከአገር በላይ እንዳልሆነ በሚገባ መነገር አለበት፡፡ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ ማስተናገድ ያቃታቸው ጥጋበኞች ጦር ባነሱ ቁጥር አገር ጭንቅ ውስጥ መግባት የለባትም፡፡ ከጀብደኝነትና ከጦረኝነት አስተሳሰብ ሳይላቀቁ ሕዝባዊ ነኝ ማለት አይቻልም፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ እኩልነት፣ ነፃነትና ማኅበራዊ ፍትሕ ነው፡፡ በሕዝብ ስም መነገድ ይቁም፡፡

በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ክፍት ለማድረግ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ያሉ ተዋንያን በሙሉ በቅርቡ ለሚያጋጥማቸው ሁሉን አቀፍ ፉክክር ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ አለባቸው፡፡ እዚህ ላይ ምን ያህሉ የውጭ ባንኮች በቅርቡ ገበያውን ይቀላቀላሉ የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግሥት ዝግጅቱን አጠናቆ መምጣት ሲጀምሩ እጅግ የዘመነ አሠራር ማስተዋወቃቸው አይቀሬ ነው፡፡ እነሱ መጡም ቀሩም ለዘመኑ የሚመጥኑ የባንክ አገልግሎቶችን ለማቅረብ የሚቻለው፣ የአገር ውስጥ ባንኮች አቅማቸውን አስተባብረው ሲጠናከሩ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ መግባታቸው ሊፈጥር የሚችለውን ችግር መተንተን አያዋጣም፡፡ በአዲሱ ዓመት የአምናውንና የካቻምናውን ዓይነት አገልግሎት በማስታወቂያ እያስነገሩ መቀጠል አይቻልም፡፡ የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ የሚመጡት ለፅድቅ እንዳልሆነ ስለሚታወቅ፣ ካፒታልንና የሠለጠነ የሰው ኃይልን አቀናጅቶ ለፉክክሩ ዝግጁ መሆን ያዋጣል፡፡ ግለሰቦችና የተደራጁ ቡድኖች የሚበለፅጉበት የባንክ የብድር አገልግሎት ሥርዓት ባለው መንገድ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለንግድ፣ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለቴክኖሎጂ፣ ወዘተ በፍትሐዊነት የሚሰጥበት ፉክክር እንዲፈጠር መንገዱን መጥረግ ተገቢ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ተቆጥረው የማያልቁ የሀብት ፀጋዎች ላይ ተቀምጣ የምትቸገር አገር መሆኗ ያናድዳል፡፡ ከግብርና ምርቶች ጤፍ፣ ስንዴ፣ ምስር፣ አተር፣ ገብስ፣ በቆሎና ሌሎች አዝርዕቶች በስፋት ሊመረቱባት የምትችለው ኢትዮጵያ የምግብ ተመፅዋች ናት፡፡ ሥጋ፣ ዶሮ፣ ዓሳ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ ዓይብና የመሳሰሉትን በገፍ ማምረት የሚገባት ኢትዮጵያ በሚያሳዝን ሁኔታ ምንም እንደሌላት ይቆጠራል፡፡ ዘይት፣ ስኳር፣ ሲሚንቶና ሌሎች ቁሳቁሶችን በብዛት አምርታ ለጎረቤት አገሮች ገበያ መትረፍ የነበረባት ኢትዮጵያ በእጥረት ትሰቃያለች፡፡ ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ምን ይሆን ሲባል መልሱ ስንፍና ነው፡፡ በጥናት ላይ የተመሠረቱ አዋጭ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ማውጣት ያለበት መንግሥት ከድሮ ጀምሮ ምን እንደሚያፈዘው አይታወቅም፡፡ የሥራ ባህልን በመቀየር ቢያንስ በልቶ ማደር ብርቅ እንዳይሆን ማድረግ ሲቻል፣ ከመሥራት ይልቅ ወሬ ላይ ተጥድ ውሎ ማደር አሁንም እንደበረታ ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ከግለሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ድረስ ሠርቶ ለመለወጥ በአግባቡ ካልታቀደ፣ በየቀኑ የሚያሻቅበውን የዋጋ ግሽበት ማንም ማስቆም አይችልም፡፡ ምንም ሳይጠፋ መሥራት ባለመቻል መራብም ሆነ መቸገር ይቅርታ የሌለው በደል ነው፡፡

አንዳንዴ ከጎረቤት አገር ልምድ መቅሰም ተገቢ ነው፡፡ ጎረቤት ኬንያ በቅርቡ ባካሄደችው ምርጫ ዊሊያም ሩቶ አሸናፊነታቸው ሲገለጽ፣ ተሸናፊው ራይላ ኦዲንጋ ውጤቱን አልቀበልም ብለው በቀጥታ አቤቱታቸውን ያሰሙት ለኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ የቀረቡለትን መረጃዎች በሚገባ ከመረመረ በኋላ ሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ፣ የዊሊያም ሩቶን አሸናፊነት ማፅናቱ ይታወሳል፡፡ እዚህ ላይ መገንዘብ የሚገባው ኬንያውያን በምርጫ ጊዜ ከሚያጋጥማቸው ጭቅጭቅና ደም መፋሰስ ተላቀው፣ ውሳኔውን ለፍትሕ ሥርዓቱ መስጠታቸው ምን ያህል እንደጠቀማቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን የመሰለ አርዓያነት በመቅሰም ችግርን በሕግ ብቻ መፍታት መልመድ አለባቸው፡፡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት መጣል የሚቻለው ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት በመመሥረት ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ማሰብና ዴሞክራቲክ መሆን ሲቻል ደም መፋሰስ ይቀራል፡፡ ለአዲሱ ዓመት አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት ሲደረግ፣ ለሕግ የበላይነት መገዛት አስፈላጊነት አፅንኦት መስጠት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ወደፊት መራመድ የምትችለው ሕግና ሥርዓት ሲኖር ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ችግሮች መላ ይፈለግላቸው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...

‹‹ኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቀልበስ የፖሊሲ ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ›› ዓለም ባንክ

በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይፋ ሊያደርግ ነው

የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዳ ሪፎርም ማጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...